በአምስቱ የካልቪኒዝም ነጥቦች የማመን ዐሥር ውጤቶች

ከታች የተዘረዘሩት ዐሥር ነጥቦች፣ በካልቪኒዝም አምስቱ ነጥቦች ማመን ስላለው ተጽእኖ የግል ምስክርነቴ ነው። በቅርቡ በዚህ ርዕስ ላይ ሴሚናር አስተምሬ ስጨርስ፣ የሴሚናሩ ተካፋዮች እነዚህን  የግል ምስክርነቶች እንዲያገኙት በማሰብ በበይነ መረብ ላይ እንድለጥፈው ጠየቁኝ።  እኔም ያንን ለማድረግ ደስተኛ ነኝ። እነርሱ በርግጥ የትምህርቱን ይዘት ከ Desiring God Ministries ድህረ ገጽ ላይ የሚገኘውን ይወስዳሉ፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እኔ “ካልቪኒዝም” የምለውን አስተምህሮ ያስተምር እንደሆነ እንደ ቤርያ ሰዎች ይመረምሩ ዘንድ ተስፋ በማድረግ ለሌሎች እዚህ እጽፍላቸዋለሁ።

  1. እነዚህ እውነቶች እግዚአብሔርን እንድፈራ እና እውነተኛ እግዚአብሔርን ማከል ወደረገ የአምልኮ ጥልቀት ይመሩኛል

በ70ዎቹ መገባደጃ ላይ ኤፌሶንን በቤቴል ኮሌጅ እያስተማርኩ፣ የእግዚአብሔርን ሥራ አጠቃላይ ግብ የሚገልጠውን ሐረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ስመለከት አስታውሳለሁ። ሐረጉም “የጸጋው ክብር ይመስገን ዘንድ” የሚል ነበር (ኤፌሶን 1፥6)።

ይህ ክፍል እግዚአብሔርን ማገዝ እንደማንችልና የእርሱን ፍላጎቶች ለማሟላት ስንጥር ሳይሆን በእርሱ ስንረካ ክብሩ የበለጠ እንደሚያበራ እንዳስተውል አድርጎኛል። “ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነው፤ ለእርሱ ለዘላለም ክብር ይሁን” (ሮሜ 11፥36)። አምልኮ በራሱ የመጨረሻ ግብ ይሆናል።

ፍቅሬ ምን ያህል ዝቅተኛ እና በቂ እንዳልሆነ እንዲሰማኝ አድርጓል። ይህም በመዝሙረ ዳዊት ላይ ያሉትን ጥልቅ ጌታን የመፈለግ መዝሙሮች ይበልጥ እንድረዳቸዉ በማድረግ የማምለክ ጥማቴን ጨምሮልኛል።

  1. እነዚህ እውነቶች መለኮታዊ ነገሮችን ከማቃለል ይጠብቁኛል

ባህላችን መጥፎ ከሆነበት ነገር አንዱ አስመሳይነትን፣ ተፈላጊ የመሆን ጥማትን እና የስኬት ሕይወትን ማራገቡ ነው። ቴሌቪዥን ደግሞ የዚህ የአስመሳይነት እና የከንቱነት ሱሳችን ዋና መጋቢ ነው።

እግዚአብሔር በዚህ ባህል ውስጥ ተውጧል። ስለዚህም መለኮታዊ ነገሮች ይቃለላሉ።

በዘመናችን ትጋት ከመጠን በላይ የሚባል አይደለም። ምናልባት ሚዛን የሳቱ አንዳንድ ሰዎች ዘና ለማለት እና ስለ አየር ሁኔታ ለማውራት እንኳ ጊዜ የሌላችው በጥድፊያ የተሞሉ ይኖሩ ይሆናል።

