ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል በመሠረታዊነት የክርስቲያኖች ቃል በመሆኑ፣ ተለይቶ ለክርስትና ብቻ ሊውል ይገባል። ምንም እንኳ ሌሎች ሃይማኖቶች ምኩራብ እና መስጊድ የሚሉ ቃላት ቢኖሯቸውም፣ የአምልኮ ስፍራቸውን፣ “ቤተ ክርስቲያን” ብለው የሚጠሩት ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው።
በቦታዎችና በሰዎች ስም የተሠየሙ አብያተ ክርስቲያናት አሉ፤ ነገር ግን መቼም ቢሆን እነዚህ ሰዎች መነሻ ወይም ባለ ቤት ሊሆኑ አይችሉም፤ የቤተ ክርስቲያን ባለ ቤት ክርስቶስ ነውና። በርግጥ፣ ኢየሱስ ለስምዖን ጴጥሮስ እንዲህ ተናግሯል፤ “አንተ ጴጥሮስ ነህ፤ በዚህ ዐለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ” (ማቴዎስ 16፥18፤ ማቴዎስ 18፥17ንም ይመልከቱ)። ቤተ ክርስቲያን የሚለው የግሪኩ ቃል ኤክሌሲያ የሚል ነው፤ ይህም፣ ለኢየሱስ ብቻ የሚገዛ የአማኞችን አካል ለመመሥረት፣ ከዚህ ዓለም የሰው ዘር ተጠርቶ የወጣ ማለት ነው። ይህም በብሉይ ኪዳን ዘመን ከሚገኙ ከእግዚአብሔር ሕዝቦች ጋራ ቀጣይነት የለውም ማለት አይደለም። በርግጥ አለው። ቤተ ክርስቲያን፣ በነቢያትና በሐዋርያት መልእክት የሚመሩ የአማኞችን አዲስ ማኅበር ትይዛለች ማለቱ የተሻለ ነው። በሌላ አገላለጽ፣ እነዚህ አማኞች መነሻቸውን የሚያገኙት በብሉይና በአዲስ ኪዳናት ነው። ከዘፍጥረት እስከ ራእይ፣ በመጻሕፍት ውስጥ የተጣመረ ወርቃማ ክር አለ፤ ይህም መለኮታዊ መልእክት፣ “እኔ አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝቦቼ ትሆናላችሁ” የሚል ነው።
ቤተ ክርስቲያን ዓለም ዐቀፋዊት ናት፤ እናም ምንም ያህል ጭቈናና ስደት ቢደርስባትም፣ በዓለም ላይ ትኖራለች። በሁሉም ቦታ የሚገኙ አማኞች፣ የሐዋርያቱን የእምነት አንቀጽ በቃላቸው ይሉታል፤ “…በቅድስት ዐለም ዐቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን፣ በአማኞች አንድነት አምናለሁ።” እናም ይህች ቤተ ክርስቲያን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ትኖራለች። ኢየሱስ ከዕርገቱ በፊት፣ ለቤተ ክርስቲያን የመጨረሻ ቃል አድርጎ የሰጠውን ተስፋ ተቀብላለች፤ “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋራ ነኝ” (ማቴዎስ 28፥20)። በርግጥ፣ ይህ ለእያንዳንዱ አማኝ የሚያጽናና ተስፋ ነው። በሕይወታችን ውስጥ በምናደርጋቸው በእያንዳንዱ ርምጃዎች፣ እንዲሁም በየዕለቱና በየሰዓቱ ኢየሱስ ከእኛ ጋራ ዐብሮ አለ።
