ካልቪናዊያን የሰከኑ እና ቸሮች ሊሆኑ ይገባል

ለአንድ ካልቪናዊ ቁጡ እና ደግነት የጎደለው ተደርጎ ከመግለጽ የከፋ መግለጫ እምብዛም የለም። እንዴት ነው የእግዚአብሔርን ትልቅነት ለመረዳት እየተፋለሙ ያሉ ሰዎች፣ መልሰው በመከራ ውስጥ ያለውን ኅብረተሰብ ሰላም የሚነሱት? ደግሞስ እንዴት ነው የጸጋን አስተምህሮ ያለምንም እፍረት እየወደዱ፣ አካሄዳቸው ግን ጸጋ ያልተሞላበት ሊሆን የሚችለው? እኛ ካልቪናዊያን እግዚአብሔር በድነት፣ እንዲሁም በሁሉ ነገር ላይ ሉዓላዊ መሆኑን በግልጽ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነትን እናምናለን። ታዲያ እግዚአብሔር ገና አላበራቸውም ብለን የምናምናቸውን ዐይኖች መጠንቆል፣ እግዚአብሔርን ራሱን እንደማንጓጠጥ እንደሚቆጠር እንዴት አይታየንም?

የተወደደው ፓስተርና የመዝሙር ደራሲ ጆን ኒውተን (1725-1807)፣ “ካልቪናዊያን ከሰዎች ሁሉ ይልቅ ጭምቶች እና ታጋሾች ሊሆኑ ይገባቸዋል” ሲል ይናገራል። እናምናለን ብለን የምንናገረውን የእውነት የምናምን ከሆነ፣ ዓለማችን ምንም ያህል ቁጡና ደግነት የጎደላት ብትሆን፣ እኛ ካልቪናዊያን ከሁሉ በላይ የሰከንን እና ቸሮች ልንሆን ይገባል። እንዲሁም የጸጋ አስተምህሮን አብረውን የሚያምኑ ወንድም እና እኅቶች የዚህን የተትረፈረፈ ጸጋ አስተምህሮ በማይጋሩ ሰዎች አለማመን ወይም ጭካኔ ላይ ቁጣን በሚያሳዩበት ወቅት ለሚያደርጉት ነገር ኀላፊነት እንዳለባቸው ልናስታውሳቸው ይገባል።

ይሁን እንጂ ካልቪናዊያን አምናለሁ ብለው በሚመሰክሩት ጸጋ ልክ መኖር ሳይችሉ ሲቀሩም ልንደነግጥ አይገባም። በመሠረቱ በፍጹም ውድቀት የምናምን ነንና። በቂ ምክንያት ባይሆንም ልንደነግጥ ግን አይገባንም።

“ዘ ጎስፕል ኮአሊሽን” የሚባለውን ድርጅት የመሠረተው ዲ.ኤ.ካርሰን የተባለ አንድ ፕሮፌሰር እንደሚናገረው፣ “እኛ የሰው ልጆች ማንኛውንም እውነተኛ አስተምህሮ የማጣመም እና ወደ አስቀያሚ ቅርጽ የመቀየር አቅም አለን። እነዚህን አስተምህሮዎች ልክ ባልሆነ ባሕርይ ይዘን ራሳችንን የበላይ አድርገን ልንቆጥር እንችላለን። ይህም የሆነ ዐይነት ትዕቢት ሊፈጥር ይችላል።”

ካልቪናዊያን የበለጠ ለመከራ የተዘጋጁ ናቸው?

የቁጡ ካልቪኒስቶች መኖር አንዱ አሳዛኝና ተጨባጭ እውነታ ነው። ተለዋዋጭ ባሕርያት በየትኛውም ዘመን ሊከሰቱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ማኅበረሰባችን በወደቀበት በዚህ ዘመን የበለጠ ተጋላጮች እንሆናለን። ይህም ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትና ላይ ተቃውሞ በበዛ ቁጥር የበለጠ አንገብጋቢ ያደርገዋል።

እግዚአብሔር በአሠራሩ መልካም እንደሆነ እንዲሁም ነገሮች በእርሱ ቁጥጥር ውስጥ እንዳሉ ማመን የበለጠ ገር እና ታጋሽ እንድንሆን ሊያደርገን ይገባል። ይሁን እንጂ በባህል ነውጥ ውስጥ ስንሆንም ጭምር የሰከንን እንድንሆን ሊያደርገን ይገባልን? በባለፈው ትውልድ ዘንድ የነበረው የካልቪናዊነት ማንሰራራት በክርስቲያኖች ላይ እየመጣ ያለውን ግፊት ብሎም ስደት ተቋቁመን መጋፈጥ እንድንችል ዝግጁ ያደርገናል ወይ ስል ካርሰንን ጠይቄው ነበር።

