በትውልድ መካከል አቅጣጫ ቀያሪው ጉዳይ ስለ ውጤታማ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ያለው አረዳድ እና ስለሚገልጠው እውነታዎች ነው።
“በትውልድ መካከል ልዩነት ፈጣሪው ጉዳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ነው” ብቻ ለምን አላልኩም? በርግጥ የዐረፍተ ነገሩም አወቃቀር ትንሽ ለመረዳት አዳጋች ሊሆን ይችላል። ልዩነት ፈጣሪ ለሚለውም ሐሳብ አስቀድመን ሊያግባባ የሚችልን ትርጓሜ ሰጥተነው ብናልፍ መልካም ነው። ከዚህ ቀደም ስለ የውሃ ተፋሰስ ሰምተው ያውቃሉ? ተፋሰስ ማለት በአንድ በኩል ያሉት ወንዞች በሙሉ ወደ አንድ ባሕር እንዲፈሱ፣ በሌላኛው ጎን ያሉት ደግሞ ወደ ሌላ ባሕር እንዲፈሱ፣ የተለያዩ ወንዞችን ፍሰት የሚከፋፍል የከፍታ ቦታ ነው። በፍሰቱ ጊዜ ወንዞቹ በብዙ ጠመዝማዛ እና ዘወርዋራ መንገዶች ቢያልፉም፣ መዳረሻቸው ወደ ሆነው ባሕር ግን የሚያደርጉትን ፍሰት የሚወስነው በወንዞቹ መካከል ልዩነትን የሚፈጥረው ያ ከፍታ ቦታ (የውሃው ተፋሰስ) ነው።
ልዩነት ፈጣሪ ጉዳይ ስንልም እንዲሁ ነው። የሰው ልጅ ሐሳብ ልዩነት ፈጣሪ ወደ ሆነ ጉዳይ ሲቀርብ በጉዳዩ ዙሪያ ያለው የአመንክዮና የልቦና አቅጣጫ ብዙ ዘወርዋራና ጠምዝማዛ አካሄድ ኖሮት ወደ አንድ አልያም ወደ ሌላ መዳረሻ የሚወስድን የአስተሳሰብና የስሜት ጉዞን ያበጃል።
ሁሉም ጉዳይ ደግሞ አቅጣጫ ቀያሪ አይደለም። ሰዎች በሆኑ ጉዳዮች ላይ የግል አቋም ሊኖራቸው ቢችልም ግን አንዱ ከአንዱ እየራቀ ወደ ተለያየ የባሕር መዳረሻ ሲወስዳቸው ሁሌ አይታይም። ልዩነት ፈጣሪ ጉዳይ ስንል ግን ወሳኝ፣ መሠረታዊ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑ፣ በዙሪያቸው ያለው መልክዓ ምድር ተመሳሳይ ቢመስልም እንኳ ወንዞቹ ግን ተለያይተው እንደሚፈሱና መዳረሻቸውም የተለያየ እንደሆነ ነው።
የቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን
በመቀጠል መብራራት ያለበት ሐሳብ ቢኖር፣ “የቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን” የሚለው ነው። በ”Desiring God” ሚኒስትሪ የእምነት መግለጫ የቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን እንዲህ ተገልጿል፦
“በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ እውነትና ትክክል ስለሆነው ማንኛውም ነገር ለመመዘን የበላይና የመጨረሻ ባለሥልጣን ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት በቀጠታ ባልተዳሰሱት ጉዳዮችም ቢሆን የእውነትነትና ትክክለኛነት ተመን የሚያገኘው ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር በመስማማት ባለው መመዘኛ ነው።”
እንዲህ ለማመናችን መሠረቱ የሚከተለው ነው፦
“ስድሳ ስድስቱን የብሉይና የአዲስ ኪዳን መጽሐፍት የያዘው መጽሐፍ ቅዱስ የማይሳሳት፣ በእስትንፋሰ እግዚአብሔር የተነደፈ እና በመጀመሪያ ቅጂዎቹ ሕጸጽ የሌለበት ስለሆነ ነው።”
በአጭሩ ሲቀመጥ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር ቃል ናቸው የሚለው ሐቅ የሚያሳየን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምህርቶች በሙሉ እውነት እንደሆኑ እና በሚያዘን ሁሉ ደግሞ ልንታዘዛቸው የሚገባ እንደ ሆነ ነው። እውነት ስለሆነው ነገርና ጽድቅ ስለሆነው ነገር መደምደሚያን ለመስጠት የመጨረሻ ባለሥልጣን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ራሱ የሚናገረውም እንዲሁ እንደሆነ እናምናለን።
“ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ” (2ኛ ጢሞቴዎስ 3፥16)።
“ምክንያቱም ትንቢት ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩት እንጂ ከቶ በሰው ፈቃድ የመጣ አይደለም” (2ኛ ጴጥሮስ 1፥21)።