በመሰናበቻ ንግግሩ ላይ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱና ለተከታዮቹ ሁሉ ብዙ ተጨማሪ ነገር ተናግሯል። ታላቁ ተልዕኮ በመባል የሚታወቀውን ቃል ለቤተ ክርስቲያን ሰጠ (ማቴዎስ 28፥19-20)። በሌላ አገላለጽ፣ የድነትን ወንጌል ይዛችሁ ወደ ዓለም ከወጣችሁ በኋላ፣ አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ ልታደርጓቸው ይገባል ማለቱ ነው። የአይሁድ ሐዋርያት ወደ ተበተኑት የአይሁድ ወገኖች ብቻ ይሂዱ ማለቱ ሳይሆን፣ ወንጌሉ በዓለም ላሉ ሰዎች ሁሉ መሰበክ አለበት ማለቱ ነው።
የአሕዛብ ሐዋርያ ሆኖ የተጠራው ጳውሎስ፣ አይሁድንም አሕዛብንም የሚቀበሉ አብያተ ክርስቲያናትን መሠረተ። በርግጥ፣ በመጀመሪያ የሚስዮናዊ ጒዞው፣ ሙሉ በሙሉ የአሕዛብ አገር በሆነችው በመካከለኛይቱ ቱርክ፣ የልስጥራንና የደርቤን አብያተ ክርስቲያናት አቋቁሟል። እናም ጳውሎስ በሮም ውስጥ፣ በኋላ የሚስዮን ዋና መሥሪያ ቤት በሚሆነው ራሱ በተከራየው ቤት፣ እስረኛ ሆኖ ሁለት ዓመት ኖሯል፡፡ በዚያም በመላው የሮም ግዛት፣ ማለትም፣ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ሚስዮናዊያንን ልኳል (ሐዋርያት ሥራ 28፥28-31፤ ከሐዋርያት ሥራ 1፥8 ጋር አነጻጽር)። በተመሳሳይ፣ ሐዋርያው ቶማስ የህንድ ደቡብ ምዕራባዊ ጠረፍ ወደ ሆነችው፣ ወደ ኬራላ ግዛት ድረስ ሄዷል። ዛሬም ቢሆን፣ በዚያ የሚገኙ ክርስቲያኖች የቅዱስ ቶማስን ስም በቋንቋቸው ማር ቶማ በማለት ይጠራሉ። ትውፊታቸው ወደ መጀመሪያው ምእት ዓመት አጋማሽ ተመልሶ በመሄድ፣ ቶማስ ሰባት አብያተ ክርስቲያናትን እንደ መሠረተ የሚገልጽ መረጃን ይሰጣል።
ሐዋርያቱ፣ “ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” የሚለውን የኢየሱስን ትእዛዝ ቃል በቃል ተረድተውታል፡፡ ይህ የማያቋርጥ ግዴታን ያዘለ ትእዛዝ ነው። ደቀ መዝሙር የሚለው ቃል፣ አማኞችን በማፍራት ብቻ የሚገለጽ አይደለም፤ ምክንያቱም ቃሉ በመሠረታዊነት፣ በቂ ሥልጠናን የሚቀበል ተማሪ መሆን ማለት ነው። ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ፣ ደቀ መዝሙር የሚለውን ቃል የተለያዩ ሰዎችን ለመግለጽ መጠቀሙን ማስተዋል አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በሐዋርያት ሥራ 9፥10፣ ኢየሱስ ወደ ጳውሎስ መልእክተኛ አድርጎ የላከውን የደማስቆውን ሐናንያ፣ ደቀ መዝሙር ብሎ ገልጾታል። በሌላ አገላለጽ፣ በአራቱ ወንጌላት ውስጥ፣ የኢየሱስ የቅርብ ተከታዮች ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት በመባል ይታወቃሉ። ነገር ግን ከበዓለ ዐምሳ በኋላ፣ እነዚህ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሆነው ሲሾሙ፣ አዳዲስ አማኞች ደግሞ ደቀ መዛሙርት በመባል የሚታወቁ ሆነዋል።
