መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ-መለኮት እና የኅብረት አምልኮ

እንደ ቤተ ክርስቲያን ለአምልኮ ስንሰበሰብ በርግጥ ምን እያደረግን ነው? በሳምንታዊ የኅብረት አምልኳችንስ ምን ማድረግ እንዳለብን እንዴት እናውቃለን?

በተለምዶ፣ ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ለእነዚህ ጥያቄዎች መመሪያ ለማግኘት ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት ዘወር ይላሉ፤ ነገር ግን በየትኛው የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል ውስጥ ይህንን ልናገኘው እንችላለን? በብሉይ ኪዳን አምልኮን በተመለከተ ማለትም ስለ ጸሎቶች እና መሥዋዕቶች፣ ስለ መዘምራን እና ጸናጽል እና ስለ ሌሎች ብዙ ነገሮች በብዙ ክፍሎች ተጽፎ እናገኛለን። ነገር ግን እነዚያ ሁሉ ነገሮች በእውነት በአሁኑ ጊዜ በአዲስ ኪዳን የአማኞች ኅብረት ላይ ተግባራዊ መሆን ይችላሉ?

እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስፈልገን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የአምልኮ ሥነ መለኮት ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ መለኮት በቅዱሳት መጻሕፍት ሰፊ የታሪክ መስመር ላይ አንድነትን እና ልዩነትን፣ የቀጠለውን እና የተቋረጠውን እንድንከታተል የሚረዳን ትምህርት ነው።

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሁሉንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነውን የኅብረት አምልኮ ሥነ መለኮትን በአጭሩ እቀርባለሁ። አራት ደረጃዎች ወደዚያ ይወስዱናል፦

(1) በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኝ የኅብረት አምልኮ፣

(2) በክርስቶስ ሙላትን/ ፍፃሜን ማግኘት፣

(3) በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኝ የኅብረት አምልኮ፣

(4) ለጋራ አምልኮ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ።

  1. በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኝ አምልኮ

ዘፍጥረት 3 ላይ የእግዚአብሔር ሕዝብ ከፊቱ ከተባረረበት ጊዜ አንሥቶ፣ እግዚአብሔር እነርሱን ወደ ራሱ ለመሰብሰብ ሲሠራ ቆይቷል። [2] እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት ሲሠቃዩ ከነበረበት እግዚአብሔር አዳናቸው፤ ይህም ከጭቆና ነፃ እንዲወጡ ብቻ ሳይሆን በፊቱ እንዲያመልኩትም ነበር (ዘፀአት 3፥1218)። እግዚአብሔር ሕዝቡን ከግብፅ አውጥቶ ወደ ማደሪያው አመጣቸው (ዘፀአት 15፥13 17)።

ያ የመኖሪያ ቦታ የት ነው? በመጀመሪያ፣ ማደሪያው፣ ካህናቱ ለሰዎች ኀጢአትና ርኩሰት መሥዋዕት የሚያቀርቡበት በልዩ ሁኔታ የተሠራው ድንኳን ነው። በዘፀአት 29፥44-46 እናነባለን።

የመገናኛውን ድንኳንና መሠዊያውን እቀድሳለሁ። ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን እቀድሳለሁ። በእስራኤል ሕዝብ መካከል እኖራለሁ፥ አምላክም እሆናቸዋለሁ።  እንዲሁም በመካከላቸው እኖር ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ።

የዘፀአት(እስራኤልን ነጻ የማውጣት) ግቡ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል እንዲኖር ነበር፤ ይህንንም ያደረገው በቅዱስ ስፍራ (የመገናኛው ድንኳን) እና ለዚሁ ዓላማ በሾማቸው ሰዎች (ክህነት) አማካይነት ነው።

እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከግብፅ ባወጣቸው ጊዜ ሕዝቡ አድርጎ ወደ ራሱ አምጥቷቸዋል። ከእስራኤል ጋር ያለውን አዲስ ግንኙነት ያጸናበት መንገድ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን በማድረግ ነው፤ ይህም በተለምዶ “የሙሴ ኪዳን” ተብሎ ይጠራል። በዘፀአት 19 ላይ ጌታ ሕዝቡን ከግብፅ እንዴት ነፃ እንዳወጣቸው ያስታውሳቸዋል፤ ከዚያም የቃል ኪዳኑን ሕግጋት የሚታዘዙ ከሆነ የእርሱ ውድ ርስት እንደሚሆኑ ቃል ገብቷል (ዘፀአት 19፥1-6)።

እግዚአብሔር በዘፀአት 24 ላይ ከሕዝቡ ጋር ይህንን ቃል ኪዳን እና የዘፀአትን ሕግጋት ሁሉ አጸና። ዘሌዋውያን፣ ዘኍልቍ እና ዘዳግም ይህንን የቃል ኪዳኑን ሕግጋት ዘርዝረው አብራርተውታል። እነዚህ ሁሉ ዝርዝሮች እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር በገባው በዚህ ልዩ ቃል ኪዳን ውስጥ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር እና እርስ በርሳቸው እንዴት ሊኖሩ እንደሚገባ ይገልጻሉ።

ይህም በዘሌዋውያን ውስጥ የተገለጹት ዝርዝር መሥዋዕቶች እና የመንጻት ሥርዐቶች በቃል ኪዳኑ ኅብረት ውስጥ ያሉ ጥሰቶችን የሚታደስባቸው መንገዶች ናቸው። የአምልኮው ሥርዐት ቃል ኪዳኑን ይጠብቃል።

በዓመት ውስጥ በጣት ለሚቆጠሩ ጊዜያት ያህል፣ ለፋሲካ፣ ለበኵራት፣ ወዘተ ክብረ በዓላት  (ዘሌዋውያን 23) ሁሉም እስራኤላውያን በአንድነት በማደሪያው ድንኳን በጌታ ፊት እንዲሰበሰቡ ታዝዘዋል። ከእነዚህ በዓላት ሌላ ዘወትር የሚቀርበው የመሥዋዕት ሥርዐት የሚከናወነው፣ በካህናቱና ለኀጢአት ወይም ለመንፃት መሥዋዕት ማቅረብ ሲያስፈልጋቸው ወደ ማደሪያው ድንኳን (በኋላም ወደ ቤተ መቅደሱ) በሚመጡት እስራኤላዊያን ግለሰቦች ነው።

በሌላ አነጋገር፣ ለእስራኤላውያን፣ ይህ የኅብረት አምልኮ ልዩ እና በዓመት ውስጥ ጥቂት ጊዜ ብቻ የሚቆይ በዓል ነበር። አምልኮን የሚረዱት ለጌታ ብቻ የሆነ መሰጠት(devotion) እንደሆነ እና እስራኤላውያን ሌት ተቀን እንዲለማመዱ የተጠሩት ነገር እንደ ነበር ነው (ዘዳግም 6፥13–15)። ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር መገኘት ከመቅረብ አንጻር አምልኮ ለተወሰኑ ሰዎች፣ ቦታዎች እና ጊዜያት ብቻ የተወሰነ ነበር። እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ተቀመጧል፤ አዎ፣ ነገር ግን ያ መገኘት በማደሪያው ድንኳን ላይ ብቻ ተወስኖ በካህናቱ ይጠበቅ ነበር።