ሮበርትሰን ኒኮል ስለ ስፐርጅን ሲናገር፣ “አስቂኝ መልክ ያለው የወንጌል ስርጭት ብዙዎችን ሊስብ ይችላል፤ ነገር ግን ነፍስን በአዘቅት ውስጥ ያስቀምጣል፤ እናም የእምነትን መሠረት ይንዳል። ሚስተር ስፐርጅን ብዙ ጊዜ ስብከቱን የማያውቁ ቀልደኛ ሰባኪ እንደሆነ ያስባሉ፤ እንደ እውነቱ ከሆነ እንደ እርሱ ያለ ድምጹ ወጥ የሆነ ትጉ፣ ቅን እና አክባሪ ሰባኪ አልነበረም።” (Quoted in The Supremacy of God in Preaching, p. 57)

  1. እነዚህ እውነቶች፣ በራሴ ድነት እጅግ እንድደነ ያደርጉኛል

በኤፌሶን 1 ላይ እግዚአብሔር ያደረገውን ታላቁን ማዳን ካስቀመጠ በኋላ፣ ጳውሎስ በዚያ ምዕራፍ የመጨረሻ ክፍል ላይ እንዲህ ይጸልያል፦ የዚያ ትምህርት ውጤት የልባችን ዐይኖች በርተው በተስፋችን፣ በርስታችን ክብር ባለጠግነት፣ እና በእኛ ውስጥ በሚሠራው የእግዚአብሔር ኃይል እንድንደነቅ ነው። ይህም ኃይል ከሙታን የማስነሥት ኅይል ነው።

እያንዳንዱ የትምክህት መሠረት ተወግዷል። ከተሰበረ ልብም ደስታ እና ምስጋና ይፈልቃል።

የጆናታን ኤድዋርድስ እግዚአብሔርን መምሰል ማደግ ጀመረ። እግዚአብሔር የራሱን ግርማና የእኛን ክፋት ሲያሳየን፣ ያኔ የክርስትና ሕይወት ከተለመደው የቅድስና መንገድ የተለየ ይሆናል። ኤድዋርድስ እንዲህ ሲል በሚደንቅ ሁኔታ ገልጾታል፦

የቅዱሳን ፍላጎት፣ ምንም እንኳ በቅንነት ቢሆንም የትሕትና ነው። ተስፋቸው ትሑት ተስፋ ነው። ደስታቸውም በቃላት የማይገለጽ እና በክብር የተሞላ ቢሆንም ትሑት ከተሰበረ ልብ የሚወጣ ነው። እናም ክርስቲኖችን የበለጠ በመንፈስ ድሆች እና እንደ ትንሽ ልጅ የሚያደርግ ነው።  ዝቅ የማለትን ባህሪይ የተላበሰ ነው። (Religious Affections, New Haven፥ Yale University Press, 1959, pp. 339f)

  1. እነዚህ እውነቶች ወንጌሉን ከሚመስሉ፣ ሰው ተኮር ትምህርቶች እንድጠነቀቅ ያደርጉኛል

በመጽሐፌ “The Pleasures of God” (2000) ከገጽ 144-145 በ18ኛው ክፍለ ዘመን በኒው ኢንግላንድ የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት መንሸራተት ወደ አርሚኒያኒዝም እና ከዚያም ወደ “ሁሉም ሰው ይድናል” (universalism)፣ በመጨረሻም ደግሞ ሥላሴን ወደ መካድ (Unitarianism) እንዳመራ አሳይቻለሁ። በ19 ኛው ክፍለ ዘመን ከስፐርጅን በኋላ በእንግሊዝ ተመሳሳይ ነገር ተከስቷል።

ኢየን መሪይ Jonathan Edwards፥ A New Biography (Edinburgh፥ Banner of Truth, 1987) በሚለው መጽሐፉ ገጽ. 454 ላይ ተመሳሳይ ነገር አስቀምጧል፦ በሰሜን አሜሪካ የካልቪኒዝም መረዳት እየቀነሰ ሄደ። ኤድዋርድስ በትክክል ባስቀመጠው የውድቀት ሂደት፣ ከታላቁ መነቃቃት በኋላ አርሚኒያኒዝምን የተቀበሉት የኒው ኢንግላንድ ጉባኤያት አብያተ ክርስቲያናት ቀስ በቀስ ስላሴን ወደ መካድ ዩኒታሪዝም (Unitarianism) እንዲሁም “ሁሉም ሰው ይድናል” (universalism) በቻርለስ ቻውንሲ መሪነት ተቀበሉ።

