መጋቢዎች ለሕዝባቸው እንዲጸልዩ የቀረበ ጥሪ

መጋቢ ለመሆን በእግዚአብሔር ከተጠራህ፣ ለሕዝብህ መጸለይ እንደምትፈልግ እርግጠኛ ነኝ። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ምኞት በጭራሽ በቂ አይደለም።

ጌታችን የራሱን ሰዎች ደቀ መዛሙርቱን፣ “በዚህ ተቀመጡ ከእኔም ጋር ትጉ” ብሎ በጠየቀ ጊዜ ከሚወዱት ሰው ጋር በታማኝነት ለመትጋት እና ለመጸለይ ፍላጎት እንደነበራቸው እርግጠኛ ነኝ። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ያ ፍላጎት በቂ አልነበረም። ይልቁንም፣ እያንዳንዱ መጋቢ ወደ ጸሎት ሲመጣ “መንፈስ በእርግጥ ፈቃደኛ ነው ሥጋ ግን ደካማ ነው” (ማቴዎስ 26፥41) ለሚለው እውነት የማይረሱ ምሳሌዎች ሆኑ። እንቅልፍ አጥተህ ለሕዝብህ ለመጸለይ ምን ያህል ጊዜ አዲስ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል? ግን ምን ያህሉን ጊዜ በዓኖችህ መድከም የተነሣ ዕቅድህ ሳይሳካ ቀርቷል? ልክ ዐይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበር እንደሚል (ማቴዎስ 26፥43)።

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ጸሎትን በሚያበረታቱ የአምላክ ቃል እውነቶች የዛሉትን ዓይኖቻችንን ማበርታት ነው። እነዚህ ማሰላሰሎች ነፍሳችሁ በሐዋርያዊ ጩኸት እንድትነሣ ያደርጋታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ “ራሳችንን ለጸሎት እናተጋለን” (የሐዋርያት ሥራ 6፥4)።

ለዚህም፣ ከጸሎት አልባ እንቅልፋችን ያስወጣናል ብዬ ተስፋ የማደርገውን ስድስት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶች አቀርባለሁ።

  1. ለሕዝብህ አለመጸለይ ኃጢአት ነው

ጸሎት አልባነት ኃጢአት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ታማኝ መሆን አለብን። ስለ ሕዝቡ መጸለይ ያልቻለ መጋቢ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስበክ ፈቃደኛ እንዳልሆነ መጋቢ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ነው። ክርስቲያን ከመሆናችን በጣም ጣፋጭ እውነታዎች አንዱ “የጽድቅ ባሪያዎች” መሆናችን ነው (ሮሜ 6፥18)። ምንም እንኳ “የሥጋ ምኞት” ወደ ኃጢአት የሚጎትተን ቢሆንም (ገላ. 5፥16) አማኞች አሁንም ትክክል የሆነውን ለማድረግ የማያቋርጥ ፍላጎት አላቸው። እግዚአብሔር ሕጉን በአእምሯችንና በልባችን ጽፏል (ኤር. 31፥33፤ ዕብ 8፥10)፤ ስለዚህ ጽድቅን መውደድና ክፋትን መጥላት እንፈልጋለን (መዝ. 45፥7፤ ዕብ. 1፥9)። መንፈስ ቅዱሱ ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ውስጥ ኃጢአትን እንዲታገሡ በፍጹም አይፈቅድም። ልክ የሚያገለግሉት ጉባኤ እንደማይታገሱ፣ መጋቢዎች ጸሎት አልባነትን በሕይወታቸው ውስጥ በመታገሥ ደስተኞች ሊሆኑ አይችሉም፤ ምክንያቱም ጸሎት አልባ መሆን ኃጢአት ነው።

