ሺህ ጊዜ ሞቶ መኖር የቀጠለ

አዶኒራም ጀድሰን (1788-1850)

አዶኒራም ጀድሰን በሕይወት ዘመኑ የደረሱበት መከራዎች ታሪክ እጅግ አስገራሚ ነው። “ይህኛውስ አሰቃቂ ነው፤ ከዚህ የባሰ ምንም ሊደርስበት እና ሊቋቋመው አይችልም” ስትሉ ሌላ ደግሞ ይገጥመዋል። እንዲያውም ከእግዚአብሔር ረጅም ታሪካዊ እይታ አንፃር ካላየነው በስተቀር በጣም አስደንጋጭ ሊሆንብን ይችላል። ሺህ ጊዜ የሞተው ዘር በማይናማር (ቀድሞ በርማ ተብላ በምትታወቀው ቦታ) ስለ ክርስቶስ ላለ ታላቅ እንቅስቃሴ ሕይወትን ሰጥቷል።

«የጀድሰን ሕይወት፣ ደግማ ደጋግማ በማይናማር አፈር ውስጥ ወድቃ የሞተች የስንዴ ፍሬ ናት።»

አዶኒራም ጀድሰን ሐምሌ 1813 በርማ ሲገባ፣ ቦታው በጥል የተሞላ እና ፈጽሞ በወንጌል ያልተደረሰ ነበር። ከጥቂት ወራት በፊት በህንድ እያሉ ዊሊያም ኬሪ ጀድሰንን እንዳይሄድ ነግሮት ነበር። ሕግ አልባ በሆነ ጭቆና፣ ከሲያም ጋር በነበረው አስፈሪ ጦርነት፣ የጠላት ወረራዎች፣ ተከታታይ ዐመፆች፣ እና የሃይማኖት መቻቻል አለመኖር ምክንያት ዛሬ ላይ ቢሆን ኖሮ እንደ ዝግ አገር ይወሰድ ነበር። ከዚያ በፊት የነበሩት ሚሽነሪዎች ሞተው ወይም ጥለው ወጥተው ነበር።

ነገር ግን ጀድሰን ወደዚያ የሄደው በጊዜው ለ17 ወራት ሚስቱ ከነበረችው የ23 ዓመት ሴት ጋር ነበር። በዚያች ሰዓት 24 ዓመቱ የነበረ ሲሆን፣ ከ33 ዓመት በኋላ አንድ ጊዜ ወደ ኒው ኢንግላንድ ከመሄዱ በስተቀር በ61 ዓመቱ እስኪሞት ድረስ ለ38 ዓመታት ያክል እዛው ሲሠራ ነበር። የከፈለው መሥዋዕትነት ታላቅ ነበር። ወደ አፈር ውስጥ የወደቀ እና ደግሞ ደጋግሞ የሞተ ዘር ነበር።

ያልተለመደ የትዳር ጥያቄ

ጥቅምት፣ 1808 ፣ ጀድሰን በኒውተን ማሳቹሴትስ በሚገኘው አንዶቨር ሴሚናሪ የገባ ሲሆን፣ ታህሳስ 2 ላይ ራሱን ፈጽሞ ለእግዚአብሔር ሰጠ። በአንዶቨር ሴሚናሪ በወንጌል ያልተደረሱ ቦታዎችን በወንጌል ለመድረስ ታላቅ መቀጣጠል ነበር። ሰኔ 28፣ 1810 ላይ ጀድሰን እና ሌሎችም በምስራቅ ለሚደረገው የሚሽነሪ አገልግሎት ራሳቸውን አቀረቡ። የዚያኑ ዕለት አን ሃሰልታይንን አገኛት እና በፍቅር ወደቀ። አንን ከተዋወቃት ከአንድ ወር በኋላ ሊያገባት እንደሚፈልግ ገለፀ፤ በመቀጠልም ለአባቷ የሚከተለውን ደብዳቤ ፃፈ፦

