በዩናይትድ ስቴትስ ከተካሄደው የምርጫ ወቅት በተሻለ፣ ስለ “ሁለቱ መንግሥታት” አስተምህሮ የሚያስታውሰን ጊዜ የለም፤ ይህም የአሜሪካ ፕሮቴስታንቶች ከእምነታቸውና ከልምምዳቸው ይልቅ፣ በፖለቲካ ታማኝነታቸው ምክንያት የተከፋፈሉ የሚመስሉበት ወቅት ነው።
በ410 ዓ.ም. ሮም በአረማውያን ከተጠቃችና ከተመዘበረች በኋላ በተከሠተው ድንጋጤ መኻል፣ የሂፖው ጳጳስ የነበረው፣ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን አባት ኦገስቲን፣ ታዋቂውን “የእግዚአብሔር ከተማ” (City of God) የተሠኘውን መጽሐፍ ጻፈ። ሌላው ታዋቂ የቤተ ክርስቲያን አባት ጄሮም፣ ተስፋ በመቊረጥ እንዲህ አለ፤ “ሮም ከወደቀች ዘንዳ፣ በቤተ ክርስቲያን ላይስ የሚከሠተው ምን ይሆን?” እንደ አንድ አገር ወዳድ፣ ኦገስቲንም ተመሳሳይ ቊስል እንደ ተሰማው ጥርጥር የለውም፤ ነገር ግን እንደ አንድ ክርስቲያን መጋቢ፣ ኦገስቲን ኩነቱን እንደ መግቦታዊ አጋጣሚ አድርጎ በመቀበል፣ እግዚአብሔር ለሚስዮናውያን የሚስዮን ሜዳ (mission field) ያመቻቸላቸው ጊዜ መሆኑን ገለጸ። ከሕዝባዊ ሃይማኖት ጋራ በመቀየጥ የክርስትና እምነት በተዳከመባት በግዛቱ ሥር፣ ጥያቄው ብዙ “ሚሲዮናውያን” ቀርተው ይሆን? የሚለው ነበር።
በእኛ ሥልጣኔና ባህል ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታ ቢያጋጥመን፣ ኦገስቲን ለቀውሱ ያቀረበው ጥበብ በርግጥ ያስፈልገናል። ልክ እንደ ሌሎች ታላላቅ መጻሕፍት፣ የእግዚአብሔር ከተማ የተሠኘው መጽሐፉ፣ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች በልዩ ልዩ መንገድ ቢተረጐምም፣ የሁለቱ መንግሥታት አስተምህሮ ተብሎ የሚጠራውን ትምህርት ለመፍጠር ያበረከተው አስተዋጽኦ ግን አያከራክርም።
እንደ ኦገስቲን ገለጻ፣ በሁለቱ ከተሞች ማለትም በእግዚአብሔር ከተማና በሰው ከተማ መኻል ያለው ልዩነት፣ በሁለቱ ፍቅሮች ላይ የተመሠረተ ነው፤ እነርሱም የእግዚአብሔር ፍቅርና የራስ ፍቅር ናቸው። ፊተኛው ወደ እውነተኛ ኅብረትና የጋራ ወደ ሆነ የመስጠት እና የመቀበል አንድነት ያመራል፤ ኋለኛው ግን ሁከትን፣ ጦርነትንና በሌሎች ላይ የበላይ የመሆን ምኞትን ይወልዳል።
ኦገስቲን እንደሚለው፣ በዋናነት፣ እነዚህ ሁለቱ ፍቅሮችና ሁለቱ ከተሞች የተመሠረቱት በእግዚአብሔር ዘላለማዊ አስቀድሞ ውሳኔ ላይ ነው። የሰው ከተማ መጨረሻው ጥፋት ቢሆንም፣ እግዚአብሔር ከዚህ ጥፋት አዲስ ከተማን (ቤተ ክርስቲያንን) እየፈጠረና በክርስቶስ ዳግም ምጽአት የመጨረሻው ሰላምና ፍትሕ እስኪሆን ደረስ አሮጌውን ከተማ በጋርዮሽ ጸጋው እየጠበቀ ነው።
