መጋቢ እና የወንጌል ሥርጭት፦ ታዳሚያንን መፈለግ

ወንጌልን ለማሰራጨት ምን ያስፈልግሃል? ይዘቶቹ ብዙ አይደሉም። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እና ያንን የምሥራች የሚሰብክ ወንጌላዊ ያስፈልግሃል። ሌላ አንድ ተጨማሪ የሚያስፈልግህ ነገር አለ፤ ይኽውም ቢያንስ አንድ በወንጌሉ ያላመነ ታዳሚ ያስፈልግሃል።

ለብዙ መጋቢያን ይህ የመጨረሻው ይዘት ፈታኝ ክፍል ነው። መጋቢው በአንድ ሳምንት ውስጥ ለስብከት ዝግጅት፣ በስብሰባ፣ በምክር አገልግሎት፣ በአስተዳደር፣ በሆስፒታል ጉብኝት እያደረገ፣ በተጨማሪም ለራሱ መንፈሳዊ ሕይወትና ለቤተሰቡ እየተጠነቀቀ፣ እንዴት ነው የምሥራቹን ለማያምኑ ሰዎች ለመስበክ ጊዜ የሚያገኘው?

በአንድ በኩል፣ ይህ ጥሩ እና አስፈላጊ ውጥረት ነው። ወደ መጋቢነት ጥሪ ሲመለስ፣ አንድ አገልጋይ ከስብከተ ወንጌል ግንባር ወጥቶ ወደ ማዘዣ ካምፕ ይገባል። ከእንግዲህ እጅ ለእጅ የሚዋጋ ወታደር ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ቅድሚያ የሚሰጠው እንደ ጄኔራል መሆን ነው። ሥራው ንድፍ ማውጣትን፣ ማስታጠቅን እና ውክልና መስጠትን ያካትታል (ኤፌሶን 4፥12 ይመልከቱ)። ወንጌላውያንን በማሰልጠን፣ ወንጌልን በማስተማር እና በየሳምንቱ ለተሰበሰቡ አማኞች ወንጌልን በመስበክ፣ መጋቢው የወንጌል አገልግሎቱን እየጎዳ ሳይሆን ይልቁኑ እያሰፋው ነው። ይህ መልካም እና ትክክል ነው። መጋቢያኑ መንጋውን ለመንከባከብ እና በአገልግሎት ለማሰልጠን ልዩ የሆነውን እግዚአብሔር የሰጣቸውን ኅላፊነት በማስቀደማቸው የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማቸው አይገባም። መጋቢው የወንጌል አገልግሎት ብቸኛ ባለቤት ሳይሆን የወንጌል አገልግሎት አሳላጭ ነው።

ይህ ማለት ግን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በራሱ መጥፋት አለበት ማለት አይደለም። ጳውሎስ ወጣቱ መጋቢ ጢሞቴዎስን “የወንጌላዊነትን ሥራ እንዲሠራ” አዘዘው (2ኛ ጢሞቴዎስ 4-5)። ታላቁ ጄኔራል እንኳ በልቡ ወታደር ነው። አንድ መጋቢ ሌሎች እንዴት ወንጌልንማሰራጨት እንዳለባቸው ማስተማሩ በጣም ተመችቶት መኖር የለበትም፤ ይህ ከሆነ ወንጌልን በግሉ ለማካፈል ያለው ቅንዓት እየጠፋ ይሄዳል። ለወንጌል አገልግሎት የሚቀኑ መጋብያን፣ ቀናተኛ የሆኑ ጉባኤዎች ይኖራቸዋል። አልፎ አልፎ ወንጌልን የሚሰብኩ መጋብያን ግን ጉባኤዎቻቸው በተመሳሳይ መልኩ ለወንጌል ምስክርነት ይቀዛቀዛሉ።

መጋቢ ወንጌል ስርጭትን ሊያዳብር የሚችልባቸው አምስት መንገዶች

ታዲያ አንድ መጋቢ እንዴት የወንጌል ስብከት ዕድሎችን መፍጠር ይችላል? በዚህ ረገድ እኔም እንደ ማንኛውም አገልጋይ ዕድገት ስለሚያስፈልገኝ፣ በተጣበበ ጊዜያቸው ውስጥ ለወንጌል አገልግሎት እንዴት ቅድሚያ እንደሚሰጡ መጋቢ ጓደኞቼን አነጋግሬያቸው ነበር። በመልሶቻቸው መሠረት፣ አምስት ምክሮች እነሆ፦