ኢየሱስ፣ “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴዎስ 28፥19) በማለት ሲናገር፣ ሁለት ርምጃዎችን በመከተል ይህን እንድናደርግ ነግሮናል፤ በመጀመሪያ፣ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም በማጥመቅ ሲሆን በሁለተኛነት፣ ኢየሱስ ያዘዛቸውን ሁሉ እንዲጠብቁ በማስተማር ነው። ከመጀመሪያው የትምህርት ጊዜ በኋላ፣ አባላት የሚሆኑ ሰዎች ሥሉስ አሐዱ በሆነው የእግዚአብሔር ስም ተጠምቀው የቤተ ክርስቲያኒቷ አካል ይሆናሉ፤ ይህም ልዩ መብቶችንና ግዴታዎችን ይሰጣቸዋል።
ሥሉስ አሐዱ ከሆነው አምላክ ጋራ ንቁ ግንኙነት አለን፤ ይህም ማለት አብ፣ ወንድና ሴት ልጆቹ አድርጎ ይጠራናል፤ ወልድ ደግሞ፣ እንደ ወንድሞቹና እኅቶቹ ያየናል፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በእኛ ውስጥ ያድራል። ከዚህ የሚበልጥ ነገር አለ፤ ምክንያቱም ጳውሎስ ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋራ ዐብረን ወራሾች እንደ ሆንን ይናገራል (ሮሜ 8፥17)። ምን ዐይነት የመጽናናት ምንጭ ይሆን! ይህ ማለት፣ የአብ ዘር እንደ መሆናችን መጠን፣ በማንኛውም ሰዓት የርሱን ስም በመጥራት ማስተዋልን፣ ጥበብንና መረዳትን እንዲሰጠን እንለምነዋለን ማለት ነው። ኢየሱስ ወንድማችን ስለ ሆነ፣ በማንኛውም ሰዓትና በየትኛውም ቦታ ልንጠራው እንችላለን። መንፈስ ቅዱስም በድፍረት እንዲሞላን፣ ከክፉና ከሚጐዳ ነገርም እንዲጠብቀን እንለምነዋለን።
በባለፈው የ“ፕሮ ኤክሌሲያ” ተከታታይ ዕትም ላይ እንዳየነው፣ ልዩ መብቶችና ግዴታዎች ዐብረው ይሄዳሉ። ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ስናደርግ፣ ኢየሱስ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲጠመቁ፣ ያዘዘውንም ሁሉ ይጠብቁ ዘንድ እንድናስተምራቸው አዝዞናል። የዚህ ተልእኮ ሁለተኛው ገጽታ፣ ኢየሱስን እንዲታዘዙ ማስተማሩ፣ በመጀመሪያና ከሁሉ አስቀድሞ የመጋቢያንና የአስተማሪዎች ግዴታ ነው፤ ሰዎቹን ቅዱሳት መጻሕፍትን ማስተማር፣ በሁለተኛነት ደግሞ ከልባቸው በታማኝነት ቃሉን እንዲፈጽሙ መምከር ነው። በቀላል መንገድ ለማስቀመጥ፣ ሕዝቡ መመሪያን ለማግኘት ወደ መጋቢያቸው ይመለከታሉ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ቊልፍ ሰው እንደ ሆነ አድርገው ይመለከቱታል።
ሕዝቡ ወደ አምልኮ መርሓ ግብር የሚመጣው አብዛኛውን ጊዜ ለአንድ ሰዓት ብቻ ሲሆን፣ ግማሹን ጊዜ ደግሞ የሚወስደው በዝማሬና በጸሎት መሆኑ የታወቀ የሕይወት እውነታ ነው። ይህም፣ ሁለተኛው አጋማሽ ከሠላሳ ደቂቃ በላይ ለማይፈጅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ የሚውል መሆኑን ያመለክታል። በውጤቱም፣ በቤት ውስጥ ትጋትን የተሞላ ንባብ ከሌለ በቀር፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት ዕውቀታቸው በጣም ደካማ ይሆናል። ዕውቁ የስታቲስቲክ ምሁር ጆርጅ ባርና፣ አሜሪካን ቤተ ክርስቲያን በሚሄዱ ሰዎች መካከል ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ጥናት አድርጎ እዚህ ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