በዚህ የጋርዮሽ ጸጋ ዘመን፣ እግዚአብሔር፣ “ዝናቡን ለጻድቃንም ለኀጥኣንም ያዘንባል”፤ ርኅራኄውንም እንድናንጸባርቅ ጠርቶናል (ማቴዎስ 5፥43-48)። ስለዚህ ክርስቲያኖች ሁለት ጥሪዎች አሏቸው፤ እነርሱም፣ የርሱ አካል እንድንሆን በክርስቶስ የተደረገው ከፍ ያለ ጥሪ እና ዜጎች፣ ወላጆች፣ ልጆች፣ ጓደኞች፣ ዐብሮ ሠራተኞችና ጐረቤቶች እንድንሆን ወደ ዓለም የተጠራንበት ጥሪ ናቸው። እግዚአብሔር ለፍጥረቱ አሁንም ታማኝ ስለ ሆነ፣ አንጻራዊ ሰላምና ፍትሕ ያላት ምድራዊ ከተማ ልትኖር ትችላለች፤ እርሱ ለዕቅዱና ለዐላማው ታማኝ ስለ ሆነ፣ እውነተኛ ሰላምና ፍትሕ የምታመጣ ቤተ ክርስቲያን በየጊዜውና በየቦታው አለች። ይህንም የሚያደርገው፣ በቅድሚያ ኀጥኣንን ከክርስቶስ ጋራ አንድ በማድረግ (በማስታረቅ)፣ ቀጥሎም አንድ ቀን ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ጠብን ሁሉ ከምድር በማጥፋት ነው።
ይህን ተከትሎም፣ እያንዳንዱ ከተማ በተለያዩ መንገዶች የተለያዩ ዐላማዎችን የሚያራምድበት የራሱ አገዛዝ ይኖረዋል። አንዳንድ ዜጎቿ ወደ እግዚአብሔር ከተማ ዜግነት ቢለወጡም፣ ምድራዊቷ ከተማ ሁልጊዜ ባቢሎን ናት። ልክ እንደ ዳንኤል፣ አማኞች ለከተማዋ ይጸልያሉ፤ በርሷ ውስጥ ይሠራሉ፤ ለአጠቃላይ ደኅንነቷ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፤ እንዲያውም በሠራዊቷ ውስጥ ሆነውም ይዋጋሉ። ነገር ግን፣ ስደተኞችና ተጓዦች መሆናቸውን በጭራሽ አይረሱም። ባቢሎን ፈጽሞ የተስፋይቷ አገር አይደለችም።
ቤተ ክርስቲያን በምድራዊቷ ከተማ ሊኖር ከሚችለው አንጻራዊ ሰላም ተጠቃሚ ልትሆን ብትችልም፣ የእግዚአብሔር መንግሥት የምትስፋፋው፣ ግዛቱ አስገዳጅ ኀይላትን ተጠቅሞ ሰዎች እንዲያምኑ በማድረግ ሳይሆን፣ በወንጌሉ ዐዋጅ አማካይነት ነው City of God, 19.26–27)። እነዚህን ሁለት ከተሞች፣ “አሁን ባለው ዐላፊ ዓለም ውስጥ፣ የተቀላቀሉና የተዋሐዱ ሆነው እናገኛቸዋለን (11.2)። ኅብረተ ሰቡን ለመጠበቅና ለማስፋፋት፣ ክርስቲያን ካልሆኑ ዜጎች ጋራ የምናደርጋቸው መልካም ተግባራት በርግጥ በጎ ቢሆኑም፣ የመጨረሻ በጎዎች (ultimate goods) ግን አይደሉም። ክርስቶስ በክብር ተመልሶ ከመጣ በኋላ፣ ምድራዊቷ ከተማ በጭራሽ ወደ እግዚአብሔር ከተማ አትለወጥም። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ፖለቲካን መቅረብ ያለበት፣ ዓለምን እንዴት በሚገባ ማዳን ይቻላል በሚል ጥያቄ ሳይሆን፣ በዚህ በመካከለኛው ዘመን ዓለምን እንዴት በሚገባ አገለግላለሁ በሚል ጥያቄ ነው።