1. ፈጠራን አክልበት

በመጀመሪያ፣ የፈጠራ ሰው ሁን። ብዙ ጊዜ የማያምኑትን ሰዎች ለመገናኘት ቀልጣፋ መሆን አለብህ። በአንድ ትንሽ ከተማ ውስጥ የሚያገለግል አንድ መጋቢ እርሱ እና የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ብዙውን ጊዜ የሽማግሌ ስብሰባዎቻቸውን የሚያደርጉት ከቢሮ ውጭ እንደሆነ ነግሮኛል። እንዲህ የሚያደርጉት በእግረ መንገድ የሚመጡ ሰዎችን ምናልባት ካገኙ በዛው ሊመሰክሩላቸው ስለፈለጉ ነው።

ሌሎች ደግሞ በትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ቦታ የወንጌላዊነት ዕድሎችን መፍጠር እንደ አንድ መንገድ ጠቅሰዋል። ከክርስቲያን ጓደኞች ጋር ሁሌ ከመዝናናት፣ ሕዝብ የሚያዘወትራቸውን የቡድን መዝናኛ ቦታ ማግኘት ትችል ይሆናል። ይህም ለአዲስ ወዳጅነት በር ይከፍታል። በአረብ ባህረ ሰላጤ የሚኖር አንድ ሰባኪ፣ በአካባቢያቸው ካሉ ሰዎች ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት ከሚያስችሉት ጥሩ መንገዶች አንዱ የቤተሰብ መዋኛ ቦታ እንደሆነ ተናግሯል።

ንቁ እና ቀልጣፋ መሆን ከጎረቤት ወይም ከሬስቶራንት አስተናጋጅ ጋር የሚደረግ ተራ ውይይት ወደ መንፈሳዊ ጉዳዮች ለመቀየር መሞከርን ያካትታል። አንድ ሰው ስለ ዜና፣ ስፖርት፣ ወይም የአየር ሁኔታ እንኳ ሳይቀር፣ ወደ ጥልቅ ውይይት ሊመራ የሚችል ስለ እግዚአብሔር ወይም ስለወደቀው ዓለም ጠቃሚ የሆነ እውነት ለማቅረብ ብዙውን ጊዜ ክፍት ይሆናል። ለዚህ ደግሞ፣ የፈጠራ ክህሎት እና አስተሳሳብ ብቻ ሳይሆን የሰውን ፍርሃት አሸንፈን ክርስቶስን ለማካፈል በሚያስቸግር ጊዜም ቢሆን በመንፈስ የሆነ ድፍረት እና ፍቅር ያስፈልገናል።

2. ወጥነት ያለህ ሁን

ሁለተኛ፣ ወጥነት ያለው መጋቢ ሁን። ሠራተኞቹን ለማወቅ ደጋግመህ በተመሳሳይ ምግብ ቤት ለመብላት ፈቃደኛ ነህ? ይህንን ወጥነት ለዓመታት የእኔ መጋቢ ለወንጌል ሲል አብነት አድርጎታል። በዚህ ምክንያት ሁሉም አስተናጋጆች መንፈሳዊ ጥያቄ በእራት ጊዜ የሚያቀርቡለት ቄስ ሆኗል እያልን እንቀልድበት ነበር።

ሌላ ጓደኛዬ ደግሞ በየሳምንቱ ተመሳሳይ ላዎንደሪ ቤት በማዘውተር እና ከሠራተኞች ጋር ለመነጋገር ዕድሎችን በመፍጠር ስላገኘው ፍሬ አጫውቶኛል። በመጨረሻም አንዷ ሠራተኛ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመምጣት ክርስቶስን በማመን በዚያ ካሉ ሴቶች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀምራለች ።

3. ንቁ ሁን

ሦስተኛ፣ ንቁ ሁን። በዙሪያችን ላሉት የጠፉ ሰዎች ግንዛቤ እንዲኖረን መጸለይ አለብን። በእንግሊዝ የሚኖር አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ተማሪ በባቡር ውስጥ ምን ያህል ሰዎች የማያምኑ ሰዎች ሆነው ከእርሱ አጠገብ እንደሚቀመጡ ሲገነዘብ መጽሐፍ ቅዱሱን ከፍቶ በግልጽ እንደሚያነብ ተናግሯል። ከዚያም ብዙ ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ያሉ ውይይቶች መነሣታቸው አይቀርም።

