የቤተ ክርስቲያን ዲሲፕሊን ምንድን ነው?

መልስ

  • የቤተ ክርስቲያን የዲሲፕሊን ሥርዓት የአንድን ሰው ኃጢአት ፊት ለፊት የመቃወም እና ወደ ንሰሓም የመምራት ተግባር ነው። ይህም ሰው የማይመለስ ከሆነ፣ ከባድ በሆነ ንሰሓ-አልባ ኃጢአት ምክንያት፣ አንድን ክርስቲያን ነኝ የሚልን ሰው፣ ከቤተ ክርስትያን አባልነት እና የጌታ እራትን ከመውሰድ ወደ ማገድ ደረጃም ሊደርስ ይችላል።
  • ሰፋ አድርገን ስንመለከተው፣ ዲሲፕሊን፣ ቤተ ክርስትያቲያን አባላቷ ቅድስናን እንዲከታተሉ እና ኃጢአትን እንዲቃወሙ ለማገዝ የምታደርገው ማንኛውም ዓይነት ተግባር ነው። ይህም ስብከትን፣ ትምህርትን፣ ጸሎትን፣ የሕብረት ዝማሬን፣ ተጠያቂነት የሞላበት ግንኙነትን፣ እንዲሁም የእረኞችንና የሽማግሌዎችን ፈሪሓ እግዚአብሔር የሞላበትን ክትትል ያጠቃልላል።
  • አንዳንድ ጊዜ ሰዎች፣ የመጀመሪያውን “የማቅናት ዲሲፕሊን”፣ ሁለተኛውን ደግሞ “ገንቢ ዲሲፕሊን” ብለው በመጥራት፣ በእነዚህ ሁለት ዓይነት የዲሲፕሊን አደራረጎች መካከል ልዩነትን ይፈጥራሉ።
  • የማቅናት ዲሲፕሊን፦ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ልክ እንደ ማቴዎስ 18÷15-17፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 5÷1-13፣ 2ኛ ቆሮንቶስ 2÷6፣ እና 2ኛ ተሰሎንቄ 3÷6-15 ባሉ ክፍሎች ላይ ተጠቅሷል፤ ደግሞም እንዲፈጸም ታዝዟል።
  • ገንቢ ዲሲፕሊን፦ በአዲስ ኪዳን ልክ እንደ ኤፌሶን 4÷11-12 እና ፊልጵስዩስ 2÷1-18 ባሉ፣ ቅድስናን ስለ መከታተል እና በእምነት እርስ በርስ ስለ መገንባት በሚገልጹ ብዙ ክፍሎች ውስጥ ገንቢ ዲሲፕሊን ተጠቅሷል። በእርግጥ፣ ሐዋርያት ለቤተ ክርስቲያን የጻፏቸው የአዲስ ኪዳን መልእክቶች፣ ባመኑበት እምነት እንዲገነቡ እና እንዴት እንዲኖሩ ለማገዝ ስለሆነ፣ ገንቢ ዲሲፕሊንን የማሳያ ምሳሌዎች አድርገን ልንወስዳቸው እንችላለን።