የሕዝቦች ወገኖች ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ስጡ፤ ክብርንና ብርታትን ለእግዚአብሔር ስጡ። (መዝሙር 96፥7)
ዘማሪው “ብርታትን ለእግዚአብሔር ስጡ” ሲል፣ ምን እያለ ነው? ብርታትን ለእግዚአብሔር ስንሰጥ ምንድን ነው የምናደርገው?
በመጀመሪያ፣ በእግዚአብሔር ጸጋ፣ ትኩረታችንን ወደ እግዚአብሔር እናደርጋለን፤ ብርቱ እንደሆነም እናስተውላለን። ከዚያም ለብርታቱ ታላቅነት አድናቆታችንን ከብዙ ፍርሃት ጋር እናቀርባለን። የሚገባውንም ክብር እንሰጣለን።
በብርታቱ እንደነቃለን። ይህንን አድናቆት መስጠት ያለው አድናቆት የሚያደርገው (“ብርታትን ስጡ” የሚለው ማለት ነው) የኃይሉ ታላቅነት የእኛ ሳይሆን የእርሱ በመሆኑ በመደሰታችን ነው።
እኛ ደካሞች፣ እርሱ ደግሞ እጅግ ብርቱ በመሆኑ ጥልቅ የሆነ ብቃት ይሰማናል። እንደዚህ መሆኑንም እንወደዋለን። በእግዚአብሔር ብርታት አንቀናም። የእርሱን ኃይል ለመውሰድም አንስገበገብም። ብርታት ሁሉ የእርሱ በመሆኑ ደስ ይለናል።
ሁለንተናችን ከራሱ ወጥቶ የእርሱን ኀይል በማየት ይደሰታል — ልክ በረጅም ርቀት ሩጫ ውድድር ያሸነፈንን ጀግና ሯጭ ሲሸለም ስናይ፣ በራሳችን ሽንፈት ከመበሳጨት ይልቅ የእርሱን ብርታት በማድነቅ ታላቅ ደስታን እንዳገኘን አርጋችሁ ቁጠሩት።
የሕይወትን ጥልቅ ትርጉም የምናገኘው፣ ስለራሳችን ኀይል በማሰብ ወይም በመመካት ሳይሆን፣ ልባችን በፈቃደኝነት ራሱን ትቶ የእግዚአብሔርን ኀይል ማድነቅ ሲጀምር ነው። ይህን ስናደርግ አንድ ነገር እንረዳለን፦ አምላክ አለመሆን፣ ለመሆንም አለማሰብ ሆነ አለመፈለግ፣ እጅግ በጣም ዕረፍትና እፎይታ ያለበት አስደሳች ነገር ነው።
ለእግዚአብሔር ኀይል ስንገዛ፣ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ሁሉ የፈጠረበትን ምክንያት በእርሱ አምላክነት እና ብርታት እንድንደሰት እና እንድንረካ መሆኑን እንረዳለን። አምላክ ለመሆን ከመፈለግ ይልቅ በእርሱ ጌትነት ሥር በማረፍ፣ ልናገኝ የምንችለውን ከፍተኛ ደስታ እና እርካታ እናጣጥማለን። ሁሉን የሚያረካውና የነገሮች ሁሉ ምርጡ ፍጻሜ የሚሆነው፣ ወሰን የሌለውን አምላክ ለዘለዓለም ማድነቅ ነው። ይህንን ስንረዳ ልባችን ያርፋል፣ ሰላምም ይሞላል።
የትኛውም ኀይል ከእኛ እንደሆነ አድርገን ለመውሰድ በጥቂቱም ቢሆን ስንፈተን እንደነግጣለን። እግዚአብሔርም ደካማ ያደረገን ከዚህ ሊጠብቀን ነው፦ “ነገር ግን ይህ እጅግ ታላቅ ኀይል ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ አለመሆኑን ለማሳየት፣ ይህ የከበረ ነገር በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን” (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥7)።
አቤት ይህ እንዴት ያለ ፍቅር ነው! እግዚአብሔር የእርሱን ኀይል በማድነቅ የሚገኘውን ከፍታ፣ በማይረባ ማንነታችን ለመመካት በምናደርገው ከንቱ ሙከራ እንዳንተካው ይጠብቀናል። በእርግጥም አምላክ ለመሆን ከመፍጨርጨር ይልቅ፣ አምላክ የሆነውን እግዚአብሔርን ማየት ታላቅ ደስታ ነው!