በመካከለኛው ዘመን ሁሉ፣ እስራኤል በሲና ከእግዚአብሔር ጋራ ያደረገችው ብሔራዊ ቃል ኪዳን ለክርስቲያኑ ዓለም (christendom) ምሳሌ ሆኖ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። በጦርነቱ ሰማዕታት የሚሆኑ ወዲያውኑ ወደ ገነት እንደሚገቡ ተስፋን በመስጠት፣ ጳጳሳት በ“ከሓዲዎች” (አብዛኛውን ጊዜ ሙስሊሞች) ላይ የመስቀል ጦርነትን ያውጁ ነበር። ነገሥታት ራሳቸውን እንደ ንጉሥ ዳዊት አድርገው በመቊጠር፣ የጌታን ሠራዊት እየመሩ ቅድስቲቱን ምድር ያነጻሉ። የክርስቲያን ግዛት ወይም የክርስቲያን አገር የሚለው ሐሳብ፣ ሁለቱን ከተሞች የመቀየጥ ውጤት ነው። ሉተርና ካልቪን የኦገስቲንን የ“ሁለቱ መንግሥታት”ን ሐሳብ ዳግም ያደሱት፣ በክርስቶስ መንግሥትና በእስራኤል ምድራዊ አገዛዝ ዙሪያ ከነበረው ከዚህ መቀየጥ በተቃርኖ ነበር።
እንደ ኦገስቲን፣ ሉተር በ“ሰማያዊ ነገሮች”ና በ“ምድራዊ ነገሮች”፣ በእግዚአብሔር ፊት ባለ ጽድቅና በሰዎች ፊት ባለው ጽድቅ መኻል ያለው ልዩነት ላይ አጽንኦት ሰጥቷል። በአንድ በኩል፣ ሐዳሲያኑ፣ በቃል ስብከት የሚስፋፋውን የክርስቶስ መንግሥትና ምድራዊውን መንግሥት፣ ሮም መቀየጧን ይቃወሙ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ምድራዊቷን ከተማ እንደ ክፉና የክርስቲያኖች ተሳትፎ እንደማያስፈልጋት የሚቈጥረውን የአና ባፕቲስት እንቅስቃሴንም ይቃወሙ ነበር።
ካልቪን፣ “ሰው ሠራሽ መንግሥት” በማለት የሚጠራውን የክርስቲያኑን ዓለም ዕሳቤ በመቃወም፣ እንዲህ ብሏል፣ “በሁለት ድርብ መንግሥት ሥር እንዳለን መገንዘብ አለብን…ስለዚህ (እንደ ተለመደው) ፈጽሞ የተለያዩ ባሕርያት ያሏቸውን ሁለቱን መንግሥታት፣ በሞኝነት እንቀይጣቸዋለን።” አካልና መንፈስ በባሕርያቸው (intrinsically) እርስ በርሳቸው ሳይቃረኑ የተለያዩ ነገሮች እንደ ሆኑ ሁሉ፣ “የክርስቶስ መንፈሳዊ መንግሥትና ሕዝባዊ ሥልጣንም ፍጹም የተለያዩ ናቸው። …ይሁን እንጂ ይህ ልዩነት የመንግሥትን መላ ተፈጥሮ እንደ ረከሰ፣ ከክርስቲያኖች ጋራ ምንም ግንኙነት እንደሌለው አድርጎ ወደ መቊጠር አያመራንም።” እነዚህ ሁለት መንግሥታት “የተለያዩ” ናቸው፤ ሆኖም ግን “በተቃርኖ አይደሉም” (Institutes of the Christian Religion, 4.20.1-2)።
