በወጣትነታችን ፈጣሪን ማሰብ ያለብን ለምንድን ነው?

በወጣትነት ጊዜ ፈጣሪን ለማሰብ አራት ምክንያቶች

ጠላታችን፣ “ወጣትነት ለመደሰት፣ ጉልምስና ለንግድ፣ እርጅና ለሃይማኖት” የሚል ብሂል አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ፣ “ወጣትነትም፣ ጉልምስናም፣ እርጅናም ለፈጣሪ ነው!” ይላል።

ይሁን እንጂ፣ ወጣትነት ፈጣሪን ወደ መዘንጋት የምናዘነብልበት (ለመዘንጋት የምንጣጣርበት?) ወቅት የመሆኑን ያህል፣ ፈጣሪያችንን ለማሰብ መሥራት የሚኖርብን ጊዜም ነው (መክብብ 12፥1)። የፈጠረን፣ የሚያስፈልገንን የሚሰጠን፣ የሚጠነቀቅልን፣ የሚጠብቀን፣ የሚቈጣጠረን ብቻ ሳይሆን የሚያድነንም ጭምር እርሱ መሆኑን እናስብ። ይህ ለማስታወስ ብዙ ነው፤ ሆኖም ግን በወጣትነታችን ወቅት ብንጀምረው ይበልጥ ቀላል ይሆናል!

  1. በኀይል የተሞላ ዕድሜ

ያም ሆነ ይህ፣ እግዚአብሔር በወጣትነት ዕድሜያችን ፈጣሪያችንን እንድናስብ ያዘዘበት ምክንያት፣ ይህ ብቻ አይደለም። የሕይወታችን በዐቅም የተሞሉ ዓመታት እነዚህ በመሆናቸውም ጭምር ነው።

ፈጣሪያችንን ለማገልገል፣ እስክንዝልና ‘ነዳጅ ጨርሰን’ በፍጥነት መራመድ እስኪሳነን ድረስ ለምን እንጠብቃለን? የፈጠረን አምላክ፣ ይበልጥ ንቁና ጤናማ የሆንባቸው ዓመታት ይገቡታል። ሰውነታችን (በአንጻራዊነት) ጠንካራና ፈርጣማ፣ አእምሮአችን ስልና ብሩህ፣ የስሜት ሕዋሶቻችን ክፍትና ንቁ፣ ተነሣሽነታችን አዎንታዊና ግልጽ፣ ውሳኔያችንም ጠንካራና ጽኑ የሚሆኑበት ዕድሜ ነው። ጉልበታም በሆናችሁበት ጊዜ ፈጣሪያችሁን ዐስቡ።

  1. ለንቃት ቅርብ የሆነ(Sensitive) ዕድሜ

ከመካከለኛም ሆነ ከእርጅና ዕድሜ ይልቅ፣ በለጋ የወጣትነት ዕድሜ፣ ክርስቲያኖች የሆንን ሰዎች ብዙዎች የመሆናችን ምክንያት ምን ይሆን? ምክንያቱም የወጣትነት ዓመታት ለስሜት ቅርብ ስለ ሆኑ ነው። “የአጠቃላይ ውድቀት” እምነታችንን ሳንተው፣ ወጣትነት ለማመንና ንስሓ ለመግባት “ቀለል” ያለ ዕድሜ ነው ማለት እንችላለን። በፍጹም ቀላል አይሆንም፤ ሆኖም ግን በአንጻራዊነት ቀለል ያለ ነው። ቀለል ያለ የሚሆነውም ዕድሜ እየጨመረ በሄደ መጠን ልብ እየጠነከረ፣ ኅሊና እየደነዘዘ፣ ኀጢአትም በጥልቀት ሥር እየሰደደና “ሙት”ነታችንም ይበልጥ እየጨመረ ስለሚሄድ ነው።

የመንፈሳዊ እርጅና ክፉ ቀናት ከመምጣታቸው በፊት፣ ይህን የወጣትነታችንን ንቁነትና አዲስ ነገርን የመቀበል ባሕርይን  ፈጣሪያችንን ለማሰብ እናውለው።