2. በክርስቶስ ሙላትን(ፍፃሜን) ማግኘት

በቅዱሳት መጽሐፍት ታሪክ ውስጥ የለውጡ ማዕከል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔር ወልድ ሥጋ መሆን ነው። የእግዚአብሔር ተስፋዎች ሁሉ በእርሱ ተፈጽመዋል (2ኛ ቆሮንቶስ 1፥20)። ሁሉም የብሉይ ኪዳን ተምሳሌቶች ማለትም የክህነት፣ የቤተ መቅደስ እና የንግሥና ተቋማት፣ የስደት፣ የግዞት እና ከግዞት የመመለስ ክስተቶች ፍጻሜያቸውን በእርሱ አግኝተዋል። ስለዚህ ሙሉውን የመጽሐፍ ቅዱስ የአምልኮ ሥነ መለኮት ለመረዳት፣ ኢየሱስ የሙሴን ኪዳን አምልኮ እንዴት እንደ ፈጸመ እና እንደ ለወጠ መረዳት አለብን።

እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል መገኘቱን የገለጠበት በመጀመሪያ በድንኳኑ ቀጥሎም በመቅደሱ ነበር። ኢየሱስ እነዚህን የብሉይ ኪዳን መዋቅሮች ፈጽሟል፤ ስለዚህ ተክቷቸዋል። ዮሐንስ ቃል ሥጋ እንደሆነ እና ቃል በቃል በእኛ አደረ ወይም “ደነኮነ” (Tabernacled among us) ብሎ በዮሐንስ ወንጌል 1፥14 ይነግረናል። ኢየሱስ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ” በማለት ቃል ገባ (ዮሐንስ 2፥20)። በሌላ አነጋገር፣ የኢየሱስ አካል አሁን ቤተ መቅደሱ፣ እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚገናኝበት፣ መገኘቱን የሚገልጥበት እና ኀጢአታቸውን የሚያስወግድበት ቦታ ነው (ዮሐንስ 2፥21–22)። ለዚህ ነው ኢየሱስ ሰዐቲቱ ደርሳለች ብሎ የተናገረው። ለዚህም ነው ኢየሱስ እውነተኛ አምላኪዎች በኢየሩሳሌም አምልኮ ማድረግ ሳያስፈልጋቸው በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል ያለው (ዮሐንስ 4፥21-24)።

ኢየሱስ የኢየሩሳሌምን ምድራዊ ቤተ መቅደስ ወደ ፍጻሜ አመጣው፤ እንዲሁም ተካው። በአሁኑ ጊዜ እርሱ(ኢየሱስ) እውነተኛ አምላኪዎች እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት “ቦታ” ነው። [3]

ኢየሱስ ከሙሴ ቃል ኪዳን፣ ከማደሪያው ድንኳን እና ከመቅደሱ ጋር የተያያዘውን አጠቃላይ የመሥዋዕትን ሥርዐት ፈጽሟል፤ እንዲሁም ተክቷል። የዕብራውያን መልእክት፣ “ራሱን በሰጠ ጊዜ፣ ስለ ኀጢአታቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት አቅርቧልና” በማለት በየዕለቱ መሥዋዕት ማቅረብ ከሚያስፈልጋቸው ካህናት በተለየ፣ ኢየሱስ የሕዝቡን ኀጢአት ማስተሰረዩን ይነግረናል  (ዕብራውያን 7፥27)። የኢየሱስ የአንድ ጊዜ መሥዋዕትነት እንደ አሮጌው ኪዳን መሥዋዕት ውጫዊውን ሥጋ ብቻ የሚያነጻ ሳይሆን፣ ይልቁንም ኅሊናችንን ያነጻል፤ እንዲሁም ውስጣችንን ያድሳል (ዕብራውያን 9፥13-14)። ኢየሱስ ሕዝቡን በአንድ መሥዋዕት ፍጹማን ስላደረጋቸው፣ ከእንግዲህ የወይፈኖችና የፍየሎች መሥዋዕት አያስፈልግም (ዕብራውያን 10፥1–41011–18)።

