“የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ” የሚለው ሐረግ በራሱ፣ የአብዛኛውን ክርስቲያን አእምሮን ታላቅ ድንጋጤ ውስጥ በሚከትቱ ምስሎች የሚሞላ ይመስላል። በአሁኑ ጊዜ ስለ ቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ያለን ምስል፣ ምን ማድረግ እንደምንችልና ምን ማድረግ እንደማንችል የሚነግሩን ከጨቋኞችና ከቊጥጥር ውጪ ከሆኑ የአምባገነኖች አመራር ጋር የተያያዘ ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጪ፣ ሥልጣንን ያለ አግባብ መጠቀምን የሚመለከቱ የአደባባይ ድርጊቶችን ከግምት ካስገባን ይህ የሚደንቅ አይሆንም። በተጨማሪም፣ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ከዘመነኛው የክርስቲያናዊ ዐርነት ግንዛቤ ጋራ የሚገናኝ አይመስልም የሚል አስተሳሰብ አለ፤ ይህም እያንዳንዱ ክርስቲያን ከክርስትና እምነትና ሕይወት ጋራ በተያያዙ ጒዳዮች ሁሉ የራሱ ዳኛ እንደ ሆነ የሚናገር ግንዛቤ ነው። ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ከታሪክ አንጻር እንደ ቤተ ክርስቲያን “መለያ ምልክት” የተቈጠረበትን ምክንያት ለመረዳት፣ እውነተኛ ዐላማው ምን እንደ ሆነ ማስታወስ ይኖርብናል።
የቤተ ክርስቲያን መለያ ምልክት
ከሐዳስያኑ ጊዜ ጀምሮ፣ እውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያንን ከሐሰተኛዋ ለመለየት፣ የነገረ መለኮት ምሁራኑ የቤተ ክርስቲያን ሦስት “መለያ ምልክቶችን” ገልጸዋል፤ እነርሱም፣ ቃለ እግዚአብሔርን በአግባቡ መስበክ፣ የቤተ ክርስቲያን ሥርዐትን በአግባቡ መፈጸምና የቤተ ክርስቲያንን ተግሣጽ በአግባቡ ማከናወን ናቸው። አንዲት እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን፣ የእግዚአብሔርን ቃል ታስተምራለች፤ እንዲሁም የክርስቶስን ቃል በመታዘዝ፣ የቤተ ክርስቲያን ሥርዐቶችን ትፈጽማለች ብሎ ማሰብ አከራካሪ ባይሆንም፣ እርሷ እንድትኖር የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ አስፈላጊ መሆኑን ብዙ ክርስቲያኖች ይጠራጠራሉ። ነገር ግን፣ እንደ እውነታው ከሆነ፣ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ሐሳብ ከመጀመሪያዎቹ ከሁለቱ ጋራ ዐብሮ የሚሄድ ዐቢይ ምልክት ነው። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ ቃሉን በአግባቡ ማስተማርና መስበክ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም ልንታዘዘውና ልንተገብረው እንደሚገባ ይነግረናል(ሮሜ 2፥13፤ ያዕቆብ 1፥22)፡፡ ቤተ ክርስቲያንስ ሥርዐቶቹን ለማን ተግባራዊ እንደሚሆኑ ሳትወስን በአግባቡ ማስተዳደር የምትችለው እንዴት ነው? የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ፣ ጌታ ቤተ ክርስቲያኑን ማለትም የእርሱን ቤተ ሰብ ለመለየትና ለመገንባት ያወጣው አሠራር ነው።
ቤተ ክርስቲያን ተቋም ብቻ አይደለችም፤ እግዚአብሔር ኀጢአተኞችን ለራሱ ለመቤዠትና ከራሱ ጋራ ለማስታረቅ ያለው ዐላማና ዕቅድ ሕያው መገለጫ (embodiment) ናት። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምነው ያ በእምነት የጸደቀ ሰው፣ ልጅም የሚሆነው በእምነት ነው። ታላቁና አሐዱ ሥሉሱ አምላካችን፣ ሕዝቡ በፍርድ ወንበሩ ፊት በደለኛ አለመሆናቸውን በማወጅ ብቻ አይረካም (ሮሜ 5፥1)። በተጨማሪም እያንዳንዳቸውን የተዋጁ ኀጢአተኛ ልጆቹን፣ የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ አካል ያደርጋቸዋል (ዮሐንስ 1፥12)። ቤተ ክርስቲያንን እንደ ቤተ ሰብ ስንመለከት፣ የተግሣጿን ዐላማና በረከት ማየት እንጀምራለን። ልክ ልጆቻቸውን ከልብ የሚወድዱ አባቶችና እናቶች እነርሱን ለማቅናትና ለማበረታታት ጊዜ መውሰድ እንደሚገባቸው ሁሉ፣ ጌታንና ሕዝቡን የሚወድዱ መጋቢያንና ሽማግሌዎች እነርሱን ለማቅናትና ለማበረታታት ጊዜ ሊወስዱ ይገባል።
