አዶኒራም ጀድሰን (1788-1850)
አዶኒራም ጀድሰን በሕይወት ዘመኑ የደረሱበት መከራዎች ታሪክ እጅግ አስገራሚ ነው። “ይህኛውስ አሰቃቂ ነው፤ ከዚህ የባሰ ምንም ሊደርስበትና ሊቋቋመው አይችልም” ስትሉ ሌላ ደግሞ ይገጥመዋል። እንዲያውም ከእግዚአብሔር ረጅም ታሪካዊ እይታ አንጻር ካላየነው በቀር በጣም አስደንጋጭ ሊሆንብን ይችላል። በማይናማር (ቀድሞ በርማ ተብላ በምትታወቀው ቦታ) ሺሕ ጊዜ የሞተው ዘር ስለ ክርስቶስ ላለ ታላቅ እንቅስቃሴ ሕይወትን ሰጥቷል።
«የጀድሰን ሕይወት፣ ደግማ ደጋግማ በማይናማር አፈር ውስጥ ወድቃ የሞተች የስንዴ ፍሬ ናት።»
አዶኒራም ጀድሰን ሐምሌ 1813 በርማ ሲገባ፣ ቦታው በጥል የተሞላ እና ፈጽሞ በወንጌል ያልተደረሰ ነበር። ከጥቂት ወራት በፊት በሕንድ እያሉ ዊሊያም ኬሪ ጀድሰንን እንዳይሄድ ነግሮት ነበር። ሕግ አልባ በሆነ ጭቆና፣ ከሲያም ጋር በነበረው አስፈሪ ጦርነት፣ የጠላት ወረራዎች፣ ተከታታይ ዐመፆች፣ እና የሃይማኖት መቻቻል አለመኖር ምክንያት ዛሬ ላይ ቢሆን ኖሮ እንደ ዝግ አገር ይወሰድ ነበር። ከዚያ በፊት የነበሩት ሚሽነሪዎች ሞተው ወይም ጥለው ወጥተው ነበር።
ነገር ግን ጀድሰን ወደዚያ የሄደው በጊዜው ለ17 ወራት ሚስቱ ከነበረችው የ23 ዓመት ሴት ጋር ነበር። በዚያ ወቅት 24 ዓመቱ የነበረ ሲሆን፣ ከ33 ዓመት በኋላ አንድ ጊዜ ወደ ኒው ኢንግላንድ ከመሄዱ በቀር በ61 ዓመቱ እስኪሞት ድረስ ለ38 ዓመታት ያክል እዛው ሲሠራ ነበር። የከፈለው መሥዋዕትነት ታላቅ ነበር። ወደ አፈር ውስጥ የወደቀ እና ደግሞ ደጋግሞ የሞተ ዘር ነበር።
ያልተለመደ የትዳር ጥያቄ
ጥቅምት፣ 1808 ፣ ጀድሰን በኒውተን ማሳቹሴትስ በሚገኘው አንዶቨር ሴሚናሪ የገባ ሲሆን፣ ታህሳስ 2 ላይ ራሱን ፈጽሞ ለእግዚአብሔር ሰጠ። በአንዶቨር ሴሚናሪ በወንጌል ያልተደረሱ ቦታዎችን በወንጌል ለመድረስ ታላቅ መቀጣጠል ነበር። ሰኔ 28፣ 1810 ላይ ጀድሰን እና ሌሎችም በምሥራቅ ለሚደረገው የሚሽነሪ አገልግሎት ራሳቸውን አቀረቡ። የዚያኑ ዕለት አን ሃሰልታይንን አገኛት እና በፍቅር ወደቀ። አንን ከተዋወቃት ከአንድ ወር በኋላ ሊያገባት እንደሚፈልግ ገለጸ፤ በመቀጠልም ለአባቷ የሚከተለውን ደብዳቤ ጻፈ፦