“ያደርገናል ብዬ አምናለሁ። በሚገባ ዝግጁ ሊያደርገን ይገባል ባይ ነኝ። በተለይም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የእግዚአብሔርን መግቦት ሙሉ ለሙሉ በመታመን እና ወይኔ እግዚአብሔር በዚህኛውስ ተሸነፈ ወይም የመሳሰሉ አሳቦችን እንዳናስብ በማድረግ አዎን ሊያዘጋጁን ይገባል። ይሁን እንጂ ከሁኔታው የበለጠ ብዙ ነገር እንናገራለን። ኀጢአታችንን እናውቃለን።

“ካልቪናዊ ስለሆንክ ከሌላው የተሻለ የዚህን ዓለም ጫና መቋቋም ትችላለህ ብዬ ለማለት አልደፍርም” በማለት ካርሰን ያክላል “ይልቁንም ራስህን ካልቪናዊ እንደሆንክ የምትቆጥር ከሆነ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊ መልካምነት ለመታመን ራስህን አስለምድ። በበላይነት የምንጓደድበት እና የተሻልን እንደሆንን የሚሰማን ጊዜ አይደለም። ጊዜው የንስሓ እና እግዚአብሔርን ምሕረት የምንለምንበት ነው።  

ባዶውን ስፍራ የእግዚአብሔር ትልቅነት ይሞላዋል

“እግዚአብሔር ትልቅ ነው” የሚለው አስተምህሮ እንዲያንሰራራ አስተዋፅኦ ካደረጉ ነገሮች ውስጥ አንዱ፣ በቀደመው ትውልድ ለነበረውና ለተቃለለው የወንጌላዊያን አስተምህሮ የተሰጠው ምላሽ ነበር። አንዳንዶች በጣም ቀላልና ላይ ላዩን የሆነ አደረጉት። ኢየሱስን እመን እና እንደ ግል አዳኝህ አድርገህ ተቀበል፤ ከዚያም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ይሆናል ይላሉ። ሰዎች የሚፈልጉት ይበልጥ የሚታመን ነገርን እንዲሁም የበለጠ ኀይል ያለውንና የሚቀይር ነገርን እንጂ መጨረሻው እንዲህ የቀለለውን አስተምህሮ አልነበረም።

እግዚአብሔርን በትልቅነቱ የማቅረብ ያልተበረዘው አስተምህሮ ለብዙዎች ባዶነታቸውን ሞልቶላቸዋል። እንዲሁም ታማኝ ክርስቲያኖችን ያነጣጠሩና በዚህ ዘመን እየጨመረ በመጣ በዓለማዊ ምሁራን ለሚሰነዘሩ ስድቦች፣ ማንጓጠጥ እና ተቃውሞ አዘጋጅቷቸዋል። በዙሪያችን ያለው ዓለም እየተናወጠ ያለ ሲመስለንም ጭምር፤ የእግዚአብሔር ነጻ ጸጋ አስተምህሮ ኀጢአተኞች ሆነን እንኳ፣ በመመረጥ ውስጥ፣ በተደረገልን ስርየት ውስጥ፣ በድነት ውስጥ፣ በመጽናት ውስጥ ብሎም በሁሉም ነገር ውስጥ የተጠበቅን ሰዎች እንድንሆን ሊያደርገን ይቻለዋል ደግሞም እንድንሆን ሊያደርገን ይገባል።

መከራን አናሞካሸውም

በእግዚአብሔር መግቦት እያንሰራራ ያለው ካልቪናዊነት እየመጣ ላለው ወጀብ ለብዙ ክርስቲያኖች ያስፈልጋቸው የነበረውን መልሕቅነት ለመስጠት በጊዜው የደረሰ ሳይሆን አይቀርም። ይሁን እንጂ አንድ በግልጽ ልንለው የሚያስፈልገው ነገር በእግዚአብሔር ፍጹም ሉዓላዊነት ማመን መከራን እናሞካሻለን ማለት እንዳልሆነ ነው። በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ካናዳ ውስጥ ፕሮቴስታንቶች ላይ ይደርስ የነበረውን ጥላቻ መከራን የሚቀበል ባፕቲስት ሆኖ በማደጉ፣ ካርሰን ይህንን ከግል ሕይወቱ በሚገባ የሚያውቀው ነው።