ተግሣጽና ደቀ መዝሙርነት
በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ተግሣጽ ያለውን ቦታ በተሻለ ሁኔታ ለማድነቅ፣ ተግሣጽን(discipline) በግለ ሰብ ደረጃ ከሰማናቸው (በተመክሮ ካሳለፍናቸው) ይልቅ፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ መነጽር ልንመለከተው ይገባል። ተግሣጽ የሚለው ቃል ፈተናን፣ ፍርድንና ቅጣትን ያስታውሰናል፤ ይህ ደግሞ ወዲያውኑ ራሳችንን እንድንከላከል ሊያደርገን ይችላል። ነገር ግን ዋነኛው የተግሣጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አጠቃቀም ይህ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱሳዊው ተግሣጽ፣ “ደቀ መዝሙር” ከሚለው ከሌላው ታዋቂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል ጋር በጣም የተያያዘ ነው። ደቀ መዝሙር፣ የሚማር ማለት ነው (ማቴዎስ 10፥24)፤ እናም በአዲስ ኪዳን ውስጥ፣ ደቀ መዝሙር የኢየሱስን ትእዛዛት በሙሉ መጠበቅን በተመለከተ፣ ልዩ የሆነ የማመሳከሪያ ሐሳብ አለው (ማቴዎስ 28፥19-20)። በተመሳሳይ መንገድ፣ ተግሣጽ የኢየሱስን መንገዶች መማር ነው። ጳውሎስ በኤፌሶን 6፥4 በዚህ ዐውድ ይጠቀመዋል፣ “አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው።” በርግጥ፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለተግሣጽ የዋለው የጽርዕ (ግሪክ) ቃል፣ ሰፋ ባለው ዐውድ (በተለይም ለልጆች) ትምህርትን ወይም ምክርን የሚወክል ቃል ነው። አንድን ሰው መገሠጽ፣ ሊሄድበት በሚገባው መንገድ ማሠልጠን ማለት ነው (ምሳሌ 22፥6)፤ እንዲሁም ውድ የሆነን ሰው (ዕብራውያን 12፥5-11) በፍቅር መገንባት ነው (ራእይ 3፥19)።
ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌ ደግሞ፣ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ዕውቀት እንድናድግ አስፈላጊ መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። ተግሣጽ፣ አንድ አፍቃሪ አባት ልጁን የሚያስተምርበት መንገድ ከሆነ፣ ከሰማያዊ አባታችን የሚሰጠንን መመሪያ እንዴት አንቀበልም? ጌታ ከርሱ የበታች የሆኑ እረኞችን ለቤተ ክርስቲያን የሰጠበት ዐላማ፣ መንጋውን ለመገንባትና ለማስታጠቅ ነው፤ እነዚህንም እረኞች ሕዝቡን ለመገሠጽ ይጠቀማቸዋል (ኤፌሶን 4፥11-16)። በመጀመሪያና ከሁሉም በላይ፣ ተግሣጽ የሚጀምረው ከቃለ እግዚአብሔር ትምህርት ነው። የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ፣ መደበኛ ከሆነ ርምጃ በመነሣት መጀመር የለበትም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር፣ መመሪያና ተግሣጽ በመስጠታቸው ይጀምራል። በጌታ ለመታነጽ፣ የርሱን ትእዛዛት ማወቅ አለብን። በትክክለኛው ጐዳና ለመሆን፣ የጌታን መንገዶች ማወቅ አለብን። እንደ እውነታው ከሆነ፣ ተግሣጽን የምትለማመድ ቤተ ክርስቲያን አካላት መሆን ካልፈለግን፣ በቃለ እግዚአብሔር የመመራትን እንዲሁም ለርሱ ተጠያቂ የመሆን መብታችንን እያጣን ነው።
የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ምን ይመስላል?
የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ፣ የእውነተኛ ቤተ ክርስቲያን መለያ ምልክትና እግዚአብሔር ለልጆቹ ያለው በፍቅር የተሞላው ተግሣጹ መዘርጋት ከሆነ፣ በብዙ አብያተ ክርስቲያናት የማይተገበረው ለምንድን ነው? አቅልለው የሚመለከቱትስ ለምንድን ነው? የእንደነዚህ ዐይነት ጥያቄዎች መልስ ብዙውን ጊዜ የሚገኘው፣ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ በትክክል በማይተገበርበት መንገድ ላይ ነው። ልክ ወላጆች ልጆቻቸውን በመገሠጽ ረገድ ታማኞችና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ እንደሚገባቸው፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም ሥልጣናቸውን በወጥነትና በፍቅር መጠቀም አለባቸው። ብሉይ ኪዳን ከመድሎ አደገኛነት (ለምሳሌ ያዕቆብ ለዮሴፍና ለወንድሞቹ እንደ ሆነው)፣ እንዲሁም ተግሣጽን ከመተግበር መጒደል ጋራ በተያያዘ (ለምሳሌ እንደ ኤሊና ልጆቹ)፣ በማስጠንቀቂያ የተሞላ ነው። ጌታ የሚወድዳቸውን በርግጥ ይገሥጻል (ዕብራውያን 12፥6)፤ ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ ልታደርግ ይገባል። ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ከፍቅር የመነጨ ድርጊት መሆኑን ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባም። ይህም፣ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ሊስተካከል የማይችል ሁኔታ ከተፈጠረ በኋላ ብቻ ልንመዝዘው የሚገባ መሆን የለበትም ማለት ነው። ተግሣጽ፣ ፍርድ የሚታወጅበት “የመጨረሻው ነጥብ”[1] አይደለም። መጽሐፍ ቅዱሳዊው የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ፣ ወደ አብያተ ክርስቲያናት ሊሠራጭ የሚገባ ኀላፊነት፣ ዕድገት፣ ይቅርታንና ጸጋን የያዘ ባህል ነው። እያንዳንዳቸው የቤተ ክርስቲያን አባላት፣ ሌሎች ከኀጢአት ጋራ ሲታገሉ የማገዝ ኀላፊነት አለባቸው፤ ይህንም የሚያደርጉት በፍርድና በትችት ሳይሆን፣ በየዋህነትና ማደስን በሚመኙ ዐይኖች፣ ራሳቸውም ለፈተና የተጋለጡ መሆናቸውን በማወቅ ነው (ገላትያ 6፥1)። ማቴዎስ 18 ለፍርድ ቤት ክርክር የሚሆን ዐይነት አማራጭን አይገልጽም፤ ወደ ትልልቅ ርምጃዎች (ለምሳሌ፦ ወደ ቤተ ክርስቲያን መውሰድ) ከመሄዳችን በፊት፣ ትናንሽ ርምጃዎችን (ለምሳሌ፦ በአካል መሄድ) በትዕግሥት በመፈጸም እርስ በርስ በፍቅር ሊኖረን የሚገባውን መስተጋብር ለማሳየት የተሰጠ መመሪያ ነው።
የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከመገሠጽ ጋራ በተያያዘ ያላቸው ሥልጣን የራሳቸው ሳይሆን፣ የክርስቶስ የእረኛነት ሥልጣን መሆኑን ሁልጊዜ ማስታወስ አለባቸው። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ናት (ኤፌሶን 1፥22-23፤ ቈላስይስ 1፥18)፤ እናም ጒድፍ አልባ እንድትሆን እየገነባት ያለው እርሱ ነው (ኤፌሶን 5፥27)። በመሆኑም መሪዎች ችግሮችን ቶሎ ለመፍታት ሲሉ፣ በገዢነት ወይም በአምባገነንነት ርምጃ ከመውሰድ (1ጴጥሮስ 5፥3)፣ ወይም አንዳንዶችን እየገሠጹ ሌሎችን በመተው መድሎን ከማሳየት (ያዕቆብ 2፥1) በተቻላቸው ዐቅም ሊቈጠቡ ይገባል። አባላት ደግሞ የተግሣጽ ሂደት ምስጢራዊ የቅጣት