“እኛ የምንናገረው ይህን ነው፤ ከሰው ጥበብ በተማርነው ቃል ሳይሆን፣ ከመንፈስ በተማርነው ቃል እንናገራለን፤ መንፈሳዊ እውነትንም የምንገልጸው በመንፈሳዊ ቃል ነው” (1ኛ ቆሮንቶስ 2፥13)።
“ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ፈጽሞ አያልፍም” (ማቴዎስ 24፥35)።
“የእግዚአብሔር ቃል ሁሉ እንከን የለበትም፤ እርሱ ለሚታመኑበት ሁሉ ጋሻቸው ነው” (ምሳሌ 30፥5)።
“የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን ‘አማልክት’ ካላቸውና መጻሕፍም ሊሻር የማይቻል ከሆነ” (ዮሐንስ 10፥35)።
እነዚህን መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ የጽሑፍ አንደበት የሚያቀርበውን ማስረጃ፣ ማንኛውም ሰው (እግዚአብሔር በቸርነቱ በዚያ ውስጥ ያለውን እውነታ እንዲያይ ከቸረው) መረዳት የሚችለው ግልጽ ጉዳይ ነው።
ውጤታማ ሥልጣን
ለምን “በትውልድ መካከል ልዩነት ፈጣሪው ጉዳይ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ነው” ብቻ አላልኩም? ለምንስ ውጤታማ የሚልን ቃል በመጨመር መግለጹ አስፈለገ? “በትውልድ መካከል ልዩነት ፈጣሪው ጉዳይ ውጤታማ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ነው…።”
ይህ የተባለበት ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ልዩነት ፈጣሪው ጉዳይ የሚሆነው በሐሴት የሚታዘዝን ልብና የተለወጠ ምልከታ ያለው አእምሮን በማበጀት ውጤታማ እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው የሚለውን እውነት አድርጎ ሳይቀበሉ ፤ የከበረ ነው ለሚለውም ክብር ሳይሰጡ፣ እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን እንዳለው መናገር ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለሚለው በእውነትነቱ እውቅና ካልሰጠነው፣ ሐሴት አድርጉ በሚለው ሐሴት ካላደረግን፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን እናምናለን ብንልም ነገር ግን በእኛ ሕይወት ላይ ውጤታማ አይደለም ማለት ነው። ከዚህም የተነሣ ልዩነት ፈጣሪ ሆኗል ብሎ መናገር አይቻልም።
ለምሳሌ፦ መጽሐፍ ቅዱስ አማኞችን እንዲህ ይላቸዋል፤ “ሞታችኋልና፤ … እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፣… ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰውሮአልና…” (ቈላስይስ 3፥1፣ 3)። ይሄ እውነት ሆኖ ሳለ፣ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ግን ከዚህ እውነት ጋር ስምምነት ያለው ነገር በአዕምሮአቸው ውስጥ የለም። በሕይወታቸው ላይ የዚህን እውነት መገኘት በነጸብራቅነት እንዲያሳዩ ቢጠየቁ እነሆኝ የሚሉት ፍሬ የለም፤ ማለትም እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በአእምሮአቸው ውስጥ ውጤታማ ባለሥልጣናት አይደሉም ማለት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ መልካምና ክቡር በሚላቸው ነገሮች ዙሪያም ተመሳሳይ ምልከታን ማካሄድ እንችላለን። ፊልጵስዩስ 3፥8 እና ማቴዎስ 13፥44 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ካለንና ወደ ፊት ልናካብት ከምንችለው ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ክቡር እንደሆነ ያስተምሩናል። ነገር ግን በሺህዎች የሚቆጠሩ “ክርስቲያን ነን” ባዮች ከክርስቶስ ይልቅ ለሌላ ነገር ክብር ይሰጣሉ። ሐሴት የሚያደርጉት በክርስቶስ እንደሆነ እምብዛም ሲናገሩ አይሰማም። ሕያው ሆኖ በዕለት ተለት እንቅስቃሴያቸው የሚገለጠው አስተሳሰባቸውንና ቃለ ምልልሳቸውን የሞሉት ፊልሞች፣ ማኅበራዊ ድረ ገጾች፣ ስፖርቶች እንዲሁም ፖለቲካ ናቸው።