ኢየሱስ የሌዋውያንን መሥዋዕቶች አሟልቷል፤ እንዲሁም ተክቷል። ደሙ አሁን የዘላለምን ቤዛነታችንን ያጸናል (ዕብራውያን 9፥12)።

እንደዚህ እያብራራሁ መቀጠል እችል ነበር። ዋናው ነጥብ የኢየሱስ የማዳን ሥራ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ባለው ግንኙነት ሥር ነቀል ለውጥ አምጥቷል ነው። ኢየሱስ የመረቀው አዲሱ ቃል ኪዳን አሮጌውን ማለትም እግዚአብሔር በሲና በሙሴ በኩል የገባውን ኪዳን ያረጀ አድርጎታል (ዕብራውያን 8፥6–713)። አሁን፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ በኢየሱስ መሥዋዕት በማመን ኀጢአታቸው ይሰረይላቸዋል። አሁን፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ በክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት እና በውስጣቸው በሚኖረው መንፈስ አማካይነት የእርሱን የጸጋ መገኘትን (presence) ይለማመዳሉ። አሁን፣ ሁሉም የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር የመቅረብ ሙሉ መብት አላቸው (ዕብራውያን 4፥1610፥19–22)፣ እንደ ቀድሞው ጥቂት ቁጥር ያላቸው ካህናት ብቻ አይደሉም።

3. በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኝ የኅብረት አምልኮ

ይህ ሁሉ በአዲሱ ኪዳን ዘመን ላለው የኅብረት አምልኮ ምን ማለት ነው? ሊታወቅ የሚገባው የመጀመሪያው ነገር የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሕግጋቶች በሁሉም አማኞች ሕይወት ላይ ተግባራዊ ሆነዋል። በሮሜ 12፥1 ጳውሎስ “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ እርሱም የእናንተ መንፈሳዊ አምልኮ ነው” ብሎ ጽፏል ። አሁን እኛ እራሳችንን እንጂ እንስሳትን አንሰጥም። የክርስቲያን ሕይወቱ በሙሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት የሆነ አገልግሎት ነው።

ወይም ዕብራውያን 13፥15ን እንመልከት፦ “ስለዚህ ዘወትር የምስጋናን መሥዋዕት ይኸውም ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በኢየሱስ አማካይነት ለእግዚአብሔር እናቅርብ።” ምስጋናችን መሥዋዕታችን ነው፤ እናም ያለማቋረጥ እናቀርባለን ይህም በእሁድ ጠዋት ለአንድ ሰዓት ብቻ የሚደረግ አይደለም። የእግዚአብሔርን ስም የሚያውቁ የከንፈሮች ፍሬ የምስጋና መዝሙሮችንም ያጠቃልላል፤ ነገር ግን በይበልጥ በድፍረት ወንጌሉን በአደባባይ መናገር፣ የእውነትንና የፍቅርን ቃል ለሌሎች መናገር፣ የምንናገረውን ቃል ሁሉ በክርስቶስ ሥልጣን ሥር ማድረግ ነው።

ይህ ማለት “አምልኮ” በዋናነት በእሁድ ቤተ ክርስቲያን የምናደርገው ነገር አይደለም ማለት ነው። ይልቁንም አምልኮ መላው ሕይወታችንን የሚሸፍን መሆን አለበት። አምልኮ ለክርስቲያን በተቀደሰ ጊዜና ቦታ የተገደበ አይደለም፤ ምክንያቱም እኛ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር በእምነት አንድ ስለሆንን እና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ስለሆንን ነው። እነዚህ ሁለቱ ምክንያቶች በግልም ሆነ በጋራ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንድንሆን አድርገውናል (1ኛ ቆሮንቶስ 3፥16–176፥19ኤፌሶን 2፥22)።