ዘዴ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ኀጥኣንን ለማደስ፣ ግንኙነቶችን ለመፈወስና ቃሉን ለማክበር የሚጠቀምበት መንገድ መሆኑን ማወቅ አለባቸው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ተግሣጽ በቀን ብርሃን እንዳይታይ ብለው መፍራት የለባቸውም፤ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ፣ የአባላቱን መልካም ስም አላስፈላጊ በሆነ አደባባይ ላይ ሊያሰጡ ከሚችሉ ሐሜቶች ለመጠበቅ የተቻላቸውን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በመጨረሻም የሚፈለገው ነገር፣ እንዲሁ መፍትሔ ማምጣት ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን አማኙ በግለ ሰብ ደረጃ እንዲጠነክር እንዲሁም የክርስቶስ መላው አካል እንድትጠናከር ማድረግ ነው።
የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ዐላማው ምንድን ነው?
በመጨረሻም፣ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ጸሎትን፣ በጥንቃቄ ማሰብን እንዲሁም ወጥነትን የሚጠይቅ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ለቤተ ክርስቲያን ሕይወት አስፈላጊ ዐላማዎች አሉት። የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ሦስት ዋና ዐላማዎች አሉት። የመጀመሪያው፣ ኀጥኡን ወደ ቤተ ክርስቲያን፣ በመጨረሻም፣ ወደ ጌታ ዳግም የምንጠራበት ነው። በፍቅር የሚተገበር የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ፣ አንድን ኀጥእ ስለ ኀጢአቱ ለመውቀስ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን እንደምትወድደው፣ ተስፋ እንደማትቈርጥበትና ወደ ሙሉ ኅብረት ተመልሶ እንዲመጣ እንደምትፈልግ ለማሳየት የሚያስችል ኀይለኛ መንገድ ነው። እንደ እውነታው፣ ተግሣጽ በዐይናችን ፊት የሚገለጥ ወንጌል ሊሆን ይችላል። ኀጢአታችንን አምነን መቀበል፣ ንስሓ መግባት እንዲሁም ነጻውንና ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠልንን ይቅርታ መጠየቅ አለብን።
ሁለተኛው፣ የቤተ ክርስቲያንን ንጽሕና እንዲሁም በሚያየው ዓለም ፊት ምስክርነቷን ለማስጠበቅ፣ ተግሣጽ አስፈላጊ ነው። ይህ ግን ፍጽምናን የሚያሳይ የግብዝነት ጭምብል እናጥልቅ ማለት አይደለም፤ ይልቁንስ የእግዚአብሔር ቃል የሕይወታችን ሚዛን እንደ ሆነና፣ ፍጹማን ሳይሆኑ፣ ይቅር የተባሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን ለዓለም እንገልጻለን ማለት ነው።
የመጨረሻውና ዋናው፣ የቤተ ክርስቲያን ተግሣጽ ለእግዚአብሔር ክብር የሚደረግ ነው። ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ክብር በሕያውነት የሚያንጸባርቁ ናቸው፤ እኛም የርሱን የፍቅርና የቅድስና ባሕርይ ለማንጸባረቅ ጥረት ስናደርግ፣ የርሱን ክብር ይበልጥ እናንጸባርቃለን (ኤፌሶን 3፥10)። ቅዱሱ እግዚአብሔር አፍቃሪም መሆኑን፣ ከተግሣጽ የተሻለ ምን ማሳያ መንገድ አለ? የተሰናከሉትን በፍቅርና በትሕትና መንፈስ ለማደስ ስንጥር፣ የከበረ ባሕርይ እናሳያለን፤ ይህም በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ የመታደስ ሁሉ ምንጭ ወደ ሆነው አምላክ ያመለክታል(1 ጴጥሮስ 2፥12)፡፡