በሚመጣው የፀደይ ወቅት መባቻ ልጅዎን ፈጽመው በዚህ ዓለም ዳግም ላያይዋት ለመለያየት ፈቃደኛ ኖትን? መለየቷን እና ለሚሲዮናዊ ሕይወት ችግሮችና መከራዎች አልፋ መሰጠቷን ይፈቅዱ እንደ ሆን፣ ደግሞም ውቅያኖስ ሊያመጣ ለሚችላቸው አደጋዎች፣ የህንድ ደቡባዊ አየር ባሕርይ አደገኛ ተጽእኖ ፣ ለሁሉም ዐይነት ማጣትና ጭንቀቶች፣ ለውርደት፣ ስድብና ስደት ምናልባትም ለአሰቃቂ ሞት እንድትጋለጥ ይፈቅዱ እንደ ሆን እጠይቃለሁ። ሰማያዊ ቤቱን ትቶ ስለ መጣውና ለእርሷ እንዲሁም ለእርሶ ሲል ስለ ሞተው ሲሉ፣ እየጠፉ ላሉት የማይሞቱ ነፍሳት ሲሉ፣ ስለ ጽዮን ሲሉ፣ እንዲሁም ስለ እግዚአብሔር ክብር ሲሉ ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ ጋር ይስማማሉን? በቅርቡ፣ በክብር ዓለም የጽድቅ አክሊል ለብሳ በእርሷ አማካይነት ከዘላለም ዋይታና ሰቆቃ በዳኑ አሕዛብ ምክንያት ለአዳኟ ክብር በሚገባ በምስጋና አድናቆት አሸብርቃ ልጅዎን በማግኘት ተስፋ ከዚህ ሁሉ ጋር ይስማማሉን? (ወደ ወርቃማው ዳርቻ 83)
አባቷ በሚያስደንቅ ሁኔታ ራሷ መወሰን ትችላለች ብለው መለሱ። አዶኒራምና አን የካቲት 5፣ 1812 ዓ.ም. ተጋቡ። ከዚያም ከሌሎች ሁለት ጥንዶችና ገና ያላገቡ ሁለት ሰዎች ጋራ በመሆን ወደ ሕንድ አቀኑ። መርከቡ ሊሰጥም ይችላል ብሎ በማሰብ፣ የሄዱት በሁለት መርከብ ተከፍለው ነበር። በሕንድ ጥቂት ጊዜ ከቆዩ በኋላ አዶኒራምና አን ወደ አዲስ ቦታ ለመሄድ ቆረጡ። ሐምሌ 13፣ 1813 ላይ ራንጉን በርማ ደረሱ።
ረጅምና የሚያሠቃይ መኸር
በበርማም 42 ዲግሪ በሚደርስ ሞቃት አየር ውስጥ ከኮሌራ፣ ማሌሪያ፣ የአንጀት ኢንፌክሽንና የማይታወቁ ሰቆቃዎች ጋር የዕድሜ ልክ ትግል ተጀመረ። በዚህም ውስጥ አንን ብቻ ሳይሆን ሁለተኛዋን ሚስቱንም፣ ከዐሥራ ሦስት ልጆቹ ውስጥ ሰባቱን፣ እንዲሁም አብረውት የሚሠሩትን ተራ በተራ በሞት አጣቸው።
በገጠሙት ተግዳሮቶችና መሰናክሎች ሁሉ ውስጥ ጀድሰን ቋንቋውን ለመማር፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎምና በየመንገዱ ወንጌልን ለመመስከር ይተጋ ነበር። እርሱና አን እዚያ ከደረሱ ከ6 ዓመት በኋላ ማኡንግ ናው የተባለውን የመጀመሪያውን ሰው አጠመቁ። ዘሩን መዝራት ረዥም ጊዜ የፈጀና ከባድ ነበር። ማጨዱ ግን የባሰና ብዙ ዓመታትን የወሰደ ነበር። ነገር ግን በ1831 እዚያ ከደረሱ ከ19 ዓመታት በኋላ በምድሪቱ አዲስ መንፈስ ነበር። ጀድሰን እንዲህ ሲል ጽፏል፡-
የጥያቄ መንፈስ በምድሪቱ ወርድ እና ስፋት ሁሉ በሁሉም ቦታ እየተንሰራፋ ነው። ለጠየቁን ብቻ እየሰጠን ወደ 10,000 የሚጠጉ ትራክቶችን አሰራጭተናል። ወደ 6,000 የሚሆኑ ማመልከቻዎች በቤት ውስጥ ደርሰውናል። አንዳንዶቹ የሚመጡት ከሲያምና ከቻይና ድንበር የሁለትና ሦስት ወር ጉዞ ተጉዘው ነው። “ጌታዬ የዘላለም ሲዖል እንዳለ ሰምተን