በሰዎች ልጆች ፊት፣ ለሚፈሩህ ያስቀመጥሃት፣ መጠጊያ ላደረጉህም ያዘጋጀሃት፣ በጎነትህ ምንኛ በዛች! (መዝሙረ ዳዊት 31፥19 )
በመዝሙር 31፥19 ላይ የሚገኙ ሁለት ወሳኝ እውነቶችን ተመልከቱ።
1. የጌታ በጎነት
ልዩ የሆነ የእግዚአብሔር በጎነት አለ። የእግዚአብሔር በጎነት የተለየ የበጎነት ዓይነት ነው። ይኸውም፣ እግዚአብሔር ፀሓይን ለክፉዎችና ለደጎች በማውጣት ለሰዎች ሁሉ የሚያሳየው መልካምነት አይደለም (ማቴዎስ 5፥45)። ነገር ግን መዝሙረኛው እንደሚለው፦ “ለሚፈሩት” ልዩ የሆነ በጎነት አለው።
ይህ በጎነት ከመታወቅ የሚያልፍና የተትረፈረፈ ነው። ወሰን የለውም። ለዘላለምም ይኖራል። ሁሉን ነገርም ያቀፈ ነው። ለሚፈሩት ብቻ የሆነ ልዩ በጎነት ነው። ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ ይደረግላቸዋል (ሮሜ 8፥28)። ደግሞም በሮሜ 5፥3-5 መሠረት፣ ህመማቸው እንኳ ሳይቀር ትርፍን ያስገኝላቸዋል።
እርሱን የማይፈሩት ግን ጊዜያዊ መልካምነቱን ያገኛሉ። ሮሜ 2፥4-5 ይህንን ሃሳብ እንዲህ ሲል ይገልጠዋል፦ “ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሓ የሚመራህ መሆኑን ሳትገነዘብ፣ የቸርነቱን፣ የቻይነቱን የትዕግሥቱን ባለጠግነት ትንቃለህ? ነገር ግን በድንዳኔህና ንስሓ በማይገባ ልብህ ምክንያት ትክክለኛ ፍርዱ ሲገለጥ በእግዚአብሔር የቊጣ ቀን በራስህ ላይ ቊጣን ታከማቻለህ።” ቸርነት። መቻል። ትዕግስት። በጎነት። ነገር ግን ከድንዳኔ ጋር እንጂ እግዚአብሔርን ከመፍራት ጋር አይገናኝም።
የመጀመሪያው እውነት ይህ ነው፦ የጌታ በጎነት።
2. እግዚአብሔርን መፍራት
እግዚአብሔርን መፍራት ማለት ከእርሱ መራቅን መፍራት ማለት ነው። ስለዚህም፣ እግዚአብሔርን መጠጊያ በማድረግ ይገለጣል። ለዚህም ነው በመዝሙር 31፥19 ላይ እነዚህ ሁለት ሁኔታዎች የተገለጹት — እግዚአብሔርን መፍራት እና መጠጊያ ማድረግ። “በሰዎች ልጆች ፊት፣ 1) ለሚፈሩህ ያስቀመጥሃት፣ 2) መጠጊያ ላደረጉህም ያዘጋጀሃት፣ በጎነትህ ምንኛ በዛች!”
የሚቃረኑ ሃሳቦች ይመስላሉ። ፍርሃት አባራሪ ይመስላል፤ በሌላ በኩል ደግሞ መጠጊያ ማድረግ ጋባዥ ይመስላል። ነገር ግን ይህ ፍርሃት ከእርሱ የመራቅ ፍርሃት ወይም ከእርሱ የመሸሽ ፍርሃት መሆኑን ስንመለከት፣ ያኔ እንዴት አንድ ላይ እንደሚሄዱ እንረዳለን።
በቅዱሳን ልብ ውስጥ እውነተኛ መንቀጥቀጥ አለ። “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ” (ፊልጵስዩስ 2፥12)። ነገር ግን፣ ይህ መንቀጥቀጥ ልክ አንድ ልጅ አባቱ በባህር ውስጥ ከመስጠም ጎትቶ ካወጣው በኋላ፣ በአባቱ እቅፍ ውስጥ ሆኖ እንደሚንቀጠቀጠው ዓይነት ነው። አባታችን አያስፈልገንም ብለን ባሰብነው አስፈሪ ሃሳብ ላይ መንቀጥቀጥ ማለት ነው።
ስለዚህ የጌታን በጎነት አክብሩት ደግሞም ውደዱት። ከእርሱ መራቅን ፍሩ። ከኃጢአት ሁሉ ሽሹና እርሱን መጠጊያ አድርጉት። “ለሚፈሩህ ያስቀመጥሃት፣ መጠጊያ ላደረጉህም ያዘጋጀሃት፣ በጎነትህ ምንኛ በዛች!”