ታዲያ አሁን በዚህ በአዲሱ ኪዳን ውስጥ የኅብረት አምልኮን የሚገልጸው ምንድን ነው? ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ እና መስበክ (1ኛ ጢሞቴዎስ 4፥14)፤ ቅኔዎችን፣ ውዳሴዎችን እና መንፈሳዊ መዝሙሮችን በአንድነት መዘመር (ኤፌሶን 5፥18–19ቆላስይስ 3፥16)። መጸለይ (1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥1–28)፤ የጥምቀትን እና የጌታን እራት ሥርዐቶች ማክበር (ማቴዎስ 28፥191ኛ ቆሮንቶስ 11፥17–34)፤ ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እርስ በርሳችን መነቃቃት (ዕብራውያን 10፥24-25)።

በአዲሱ ኪዳን ውስጥ ስለ ኅብረት አምልኮ በጣም አስደናቂ ከሆኑት ነገሮች አንዱ መላውን አካል በመገንባት ላይ ያለው የማያቋርጥ ትኩረት ነው። ጳውሎስ፣ “የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁም በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁም ለእግዚአብሔር ዘምሩ” በማለት ጽፏል (ቆላስይስ 3፥16)። ለጌታ ስንዘምር እርስ በርሳችን እንማማራለን፤ እንመካከራለን። እግዚአብሔርን ስናመሰግን እርስ በርሳችን እንገነባባለን። ጳውሎስ በኅብረት ስንሰበሰብ የምናደርገው ነገር ሁሉ በክርስቶስ ያለውን አካል ለማነጽ በማሰብ እንዲሆን ብዙ መክሯል (1ኛ ቆሮንቶስ 14፥26)።

በቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ስብሰባውን ልዩ የሚያደርገው የምናመልክበት ጊዜ መድረሱ ሳይሆን እግዚአብሔርን አንድ ላይ በማምለክ እርስ በርስ የምንታነጽበት ጊዜ መሆኑ ነው።

ክርስቶስ በመረቀው በአዲሱ ኪዳን ምክንያት በአዲስ ኪዳን ዘመን የሚደረገው አምልኮ፣ በአሮጌው ኪዳን ይደረግ ከነበረው የኅብረት አምልኮ የተለየ መልክ አለው። በዓመት ለጥቂት ጊዜያት ብቻ የነበረው የኅብረት ስብሰባ አሁን በየሳምንቱ ሆኗል። በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ከመሰብሰብ ይልቅ አማኞች በሚኖሩበት ቦታ በየትኛውም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይሰበሰባሉ። የእግዚአብሔር መገኘት በቅድስተ ቅዱሳን ብቻ ተወስኖ በካህናቱ ተጠብቆ ከመቆየቱ ይልቅ፣ እግዚአብሔር አሁን በመንፈሱ በሁሉም ሕዝቡ ውስጥ ይኖራል፤ እናም ክርስቶስ ሕዝቡ በሚሰበሰቡበት ቦታ ሁሉ አብሯቸው አለ (ማቴዎስ 18፥20)። እጅግ ብዙ የሆኑ ተከታታይ መሥዋዕቶችን እና መባዎችን ከማቅረብ ይልቅ ክርስቲያኖች ቃሉን ለመስማት፣ ቃሉን ለመስበክ፣ ቃሉን ለመጸለይ፣ ቃሉን ለመዘመር  እና ቃሉን በሥርዐቶች ውስጥ ለማየት ይሰበሰባሉ። ሁላችንም በክርስቶስ ወደ ሙሉ ሰውነት እንድንደርስ ይህ ሁሉ አካልን በፍቅር ለማነጽ ያለመ ነው (ኤፌሶን 4፥11-16)።

4. ለጋራ አምልኮ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ

በኅብረት የምናመልክበት ጊዜ ላይ ምን ማድረግ እንዳለብን እንዲያስተምረን መጽሐፍ ቅዱሳችንን የምናነበው ታዲያ እንዴት ነው?