እንዲሁም፣ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ብዙ ጊዜን፣ ትኵረትንና ጒልበትን የሚወስደው የመጽሐፍ ቅዱስን ይዘት ለሰዎች ማስተማር፣ ሰዎች ራሳቸውን በደንብ ካላዘጋጁባቸው ሁለት አቅጣጮች መኻል አንዱ መሆኑ በጣም የሚደንቅ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጣውን፣ ጠቃሚ የሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶችን ለማስተማር የሚረዳውን ቴክኖሎጂ የመጠቀሙ አዝማሚያ (trend)፣ ሰባኪዎቻችንና የሃይማኖት አስተማሪዎቻችን ካሏቸው መሣሪያዎች በተጨማሪ ዐጋዥ ነው። ቢሆንም ጥናቱ እንደሚያመለክተው ብዙ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ክርስትና እምነት ወይም በዓለም ውስጥ ስላላቸው ሚና በቂ ዕውቀት እንዳላቸው አይሰማቸውም፤ ብዙዎቹም ግድ አይሰጣቸውም።
ከዚህም በላይ አለ። የዊሎው ክሪክ ማኅበረ ሰብ ቤተ ክርስቲያን መጋቢ የሆነውና ስኬታማው ሰባኪ ቢል ሃይብልስ፣ ባለፈው ዓመት፣ ዐሥራ ሁለት ሺሕ አባላት ያሉባትን ሜጋ ቤተ ክርስቲያናኑን ከመምራት እንደ ጐደለ (እንደ ፎረሸ) መግለጫ ሰጥቷል። በመንፈስ የበሰሉ ክርስቲያኖችን ባለማፍራቱ ስሕተት እንደ ሠራ ተቀብሏል። በሺሖች የሚቈጠሩ ሰዎችን ደርሷል፤ ነገር ግን ደቀ መዛሙርት አላደረጋቸውም። በዚህ ጕዳይ ሃይብልስ ብቻ ሳይሆን፣ ራሳቸውን የመረመሩ መጋቢያን ከርሱ ጋራ ይስማማሉ።
የእያንዳንዱ መጋቢ ዐላማ፣ የቤተ ክርስቲያን አባላት ወደ ሥራ ገበታ በቃለ እግዚአብሔር ዕውቀት እንዲገቡና በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው እንዲተገብሩት ማስታጠቅ ነው። ይህም ማለት፣ የሚገዛውና የሚሸጠው ሰው፣ ሁሉን ነገር የሚያየው የእግዚአብሔር ዐይን ሁልጊዜ ማንኛውንም ግብይት እንደሚመለከት መገንዘብ ይኖርበታል። በተለየ መንገድ ለማስቀመጥ፣ ሁላችንም ሁልጊዜ በእግዚአብሔር መገኘት ውስጥ ነን፤ ይህም “ኮራም ዴኦ” በተሠኘው በላቲኑ ሐረግ የተጠቃለለ ነው።
በጥቅምት 10/1898 ዓ.ም. (እ.አ.አ.)፣ የደች የሥነ መለኮት ምሁርና መሪ የሆነው ዶ/ር አብርሃም ኩይፐር በፕሪንስተን ሥነ መለኮታዊ ሴሚናሪ ላይ ተከታታይ ትምህርቶቹን ሰጠ። በዓለም ውስጥ ክርስቶስ “የእኔ ነው” ያላለው፣ አንድ ካሬ ኢንች ስፋት እንኳ እንደሌለ በመግለጽ የክርስትናን ንጽረተ ዓለም አስቀምጧል። ስለዚህ፣ ማንም ሰው በሕይወት ውስጥ የተከበረ ሥራ ላይ ተሰማርቶ ከተገኘ፣ ለኢየሱስ ክርስቶስ መገዛት አለበት። ምክንያቱም፣ ጳውሎስ እንደ ጻፈው፣ የተሰወረ የጥበብና የዕውቀት ሀብት ሁሉ የሚገኘው በርሱ ዘንድ ነው (ቈላስይስ 2፥3)። ይህ ማለት፣ ሁሉም የሕይወት እውነታና ሁሉም ነገር የክርስቶስ ንብረት ነው።