ነቢዩ ሳሙኤል ለእስራኤል ሕዝብ እንደሚጸልይ ቃል በገባ ጊዜ በግልጽ “ስለ እናንተ ሳልጸልይ በመቅረቴ እግዚአብሔርን እበድል ዘንድ ከእኔ ይራቅ” (1ኛ ሳሙኤል 12፥23) በማለት ለእስራኤል ሕዝብ ተናግሯል። ሳሙኤል ለእግዚአብሔር ሕዝቦች አለመጸለይ በአምላክ ላይ የተፈጸመ ኃጢአት እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ሳሙኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል መሪ ነበር። ሳሙኤል እነዚህን ፍላጎቶች ብቻውን ሊያሟላ በሚችለው በጅሆቫ-ጃይራ ፊት ሳያቀርብ ሕዝቡን እንደሚንከባከባቸው እንዴት ሊናገር ይችላል?  ሳሙኤል ሕዝቡ እግዚአብሔርን በጸሎት እንዲፈልጉ ካልመራቸው እንዴት የእግዚአብሔርን ሕዝብ እየመራሁ ነው ማለት ይችላል? የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሳይጸልይ መምራት ማለት “እረኛ እንደሌላቸው በጎች” መተው ማለት ነው (ማቴዎስ 9፥36)።  እንደ መጋቢዎች፣ ከኃጢአት እንድንሸሽ እና ጽድቅን እንድንከተል ተጠርተናል። ካለመጸለይ ኃጢአት መሸሽ እና ስለ ሕዝባችን የመጸለይን ጽድቅ እና አስደናቂ ልማድ መልበስን መማር አለብን።

  1. ስለ ሕዝብህ መጸለይ እግዚአብሔር ያከብራል

ስለጸሎት ከምወዳቸው ጥቅሶች አንዱ መዝሙረ ዳዊት 50፥15 ነው፦ “በመከራ ቀንም ጥራኝ፤ አድንሃለሁ አንተም ታከብረኛለህ።”

እያንዳንዱ የጭንቅ ቀን እግዚአብሔርን የማክበር ዕድል ነው። የታመሙትን በማጽናናት፣ አዲስ የዳኑ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት በማድረግ እና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉትን በመምከር ስናሳልፍ አንዳንድ ጊዜ ከእውነተኛው ጥሪያችን የተዘናጋን መስሎ ሊሰማን ይችላል፣ ነገር ግን ይህ ስሕተት ነው።

በመንገዳችን የሚመጣ እያንዳንዱ ችግር እግዚአብሔርን ለእርዳታ በመጥራት እርሱን የማክበር አጋጣሚ ነው።ጸሎታችንን ሲመልስ እና በምንጸልይላቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥ ሲሠራ ክብሩን ይወስዳል። የታመሙትን ሲያጽናና ወይም ያጋጠሙንን የሎጂስቲክስ ጉዳዮች ሲያስተካክል ሥራውን ስለሰራ ክብሩን እግዚአብሔር ይወስዳል።

የጆን ኒውተን (1725-1807) ከመዝሙሮቹ በአንዱ ውስጥ ያለውን ምክር መውሰድ እንችላለን፦

ነፍሴ ነይ! ልብስሽን አዘጋጅ፤

ኢየሱስ ጸሎትን መመለስ ይወዳል፤

እርሱ ራሱ እንድትጸልዪ አዝዞአል።

ስለዚህ አይሆንም አትበይ፤

ስለዚህ አይሆንም አትበይ።

ወደ ንጉሡ እየመጣህ ነው፤

ታላላቅ ልመናዎችን በፊቱ አቅርብ፤

ጸጋውና ኃይሉ እንደዚሁ ናቸውና።

ማንም ፈጽሞ ከመጠን ያለፈ መጠየቅ አይችልም፤

በጭራሽ ማንም ብዙ ሊጠይቅ አይችልም።

ጌታ በመከራችን መካከል እንዲሠራ ስንጠይቀው የሚገባውን ክብር እንሰጠዋለን።

  1. ለሕዝባቸው የሚጸልዩ መሪዎችን እንድንመስል ተጠርተናል

ዕብራውያን 13፥7 ስለ ቤተ ክርስቲያናችን መሪዎች እንድናስብ ይነግረናል፦ “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ። የአኗኗራቸውን ውጤት ተመልከት፤ በእምነታቸውም ምሰላቸው” በማለት ተናግሯል። የቤተ ክርስቲያን ታላላቅ መሪዎችን ብትመረምር አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ፤ ይኽውም ለጸሎት ቁርጠኛ መሆናቸው ነው። ይህንንም በሐዋርያው ጳውሎስ ሕይወት ውስጥ እንመለከታለን። እርሱና የአገልግሎት አጋሮቹ ስለቆላስይስ ሰዎች ከሰሙበት ቀን ጀምሮ “ስለ እነርሱ መጸለይን እንዳላቆሙ” ይነግራቸዋል (ቆላስያስ 1፥9)።

