ክርስቲያናዊ ሄዶኒዝምን በተመለከተ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አፈታትን ተከትሎ ሙግት ማቅረብ አንድ ነገር ነው። ሰዎች ይሄ እውነት ልባቸው ውስጥ ሰርጾ እንዲገባ መርዳት ግን ከዚህ የላቀ እና ከባዱ ነገር ነው። አሁን ላደርግ የምሞክረውም ይህንን ነው።
በመጀመሪያ ግን ክርስቲያናዊ ሄዶኒዝም ምንድን ነው?
ክርስቲያናዊ ሄዶኒዝም፣ “እግዚአብሔር ከመቼውም ይልቅ በእናንተ የሚከብረው፣ እናንተ ከምንም በላይ በእርሱ ስትረኩ ነው” በሚለው እምነት ላይ የተመሠረተ የሕይወት መንገድ ነው። ሁሉን አቃፊና እጅግ አስደሳች እውነት ነው። የዚህ አንድምታ ደግሞ እውነተኛ አምልኮ እና እውነተኛ በጎ ባሕርይ ሁሉ በእግዚአብሔር ውስጥ ደስታን ከመፈለግ ይጀምራል የሚል ነው።
ይህ የሆነበት ምክንያት እውነተኛ አምልኮ እና በጎ ባሕርይ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ለማክበር ካለ ፍላጎት ስለሚመነጭ ነው። ምክንያቱም እኛ የተፈጠርነው እግዚአብሔርን ለማክበር ነው (ኢሳይያስ 43፥7)። ጳውሎስም በመልእክቱ እንዲህ ሲል ይህንን አስቀምጧል፦ “ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” (1ኛ ቆሮንቶስ 10፥31)። ስለዚህ እግዚአብሔርን ለማክበር ካለን ፍላጎት ያልመነጨ የትኛውም መልካም ሥራ ወይም አምልኮ ኀጢአት ነው።
በሌሎች ነገሮች ካለን ደስታ ባነሰ መልኩ በእግዚአብሔር ደስ የምንሰኝ ከሆነ በዚያ ነገር እርሱ አይከብርም። ምክንያቱም ለእግዚአብሔር ያለን ቦታ ያነሰ ነው። ይህንን ከተረዳን፣ በምናደርጋቸው ድርጊቶች ሁሉ በእግዚአብሔር ደስ መሰኘታችንን ለማረጋገጥ ቸል አንልም። በድርጊቶቻችን ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበርነው ከሆነ፣ ከምንም ነገር በላይ በእርሱ መደሰትን ዓላማ ልናደርግ ይገባል።
ኢየሱስ፣ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ሲል፣ ስንሰጥ ይህንን እውነት ችላ ማለት አለብን ማለቱ አይደለም (የሐዋርያት ሥራ 20፥35)። እንዲያውም ጳውሎስ በዚያው ጥቅስ ላይ በምንሰጥበት ጊዜ፣ “ይህንን የጌታ የኢየሱስን ቃል እናስታውስ” ብሏል። የምንሻው በረከት ራሱ እግዚአብሔርን ካልሆነ እና ዓላማችንም ሌሎችን ወደዚህ ሐሴት ለመጥራት ካልሆነ፣ ለመባረክ ከመፈለግ የተነሣ ብቻ ለሌሎች መስጠት ራስ ወዳድነት ነው።
ተወዳጁን ጥቅስ መረዳት
ነገር ግን ሁሉም ወደ ክርስቲያናዊ ሄዶኒዝም መረዳት በትክክል አይደርሱም። ይህን መረዳት ለመያዝ ከሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በላይ የምንጠቀመው ጥቅስ 2ኛ ቆሮንቶስ 6፥10 ነው፤ “ሐዘንተኞች ስንሆን ሁል ጊዜ ደስተኞች ነን”
በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ማብራሪያ ወይም ምሳሌዎችን ሰጥቼ አላወቅም። በዚህ ጽሑፍ ግን ሁለቱንም አጠር ባለ ሁኔታ ማድረግ እፈልጋለሁ።
በ2ኛ ቆሮንቶስ 6፥3-10 ላይ፣ ጳውሎስ በአኗኗሩ በማንም መንገድ ላይ ዕንቅፋት እንዳላስቀመጠ (ቁጥር 3) ይልቁንም ራሱን በቻለው መንገድ እንደ አገልጋይ እንዳቀረበ በ30 የሕይወት ተሞክሮዎቹ ያስረዳናል።
ከእነዚሁ ሠላሳ የሕይወት ተሞክሮዎች መካከል አንዱ፣ “ሐዘንተኞች ስንሆን ሁልጊዜ ደስተኞች ነን” የሚለው ነው። ከሌሎች ተመሳሳይ ጥንዶች ጋር አብሮ ተቀምጧል፦ “በክብርና በውርደት፣ በመመስገንና በመሰደብ ኖረናል፤ ደግሞም እውነተኞች ስንሆን ሐሰተኞች ተብለናል፤ የታወቅን ስንሆን እንዳልታወቅን ሆነናል፤ ሞተዋል ስንባል እነሆ በሕይወት አለን፤ ብንደበደብም አልተገደልንም፤ ሐዘንተኞች ስንሆን ደስተኞች ነን፤ ድኾች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን፤ ምንም የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው” (2ኛ ቆሮንቶስ 6፥8-10)።
ለጳውሎስ እውነት የሆነው የቱ ነው?
በአንድ ወቅ እንዲህ የሚል ጥያቄ ደርሶኝ ነበር፦ “…ሐሰተኞች ተብለናል” የሚለውን እንደ እውነት ሳንወስድ፣ “ሐዘንተኞች ስንሆን” የሚለውን ግን ለምን እንደ እውነት እንወስዳለን? ለምንስ እንደ ሐዘንተኛ ተቆጥረን ነገር ግን ሁልጊዜ ደስተኛ እንደሆንን አድርገን አንረዳም?
ጳውሎስ ይህንን ማለቱ ነው ብዬ አላስብም፤ የዚህም ደግሞ ምክንያቱ ጳውሎስ እየተጠቀመ ከነበረው እውነትንና ውሸትን ከማነጻጸር መንገድ(እውነተኞች ስንሆን ሐሰተኞች ተብለናል) ሁለት እውነት የሆኑ ጥንዶችን ወደ መግለጽ መንገድ ቀይሯል(ለምሳሌ “ድኾች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እንናደርጋለን”)።
በጳውሎስ አስተሳሰብ “እንዳልታወቅን፣” “ሞተዋል፣” “ብንደበደብም፣” “ሐዘንተኞች፣” “ድኾች” እና “ምንም የሌለን” የሚሉት ሁሉም ስለ እርሱ እውነት ናቸው። ስለዚህ በቁጥር 9 መጀመሪያ ላይ ውሸት የሆኑትን እውነቱን በመናገር ካረመ በኋላ ሁለት ተቃራኒ የሚመስሉ ነገሮች ነገር ግን እውነት የሆኑ ነገሮችን መዘርዘር ይጀምራል፦ ያልታወቁ/የታወቅን፣ የሞትን/በሕይወት ያለን፣ ተደብድበናል/አልተገደልንም፣ ሐዘንተኞች/ደስተኞች፣ ድኾች/ባለጠጎች
ስለዚህ አዎን፣ ጳውሎስ ራሱን “ሐዘንተኛ” እንደሆነ ያስባል። በሮሜ 9፥2 ላይ ይህንን እንዲህ ሲል ገልጿል፤ “ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ጭንቀት በልቤ አለ . . ከክርስቶስ ተለይቼ የተጣልሁ እንድሆን እንኳ እወድ ነበር።” “የማያቋርጥ” ሐዘንና ጭንቀት! እጅግ የሚገርም ነው! ይህ ለታላቁ የደስታ ሐዋርያ እውነት ከሆነ፣ ለእኛስ እንዴት በእጅጉ አይሆንም? በእርግጥ ሕይወታችን በማያቋርጥ ሐዘኖች (እና ደስታ) ሊሞላ ይችላል። ይህ ሐዘን በውስጣችን ከሌለ እንደ ጳውሎስ የጠፉትን አንወድ ይሆናል።