ቤተ ክርስቲያን ድርጅት ናት ወይስ አካል (organism)? በእነዚህ ሐሳቦች መካከል ልዩነት መፈጠር አለበት። በአብዛኛው ድርጅት ውስጥ፣ እያንዳንዱ አባል ዓመታዊ መዋጮን እንዲከፍል ይጠየቃል፤ ነገር ግን አንድ አባል ይህን ገንዘብ ካላዋጣ፣ እንደ እውነታው ከሆነ አባልነቱ ይሰረዛል። ይህም፣ አንድ ድርጅት ሕያው አካል አለመሆኑን ያመለክታል፤ ምክንያቱም አባልነትን የሚይዘው የንግድ መልክ ባለው አካሄድ ነው። በተቃራኒው፣ ቤተ ክርስቲያን አካል ናት ስንል፣ ወዲያውኑ አካል ሕያው እንደ ሆነ እንረዳለን። አካል በሕይወት የተሞላ ነው፤ ዘወትር እያደገና እየተስፋፋ ይሄዳል። ሁለንተናዊ የሆነን የሕይወት አቀራረብ መያዝን ይጠይቃል፤ ልጆችን በክርስቲያን ቤት ውስጥ ማሳደግን፣ የባልንና የሚስትን በፍቅርና በመተማመን መንፈስ ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን፣ በዐሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች አምላክን የሚያስከብር ሕይወት እንዲኖሩ መምራትንና ማቅናትን፣ የተቸገሩትን መርዳትና ፍላጎታቸውን ማሟላትን፣ የታመሙትንና አረጋውያንን መጠየቅን፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ትመጣ ዘንድ ከልብ መጸለይን እነዚህን ሁሉ ይጠይቃል።
በሌላ አገላለጽ፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰዎች ሰንበት ማለዳ ለአንድ ወይም ለሁለት ሰዓታት የሚሰባሰቡባት ስፍራ ብቻ አይደለችም። ብዙ ጊዜ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ የሚዘነጋውን፣ የመጋቢውን ስብከት መስማትንም ብቻ አያመለክትም። ይልቁንም፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለየዕለቱ የሕይወት ክፍል በቁም ነገር በመውሰድ፣ በሥራና በንግድ፣ በሐኪሞችና በበሽተኞች፣ በጠበቆችና በደንበኞቻቸው፣ በመምህራንና በተማሪዎች፣ በመንግሥት ባለ ሥልጣናት ማለትም በፕሬዝደንቶች፣ በጠቅላይ ሚኒስትሮችና በሕግ አውጪዎች እንዲሁም በእኛ ላይ ሥልጣን በተሰጣቸው ሰዎችና በተራ ዜጎች ግዴታዎች መኻል ባሉት በእነዚህ ሁሉ ግንኙነቶች፣ የቅዱሳት መጻሕፍትን አስተምህሮ ተግባራዊ ማድረግ ነው።
ስለዚህ እንዴት መኖርና ወደ ፊትን መጠባበቅ እንችላለን? ጌታችንንና አምላካችንን በመታመን እንዲሁም ትእዛዛቱን በመጠበቅ ነው። ከርሱ ጋራ በየዕለቱ መኖር፣ ብሩህ ወደ ፊትን ከደማቅ ክብር ጋራ ያስከትላል፤ በሕይወት ጐዳና የሚመራን እግዚአብሔር ነውና። ከመዝሙረኛው ጋራ እንዲህ እንላለን፤ “እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዕወቁ፤ እርሱ ፈጠረን፤ እኛም የርሱ ነን፤ እኛ ሕዝቡ የማሰማሪያው በጎች ነን” (መዝሙር 100፥3)።