በሥራ ቦታ ወንጌልን መስበክ

በክርስትና ላይ የዓለም ተጽእኖ እየጨመረ በሄደ ቁጥር፣ በሥራ ቦታ የወንጌል አገልግሎትህ ላይ ያለው ተጽእኖ ምንድን ነው? ይህ የበለጠ ታማኝ ወይስ የበለጠ ፈሪ አድርጎሃል?

የበለጠ ብትፈራ ብዙ ልትወቀስ አይገባህም፤ ምክንያቱም የማህበራዊ ገለልተኝነት መስፋፋት እና የሰው ኅይል አመራር ፖሊሲዎች የሥራ ቦታ “መቻቻልን” ያበረታታሉ። ከዚህም የተነሣ ማኅበራዊ ሽኩቻን እና ከሥራ እንደ መባረር የመሳሰሉትን መዘዞች በመፍራት፣ ለሥራ ባልደረቦቻችን ወንጌል ላለማካፈል በተለምዶ የምንጠቅሳቸው ፍርሃቶች ናቸው።

ወንጌልን መስበክ መቼም ቢሆን አልጋ በአልጋ ሆኖ አያውቅም። ዛሬ ዛሬ በሚገጥሙን በፈተናዎቻችን ዙርያ አዲስ ነገር አለ ከተባለ፣ የተቃዋሚዎቻችን ድፍረት ነው። ከዚህ በፊት ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች “ሁሉም ያሻውን መንገድ ይከተል” ይሉ ነበር። አሁን ግን እነርሱ እኛን በአብዛኛው ጊዜ በኋላ ቀርነት ሊፈርጁን ይወዳሉ፦ “የምር፣ በዝግመተ ለውጥ (Evolution) አታምንም?” ወይም ደግሞ፤ የጥላቻ አቀንቃኝ አድርገው ያዩናል፦ “እንዴት ግብረ ሰዶምነት ኃጢአት ነው ትላለህ?” አሰሪዎች የቅጥር እና የዕድገት ውሳኔዎችን ከማድረጋቸው በፊት የተቀጣሪውን የማህበራዊ ሚዲያ ውሎ ጥልቅ ፍተሻዎችን ማድረግ ጀምረዋል።

ኩባንያዎች የክፍፍል እና የመድሎን ወሬ በመፍራት ለቦታው ተገቢ የሆነን እውነተኛ ክርስቲያን ቦታውን በማይመጥን ሌላ አማኝ ባልሆነ ሰው መተካትን መቼ ነው የሚያቆሙት? ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ከሰው በላይ እግዚአብሔርን በመፍራት ወንጌል ያካፈሉኝን ወንድሞች በጣም አመሰግናለሁ። የራሴ ድነት፣ የሥራ ቦታ ምስክርነት ፍሬ ነው።

ጠፍቶ የነበረ፣ በሥራ ቦታ ላይ የተገኘ

ከዐሥራ ሁለት ዓመታት በፊት በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኝ አማካሪ ድርጅት ውስጥ ተመራማሪ ነበርኩ። በራስ የሚተማመን፣ የማንንም እርዳታ የማይፈልግ፣ በሙያ የበለጸገ ሂንዱ ነበርኩ። በመንፈሳዊ ጉዳይ ላይ እርግጠኛ የሆነ ሰው ነው ብለህ ልታስብ ትችል ይሆናል። በእውነቱ ከሆነ፣ ስለ መንፈሳዊ ነገር እርግጠኛ እንዳልሆንኩ እኔም ብሆን አላውቅም። ክርስቶስን በንቃት የሚፈልግ ሰው እንዳል ነበርኩ ግን አውቃለሁ።

ክርስቲያን ባልደረባዬ ሃንተር በቢሮው አካባቢ ታዋቂ እና በጣም የተወደደ፣ ከፍተኛ የሽያጭ ሰራተኛ ነው። አንድ ሰው “እርሱ ክርስቲያን ነው፤ ያስታውቃል!” አለኝ። ያህ ምን ማለት እንደሆነ በዝርዝር ሁለታችንም አናውቅም ነበር። ሀንተር በአእምሮዬ ከሳልኩት የክርስቲያን ስዓል ጋር እንደማይስማማ አውቃለሁ። ክርስቲያኖች ጨዋ፣ ፋራ፣ ግብዞች፣ እና ደባሪ ሰዎች አድርጌ ነበር የማያቸው። ሃንተር ግን እንዲህ አልነበረም። ስለዚህ እሱን መከታተል ጀመርኩ።