እንደ ማስታወሻ፣ የመጋቢነት የመጠሪያ ርዕስ ጠቃሚነትን ማወቅ ተገቢ ነው። ብዙ ንግግሮች የሚጀምሩት “ምንድነው የምሠራው?” ለሚለው ጥያቄ “እኔ መጋቢ ነኝ” የሚል መልስ በመስጠት ነው፤ ይሄ ተጠያቂነት እንደሚያመጣብን ሊሰማን ይችላል። ሆኖም ግን እንደ ዕድል ተጠቀምበት። ለምሳሌ፣ እኔ እንደዚህ ዐይነት አረፍተ ነገር ለማካተት እሞክራለሁ፣ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጋቢ ነኝ። እናም ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ መንፈሳዊነት እና ስለ ኢየሱስ ስላላቸው ሐሳብ መስማት እወዳለሁ።”

እናም አንተ እንደ መጋቢ በማህበረሰብህ ውስጥ ያሉትን በወንጌል የማያምኑትን ሰዎች እንዴት ማገልገል እንደምትችል አትዘንጋ። የመጋቢነት አገልግሎት የወንጌል ዕድሎችን ይዞ ይመጣል።

4. ተባባሪ ሁን

አራተኛ፣ ተባባሪ ሁን። ምዕመኖችህ በሥራ ቦታ እና በማህበረሰቡ ውስጥ እያከናወኑት ባለው የወንጌል ሥርጭት ለመሳተፍ መንገዶችን ፈልግ። አንድ መጋቢ በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ ያሉ አንዳንድ ነጋዴዎች፣ በምሳ ሰዓት በመደበኛነት በመሰባሰብ “ስለ እግዚአብሔር የሚመራመር ቡድን” እንዴት እንዳቋቋሙ በመጥቀስ አልፎ አልፎ እንዲገኝ መጋበዛቸውን አጫውቶናል። የእንግዳ ተቀባይነት አገልግሎትን ከእምነት ባልንጀሮቻችሁ ጋር ለወንጌል አገልግሎት ማቀድ ታላቅ መንገድ ነው። በልደት ወይም የተለያዩ ድግሶች ሲዘጋጁ፣ የጋበዟቸው የቤተ ክርስቲያን አባላት ክርስቲያን ያልሆኑ ጓደኞችን ይዘው እንዲመጡ ንገሯቸው።

5. ቁርጠኛ ሁን

አምስተኛ፣ ቁርጠኝነት ይኑርህ። አንድ መጋቢ ከላይ የተጠቀሱትን ምሳሌዎች በሙሉ መቀበል የለበትም። ነጥቡ እዚያ ላይ አይደለም። ጉዳዩ የእረኝነት አገልግሎት፣ “የጠፉትን ሊፈልግና ሊያድን” የመጣውን የታላቁን እረኛ መምሰል አለበት (ሉቃስ 19፥10)። የመጋቢነት ልዩ ጥሪ እና የጊዜ ሰሌዳ በርግጠኝነት ይህንን ፈታኝ ያደርገዋል። ነገር ግን ብዙ ጊዜ የራሳችን ስንፍና እና ራስ ወዳድነት፣ ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች በላይ ከወንጌል አገልግሎት እንደሚያግደን ማመን አለብን።

ወንጌልን አጥና፤ ሐሴትም አድርግበት

ስለዚህ፣ መጋቢ ሆይ! ለስብከተ ወንጌል ያለህ ቁርጠኝነት በየሳምንቱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴህ ውስጥ ምን ይመስላል? ለመጀመር ያህል፣ ለወንጌል በሮች አዘውትረህ እንድትጸልይ ላበረታታህ።

ከሁሉም በላይ ግን ወንጌልን አጥና፤ ሐሴትም አድርግበት። “የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፣ ምክንያቱም አንዱ ስለ ሁሉ እንደሞተ እርግጠኛ ሆነናል…” (2ኛ ቆሮንቶስ 5፥14)። ውድ የሆነውን የክርስቶስን መልእክት በመመልከትና ይህ እውነት በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ታላቅ ኃይል መገንዘባችን፣ በዘመናችን ላለው ለወንጌል ምስክርነት መዳከም ከሁሉ የተሻለው መድኃኒት ነው።

ማት መርከር