በርግጥ በመጀመሪያ፣ በቤተ ክርስቲያን መደበኛ ጉባኤዎች ላይ ምን ማድረግ እንዳለብን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን አስረግጦ መናገር አስፈላጊ ይመስለኛል። ሕይወታችን ሁሉ አምልኮ ቢሆንም፣ የቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ኅብረታችን በክርስትና ሕይወት ውስጥ ልዩ ቦታ እንደሚይዝ አስታውሱ። ሁሉም ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን እንዲሰበሰቡ ይጠበቅባቸዋል (ዕብራውያን 10፥24–25)። ቤተ ክርስቲያን መገኘት ለክርስቲያን አማራጭ አይደለም። ይህም ማለት፣ በአምልኮ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን የምትሠራው እያንዳንዱ ነገር ውጤታማ ሆኖ በአባሎቿ እንዲደረጉ የሚጠበቅ ልምምድ ይሆናል ማለት ነው። ጳውሎስ ክርስቲያኖች በሰው የተቀረፁ መመሪያዎች ወይም የአምልኮ ሥርዐቶች በኅሊናቸው ላይ እንዲጫኑ እንዳይፈቅዱ አሳስቧቸዋል (ቆላስይስ 2፥16-23)።

እነዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሖች በታሪክ የአምልኮ “ገዢ መርሖች” ተብሎ ከሚጠራው ጋር እንዲጨመሩ እመክራለሁ።[4] ማለትም፣ በኅብረት ስብሰባዎቻችን ላይ፣ አብያተ ክርስቲያናት መተግበር ያለባቸው ልምምዶች፣ በቅዱሳት መጽሐፍት ውስጥ በግልጽ ትእዛዝ ሆነ በመደበኛ ምሳሌነት በአዎንታዊ መልኩ የተደነገጉትን ብቻ ነው። ከዚህ የተለየ ሌላ ማንኛውንም ነገር ማድረግ በክርስትናን ነፃነት ላይ ማመቻመች ነው፤ ስለዚህም አብያተ ክርስቲያናት እንዴት በአንድነት ማምለክ እንዳለብን ለመንገር ቅዱሳት መጻሕፍትን ሊመለከቱ ይገባል፤ እናም ቅዱሳት መጻሕፍት እንድናደርግ የሚነግሩንን ብቻ ማድረግ አለባቸው።

ነገር ግን ያ ጥያቄ ያስነሳል፤ ቅዱሳት መጻሕፍት በትክክል ምን እንድናደርግ ይነግሩናል? ይህን በትክክል ሳስቀምጥ፣ በአምልኮ ጉዳይ ላይ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መደበኛ እና አስገዳጅ እንደሆኑ እንዴት ልንናገር እንችላለን? ይህንን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ለመመለስ መጽሐፉን መግለጥ ያስፈልጋል፤ እዚህ ላይ በጣም አጭር ንድፎችን አቀርባለሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምልኮ የሚሰጠው ትምህርት ምን እንደሆነ መመርመር ጥበብን ይጠይቃል፤ ምክንያቱም ቅዱሳት መጻሕፍት የትም ስፍራ ላይ እንዲህ እና እንዲያ በማለት መደበኛና የተሟላ፣ “የአገልግሎት ሥርዐት” ስላላቀረቡልን ነው። ነገር ግን በአዲስ ኪዳን ውስጥ በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ላይ በግልጽ የተቀመጡ አንዳንድ ትዕዛዛት አሉ። የኤፌሶን እና የቆላስይስ አብያተ ክርስቲያናት ሁለቱም እንዲዘምሩ ታዝዘዋል (ኤፌሶን 5፥18-19ቆላስይስ 3፥16) እንዲሁም  የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በመዘመር ተጠርታለች (1ኛ ቆሮንቶስ 14፥26)፤ ይህም ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት መዘመር እንደሚጠበቅባቸው ይጠቁማል። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት መመራት እንዳለባት እንዲያውቅ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ጢሞቴዎስን ቅዱሳት መጻሕፍትን እንዲያነብና እንዲሰብክ አዞታል (1ኛ ጢሞቴዎስ 3፥154፥14)፤ ይህ የሚጠቁመን ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብና መስበክ ለሁሉም ቤተ ክርስቲያን የሆነ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ ለአንድ ቤተ ክርስቲያን ብቻ እንዳልሆነ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ “በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ” (ሮሜ 16፥16) እንደሚሉት ያሉ አንዳንድ ትእዛዛት ለሁሉም ቤተ ክርስቲያን የተሰጡ ትእዛዛትን የሚገልጹ ይመስላሉ (“ክርስቲያናዊ በሆነ ፍቅር መቀባበል”) የሚገልጹ ይመስላል።