“ልጅ እያለሁ በምኖርበት አካባቢ የነበረ ጫማ ሠሪን አስታውሳለሁ። የዚያን ጊዜ ሱቅ ውስጥ ጫማ የሚሸጥ ሰው ማለት አይደለም።  ጫማውን የሚሠራው ራሱ ነበር። የሰዎችን እግር ይለካና ጫማ ይሠራላቸው ነበር። የሚኖረውም ሴንት ሲሪል በምትባል ትንሽ መንደር ውስጥ ነበር። ታዋቂ ነበር። ሥራውን የሚያከናውን አነስተኛ ነጋዴ ነበር። በግልጽ በሚታይ ሁኔታ ወደጌታ ሲመጣ 90 በመቶ የሚሆነውን ደንበኛውን አጣ። እንዴት አድርጎ ሊወጣው እንደሚችል አላወቀም። ቀጥሎም ሱቁን በቦምብ አጋዩበት። ከኪዩቤክ ግዛት ቤተሰቦቹን ይዞ ኦንታሪዮ ወደምትባል ግዛት ሄደ።”

“ለእርሱ ቦታ መቀየር ብቻ ነበር። እንግሊዘኛ መማር ነበረበት። ኪዩቤክ ውስጥ ፈረንሳይኛ ስለሆነ የሚናገሩት ከዚያ በፊት ብዙም እንግሊዘኛ አያውቅም ነበር። በእኛ ቤተ ክርስቲያን እይታ ግን ያጣነው ትልቅ ነገር ነበር። ከእኛ እይታ የኪዩቤክ ግዛት ያጣቸው እውነተኛ ክርስቲያን ነበር። ይህንን የሚመስሉ ብዙ ክስተቶች ነበሩ። ይሄኛው የተጋነነው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ተከስቶ ነበር።”

“እንደዚህ ባሉ ነገሮች ውስጥ ስታልፉ የምትጋፈጧቸው ጫናዎች በወቅቱ በደስታ አይሞሏችሁም። ከጊዜ በኋላ ግን ወደ ኋላ መለስ ብላችሁ እግዚአብሔር እነዚያን አጋጣሚዎች እንዴት አድርጎ ሰዎችን ለማጠንከር እንደተጠቀመባቸውና ከ20 እና 30 ዓመታት በኋላ ለመጡ እውነተኛ ፍሬያማነት እንዳዘጋጃቸው መመልከት ትችላላችሁ። ይሁን እንጂ በእነዚያ 20 እና 30 ዓመታት ውስጥ ስታልፉ ምንም የምታሞካሹት ነገር አይደለም።

አስተምህሮአችሁ ትሑታን አድርጓችኋል?

ሁለተኛው አሳዛኝ እውነታ ደግነት የጎደላቸው ካልቪናዊያን መኖራቸው ነው። ከሌሎች ጋር ባለን መስተጋብር የምናምነውን አስተምህሮ በትክክል እየተገበርን እንደሆነ እራሳችንን በየጊዜው መጠየቅ ተገቢ ነው። ትልልቅ የማኅበረሰብ ግፊቶችን እና ማኅበረሰባዊ ቀውሶችን የሚያክሉ ትልልቅ ነገሮችንም ይሁን ወይም ከማያምኑ ጋር አሊያም ከሌሎች የክርስትና ዘርፎች ጋር  የሚኖሩን ጥቃቅን ውይይቶችን በተመለከተ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት የምናምን ሁሉ ስለ ዓለም ጉዳይ ሰከን ልንል ለሕዝቦቿም ቸሮች ልንሆን ይገባናል።

በተለይም ኒውተን አስተምህሯቸውን የማይጋሩ ሰዎች ላይ ጫን ለሚሉ ካልቪናዊያን መልካም ግን ደግሞ ገንቢ ምክር አለው። እንዲህ በማለት ያስታውሳቸዋል፦ “መራር የሆኑ፣ ቁጡ እና ንቀት ያዘሉ ቃላትን መሰንዘር ትሑት የሚያደርገው የካልቪናዊነት አስተምህሮን ያጎድፋሉ። ቀጠል አድርጎም ፊት ለፊት ይጠይቃል “ ካልቪናዊነት ትሑታን አድርጓችኋል?”።

ቶኒ ሬንኪ ሊጠቅም በሚችል ሁኔታ ከኒውተን ሕይወት እንዳጤነው፣ “ካልቪናዊነትን በትክክል ከተረዳነው የተሰበርን እንድንሆን ያደርገናል። ይህም ደግሞ ለሌሎች ግልጽ ሊሆን ያስፈልጋል” ይለናል።

ኒውተን በዘመኑ ትዕቢተኛ እና በራሱ የሚደገፍ ካልቪናዊ ለማግኘት ብዙም ችግር አልነበረበትም። እናም እንዲህ ሲል ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር፦ “ካልቪናዊነትን የትሕትናቸው ማስረጃ አድርገው የሚያቀርቡና በቃል ብቻ ፍጥረትን ዝቅ አድርገው የድነትን ክብር ለጌታ የሚሰጡ፣ ሆኖም ግን በምን ዐይነት የመንፈስ አካሄድ እንዳሉ የማያውቁ ካልቪናዊያን መኖራቸው ያስፈራኛል።”

የኒውተን ምክር ጥሩ እይታ ነው። እንዲሁም የሚወቅስ ነው። “ከማያምን ሰው” ጋር አለመግባባት ውስጥ ስትገቡ ከቁጣችሁ ይልቅ ርኅራኄአችሁ የሚያሻው እንደሆነ አስታውሱ። በኢየሱስ ከሚያምን ሰው ጋር ከሆነስ?