እንዲሁም በJ.I. Packer’s Quest for Godliness (Wheaton, IL፥ Crossway Books, 1990) ገጽ. 160 ላይ ሪቻርድ ባክስተር እነዚህን ትምህርቶች እንዴት እንደተወ እና የሚቀጥሉት ትውልዶች በኪደርሚንስተር በሚገኘው የባክስተር ቤተ ክርስቲያን እንዴት አስከፊ ፍሬ እንዳጨዱ ማንበብ እንችላለን።

እነዚህ አስተምህሮዎች ቤተ ክርስቲያን በተለያየ መልኩ ሰውን ማእከል ካደረጉ ከውጭ ጠንካራና ተወዳጅ ከውስጥ ግን ቀስ በቀስ ከሚያበላሹ እና ከሚያደክሟት አስተምህሮዎች ራሷን የምትከላከልበት ምሽግ ናቸው።

“ቤቱም የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፣ ይኸውም የእውነት ዐምድና መሠረት ነው” (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥15)።

  1. እነዚህ እውነቶች በቃላት ሊገለጽ በማይችል በዓለማዊው፣ እግዚአብሔርን በሚያሳንሰው ባህላችን እንዳዝን ያደርገኛል

እግዚአብሔር በአንዳቸውም ውስጥ እንደሌለ እያወቅኩ ጋዜጣ ማንበብ፣ የቲቪ ማስታወቂያ ወይም ቢልቦርድ ማየት ይከብደኛል።

እግዚአብሔር በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ዋናው እውነታ ሆኖ ሳለ እውነት እንዳልሆነ ነገር ሲቆጠር እየተከማቸ ያለውን የእግዚአብሔርን ቁጣ ሳስብ እፈራለሁ። እደነግጣለሁ! ብዙ ክርስቲያኖች ከዓለም ጋር ተመሳሳይ የሆነ ማስታገሻ መድሐኒት ይወስዳሉ። ነገር ግን እነዚህ የካልቪኒዝም ትምህርቶች ትልቅ መድሐኒት ናቸው።

እናም ለመነቃቃት እና ለተሃድሶ እጸልያለሁ።

በተጨማሪም እግዚአብሔርን በሁሉም ቦታ እና ሁል ጊዜ የሚያሳዩ በእግዚአብሔር የተሞሉ ሕዝቦች እንዲፈጠሩ ለመስበክ እሞክራለሁ።

እኛ የምንኖረው የእግዚአብሔርን እውነታ እና በሁሉም ሕይወት ውስጥ ያለውን የበላይነት እንደገና ለማረጋገጥ ነው።

  1. እነዚህ እውነቶች እግዚአብሔር ያቀደው እና የጀመረው ሥራ፣ በዓለም አቀፍ እና በግል ደረጃ እንደሚጨርሰው እንድተማመን ያደርጉኛል

የሮሜ 8፥28-39 ነጥብ ይህ ነው።  

እግዚአብሔር፣ ለሚወድዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን። እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው፤ ይኸውም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኵር እንዲሆን ነው። አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውን አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን አከበራቸው።

ታዲያ ለዚህ ምን እንመልሳለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል? ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን? እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስስ ማን ነው? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፣ እንዲሁም ከሞት የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እኛ ይማልዳል። ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ራቍትነት፣ ወይስ አደጋ፣ ወይስ ሰይፍ? ይህም፣ “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ ከሞት ጋር እንጋፈጣለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።

ምንም አይለየንም፤ በዚህ ሁሉ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።

  1. እነዚህ እውነቶች ሁሉንም ነገር በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ዓላማዎች ውስጥ እንዳ ያደርጉኛል ሁሉም ነገር ከእርሱ በእርሱ እና ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ለእርሱ ይሁን!