ልክ እንደ ኦገስቲን፣ ካልቪንም በተመሳሳይ ጊዜ የተፈጥሮ ሥርዐትን ደግሞም በኀጢአት ምክንያት የላቀውን ኅብረተ ሰብ ማፍራት አለመቻሉን ያረጋግጣል። በፍጥረት በተደረገው ቃል ኪዳን አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋራ እንደ ፈጣሪነቱ ሁሉም ሰው ስለ ተሳሰረ፣ በኀጢአት ምክንያት የተላለፈውን ባህላዊ ግዴታ (cultural mandate) ወራሽ ነበር። ይሁን እንጂ፣ ባህላዊ ግዴታ በጸጋ ኪዳን ውስጥ ከሚገኘው ከታላቁ ተልእኮ የተለየ ነው። የጋርዮሽ ጸጋ ግቡ ፍጥረትን ፍጹም ማድረግ አይደለም፤ ነገር ግን ኀጢአትን መግታት እንዲሁም የዜግነት ባሕርያትንና (virtues) ጥበቦችን ማነቃቃት ነው፤ ይህም፣ እግዚአብሔር የራሱን ዘላለማዊቷን ከተማ የመዋጀት ዐላማውን በመፈጸም ላይ ሳለ፣ ባህል የራሱን ጠቃሚ ነገር ግን የተገደበ፣ ጊዜያዊና ዓለማዊ ግቡን እንዲያሟላ ያደርገዋል።
መንግሥት ሕጋዊ (legitimate) የሚሆነው፣ በቀጥታ በመጽሐፍ ቅዱሳዊው ሕግ ሥር ብቻ እስከ ተመራ ድረስ ነው በማለት ችክ ላሉት አክራሪ ሐዳሲያን፣ ካልቪን ምላሽ ሲሰጥ እንዲህ በማለት ያውጃል፤“የእግዚአብሔርን ሕግ ለማክበር ፍጹም ተስማሚ በሆነው በዚህ ብዝኃነት አንድ ሰው ቅር የሚሠኝ ከሆነ፣ ይህ ሰው የሕዝቡን ደኅንነት የማይፈልግ ተንኮለኛና በጥላቻ የተሞላ ነው። በሙሴ በኩል የተሰጠው የእግዚአብሔር ሕግ ተሽሮ አዳዲስ ሕግጋት ከተመረጡ፣ ያ ሕግ ይረክሳል የሚለው የአንዳንዶች አባባል፣ ሙሉ በሙሉ ከንቱ ነው” (Institutes, 4.20.8, 14)። በመጨረሻም፣ ካልቪን እንዲህ ይላል፤ “እኛ የግብረ ገብ ሕግ በማለት የምንጠራው የእግዚአብሔር ሕግ፣ የተፈጥሮ ሕግ እንዲሁም እግዚአብሔር በሰዎች ልቡና ውስጥ የጻፈው የኅሊና ምስክርነት እንጂ ሌላ ነገር አለመሆኑ የተረጋገጠ እውነታ ነው። ጳውሎስ እንደሚጠቊመው፣ በዘመኑ በነበረው አረማዊ ሁኔታ ውስጥም እንኳ፣ የማያምኑ ሰዎች በፍትሓዊነትና በጥበብ ሊገዙ ይችላሉ (ሮሜ 13፥1-7)።”
በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ተስፋ እንዳደረጉት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ለሲናው አምላካዊ አገዛዝ (theocracy) ዳግም ነፍስ አልዘራም። ሮማውያንን ከምድሪቱ ከማስወጣት ይልቅ፣ ጠላቶቻችንን እንድንወድድ አዘዘ። ኢየሱስ ከአይሁድና ከአሕዛብ የተውጣጣችውን አዲሲቱን እስራኤል በመንፈሱ፣ በቃሉና በቤተ ክርስቲያን ሥርዐቶች አማካይነት ወደ ራሱ ሰብስቦ፣ አንድ ቀን በክብር የሚገለጠውን የጸጋ መንግሥት አበሰረ። በእነዚህ ሁለት መምጣቶች መኻል ባለው ጊዜ፣ ስንዴው ከእንክርዳዱ ጋራ ዐብሮ ይበቅላል፤ የነጐድጓድ ልጆች መልእክታቸውን በማይቀበሉት ላይ አሁኑኑ እዚሁ ፍርድን በማዘዛቸው ምክንያት ይገሠጻሉ፤ አማኞችም