እንዴት ያለ የጽናት ምሳሌ ነው! ስለ ቆላስይስ ሰዎች ካወቀበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ የማያቋርጥ ጸሎት። ወንድሞች ሆይ፣ ይህን አስቡ፤ እናም ይህን የሕይወት መንገድ ምሰሉ። በተጨማሪም የኤጳፍራን ምሳሌ እንመልከት፦ “ከእናንተ አንዱ የሆነው የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ የሆነው” ጳውሎስም “እርሱም ፍጹም ጠንክራችሁና ሙሉ በሙሉ ተረጋግታችሁ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ጸንታችሁ እንድትቆሙ ዘወትር ስለ እናንተ በጸሎት እየተጋደለ ነው” ሲል ይመሰክርለታል (ቆላ. 4፥12)። እንደ ጳውሎስና እንደ ኤጳፍራ ያሉ ፈሪሀ አምላክ ያላቸውን የጸሎት ሰዎችን ምሳሌ አስታውሱ።

  1. ለሕዝብህ መጸለይ የአዲስ ኪዳን አብያተ ክርስቲያናት ቅድሚያ የሚሰጠው ነው

በበዓለ ሃምሳ የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ የጸሎት መልስ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን መሪዎች፣ ከ100 ከሚበልጡ የክርስቶስ ተከታዮች ጋር፣ እግዚአብሔር በድንገት በኃይል ሲንቀሳቀስ እየጸለዩ እና እየጠበቁ ነበር (ሐዋሪያት 1–2)። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለ“ጸሎት” ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል (ሐዋሪያት 2፥42)፣ እና ቤተ ክርስቲያን እያደገች ስትሄድ እና የመሪነት ጥያቄዎች እየጨመሩ፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ነገሮች እንደገና ማስተካከል እንዳለባቸው ተገነዘቡ (ሐዋ. 6)። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ያሉ አንዳንድ መበለቶችን ችላ ማለታቸው ሁሉንም ነገር ማድረግ እንደማይችሉ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል።

ግን ትኩረታቸው ምን መሆን አለበት? በበጎነት ወይም በአስተዳደር ላይ ማተኮር አለባቸው? እነዚህ ጥሩ እና መንፈሳዊ አማራጮች ነበሩ (ሮሜ. 12፥6–8)፤ ነገር ግን የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ የተሻለ ነገር እንዳለ ያውቁ ነበር። በመንፈስ ቅዱስ መሪነትም ይህንን አወጁ፦ “እኛ የማእዱን አገልግሎት ለማስተናገድ ስንል የእግዚአብሔርን ቃል አገልግሎት መተው አይገባንም። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ መካከል በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ለመሆናቸው የተመሰከረላቸውን ሰባት ሰዎች ምረጡ፤ ይህን ኀላፊነት ለእነርሱ እንሰጣለን፤ እኛ ግን በጸሎትና በቃሉ አገልግሎት እንተጋለን” (የሐዋርያት ሥራ 6፥2-4)።

ሐዋርያቱ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የተናገሩትን አስተውለሃል? በጸሎትና በቃሉ አገልግሎት የሚል ነው። በእርግጥ የቅዱሳን ማኅበር መበለቶችን ለረሃብ መተው አይችልም። መሪዎቹ ግን ጸሎትን ቢተዉ ሁሉንም ነገር እንደሚያጡ ተረዱ። መሪዎቹ ለእግዚአብሔር ሕዝብ በመጸለይ ባልዲዎቻቸውን ወደ እግዚአብሔር ምሕረት ጉድጓድ ውስጥ ማጥለቅ ባይቀጥሉ ኖሮ፣ መበለቶችን ለመንከባከብ የሚያስፈልገው ልግስና ሁሉ ይደርቅ ነበር። የአዲስ ኪዳን አገልግሎት እንዲኖረን ከፈለግን የአዲስ ኪዳንን ጸሎት መረዳት እና መለማመድ አለብን።