በተጨማሪም አንዳንድ ዐውዳዊ የሆኑ ትእዛዛት ሰፋ ያለ ትርጉም ሊኖራቸው ይችላል። ለምሳሌ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ገንዘብ እንዲያስቀምጡ ነግሯቸዋል። ያ በኢየሩሳሌም ለነበሩ ቅዱሳን የተደረገ የተለየ ልገሳ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት መምህራኖቻቸውን በገንዘብ እንዲደግፉ ታዝዘዋል (ገላትያ 6፥6) ስለዚህ መስጠት በኅብረት አምልኮ ውስጥ ቦታ ሊኖረው ይችላል።

እስካሁን በአዲሱ ኪዳን ማዕቀፍ ውስጥ ስላለው አምልኮ ነው የተወያየነው። በአሮጌው ኪዳን ውስጥ ስላለውስ? በአሮጌው ኪዳንም ስለ አምልኮ ብዙ ትእዛዛት አሉት፦

በመለከት ድምፅ አመስግኑ፤ በበገናና በመሰንቆ አመስግኑት።

በከበሮና በዘፈን አመስግኑት፤ በአውታርና በእምቢልታ አመስግኑት።

ተርገብጋቢ ድምፅ ባለው ጸናጽል አመስግኑት፤ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑት።

 (መዝሙር 150፥3–5 )

ይህ ማለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ለመሆን የቤተ ክርስቲያናችን የአምልኮ መርኀ ግብር መለከት፣ በገና፣ መሰንቆ፣ ከበሮ፣ እምቢልታ፣ ጸናጽልና ጭፈራዎችን ማካተት ይኖርበታልን? የእኔ መልስ አይ የሚል ነው።

አንዳንድ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች  (ዕብራውያን 8፥6) “አሮጌው ኪዳን” ብለው የሚጠሩት (መዝሙር)’ በሙሴ ኪዳን ሥር የአምልኮ መግለጫዎች መሆናቸውን አስታውስ። በኤርምያስ 31 ላይ የተነገረው አዲስ ኪዳን አሁን ስለመጣ አሮጌው ኪዳን ጊዜ ያለፈበት ሆኗል። እኛ ከእንግዲህ በሙሴ ሕግ ሥር አይደለንም (ሮሜ 7፥1–6ገላትያ 3፥23–26)። ስለዚህ ከሙሴ ዘመን ጋር የተቆራኙ የአምልኮ ሥርዐቶች በእኛ ላይ አስገዳጅነት አይኖራቸውም። ቤተ መቅደሱ የሚገለገለው በካህናት ነበር፣ አንዳንዶቹም በቅዳሴ መዝሙር የተካኑ ናቸው (1ኛ ዜና 9፥33)። በመዝሙር 150 (2ኛ ዜና 5፥12-139፥11) ላይ የተጠቀሱ የሙዚቃ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ ሲውሉ እናያለን። ነገር ግን መዝሙር 150 ክርስቲያን እንዴት ማምለክ እንዳለበት የሚጠቁም ማሳያ አድርገን ልንወስደው አንችልም። ይልቁንም፣ ከቤተ መቅደሱ እና ከሌዋውያን ክህነት ጋር የተያያዘውን የአሮጌውን ኪዳን የአምልኮ መልክ የሚያሳይ ነው።