ከአጭር ጊዜ በኋላ በሰማይ ትገናኛላችሁ። የዚያን ጊዜ አሁን በምድር ላይ አለኝ ከምትለው ቅርብ ጓደኛ ይልቅ ውድ ይሆንልሀል። ያንን ጊዜ በአሳብህ እየተጠባበቅህ ምንም እንኳ ስሕተቱን መቃወም ሊያስፈልግህ ቢችልም በክርስቶስ አብረኸው ለዘለዓለም በመሆን ደስ የሚልህ የነፍስህ ዘመድ እንደሆነ ቁጠረው።

ይህ ምክር በኒውተን ዘመን እውነት እንደ ነበረ ሁሉ፣ ምናልባትም በእኛ ዘመን የተሰመረው መስመር በክርስትና ውስጥ ካሉ የተለያዪ ዘርፎች መካከል ካለው ይልቅ በማመን እና ባለማመን መካከል የተሰመረ በመሆኑ የበለጠ ትንቢታዊ ያደርገዋል። 

እግዚአብሔር መልካም ስለሆነ

ይሁን እንጂ ቸር እንድንሆን የሚያደርጉን የሥነ መለኮት ማጣቀሻዎች አይደሉም። ክርስቲያኖች የማይጨበጡ ግንኙነቶችን በማሰብ ብቻ ድንገት በመንፈስ ከሆነ ቸርነት ቸር አይሆኑም። ይልቁንም ነፍሳችንን የእግዚአብሔርን ቃል በመመገብ እና በውስጡ ያለውን በመምሰል ነው።

ቀደምቲቱ ቤተ ክርስቲያን ትንንሽ የቸርነት ምግባሮችን (ሐዋርያት ሥራ 10፥3324፥427፥328፥2) የማሞካሸት ታሪክ የነበራት ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ክፍሎች ላይ ክርስቲያናዊ ባሕርይ መገለጫው ቸርነት እንደሆነ ይናገራል (2ኛ ቆሮንቶስ 6፥6ቆላስይስ 3፥12ቲቶ 2፥5)። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለሰው ሁሉ ገር መሆን የሚገባቸው ሲሆን (2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥24) ሁሉም ክርስቲያኖች እርስ በእርሳቸው ርኅሩኆች እንዲሆኑ ያስፈልጋል (ኤፌሶን 4፥32)። ቸርነት የመንፈስ ፍሬ ነው (ገላትያ 5፥22)። ፍቅር ታጋሽ ነው ደግሞም ቸር ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 13፥4)። የአጽናፈ ዓለማችንን እያንዳንዷን ስፍራ የሚያስተዳድረው እግዚአብሔር ቸርነትን እንድናሳድግ ሲያዘን እርሱን እንድንመስል እያበረታታን ነው። ኢየሱስ እንደሚለን የሰማዩ አባታችን “ለማያመሰግኑ እና ለክፉዎች ቸር ነው” (ሉቃስ 6፥35)። በቸርነቱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል (ማቴዎስ 5፥45)። እንዲህ ያለው ቸርነቱ ወደ ንስሓ እንዲመራ የታለመ ነው (ሮሜ 2፥4)። እንዲህ ያለው ቸርነቱ መጻተኞችንም እንኳ ዘመናትን ባስቆጠረው የበረከት ዛፉ ላይ በእምነት ወስዶ ይተክላል (ሮሜ 11፥22)።

የዳንነው በእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር (ቲቶ 3፥4) ስለሆነ ደግሞም በቸርነቱ የገለጠልንን “ወደር የሌለውን የጸጋውን ባለጠግነት” (ኤፌሶን 2፥7) ስለምንጠባበቅ ወደ እኛ የተዘረጋውን ቸርነቱን ወደ ሌሎች ሰዎች ለማሻገር ነጻ ወጥተናል።

ካልቪናዊነት ተቃውሞን የበለጠ እንድንጋፈጥና ሌሎች ሰዎች ላይ እንዳናወጣው ሊያደርገን ይገባል። የሰዎችን ልብ መቀየር የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ እናምናለን ብለን እንናገራለን። ይህም ደግሞ የሰከኑ እና ቸር ሰዎች ወደ መሆን እንድንዘረጋ ሊያደርገን ይገባል።

ካርሰን እንደሚለው “እራሳችሁን ካልቪናዊ ብላችሁ የምትጠሩ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን ሉዓላዊ መልካምነት መረዳትን ተማሩ።”

በዴቪድ ማቲስ