  1. የሚገራ ዕድሜ

ከየትኛውም የዕድሜያችን ክፍል ይልቅ ወጣትነታችን ብዙ የምንማርበት ወቅት ነው። ይህ፣ በየትኛውም ጉዳይ ላይ የሚታይ ነው፤ ነገር ግን በተለይ ሃይማኖታዊ ትምህርትን በተመለከተ እውነት ነው። በዕድሜያቸው አመሻሽ አካባቢ ከዳኑ ክርስቲያኖች ጋራ ለመነጋገር በነበሩኝ ዕድሎች፣ ሁሉም ምን ያህል ጥቂት እንደሚያውቁና ከዚህም በኋላ ሊያውቁ የሚችሉት ትንሽ መሆኑን በማሰብ ይቆጫሉ። እኔም፣ ጌታ የሰጣቸውን ማንኛውንም ዕድል እንዲያከብሩና እንዲጠቀሙበት አበረታታቸዋለሁ፤ ቢሆንም ጥቂት ለመማር ዕጥፍ ማጥናት እንደሚጠበቅባቸው ይሰማቸዋል።

  1. አደገኛ ዕድሜ

የወጣትነት ዓመታት እንደ ፈንጂ ወረዳ፣ በብዙ ተግዳሮቶችና አደጋዎች የተሞሉ ናቸው፤ የሆርሞኖች፣ የአቻ ግፊት፣ አልኮል፣ ሱስ፣ የወሲብ ምስሎችና ፊልሞች፣ የሞራል ውድቀት ወዘተ.። እዚህም እዚያም በሚያጋጥሙት ፍንዳታዎች ሳይጎዱ ይህን ወቅት የሚሻገሩት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ከውስጥና ከውጪ፣ በየትኛውም አቅጣጫ በአደጋ የተከበበ ነው። ምን ያህል “የመጀመሪያ” ፈተናዎች፣ የመጨረሻዎች ሆነው ይሆን! ፈጣሪያችንም በዚህ የጦር ሜዳ ውስጥ እንዲጠብቀንና ተሸክሞ እንዲያሳልፈን ምንኛ ያስፈልገን ይሆን!

ለማሰብ ልብ በል

እንግዲያው በእነዚህ ምርጥ (ደግሞም አደገኛ) ዓመታት ፈጣሪያችንን ለማሰብ የሚረዱንን ጥቂት ምክሮች ልለግሳችሁ፤

  • ፈጣሪ እንዳላችሁ ርግጠኛ ሁኑ፤ በዘፍጥረት 1-2 ቀጥተኛ ትርጓሜ ላይ ጥልቅ መረዳት ይኑራችሁ፤ ደግሞም ማንኛውንም የዝግመተ ለውጥ ተጽእኖን አስወግዱ።
  • ፈጣሪያችሁን ለማወቅ ትጉ፤ ስብከቶችን፣ ማብራሪያዎችንና ጥሩ መጻሕፍትን በመጠቀም ቃሉን አጥኑ። ግን ደግሞ ራሱ የሚሰጣቸውን አጉሊዎች በመጠቀም  የእርሱን ዓለም አጥኑ።
  • የፈጣሪያችሁን ወዳጆች ተቀላቀሉ፤ ፈጣሪያቸውን በማሰብና በማክበር ከሚተጉ ፍጥረቶች ጋራ ጓደኝነትን መሥርቱ።
  • የፈጣሪያችሁን ፈለግ ተከተሉ፤ ስድስት የሥራ ቀናትን ተከትሎ የሚመጣ የዕረፍትና ሥራዎቹን የመመልከት ቀንን ያበጀና የደነገገ እርሱ ነው።
  • ድነትን ከፈጣሪያችሁ ጠይቁ፤ ፈጣሪያችሁን መግፋታችሁ የሰባበራችሁ ቢሆንም እንኳ ዳግም በርሱ መልክ ሊያበጃችሁ ፈቃደኛ ነው።  
  • ከዚሁ የድነት ርእስ ሳንወጣ፣ ከወጣትነት ዕድሜ ያለፉ አንባቢዎችን ተስፋ ማስቈረጥን አልሻም፤ ከረጅሙ የዘላለም ዘመን አንጻር፣ እናንተም ያላችሁት ገና በ”ወጣትነት” ነው፡፡  ስለዚህ እነዚህ ቀናት ይበልጥ እየከፉ ከመሄዳቸው በፊት፣ ፈጣሪያችሁን ለማሰብ ገና አልረፈደም።

ዴቪድ ሙሬይ