ሕይወት ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር የተያያዘ ነው። እርሱ በጣም አስፈላጊ ያልሆነበት ክፍል የለም። እርሱ ለሁሉም ነገር ትርጉም የሚሰጥ ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 10፥31)።

የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ዓላማ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ሲከወን ማየቴ እና ጳውሎስ “ሁሉን በፈቃዱ ምክር መሠረት እንደሚሰራው” ሲል መስማት ዓለምን በዚህ መንገድ እንድመለከት አድርጎኛል (ኤፌሶን 1፥11)።

  1. እነዚህ እውነቶች እግዚአብሔር ሰዎች እንዲለወጡ የሚደረግ ጸሎትን እንደሚመልስ ተስፋ እንዳደርግ ደግሞም ይህንን ጸሎት የመመለስ ፈቃድ፣ መብት እና ኃይል እንዳለው እንዳውቅ ያደርጉኛል

የጸሎት ግቡ እግዚአብሔር ሰብሮ እንዲገባ እና ነገሮችን እንዲለውጥ ነው፦ የሰውን ልብ ጨምሮ። የሰውን ፈቃድ መቀየር ይችላል። “ስምህ ይቀደስ” ማለት ሰዎች ስምህን እንዲቀድሱ አድርግ ማለት ነው። “ቃልህ ይሩጥ ይከበርም” ማለት ልቦች ለወንጌል ክፍት ይሁኑ ማለት ነው።

የአዲስ ኪዳን ተስፋዎች በልጆቻችን፣ በጎረቤቶቻችን እና በሁሉም የዓለም የተልእኮ መስኮች መካከል እንዲፈጸሙ እግዚአብሔርን መለመን አለብን።

“እግዚአብሔር ድንጋዩን ልብ ከውስጣቸው አውጣ፤ ሥጋ ልብም ስጣቸው” (ሕዝቅኤል 11፥19)

“አምላክ ሆይ! ይወዱህ ዘንድ ልባቸውን ግረዝ” (ዘዳግም 30፥6 )

“አባት ሆይ! መንፈስህን በውስጣቸው አሳድር እናም በሥራዐትህ እንዲሄዱ አድርግ” (ሕዝቅኤል 36፥27)

“ጌታ ሆይ ከዲያብሎስ ወጥመድም ያመልጡ ዘንድ ንሰሀንና እውነትን ማወቅ ስጣቸው” (2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥ 25-26 )

“አባት ሆይ በወንጌሉ ያምኑ ዘንድ ልባቸውን ክፈት” (የሐዋርያት ሥራ 16፥14)

  1. እነዚህ እውነቶች ሰዎች ወደ ክርስቶስ እንዲመጡ እና እንዲድኑ የወንጌል ሥርጭት ፍጹም አስፈላጊ እንደሆነ፣ ደግሞም ሰዎችን ወደ እምነት መምራት ትልቅ የስኬት ተስፋ እንዳለው ያስታውሰኛል። ነገር ግን መለወጥ በመጨረሻ በእኔ ወይም በማያምነው ሰው ጠንካራነት ላይ የተመሠረተ አይደለም

ስለዚህ ለስብከተ ወንጌል ተስፋን ይሰጣል፤ በተለይም በከባድ ቦታዎች እና ሕዝቦች መካከል።

“ከዚህ ጕረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ። እነርሱም ድምፄን ይሰማሉ” (የዮሐንስ ወንጌል 10፥16)።

ይህ የእግዚአብሔር ሥራ ነው። ራሳችሁን ወደ ሥራው  በሙሉ ልብ አስገቡ።

  1. እነዚህ እውነቶች እግዚአብሔር በመጨረሻ እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ እንድሆን ያደርጉኛል።

ኢሳይያስ 46፥9-10 የጥንቱን፣ የቀደመውን ነገር አስታውሱ፤ እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም፤ እኔ አምላክ ነኝ፤ እንደ እኔ ያለ የለም። የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ ተናግሬአለሁ ‘ዐላማዬ የጸና ነው፤ ደስ የሚያሰኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ’ እላለሁ።

አንድ ላይ ስናስቀምጠው፦ እግዚአብሔር ይከብራል፤ እኛም እንደሰታለን።