አስፈርቶናል። እንዴት አድርገን ማምለጥ እንደምንችል የሚያግዘን ወረቀት ስጠን” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ከአቫ 100 ማይል በስተሰሜን ከምትገኘው ከካታይ ድንበር የሚመጡ ናቸው። “ጌታዬ ስለ ዘላለማዊ አምላክ የሚያወራ ጽሑፍ አይተናል። እነዚህን ጽሑፎች የምትሰጠው ሰው አንተ ነህ? ከሆነ እባክህ ለእኛም እንድትሰጠን እንለምንሃለን፤ ከመሞታችን በፊት እውነቱን ማወቅ እንሻለን” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በጥቂቱ ብቻ ከሚታወቅበት ከአገሪቱ ውስጠኛ ክፍል የሚመጡ ናቸው። “የኢየሱስ ክርስቶስ ሰው አንተ ነህ? ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገር ጽሑፍ ስጠን” ይላሉ። (ወደ ወርቃማው ዳርቻ 398-99)
ነገር ግን በ1819 ጌታን በተቀበለው የመጀመሪያው ሰውና በ1831 ባለው የእግዚአብሔር ኀይል መፍሰስ መካከል የተከፈለ ታላቅ ዋጋ ነበር።
እስር ቤት እና ብቸኝነት
በ1823 አዶናሪምና አን ከራንጉን ተነሥተው 300 ማይል ወደ ውስጥ ወደምትዘልቀውና ኢራዋዲ ወንዝን ሽቅብ ወደምትጠጋው ዋና ከተማ አቫ ስፍራ ቀየሩ። ወደ ጨቋኙ አገዛዝ እንዲህ ቅርብ መሆን አስጊ ነገር ነበር። በሚቀጥለው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የብሪቴን የጦር መርከቦች ራንጉን ደረሱ። ቀጥለውም ወደቧን ደበደቡ። ወዲያዉኑ ምዕራባዊያን በሙሉ እንደ ሰላዮች መታየት ጀመሩ። አዶኒራምንም ከቤቱ ጎትተው ወሰዱት። ሰኔ 8፣ 1824 ዓ.ም. እስር ቤት ተጣለ። እግሮቹ ታሰሩ። ማታ ማታ ረጅም አግድም ቀርከሀ በታሰሩት እግሮቹ መካከል ይገባና ዘቅዝቀው ይሰቅሉታል። መሬት ላይ የሚያርፈው ትከሻውና ጭንቅላቱ ብቻ ነበር።
“መከራዎቹ በዚህ ዓለም ብዙ ተስፋ ከማድረግ እንዲላቀቅ አድርገውታል።”
አን ነፍሰ ጡር ነበረች። ነገር ግን በየዕለቱ የሦስት ኪሎሜትር ጉዞ ወደ ቤተ መንግሥት እየተጓዘች ጀድሰን ሰላይ እንዳልሆነ ትሟገትና ምሕረት እንዲያደርጉለት ትማጸን ነበር። ሕዳር 4፣ 1825 ጀድሰን በድንገት ተለቀቀ። መንግሥት ከብሪታንያ ጋር ለሚያደርገው ድርድር አስተርጓሚ እንዲሆንለት አስፈልጎት ነበር። ዐሥራ ሰባት ወራትን በእስር ቤት በሞት አፋፍ ሆኖ አሳልፎ፣ እንዲሁም ሚስቱ የምትችለውን ሁሉ እርሱን ለመንከባከብ ራሷንና ሕፃኗን መሥዋዕት እያደረገች ረጅሙ የመከራ ጊዜ አበቃ። የአን ጤንነት ተንኮታኮተ። ከዐሥራ አንድ ወራት በኋላ በጥቅምት 24፣ 1826 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች። ቀጥሎም ከ6 ወር በኋላ ልጃቸው ሞተች።