እውነተኛ የሆነ ደስታ
ስለዚህ ክርስቲያናዊ ሄዶኒዝም የሞኝነት ወይንም አላፊ የሆነ ደስታ አይደለም። አንዳንድ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ደስተኞች እንደሆኑ ለማሳየት የሚለማመዱት ልምምድ ከክርስቲያናዊ ሄዶኒዝም እጅግ የራቀ ነው። ክርስቲያናዊ ሄዶኒዝም ውስጥ የሚገኘው ደስታ አስቂኝ የሆነ አይደለም። በክርስቲያናዊ ሄዶኒዝምን ውስጥ ደስታን በሳቅ መግለጽ ይቻላል፤ ነገር ግን ለእውነተኛ ደስታ ቦታ ለሌለው፣ የታይታ እና ልቅነት ለተሞላበት መንገድ ክርስቲያናዊ ሄዶኒዝም ቦታ የለውም።
ሲ.ኤስ. ሉዊስ፣ “ደስታ በገነት የምንሠራው ትልቁ ሥራ ነው” ብሏል (Letters to Malcolm, 1964, 299)። አሜን! “በዚህ መረዳት መመላለስ አለብን። የደስታችን ምንጭም ይህ መሆን አለበት። ይህም ደስታ የሚገኘው አንደኛቸው ለሌላኛቸው የበላይነትና ምን ያገባኛል ስሜት በሌላቸው ሰዎች መሃከል ነው (Christian Reflections, 1967, 10)።
ደስ ከሚላቸው ጋር የሚደሰት፣ ከሚያለቅሱም ጋር የሚያለቅስ የዋህ ልብ አለ። አንዱ ባሕርይ አንድ ጊዜ ይታያል። ሌላኛው ደግሞ በሌላ ጊዜ ነገር ግን አንዱ ባሕርይ ለሌላኛው መገኘት መሠረት ነው። በዚህ ውስጥ ያለውን እውነተኛ የሆነ ደስታ እና ሐዘን መገንዘብ ትችላላችሁ።
ለዚህ የሚሆን የመዝጊያ ምሳሌ ልስጥ። ምሳሌው ከጆናታን ኤድዋርድስ “Religious Affections” ከተሰኘው መጽሐፍ የተወሰደ ነው። ይህ የክርስቲያናዊ ሄዶኒዝም በጥሩ ሁኔታ የተገለጸበት ክፍል ነው።
“አንድ ሰው የበለጠ የቅድስና ጥንካሬና ድፍረት ሲኖረው በራስ የመተማመን ስሜቱ ይቀንሳል። ይበልጥ ልከኛ ይሆናል። ከሲኦል ነፃ መውጣቱን ከሌሎች የበለጠ እርግጠኛ ይሆናል። የሲኦልንም ምድረበዳነት ይበልጥ ይገነዘባል። በእምነቱ ቶሎ አይናወጥም፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ቁጣ እና ማስጠንቀቂያዎች እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች መጥፋት ለማዘን ልቡ ቅርብ ነው። ጽኑ የሆነ መጽናኛ አለው። ነገር ግን ለስሜት ቅርብ የሆነ ልብ አለው። ከሁሉም በላይ ባለጠጋ ነው። ነገር ግን ከሁሉ በላይ የመንፈስ ድኻ ነው። ከሁሉም ይልቅ ረጅሙ እና ጠንካራው ቅዱስ ሲሆን ከሁሉም ያነሰና ለሕመም ቅርብ የሆነ ሕፃን ነው። (Works, Vol. 2, Yale, 364)
[1] Hedonism ለሚለው የእንግሊዘኛ ቃል የአማርኛ አቻ ትርጉም ስላልተገኘ በቀጥታ “ሄዶኒዝም” ተብሎ መተርጎሙን ልብ ይሏል።