በሚመጣው የፀደይ ወቅት መባቻ ልጅዎን ፈጽመው በዚህ ዓለም ዳግም ላያይዋት ለመለያየት ይፈቅዳሉ ወይ? መለየቷን እና ለሚሲዮናዊ ሕይወት ችግሮችና መከራዎች አልፋ መሰጠቷን ይፈቅዱ እንደሆነ፣ ደግሞም ውቅያኖስ ሊያመጣ ለሚችላቸው አደጋዎች፣ የህንድ ደቡባዊ አየር ባሕርይ አደገኛ ተፅዕኖ ፣ ለሁሉም ዓይነት ማጣትና ጭንቀቶች፣ ለውርደት፣ ስድብ እና ስደት  ምናልባትም ለአሰቃቂ ሞት እንድትጋለጥ ይፈቅዱ እንደሆነ እጠይቃለሁ። ሰማያዊ ቤቱን ትቶ ስለመጣው እና ለእርሷ እንዲሁም ለእርሶ ሲል ስለሞተው ሲሉ፣ እየጠፉ ላሉት የማይሞቱ ነፍሳት ሲሉ፣ ስለ ጺዮን ሲሉ፣ እንዲሁም ስለ እግዚአብሔር ክብር ሲሉ ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ ጋር ይስማማሉ? በቅርቡ፣ በክብር ዓለም የጽድቅ አክሊል ለብሳ በእርሷ አማካኝነት ከዘላለም ዋይታ እና ሰቆቃ የዳኑ አሕዛብ ምክንያት ለአዳኟ ክብር በሚገባ በምስጋና አድናቆት አሸብርቃ  ልጅዎን በማግኘት ተስፋ ከዚህ ሁሉ ጋር ይስማማሉ? (ወደ ወርቃማው ዳርቻ 83)

አባቷ በሚያስደንቅ ሁኔታ እራሷ መወሰን ትችላለች ብለው መለሱ። አዶኒራም እና አን የካቲት 5፣ 1812 ዓ.ም. ተጋቡ። ከዚያም ከሌሎች ሁለት ጥንዶች እና ገና ያላገቡ ሁለት ሰዎች ጋር በመሆን ወደ ህንድ አቀኑ። መርከቡ ሊሰጥም ይችላል ብሎ በማሰብ፣ የሄዱት በሁለት መርከብ ተከፍለው ነበር። በህንድ ጥቂት ጊዜ ከቆዩ በኋላ አዶኒራም እና አን ወደ አዲስ ቦታ ለመሄድ ቆረጡ። ሐምሌ 13፣ 1813 ላይ ራንጉን በርማ ደረሱ።

ረጅም እና  የሚያሰቃይ መኸር

በበርማም 42 ዲግሪ በሚደርስ ሞቃት አየር ውስጥ ከኮሌራ፣ ማሌሪያ፣ የአንጀት ኢንፌክሽን እና የማይታወቁ ሰቆቃዎች ጋር የዕድሜ ልክ ትግል ተጀመረ። በዚህም ውስጥ አንን ብቻ ሳይሆን ሁለተኛዋን ሚስቱንም፣ ከዐሥራ ሦስት ልጆቹ ውስጥ ሰባቱን፣ እንዲሁም አብረውት የሚሠሩትን ተራ በተራ በሞት አጣቸው።

በገጠሙት ተግዳሮቶች እና መሰናክሎች ሁሉ ውስጥ ጀድሰን ቋንቋውን ለመማር፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም እና በየመንገዱ ወንጌልን ለመመስከር ይተጋ ነበር። እርሱና አን እዛ ከደረሱ ከ6 ዓመት በኋላ ማኡንግ ናው የተባለውን የመጀመሪያውን ሰው አጠመቁ። ዘሩን መዝራት ረዥም ጊዜ የፈጀ እና ከባድ ነበር። ማጨዱ ግን የባሰና ብዙ ዓመታትን የወሰደ ነበር። ነገር ግን በ1831 እዛ ከደረሱ ከ19 ዓመት በኋላ በምድሪቱ አዲስ መንፈስ ነበር። ጀድሰን እንዲህ ሲል ጽፏል፡-