ይህ የሆነበት ምክንያቱ ምን ይመስልሃል? የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የላቀ የውበቱና የክብሩ አስተርእዮ ለእነርሱ በውጤታማነት ባለሥልጣን ስላልሆነ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ልክ ለስጦታ መጠቅለያ ዕቃ ዕውቅና በሚሰጠው በዚያው መንገድ እውቅና ሊሰጠው ይችላል። ይህም ለምሳሌ ምንም ያክል የስጦታው ይዘት ባይታወቅም እንኳ አንድ ሰው ስጦታን ሲቀበል “ይህን ስጦታ ወድጄዋለሁ፤ ውብ ነው” ሲል የንግግሩ አንድምታ የስጦታው መጠቅለያ ዕቃ ውብ ነው ማለቱን ነው።
ተቃርኖ ሲገለጥ
መጽሐፍ ቅዱስ እውነት እና መልካም ስለሚላቸው ነገሮች የግልም ሆነ የባህል ግጭት በሌለበት ሁኔታ ውጤታማ ያልሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን አተገባበር ትኩረትን እንዳያገኝ ሆኗል። ሰዎችም መጽሐፍ ቅዱስ ባለሥልጣን እንደሆነ ይናገራሉ። ለጊዜውም ቢሆን የሚታየው የባህል እንዲሁም የግል ስነምግባር ከመጽሐፍ ቅዱስ ግብረገብ ጋር የተስማማ ይመስላል። ከዚህም የተነሣ መጽሐፍ ቅዱስ በተጨባጭ ውጤታማ ሥልጣን እንዳለው በሚመስል ሁኔታ ይቀጥላሉ። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው።
በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ ተቃርኖ የሚከሰተው። ወንድ ከወንድ ጋር ነውር ቢፈጽም (ግብረ-ሰዶማዊነት) ኀጢአት እየሠራ ነውን? እንዲህ የሚያደርጉ ንስሓ ሳይገቡ በኀጢአታቸው ጸንተው ቢኖሩ መንግሥተ ሰማያትስ ይገባሉ? (“ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ወንደቃዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣…” 1ኛ ቆሮንቶስ 6፥9)። ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል “ጋብቻ ” ቢቋቋም፣ ጋብቻ ነው ማለት ነውን? (“ስለዚህም ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር አንድ ይሆናል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ኤፌሶን 5፥31)። የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ለተፈጥሮው ባሕርይ የሚገባ ነውን? ወይስ ለተፈጥሮአዊው ባሕርይ የማይገባ ነው? (“… ሴቶቻቸውም እንኳ ለባሕርያቸው የሚገባውን ግንኙነት ባሕርያቸው ላልሆነው ግንኙነት ለወጡ። እንደዚሁም ወንዶች ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወት ተቃጠሉ፤ ወንዶች ከወንዶች ጋር ነውር ፈጸሙ፤ ለክፉ አድራጐታቸውም የሚገባቸውን ቅጣት በገዛ ራሳቸው ላይ አመጡ” (ሮሜ 1፥26-27)። በወንድና በሴት መካከል ከሆነ ብቻ ነው ጋብቻ መልካም የሚሆነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንና ቤተ ክርስቲያንን ሊያሳይ የሚችለው ይህ ብቻ አይደለምን?
ድንገት እንዲህ ያለ ተቃርኖ በባህል ውስጥ ወይም በግል ባለው ልምምድ ሲከሰት፣ አንድ ግለሰብ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን አጸናለሁ ሲል እያለ ያለው ውጤታማውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ወደ ብርሃን ያወጣል። በዚህ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን በሐሴት እሽ ባይን ልብ እና የተለወጠ ምልከታ ያለውን አእምሮ በማበጀት ረገድ ውጤታማ ነበር? እንደ እውነትና ትክክል በምንቀበለው ነገር ላይ ለውጥን በማፍራት የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን ማጽናታችን ውጤታማ ሆኗልን? ወይስ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን ተቀብያለሁ ማለታችን በማንፈልጋቸው ትምህርቶች ዙሪያ ጥያቄ እንዳይነሳብን እንደ መሸፈኛ ብቻ የምንጠቀመው ሆኖብናል?