ጓደኛሞች ሆንን። አብረን ጊዜ ማሳለፍ ጀመርን እናም ስለ ሲምፕሰንስ፣ ሎርድስ ኦፍ ዘ ሪንግ ፣ ክርስቶስ፣ ክሪሽና፣ ቡና፣ ሥራ እና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ተጨዋወትን። ጌታ እኔን ለማግኘት ሀንተርን ሲጠቀም፣ እንደ ጓደኛ እንጂ እንደ የፕሮጀክት የሥራ ባልደረባ ተሰምቶኝ አያውቅም። እግዚአብሔር ብቻ በሚያደርገው ሉዓላዊ ጣልቃ ገብነት፣ እግዚአብሔር በሕይወቴ ውስጥ መንፈሳዊ ቀውስ ባቀናበረበት በዚያ ጊዜ ሀንተር እንዲገኝ አደረገው። እናም ሀንተር በእኔ ሕይወት ውስጥ በሚያስፈልገኝ ጊዜ እውነትን እንዲናገር ጥበብ እና ድፍረት ጌታ ሰጠው።

የሥራ ቦታ ወንጌላዊ ባህሪያት

በጊዜው በእምነቱ ገና ወጣት የነበረ ቢሆንም፣ ማንኛውም አማኝ በሥራ ቦታ ሊተገበር የሚችለው ከሃንተር የምንማረው ምሳሌ ብዙ አለ።

1. የክርስቶስ ተከታይ መሆንህን በግልጽ ሆኔታ አሳውቅ

በመጀመሪያ ክርስቶስን ከፊት ለፊት አድርገው። በሥራ ቦታ ሌሎች ክርስቲያኖችን ማግኘት ብርቅ ሊሆን ስለሚችል፣ በቢሮዎ ውስጥ ያሉ ሰዎች የክርስቶስ ተከታይ መሆንህን እንዲያውቁ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ መንገድ እራስህን ለደካማ አማኞች እና ለማያምኑት ሰዎች ምሳሌ ማድረግ ትችላለህ። ስለ ሃንተር እምነት የነገረኝ ክርስቲያን ያልሆነ የሥራ ባልደረባዬ ነበር። ይህንን በግብዝነት ወይም ኃላፊነት በጎደለው መልኩ ማድረግ የለብንም። ነገር ግን የሰንበት ውሎህን በማውሳት፣ ያለህበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመግለጽ ወይም ለሌሎች እንዴት እንደምትጸልይ ብታካፍል ሰዎች ያኔ በቀላሉ ማን እንደሆንክ ያውቃሉ።

2. ከልህቀት ጋር ሥራህን ሥራ

ሁለተኛ፣ በልህቀት ሥራ። ክርስቶስን ከፊት ለፊት ስታደርገው እኔ ሃንተርን እንዳጠናሁት በባልደረቦችህ እንደምትጠና ጠብቅ። የእግዚአብሔርን ፈጠራ፣ ዓላማ እና መልካምነት በሚያንፀባርቅ መንገድ ሥራህን ሥራ። ታማኝነትን እና ቅንነትን አሳይ። “ሳታጉረመርም ወይም ሳታማርር” ሥራ (ፊልጵ. 2፡14)። በሥልጣን ላይ ላሉት ተገዛ፣ በትሕትና አገልግል።

ይህ በራሱ የወንጌል ምስክርነት አይደለም ነገር ግን በሥራ ላይ ያለን የህይወታችን ሁኔታ የወንጌል ይዘትን ማዳከም ሳይሆን ማጠናከር አለበት።