ይህም ለቤተ ክርስቲያን ጉባኤ መዝሙር ምን ዐይነት መሣሪያ ትክክለኛ አጃቢ ሊሆን ይችላል የሚለውን ጥያቄ በራሱ አይመልስም። ማለትም በብሉይ ኪዳን ይደረግ የነበረው የእንስሳት መሥዋዕት ተግባራዊ መሆን እንደማይችል እንዲሁ ብሉይ ኪዳን ላይ የሚገኘውን አሠራር ሁሉ ለመተግበር መሞከር ከሥርዐት ውጭ መሆን ነው። ብዙ የክርስቲያን የአምልኮ ልምምዶችም ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው የአምልኮ ነገረ-መለኮት ጋር የሚጣረሱት እዚህ ላይ ነው፤ ማለትም የሌዋውያን ክህነት እና የቤተ መቅደስ አምልኮ ሥርዐትን ወደ አዲሱ የቃል ኪዳን ዘመን አምጥቶ አዲሱ ኪዳን ላይ ለመተግበር መሞከር ነው። በርግጥ ብዙ የብሉይ ኪዳን አምልኮዎች በምን ዐይነት መንገድ አምልኮአችንን ማድረግ እንዳለብን ይነግሩናል። ለምሳሌ መዝሙረ ዳዊት በአክብሮትና በፍርሀት፣ በደስታና በመደነቅ፣ በምስጋና እና በደስታ እንድናመልክ ያስተምረናል። ነገር ግን ምን ዐይነት ቁሶችን መጠቀም እንዳለብን እና ምን ዐይነት ሥርዐቶችን መከተል እንዳለብን አይገልጽም።

ይህ ማለት አሮጌው ኪዳን  በራሱ በኪዳኑ ውሰጥ ለነበረው የእግዚአብሔር ሕዝብ መመሪያ ሆኖ እንዳገለገለው ሁሉ አዲሱ ኪዳንም በዚሁ ኪዳን ላለው የእግዚአብሔር ሕዝብ የራሱን አዲስ መመሪያ ይሰጣል። በእርግጥ እግዚአብሔር አንድ የድነት እቅድ ነው ያለው፤ ያዳነውም አንድ ሕዝብ ነው። ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ከእርሱ ጋር ያለው ግንኙነት ከክርስቶስ መምጣት እና ከአዲሱ ኪዳን መመስረት በኋላ በእጅጉ ተቀይሯል።

ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ነገረ መለኮት መርሖችን መጠቀም የሚያስፈልገን ለዚህ ነው። ወደ ኅብረት አምልኮ ሥነ መለኮት ለመድረስ፣ ሁለቱን ኪዳኖች ጎን ለጎን አስቀምጠን በተምሳሌቱና በእውነተኛው መካከል ያለውን ትሥሥር መፈለግ፣ የተስፋ ቃል የሆነውን እና ፍጻሜ ያገኘውን ማስተዋል፣ የተቋረጠውን እና ቀጣይነት ያለውን መለየት መቻል አለብን።

የክርስቶስ አዲስ የቃል ኪዳን ሕዝብ፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ እንደ መሆናችን መጠን፣ እግዚአብሔር ራሱ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በነገረን መሠረት በመንፈስ እና በእውነት እናመልካለን። የክርስቶስ አዲሱ ኪዳን ሕዝቦችና የተስፋው መንፈስ ማደሪያዎች እንደመሆናችን፣ በመንፈስና በእውነት እግዚአብሔርም በቃሉ ግልጽ ባደረገው መርሕ መሠረት እናመልካለን።

ይህንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የአምልኮ ሥነ መለኮት ጽሑፍ እንዳዘጋጅ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረብኝ፣ ዴቪድ ፒተርሰን፣ ከእግዚአብሔር ጋር መሳተፍ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የአምልኮ ሥነ-መለኮት (Downers Grove፥ InterVarsity Press፣ 1992) ይመልከቱ።

                                                                                                            ቦቢ ጃሚሰን