  1. ለእግዚአብሔር ሕዝብ መጸለይ፣ ሕዝቡን ወደ ለውጥ ይመራቸዋል

እንደ መጋቢ፣ ሕዝባችን ክርስቶስን በመምሰል ሲያድግ ለማየት እንናፍቃለን። ሕይወትን በሚቀይር የመጽሐፍ ቅዱስ ኃይል ስለምናምን ስብከቶችን እናዘጋጃለን። ሰዎች መሪዎቻቸውን እንደሚከተሉ ስለምናውቅ ለመንጋው ምሳሌ እንሆናለን።

ግን እንጸልያለን? ግልጽ ለማድረግ የምክር፣ የስብከት እና የሥልጠና ዕድሎች እንፈልጋለን። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ በጸሎት የእግዚአብሔር ኃይል ካልተለቀቀ ከንቱ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ጸሎት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ቅድስና ለማስቀጠል ዋነኛ መንገድ አድርጎ ይመለከተው ነበር። ለዚህም ነው እንዲህ የጸለየው፦

እግዚአብሔር የፈቃዱን ዕውቀት በመንፈሳዊ ጥበብና መረዳት ሁሉ ይሞላችሁ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለይና መለመን አላቋረጥንም፤ የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣ ታላቅ ጽናትና ትዕግሥት ይኖራችሁ ዘንድ (ቆላ. 1፥9–11)

እውቀት፣ ጥበብ፣ ማስተዋል፣ የሕይወት ለውጥ፣ ፍሬ ማፍራት፣ ብርታት፣ ሃይል፣ ጽናት፣ እና ትዕግስት – ከዚህ በላይ ምን ልትለምኑ ትችላላችሁ! ለሐዋርያው ጳውሎስ, እነዚህ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ በጸሎት የሚመጡ ናቸው። ዳግመኛም በፊልጵስዩስ መጽሐፍ፣ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጸለየ፦

ፍቅራችሁ በጥልቅ ዕውቀትና በማስተዋል ሁሉ በዝቶ እንዲትረፈረፍ እጸልያለሁ። ይኸውም ከሁሉ የሚሻለውን ለይታችሁ እንድታውቁ፣ እስከ ክርስቶስም ቀን ድረስ ንጹሓንና ነቀፋ የሌለባችሁ እንድትሆኑ፣ ለእግዚአብሔር ክብርና ምስጋና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሚገኘው የጽድቅ ፍሬ እንድትሞሉ ነው (ፊልጵ. 1፥9–11)። ፍቅር፣ ጥልቅ ዕውቀት፣ ማስተዋል፣ ንጽሕና፣ ነቀፋ የሌለበት፣ የጽድቅ ፍሬ – ለእግዚአብሔር ምስጋና እና ክብር። በድጋሚ እነዚህ ሁሉ በረከቶች በጸሎት የመጡ ናቸው። የምናገለግላቸው ጉባኤዎች እነዚህን ባሕርያት ያሳያሉ? እኛ “ስለማንጠይቅ” (ያዕቆብ 4፥2) ላይሆኑ ይችላሉ። ጌታ ሆይ እንድንጸልይ አነሣሣን!

  1. ሎት ተራ ሰዎች ለእግዚአብሔር አስደናቂ ነገሮችን የሚያደርጉት መንገድ ነው

ለዓመታት፣ በቤተ ክርስቲያኔ ያሉ ሽማግሌዎች በያዕቆብ 5፥14 መሠረት ለታመሙ ሰዎች ለመጸለይ ለእግዚአብሔር ጥሪ ታዛዥ ለመሆን ጥረዋል። ጌታ እንዲፈውሳቸው ለመጸለይ ከታመሙ ቅዱሳን ጋር በተሰባሰብን ቁጥር፣ በያዕቆብ መጽሐፍ ውስጥ ባለ አንድ ጥቅስ እበረታታለሁ። ያዕቆብ እንዲህ በማለት ያስታውሰናል፦ “ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበር። ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፥ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ተኩል አልዘነበም” (ያዕ. 5፥17)። ይህንን ጥቅስ በምዕራፍ 5 መጨረሻ አካባቢ ማስቀመጥ የእግዚአብሔር ጥልቅ ርኅራኄ እንደሆነ ሁልጊዜ ይሰማኛል።