3. ባልደረቦችህን ውደድ

ሦስተኛ፣ ባልደረቦችህን ውደድ። በሥራ ቦታህ ክርስቲያን ካልሆኑ ሰዎች ጋር ባለህ ወዳጅነት ከልብ ሥራበት። እንደ “የፕሮጀክቶች” ባልደረባ ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር አምሳል እንደተፈጠሩ ሰዎች አድርገህ ውደዳቸው። የመተማመንን አስፈላጊነት አቅልለህ አትመልከት። እኔ እና ሀንተር መጽሐፍ ቅዱስ አብረን ያጠናነውና እግዚአብሔር ለወንጌል የሚሆን ጆሮን የሰጠኝ ከተገናኘን ከአንድ አመት ተኩል በኋላ እንደሆነ ይሰመርበት።
የምሳ ዕረፍትህን አስልተህ ተጠቀም። በምትችለው መጠን፣ የእራስህን ሕይወት ማጋራት በምትችልበትን መንገድ ለጋስ ሁን። ከቢሮ ውጪ ባሉት ቦታዎች ለመገናኘት ዝግጁ ሆን።

4. ወንጌልን ለመስበክ ተዘጋጅ

አራተኛ፣ ወንጌል ለመስበክ ተዘጋጅ። ይህ ሞኝነት ቢመስልም፣ ወንጌልን በቀላሉ እንዴት ማስረዳት እንዳለብህ እርግጠኛ ሁን። ካስፈለገህ ተለማመድ።

ጌታ እድል ሲሰጥ፣ ግልጽ ስላላደረከው ማብራሪያ ውስጥህ የሚወቅስህ ሳይሆን አእምሮህ የሥራ ባልደረባህን ለማዳመጥ እና እነሱ ለመረዳት የሚታገሉትን ለማዳመጥ ነፃነት እንዲኖርህ ተዘጋጅ። ደግሞም የሚያድነው ወንጌል እንጂ ፈጣን ማስተዋል እና ዕቅበተ ዕምነት አይደለም። ስለ ሃንተር ግልጽነት፣ ድፍረት እና በወንጌል ኅይል መታመን እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ።

5. ጸልይ

አምስተኛ፦ ጸልይ። ለሥራ ባልደረቦችህ አዘውትረህ ጸልይ። ወንጌልን ለመካፈል መልካም አጋጣሚዎችን ለማግኘት ጸልይ። በድፍረት እንድታድግ ጸልይ። እግዚአብሔር ትልቅ እና ሰው ትንሽ ሆኖ እንዲታይህ ጸልይ – በአብዛኛው ሁለቱን በማቀላቀል ሁላችንም ጥፋተኞች ነን።

እናም በቤተክርስቲያንህ ያሉ ወንድሞች እና እህቶችም እንዲጸልዩ ጋብዛቸው። በኋላ ሃንተር የወንዶቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ስለ ክርስትና እምነቱ ከጠየቅኩት ጊዜ ጀምሮ ቡድኑ እየጸለየልኝ እንደነበር ነገረኝ።

ስለ ታማኝነት የቀረበ ጥሪ

የሥራ ቦታዎች ለክርስትና የበለጠ ጥላቻ እያሳደጉ ሲሄዱ፣ እነዚህ ያየናቸው መሰረታዊ ልማዶች ይበልጥ አስፈላጊ ይሆናሉ። ስለ ቢዙ ጥሩ እድሎችን ማግኘትና ስለ የምንናገረው ቃላት ጸሎቶቼ ጌታ መልስ ለመስጠት ደግ ነው። ክርስቲያን በመሆኔ በመታወቅ፣ በሙያዊ እና በማህበራዊ ዘርፍ እምነቴን በመኖር እና ባልደረቦቼን እንደ እግዚአብሔር አምሳያ የበለጠ መውደዴ ስለ እምነቴ በግልጽ ለመናገር እድሎችን ሰጥተውኛል። እናም በአስደናቂው ጸጋው፣ አንድን ባልደረባ ወደ እምነት ለማምጣት እግዚአብሔር እኔን ሊጠቀም መረጠ።

ጌታ ጸሎታችንን እንዲመልስልን እና ስለ ክርስቶስ እንድንናገር እድሎችን እንዲሰጠን መጠበቅ አለብን። ድፍረት እንደሰጥህ ጸልይ። የማህበራዊ ግንኙነት ሀብትህን ለመጠቀም ፈቃደኛ ሁን። እግዚአብሔር ባለህበት ሥራ ቦታ ያስቀመጠህ ለዓላማ ነው።

አሾክ ናቻኒ