“ላገኘው አልቻልኩም”
የሚስቱና የልጁ ሞት ያስከተለበት ሥነ ልቦናዊ ጫና አስከፊ ነበር። ጥርጣሬ አእምሮውን ተቆጣጠረ። ሚሲዮን የሆነው ለስምና ዝና ብሎ እንጂ በትሕትና እና ራስን በመካድ ፍቅር እንዳልሆነ ጥርጣሬ ውስጥ ገባ። እንደ ማዳም ጉዮን፣ ፌኔሎንና ቶማሰ ኬምፒሰ ያሉ ካቶሊካዊ ባህታዊያን የጻፏቸውን መጻሕፍት ማንበብ ጀመረ። ይህም ደግሞ ገዳማዊ ሕይወትና ራስን መቅጣት ውስጥ እንዲገባ አደረገው። እንደ ሕይወቱ ይወድደው የነበረውን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ትርጉም ሥራውን በማቋረጥ ከሰዎች የበለጠ መሸሽ ጀመረ። ከሰዎች ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ትዕቢትን ይደግፋል፣ ወይም ፍስሐን ያበረታታሉ ብሎ ካሰባቸው ነገሮች ሁሉ ሳይቀር ራቀ። (ወደ ወርቃማው ዳርቻ 387)
ከሚኖርበት ጎጆው አጠገብ ጉድጓድ ቆፍሮ ከአጠገቡ በመቀመጥ የሥጋን የመበስበስ ሂደት ያሰላስል ነበር። ለአርባ ቀን በነብር ወደ ተወረረው ጫካ ለብቻው መሽጎ ነበር። በአንድ ደብዳቤውም ሲጽፍ መንፈሳዊ መጠውለግ ይሰማው እንደ ነበር ይናገራል፤ “እግዚአብሔር ለእኔ ታላቅ ምስጢር ሆኖብኛል። በእርሱ አምናለሁ ግን ላገኘው አልቻልኩም” (ወደ ወርቃማው ዳርቻ 391)።
ወንድሙ ኤልናታን በግንቦት 8፣ 1829 ላይ በ35 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ግር በሚያስብል ሁኔታ ለጀድሰን የመታደስ ጅማሮ ሆነለት። ምክንያቱም ከዐሥራ ሰባት ዓመት በፊት አማኝ ሳይሆን ትቶት የሄደው ወንድሙ አሁን አማኝ ሆኖ ስላረፈ ነው። 1830ን ሙሉ ለሙሉ አዶኒራም ከጨለማው እየወጣ የነበረበት ጊዜ ነው።
የተጠናቀቀ መጽሐፍ ቅዱስ እና አዲስ ሕይወት
ከመጀመሪያው አንሥቶ በተለይም በሕይወቱ እንዲህ ባለ ቅያስ ላይ ለጀድሰን የሚስዮን ትጋት ማዕከላዊ የነበረው ነገር የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ነበር። ያለ ሚስትና ልጆች ላሳለፋቸው እነዚህ የመንፈሳዊ ተሐድሶ ዓመታት ራሱን የወሰነው ሙሉ ኀይሉን ማለት በሚቻል ደረጃ የአዲስ ኪዳን ትርጉሙን እንዲሁም በብሉይ ኪዳን ትርጉም ሥራው ላይ እንዲገፋበት በተሠራች አነስተኛ ክፍል ውስጥ ነበር። በ1832 መጨረሻ የተጠናቀቀው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ሦስት ሺህ ቅጂዎች ታተሙ። የብሉይ ኪዳንን በጥር ወር መጨረሻ 1834 ዓ.ም. ላይ አጠናቀቀ።