የሚገልጣቸው እውነታዎች
በጥቅሉ “በትውልድ መካከል ልዩነት ፈጣሪው ጉዳይ ውጤታማ የሆነ የቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን ነው።” ነገር ግን በመጀመሪያው ዐረፍተ ነገር የጻፍኩት ይሄ ብቻ አልነበረም። እንዲህ ነበር ያልኩት፤ “በትውልድ መካከል ልዩነት ፈጣሪው ጉዳይ ውጤታማ የሆነ የቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣንና ቅዱሳት መጻሕፍት የሚገልጡት እውነታ ነው።” እንዲህ ያለ ትርጉም እንዲኖረው ሊያደርግ የሚችለውን በቂ ነገር አይተናል።
የኔ ዓላማ ስለ ሥልጣን ብቻ መስማማት እያወራንለት የነበረውን ውጤት ሊያስገኝልን አይችልም ወደሚለው ሐቅ ትኩረትን ለመሳብ ነው። ሥልጣናዊ ትምህርቶች የሚገልጧቸው እውነታዎች ናቸው እውነት ስለሆነው ነገር ያለንን ምልከታ በመለወጥ መልካም በሆነው ነገር እንድንደሰት የሚመሩን። የእግዚአብሔር መንፈስ እውነትን እንደ እውነት እንድናይ፣ መልካሙንም ደግሞ እንደ መልካም እንድናይ ያደርገናል። ምናልባት ሥልጣን አእምሮአችንን ይገዛው ይሆናል ነገር ግን ልባችንን አይለውጠውም።
በሥልጣን አመኔታን ስላገኙ ብቻ የቅዱሳት መጻሕፍት ትምህርቶችና የሚገልጧቸው ሐቆች ለእኛ እውነትና መልካም ሊሆኑልን አይችሉም። አእምሮአችንና ልባችን ተግባርን የሚከውኑበት መንገድ እንዲህ አይደለም። ሥልጣንህን ተጠቅመህ አንድን ሕጻን አትክልት እንዲመገብ ታስገድደው ይሆናል፤ ነገር ግን አትክልት ይወድ ዘንድ ልታስገድደው አትችልም፤ ሥልጣን ያን ሊያደርግ አይችልምና። ሥልጣን ሕጻኑን የምግብ ጠረጼዛው ጋር እንዲቆይ ያደርገው ይሆናል፤ ምግቡን እንዲያጣጥም የመፍጠር ችሎታ ግን የለውም።
ሥልጣን እውነታን እንድንቀበል ያደርገን ይሆናል፤ እንድናምነው ግን ሊያደርገን አይችልም። እንዲሁ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን ትቀበል ይሆናል፤ ምክንያቱም እንደዚያ እንድታደርግ ከአንተ ይጠበቃልና። ሆኖም ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንደ እውነታ የሚያቀርበውን ነገር እውነት እንደሆነ የሚያይና፣ መጽሐፍ ቅዱስ በመልካምነት የሚያቀርበውን ነገር ተቀብሎ በእርሱ ሐሴት የሚያደርግ፣ መለወጥን ያገኘ አእምሮና ልብ ላይኖርህ ይችላል።
የመለኮት ስጦታ
እንዲያ ያለ የአዕምሮና የልብ ለውጥ በሥልጣን ላይ ብቻ የሙጥኝ በማለት አይከሰትም፤ ይልቅ “ጌታ መልካም መሆኑን ቀምሳችሁ እንደሆን” እንደሚል ከመለኮት በሚሆን የምልከታ እና የእርካታ ስጦታ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ሐቆችን እንደ እውነትና የታመኑ እንዳሉ ለማየት አዲስ ዐይኖች ያስፈልጉናል። መጽሐፍ ቅዱስ መልካምና ጣፋጭ የሚለውንም ለመቅመስ አዲስ ስሜት ያስፈልገናል።
ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ ሚስት ለባሏ መገዛት፣ (ኤፌሶን 5፥24) ደግሞም ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ባልም እንዲሁ ሚስቱን መውደድ መልካም እንደሆነ ያስተምራል (ኤፌሶን 5፥24-25)። ይሄ እውነት ነው፤ ነገር ግን ልቡናህ ካላየው፣ ልብህም እስካልወደደው ድረስ ማንኛውም ዐይነት ሥልጣን ይህን እውነታ ለእኛ እውነትና መልካም ሊያደርገው አይችልም፤ ሥልጣን አሠራሩ በዚህ መንገድ አይደለምና።
የቅዱሳት መጻሕፍትን ሥልጣን ታጸና ይሆናል፤ ነገር ግን ውጤታማ አይደለም። የቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን ውጤታማ የሚሆነው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እውነታዎቹ የሆኑትን ያንኑ ለአንተም ሆነው ሲገኙ ነው። ያን ጊዜ እውነትን እንደ እውነት ታያለህ፤ መልካሙንም እንደ መልካም ትቀበለዋለህ፤ ሐሴትም ታደርጋለህ። ደግሞም የማይገባውንም እንደማይገባ አድርገህ ትቆጥራለህ።
የቅዱሳት መጻሕፍትን ሥልጣን ማጽናት አስፈላጊ ሆኖ ሳለ ግን ብቻውን በቂ አይደለም። እውነት የሆኑትንና መልካም የሆኑትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሀቆች በመግለጥ የእግዚአብሔር መንፈስ አዲስ ዕይታና ጣዕም ሲያበጅ፣ ያኔ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ እውነትና እንደ መልካም የሚያቀርብልንን ነገር እናየዋለን ደግሞም እንቀምሰዋለን። ይህን ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳት መጻሕፍት ቃሎች በኩል ያደርገዋል። ይህንም ሲያደርገው የቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን ውጤታማ ሆነ ማለት ነው። እርሱም በትውልድ መካከል ልዩነት ፈጣሪ በሆነው በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት ይሆናል።