የጥያቄ መንፈስ በምድሪቱ ወርድ እና ስፋት ሁሉ በሁሉም ቦታ እየተንሰራፋ ነው። ለጠየቁን ብቻ እየሰጠን ወደ 10,000 የሚጠጉ ትራክቶችን አሰራጭተናል። ወደ 6,000 የሚሆኑ ማመልከቻዎች በቤት ውስጥ ደርሰውናል። አንዳንዶቹ የሚመጡት ከሲያም እና ከቻይና ድንበር የሁለት እና ሦስት ወር ጉዞ ተጉዘው ነው። “ጌታዬ የዘላለም ሲዖል እንዳለ ሰምተን አስፈርቶናል። እንዴት አድርገን ማምለጥ እንደምንችል የሚያግዘን ወረቀት ስጠን” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ከአቫ 100 ማይል በስተሰሜን ከምትገኘው ከካታይ ድንበር የሚመጡ ናቸው። “ጌታዬ ስለዘለዓለማዊ አምላክ የሚያወራ ጽሑፍ አይተናል። እነዚህን ጽሑፎች የምትሰጠው ሰው አንተ ነህ? ከሆነ እባክህ ለእኛም እንድትሰጠን እንለምንሃለን፤ ከመሞታችን በፊት እውነቱን ማወቅ እንሻለን” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በጥቂቱ ብቻ ከሚታወቅበት  ከአገሪቱ ውስጠኛ ክፍል የሚመጡ ናቸው። “የኢየሱስ ክርስቶስ ሰው አንተ ነህ? ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገር ጽሑፍ ስጠን” ይላሉ። (ወደ ወርቃማው ዳርቻ 398-99)

ነገር ግን በ1819 ጌታን በተቀበለው የመጀመሪያ ሰው እና በ1831 ባለው የእግዚአብሔር ኃይል መፍሰስ መካከል የተከፈለ ታላቅ ዋጋ ነበር።

እስር ቤት እና ብቸኝነት

በ1823 አዶናሪም እና አን ከራንጉን ተነስተው 300 ማይል ወደ ውስጥ ወደምትዘልቀውና ኢራዋዲ ወንዝን ሽቅብ ወደምትጠጋው ዋና ከተማ አቫ ስፍራ ቀየሩ። ወደ ጨቋኙ አገዛዝ እንዲህ ቅርብ መሆን አስጊ ነገር ነበር። በሚቀጥለው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የብሪቴን የጦር መርከቦች ራንጉን ደረሱ። ቀጥለውም ወደቧን ደበደቡ። ምዕራባዊያን በሙሉ ወዲያዉኑ እንደሰላዮች መታየት ጀመሩ። አዶኒራምንም ከቤቱ ጎትተው ወሰዱት። ሰኔ 8፣ 1824 ዓ.ም. እስር ቤት ተጣለ። እግሮቹ ታሰሩ። ማታ ማታ ረጅም አግድም ቀርከሀ በታሰሩት እግሮቹ መካከል ይገባና ዘቅዝቀው ይሰቅሉታል። መሬት ላይ የሚያርፈው ትከሻውና ጭንቅላቱ ብቻ ነበር።

“መከራዎቹ በዚህ ዓለም ብዙ ተስፋ ከማድረግ እንዲላቀቅ አድርገውታል።”

አን ነፍሰ ጡር ነበረች። ነገር ግን በየዕለቱ የሦስት ኪሎሜትር ጉዞ ወደ ቤተመንግሥት እየተጓዘች ጀድሰን ሰላይ እንዳልሆነ ትሟገትና ምህረት እንዲያደርጉለት ትማጸን ነበር። ሕዳር 4፣ 1825 ጀድሰን በድንገት ተለቀቀ። መንግሥት ከብሪታንያ ጋር ለሚያደርገው ድርድር አስተርጓሚ እንዲሆንለት አስፈልጎት ነበር። ዐሥራ ሰባት ወራትን በእስር ቤት በሞት አፋፍ ሆኖ አሳልፎ፣ እንዲሁም ሚስቱ የምትችለውን ሁሉ እርሱን ለመንከባከብ እራሷን እና ሕፃኗን መሥዋዕት እያደረገች ረጅሙ የመከራ ጊዜ አበቃ። የአን ጤንነት ተንኮታኮተ። ከዐሥራ አንድ ወራት በኋላ በጥቅምት 24፣ 1826 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች። ቀጥሎም ከ6 ወር በኋላ ልጃቸው ሞተች።