በበርማ ቋንቋ የተተረጎመው የመጀመርያው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂን ተከትሎ እግዚአብሔር በልፋቱ ደስ የተሰኘ በሚመስል ሁኔታ በአዲስ ሚስት ባረከው። ከሦስት ዓመት ቀደም ብሎ በርማ ውስጥ ጆርጅ ቦርድማን የሚባል ሚስዮናዊ ሞቶ ነበር። ሚስቱ ሣራም እርሱ ከሞተ በኋላ በበርማ ቆይታ የታወቀች ሚስዮናዊት ነበረች። ከልጇ ጆርጅ ጋር ወደ አገሪቱ ውስጣዊ ክፍል ድረስ ዘልቃ ገብታ ነበር። የካቲት 1834 ላይ ጀድሰን ከሣራ ደብዳቤ ደረሰው። ሊያጫትም በመወሰን፣ ሚያዝያ 1 ሙልሜይንን ትቶ ወደ ታቮይ ተጓዘ። ሚያዝያ 10 ላይ ተጋቡ።
በበርማ ካሳለፋቸው አስደሳች ወቅቶች ውስጥ አንዱ ይህ ነበር። ነገር ግን ያለ ሕመም አልነበሩም፤ ደግሞም ከዐሥርት ዓመታትም በላይ የዘለቁ አልነበሩም። በዐሥራ አንድ ዓመት ውስጥ ስምንት ልጆችን ከወለዱ በኋላ ሣራ በጠና ስለ ታመመች ቤተ ሰቡ የባሕሩ አየር ፈውስን ቢያመጣላት ብለው ተስፋ በማድረግ ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ወሰኑ። ጀድሰን አሜሪካ ከሄደ አሁን 33 ዓመታት ሆነውታል። አሁንም እየተመለሰ ያለው ስለ ሚስቱ ሲል ብቻ ነበር። በመስከረም 1845 ዓ.ም. በአፍሪካ ጫፍ ሲደርሱ ሣራ ሞተች። ጉድጓድ ቆፍረው ሚስቱንና የልጆቹን እናት እስኪቀብሩ ድረስ መርከቢቱ በሴንት ሄሌና ደሴት መልሕቋን ጣለች። ሲጨርሱም ጉዟቸውን ቀጠሉ።
የዚህን ጊዜ አዶኒራም እንደ ቀድሞው በድባቴ ውስጥ አልተዘፈቀም። ልጆቹ ነበሩት። ነገር ግን ከዚህም በላይ መከራዎቹ በዚህ ምድር ላይ ብዙ ተስፋ ከማድረግ አላቅቀውት ነበር። ያለመመረርና ድባቴ ሕይወቱን እንዴት እንደሚጠላ እየተማረ ነበር (ዮሐንስ 12፥25)። ጀድሰን አሁን አንድ ታላቅ ፍላጎት ነበረው። እርሱም ተመልሶ ሕይወቱን ለበርማ መስጠት ነበር።
በከባድ ሁኔታና ሥቃይ የሚሞቱት ምንኛ ጥቂቶች ናቸው
ጀድሰን በአሜሪካ የነበረው ቆይታ እንዳቀደው አልሄደለትም። ሁሉንም ባስደነቀ ሁኔታ ኤሚሌ ቹባክ ከተባለች ሴት ጋር ለሦስተኛ ጊዜ ፍቅር ያዘው። ሰኔ 2፣ 1846 ዓ.ም. አገባት። 29 ዓመቷ ነበር። እርሱ ደግሞ 57። ታዋቂ ጸሓፊ ነበረች። ከጀድሰን ጋር ወደ በርማ ለመሄድ ዝናዋንና የጽሑፍ ሥራዋን ተወች። ሕዳር 1846 በርማ ደረሱ። ሁለቱም አይተውት የማያውቁት 4 የደስታ ዓመታትን እግዚአብሔር ሰጣቸው።