ለሐዋርያት ትምህርት፣ ለኅብረት፣ እንጀራውን ለመቊረስና ለጸሎት በቋሚነት ይሰባሰባሉ (ሐዋርያት ሥራ 2፥42)። ቤተ ክርስቲያን በወንጌል ስብከት፣ በጥምቀት፣ በጌታ ራት፣ በጸሎትና በተግሣጽ (discipline) አስተዳደርዋ አማካይነት፣ ለክርስቶስና እርሱ ሁሉ በሁሉ ለሚሆንበት ለሚመጣው ዘመን ምስክር በመሆን፣ በምድራዊቷ ከተማ ውስጥ የገባች የእግዚአብሔር አዲስ ኅብረተ ሰብ ናት።
በዛሬው ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ባለው የክርስቲያን ዐጥሮቻችን ሥር፣ “የክርስቲያኑን ዓለም”(Christendom) ምልከታ መለየት እንችላለን፤ ይህም፣ አንዳንዶች አሜሪካን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ነጻነትን ለማምጣት መለኮታዊ ተልእኮ የተጣለባት የክርስቲያን አገር አድርገው የሚያስቡበት ምልከታ ነው። በርግጥ፣ ክርስቲያኖች ሰማያዊውንና ዘላለማዊውን የወንጌሉን ዐርነት፣ እንዲሁም ጊዜያዊውንና ምድራዊውን ከፍትሕ የመጓደል ዐርነት የማወጅ ግዴታ አለባቸው። ነገር ግን እነዚህ ሁለቱ የተለያዩ ናቸው። ስንቀይጣቸው፣ መንግሥቱን በራሳችን እጅ ውስጥ በማስገባት፣ ከጸጋ መንግሥትነት ወደ ክብርና ኀይል መንግሥትነት እንለውጠዋለን።
ደግሞም ተቃራኒው፣ ይህም ይበልጥ አናባፕቲስትን የሚወክለው ምልከታ እንዳለ እናስተውላለን፤ ወንጌላዊው ዲ.ኤል. ሙዲ ይህን እንዲህ ሲል አረጋግጧል፣ “ይህን ዓለም እንደ ተሰበረ መርከብ እመለከተዋለሁ። እግዚአብሔር የሕይወት ማዳኛ ጀልባ ሰጥቶኝ፣ ‘ሙዲ፣ የምትችለውን ሁሉ አድን’ ብሎኛል።” እንደዚህ ምልከታ ከሆነ፣ በዓለም ውስጥ የጐረቤቶቻችንን ኑሮ ማሻሻል፣ ለሚሰጥመው መርከብ የመደገፊያ ብረቶቹን እንደ ማስዋብ ነው። ክርስቲያኖች አብዛኛውን ጊዜ የዓለማዊ ጥሪያቸውን ዋጋ ሳይገነዘቡ፣ በግል ድነታቸው (በራሳቸውም ሆነ በሌሎች) ላይ ብቻ እንዲያተኲሩ ይበረታታሉ።
ነገር ግን ከእነዚህ ሁለት መንግሥታት መኻል መምረጥ አያስፈልገንም። የሁለቱም ዜጋ እንደ መሆናችን፣ የቤተ ክርስቲያንና የዓለም ጥሪያችንን በተለያየ መንገድ እንዲሁም በተለያየ ዘዴ እንፈጽማለን። ባህልን ለማድነቅ፣ እንዲሁም ለእኛ ሆነ ክርስቲያን ላልሆኑ ጐረቤቶቻችን እግዚአብሔር የሰጠውን ስጦታዎች ተጠቅመን ለመሳተፍ፣ ባህልን “ክርስቲያናዊ” ማድረግ አይጠበቅብንም። ክርስቶስ ዳግም እስኪመለስ ድረስ በምድራዊ ጥሪዎቻችን ታማኝ እንድንሆን ብንጠራም እንኳ፣ ከአብርሃም ጋራ፣ “መሠረት ያላትን፣ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ” እንጠባበቃለን (ዕብራውያን 11፥10)።