“ላገኘው አልቻልኩም”

የሚስቱና የልጁ ሞት ያስከተለበት ሥነ ልቦናዊ ጫና አስከፊ ነበር። ጥርጣሬ አእምሮውን ተቆጣጠረ። ሚሲዮን የሆነው ለስም እና ዝና ብሎ እንጂ በትሕትና እና እራስን የመካድ ፍቅር እንዳልሆነ ጥርጣሬ ውስጥ ገባ። እንደ ማዳም ጉዮን፣ ፌኔሎን እና ቶማሰ ኬምፒሰ ያሉ ካቶሊካዊ ባህታዊያን የጻፏቸውን መጽሐፍት ማንበብ ጀመረ። ይህም ደግሞ ገዳማዊ ሕይወት እና እራስን መቅጣት ውስጥ እንዲገባ አደረገው። እንደ ሕይወቱ ይወድደው የነበረውን የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ትርጉም ሥራውን በማቋረጥ ከሰዎች የበለጠ መሸሽ ጀመረ። ከሰዎች ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ትዕቢትን ይደግፋል፣ ወይም ፍስሐን ያበረታታሉ ብሎ ካሰባቸው ነገሮች ሁሉ ሳይቀር ራቀ። (ወደ ወርቃማው ዳርቻ 387)

ከሚኖርበት ጎጆው አጠገብ ጉድጓድ ቆፍሮ ከአጠገቡ በመቀመጥ የስጋን የመበስበስ ሂደት ያሰላስል ነበር። ለአርባ ቀን በነብር ወደተወረረው ጫካ ለብቻው መሽጎ ነበር። በአንድ ደብዳቤውም ሲጽፍ መንፈሳዊ መጠውለግ ይሰማው እንደነበር ይናገራል። “እግዚአብሔር ለእኔ ታላቅ ሚስጥር ሆኖብኛል። በእርሱ አምናለሁ ግን ላገኘው አልቻልኩም።” (ወደ ወርቃማው ዳርቻ 391)

ወንድሙ ኤልናታን በግንቦት 8፣ 1829 ላይ በ35 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ግር በሚያስብል ሁኔታ ለጀድሰን የመታደስ ጅማሮ ሆነለት። ምክንያቱም ከዐሥራ ሰባት ዓመት በፊት አማኝ ሳይሆን ትቶት የሄደው ወንድሙ አሁን አማኝ ሆኖ እንዳረፈ ያመነበት ምክንያት ስለነበረው ነው። 1930ን ሙሉ አዶኒራም ከጨለማው እየወጣ ነበር።

የተጠናቀቀ መጽሐፍ ቅዱስ እና አዲስ ሕይወት

ከመጀመሪያው አንስቶ በተለይም በሕይወቱ እንዲህ ባለ ቅያስ ላይ ለጀድሰን የሚስዮን ትጋት ማዕከላዊ የነበረው ነገር የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ ነበር። ያለ ሚስት እና ልጆች ላሳለፋቸው እነዚህ የመንፈሳዊ ተሐድሶ ዓመታት እራሱን የወሰነው ሙሉ ኃይሉን ማለት በሚቻል ደረጃ የአዲስ ኪዳን ትርጉሙን እንዲሁም በብሉይ ኪዳን ትርጉም ሥራው ላይ እንዲገፋበት በተሠራች አነስተኛ ክፍል ውስጥ ነበር። በ1832 መጨረሻ የተጠናቀቀው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ሦስት ሺህ ቅጂዎች ታተሙ። የብሉይ ኪዳንን በጥር ወር መጨረሻ 1834 ዓ.ም. ላይ አጠናቀቀ።