አዶኒራምና ኤሚሊ አንድ ልጅ ነበራቸው። ነገሮች ብሩህ ይመስሉ ነበር። ነገር ግን የድሮው በሽታ አዶኒራምን የመጨረሻ አንድ ጊዜ አጠቃው። ብቸኛው ተስፋ ክፉኛ የታመመውን ጀድሰንን በመርከብ አሳፍሮ መላክ ነበር። ሚያዝያ 3፣ 1850 ዓ.ም. አዶኒራምን ተሸክመው ወደ አይል ኦፍ ፍራንስ በምታቀና አሪስቴድ ማሪ በተባለች መርከብ ላይ ከሚንከባከበው ጓደኛው ቶማስ ራኒ ጋር አድርገው ላኩት። በመከራው ወቅት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከባድ ሕመም የተነሣ ያስመልሰው ነበር። ከተናገራቸው የመጨረሻዎቹ ቃላት ውስጥ፣ “ በከባድ ሁኔታና ሥቃይ የሚሞቱት ምንኛ ጥቂቶች ናቸው” የሚል ነበር። (ወደ ወርቃማው ዳርቻ 504)
“ሺሕ ጊዜ የሞተው ዘር፣ በማይናማር ለክርስቶስ ድንቅ ሥራ እንዲኖር ሕይወትን ሰጠ።”
አርብ ከሰዓት 10፡15 ላይ ሚያዝያ 12፣ 1850 ዓ.ም. አዶኒራም ጀድሰን ከቤተ ሰቦቹና በበርማ ካለቸው ቤተ ክርስቲያን ርቆ በባሕር ላይ ሞተ። ያን ምሽት መርከቢቱ ጉዞዋን ገታች። የመርከቢቱ ሠራተኞች በጸጥታ ተሰበሰቡ። የመርከቧን የጎን መጫኛ ከፈቱ። ምንም ጸሎት አልነበረም . . . ትእዛዙን ያስተላለፈው የመርከቧ ካፒቴን ነበር። የሬሳ ሳጥኑ ወደ ጨለማው ተገፍቶ ወጣ። (ወደ ወርቃማው ዳርቻ 505)
ከዐሥር ቀን በኋላ ምንም እንኳ በወሊድ ጊዜ ቢሞትባትም ኤሚሊ ሁለተኛ ልጃቸውን ወለደች። ከአራት ወር በኋላ ባሏ እንደ ሞተ ተረዳች። ቀጣዩ ጥር ላይ ወደ ኒው ኢንግላንድ ተመለሰች። ከሦሰት ዓመት በኋላ በ37 ዓመቷ በሳንባ ነቀርሳ በሽታ ሞተች።
የሞተው ዘር ፍሬ
የጀድሰን ሕይወት በማይናማር መሬት ውስጥ ወድቃ ደግማ ደጋግማ እንደ ሞተች የስንዴ ፍሬ ነው (ዮሐንስ 12፥24)። መከራው ጥልቅ ነበር። ፍሬውም እንዲሁ። ከሁለተኛው ሚሊንየም ወደ ሦስተኛው ሚሊንየም መሻገሪያ ላይ፣ እንደ ፓትሪክ ጆንስቶን ስሌት የማይናማር (የበርማ አዲስ ስም) ባፕቲስት ጉባኤ 3,700 አብያተ ክርስቲያናትን ያቀፈና 617,781 አባላትን የያዘ፣ እንዲሁም 1,900,000 አጋሮችን የያዘ ነው። ይህም የዚህ ዘር መሞት ውጤት ነው።
ርግጥ ነው ከጀድሰን ተጨማሪ በተለያየ ጊዜ የተከሰቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎችም ነበሩ። እነርሱም መጥተው ሕይወታቸውን ሰጥተዋል። ብዙዎቹ የሞቱት ገና ወጣት ሆነው፣ ዕድሜያቸው ከጀድሰን ያነሰ ሆኖ ሳለ ነበር። በማይናማር የታየው አስደናቂ ፍሬ፣ በብዙ ሚስዮናዊያን በተለይም በአዶናሪም ጀድሰን መከራና ሞት ላይ የበቀለ ነው።
በጆን ፓይፐር