ይህን አስቡ፤ ያዕቆብ የታመሙ ሰዎች እንደሚፈወሱ ተስፋ በማድረግ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ለበሽተኛ ይጸልዩ ዘንድ እንዲጠሩ ነገራቸው። ፈውስ አልፎ አልፎ እንደማይመጣ ያስባል፤ ይህም እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያኑ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ እንዲያደርግ መጠበቅ ያለብን ነገር ነው። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በእምነት የሚጸልይ ጸሎት የታመመውን ሰው ያድነዋል። እግዚአብሔር ያስነሣዋል” በማለት ተናግሯል። እንዴት ያለ ቃል ኪዳን ነው! ሽማግሌዎቹ እግዚአብሔር ተአምር እንዲያደርግላቸው እየጠየቁ ነው። ያዕቆብ አንድ መጋቢ እንዴት እንደሚያስብ ያውቃል፦ “እኔ? እኔ ተራ ሰው ነኝ!” ያዕቆብም ይህንን በማወቅ የኤልያስን ታሪክ በማጠቃለል አስቀድሞ ተናግሯል፦ “ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነበረ፤ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ተኩል ዝናብ አልዘነበም” (ያዕቆብ 5፥17)።

ያዕቆብ እንዲህ እያለ ነው፦ “እነሆ ሽማግሌዎች፣ እናንተ ልክ እንደ ኤልያስ ናችሁ፣ እግዚአብሔር ለሦስት ዓመት ተኩል የአየር ሁኔታን ለመለወጥ እንደተጠቀመበት። በእርግጥ እግዚአብሔር እንደ እናንተ ያለ ተራን ሰው አስደናቂ ነገሮችን ለማድረግ ሊጠቀም ይችላል።” እንዴት ያለ ማበረታቻ ነው! እግዚአብሔር በአገልግሎታችን አስደናቂ ነገሮችን እንዲያደርግ ልዩ መሆን አያስፈልገንም። ይልቁንም፣ የእኛን ተራነት ሙሉ በሙሉ እና በደስታ ተቀብለን ራሳችንን ወደ አስደናቂዎቹ የእግዚአብሔር ተስፋዎች መወርወር አለብን።

ወንድሞች፣ እነዚህ ስድስት ምክንያቶች ሕሊናችሁን እንዲቀርጹ እና ልባችሁን ወደ ጥልቅ ስሜት እና ለመጸለይ ውሳኔ እንድታደርጉ እንደሚያበረታቷችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። ለሕዝባችሁ ለመጸለይ ራሳችሁን ስጡ። እግዚአብሔር አሁን ለጸሎት ወደ አዲስ ውሳኔዎች እንዲመራችሁ ለምን አትጠይቁትም? የመታዘዝ ፍሬ በእግዚአብሔር ቃል ከታደሰው አእምሮ ይውጣ (ሮሜ 12፥1-2)። ጸሎት ለእግዚአብሔር ክብር ይሰጣል፤ የቀደሙትን ታላላቅ ሰዎች አርአያነት ይከተላል፤ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ቅድሚያ የምትሰጠውን ነገር ያንፀባርቃል፤ ሕዝባችንን ይለውጣል፤ እና ተራ ሰዎች ያልተለመዱ ነገሮችን እንዲያደርጉ እግዚአብሔር ይጠቀምበታል። እንድንጸልይ እግዚአብሔር ይርዳን!

* * * * *

የአርታዒ ማስታወሻ፥ ይህ ጽሑፍ Pray for the Flock Ministering God’s Grace through Intercession (Zondervan, 2015) ከሚለው የተወሰደ ነው።

በራያን ፉለርተን