በበርማ ቋንቋ የተተረጎመው የመጀመርያው የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂን ተከትሎ እግዚአብሔር በልፋቱ ደስ የተሰኘ በሚመስል ሁኔታ በአዲስ ሚስት ባረከው። ከሦስት ዓመት ቀደም ብሎ በርማ ውስጥ ጆርጅ ቦርድማን የሚባል ሚስዮናዊ ሞቶ ነበር። ሚስቱ ሣራም እርሱ ከሞተ በኋላ በበርማ ቆይታ የታወቀች ሚስዮናዊ ነበረች። ከልጇ ጆርጅ ጋር ወደ አገሪቱ ውስጣዊ ክፍል ድረስ ዘልቃ ገብታ ነበር። የካቲት 1834 ላይ ጀድሰን ከሣራ ደብዳቤ ደረሰው። ሊያጫትም በመወሰን፣ ሚያዝያ 1 ሙልሜይንን ትቶ ወደ ታቮይ ተጓዘ። ሚያዝያ 10 ላይ ተጋቡ።

በበርማ ካሳለፋቸው አስደሳች ወቅቶች ውስጥ አንዱ ይህ ነበር። ነገር ግን ያለ ሕምም አልነበሩም፤ ደግሞም ከዐሥርት ዓመታትም በላይ የዘለቁ አልነበሩም። በዐሥራ አንድ ዓመት ውስጥ ስምንት ልጆችን ከወለዱ በኋላ ሳራ በጠና ስለታመመች ቤተሰቡ የባሕሩ አየር ፈውስን ቢያመጣላት ብለው ተስፋ በማድረግ ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ወሰኑ። ጀድሰን አሜሪካ ከሄደ አሁን 33 ዓመታት ሆነውታል። አሁንም እየተመለሰ ያለው ስለሚስቱ ሲል ብቻ ነበር። በመስከረም 1845 ዓ.ም. በአፍሪካ ጫፍ ሲደርሱ ሳራ ሞተች። ጉድጓድ ቆፍረው ሚስቱን እና የልጆቹን እናት እስኪቀብሩ ድረስ መርከቢቱ በሴንት ሄሌና ደሴት መልሕቋን ጣለች። ሲጨርሱም ጉዟቸውን ቀጠሉ።

የዚህን ጊዜ አዶኒራም እንደቀድሞው በድባቴ ውስጥ አልተዘፈቀም። ልጆቹ ነበሩት። ነገር ግን ከዚህም በላይ መከራዎቹ በዚህ ምድር ላይ ብዙ ተስፋ ከማድረግ አላቀውት ነበር። ያለመመረር እና ድባቴ ሕይወቱን እንዴት እንደሚጠላ እየተማረ ነበር (ዮሐንስ 12፥25)። ጀድሰን አሁን አንድ ታላቅ ፍላጎት ነበረው። እርሱም ተመልሶ ሕይወቱን ለበርማ መስጠት ነበር።

ጥቂቶች ብቻ ደጋግመው ይሞታሉ

ጀድሰን በአሜሪካ የነበረው ቆይታ እንዳቀደው አልሄደለትም። ሁሉንም ባስደነቀ ሁኔታ ኤሚሌ ቹባክ ከተባለች ሴት ጋር ለሦስተኛ ጊዜ ፍቅር ያዘው። ሰኔ 2፣ 1846 ዓ.ም. አገባት። 29 ዓመቷ ነበር። እርሱ ደግሞ 57። ታዋቂ ጸሐፊ ነበረች። ከጀድሰን ጋር ወደ በርማ ለመሄድ ዝናዋን እና የጽሑፍ ሥራዋን ተወች። ሕዳር 1846 በርማ ደረሱ። ሁለቱም አይተውት የማያውቁት 4 የደስታ ዓመታትን እግዚአብሔር ሰጣቸው።

አዶኒራም እና ኤሚሊ አንድ ልጅ ነበራቸው። ነገሮች ብሩህ ይመስሉ ነበር። ነገር ግን የድሮው በሽታ አዶኒራምን የመጨረሻ አንድ ጊዜ አጠቃው። ብቸኛው ተስፋ ክፉኛ የታመመውን ጀድሰንን በመርከብ አሳፍሮ መላክ ነበር። ሚያዝያ 3፣ 1850 ዓ.ም. አዶኒራምን ተሸክመው ወደ አይል ኦፍ ፍራንስ በምታቀና አሪስቴድ ማሪ በተባለች መርከብ ላይ ከሚንከባከበው ጓደኛው ቶማስ ራኒ ጋር አድርገው ላኩት። በመከራው ወቅት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከባድ ሕመም እየተነሳ ያስመልሰው ነበር። ከተናገራቸው የመጨረሻዎቹ ቃላት ውስጥ፣ “ምንኛ ጥቂቶች ናቸው ደግመው ደጋግመው የሚሞቱት” የሚል ነበር። (ወደ ወርቃማው ዳርቻ 504)

“ሺህ ጊዜ የሞተው ዘር፣ በማይናማር ለክርስቶስ ድንቅ ሥራ እንዲኖር ሕይወትን ሰጠ።”

አርብ ከሰዓት 10፡15 ላይ ሚያዝያ 12፣ 1850 ዓ.ም. አዶኒራም ጀድሰን ከቤተሰቦቹ እና በበርማ ካለቸው ቤተ ክርስቲያን ርቆ በባህር ላይ ሞተ። ያን ምሽት መርከቢቱ ጉዞዋን ገታች። የመርከቢቱ ሠራተኞች በጸጥታ ተሰበሰቡ። የመርከቧን የጎን መጫኛ ከፈቱ። ምንም ጸሎት አልነበረም . . . ትዕዛዙን ያስተላለፈው የመርከቧ ካፒቴን ነበር። የሬሳ ሳጥኑ ወደ ጨለማው ተገፍቶ ወጣ። (ወደ ወርቃማው ዳርቻ 505)

ከዐሥር ቀን በኋላ ምንም እንኳን በወሊድ ጊዜ ቢሞትባትም ኤሚሊ ሁለተኛ ልጃቸውን ወለደች ። ከአራት ወር በኋላ ባሏ እንደሞተ ተረዳች። ቀጣዩ ጥር ላይ ወደ ኒው ኢንግላንድ ተመለሰች። ከሦሰት ዓመት በኋላ በ37 ዓመቷ በሳንባ ነቀርሳ በሽታ ሞተች።

የሞተው ዘር ፍሬ

የጀድሰን ሕይወት በማይናማር መሬት ውስጥ ወድቃ ደግማ ደጋግማ እንደሞተች የስንዴ ፍሬ ነው (ዮሐንስ 12፥24)። መከራው ጥልቅ ነበር። ፍሬውም እንዲሁ። ከሁለተኛው ሚሊንየም ወደ ሦስተኛው ሚሊንየም መሻገሪያ ላይ፣ እንደ ፓትሪክ ጆንስቶን ስሌት የማይናማር (የበርማ አዲስ ስም) ባፕቲስት ጉባኤ 3,700 አብያተ ክርስቲያናትን ያቀፈና 617,781 አባላትን የያዘ፣ እንዲሁም 1,900,000 አጋሮችን የያዘ ነው። ይህም የዚህ ዘር መሞት ውጤት ነው።

እርግጥ ነው ከጀድሰን ተጨማሪ በተለያየ ጊዜ የተከሰቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎችም ነበሩ። እነርሱም መጥተው ሕይወታቸውን ሰጥተዋል። ብዙዎቹ የሞቱት ገና ወጣት ሆነው፣ እድሜያቸው ከጀድሰን ያነሰ ሆኖ ሳለ ነበር። በማይናማር የታየው አስደናቂ ፍሬ፣ በብዙ ሚስዮናዊያን በተለይም በአዶናሪም ጀድሰን መከራ እና ሞት ላይ የበቀለ ነው።

በጆን ፓይፐር