በትዳር ሕይወታችን መጀመሪያ አካባቢ፣ ባለ ቤቴ ዶና፣ ለሁለት ዓመታት በአንድ ትልቅ የሕፃናት ሆስፒታል ውስጥ የልጆች ነርስ ሆና በመሥራት አሳልፋለች። የምትሠራበት ክፍል አንገብጋቢ የህክምና ርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ታማሚዎች በተደጋጋሚ የሚያስተናግድ ሲሆን፣ አንዳንዴም ጽኑ የህክምና ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ይመጣሉ። በሥራዋ ከሚያጋጥሟት ተግዳሮቶች ሁሉ ከባዱ፣ መልካም ፍላጎት ቢኖራቸውም የተሳሳተ አመለካከት ያላቸውን የታካሚዎቿን ዘመዶች ማስተናገድ ነበር። ይህም፣ የህክምና እንክብካቤ ብታደርግላቸውም መዳን ያልቻሉ ልጆችን ማየት ከሚያሳድርባት የስሜት ጉዳት በላይ እንኳ የሚፈትናት ነበር።
ዐልፎ ዐልፎ፣ ወላጆች ወይም ጕዳዩ ያሳሰባቸው የቤተ ሰብ አባላት ቅሬታ ያቀርባሉ፤ ለታማሚና ጉዳተኛ ልጆች የታዘዘው ህክምና ላይ ጣልቃ እስከ መግባትም ይደርሳሉ። ልጃቸው የመርፌውን ሕመም ሲታገል ወይም መድኀኒት ለመዋጥ ሲገደድ መመልከቱን መቋቋም ይከብዳቸዋል። ዶናና ባልደረቦችዋ “ጨካኝ” እና “ግድ የማይላቸው” ተደርገው የሚወቀሱበት ጊዜ ሁሉ አለ።
“ለልጆች ያለኝ ፍቅር ከፍተኛ በመሆኑ፣ ፈጽሞ የልጆች ነርስ መሆን አልችልም” የሚለውን አባባል ለብዙ ጊዜያት የሰማችው ንግግር ነበር። አፍ አውጥታ መልስ ሰጥታ ባታውቅም፣ ሁሌ ወደ አእምሮዋ የሚመጣው ሐሳብ ግን ይህ ነበር፤ “ የምር፣ ይህን የማደርገው፣ ልጆችን ስለማልወድ ነው ብለሽ ታስቢያለሽ? እንዲያውም ከዚህ በተቃራኒው ነው። ልጅሽን ስለምወደው ጤናውን ለመመለስ አስፈላጊ ከሆነ፣ መድኀኒት ለመስጠትና ህመም እንዲሰማው ለማድረግ ፈቃደኛ ነኝ። ለቅሶውን ማየት ስለሚያስደስተኝ ሳይሆን፣ ለዘላቂ ጥቅሙ ሲባል፣ የዐጭር ጊዜ ህመምን መታገሥ የሚያዋጣ መሆኑን ስለማውቅ ነው።”
እግዚአብሔርም፣ ቤት ውስጥ በወላጆች ሊተገበር የሚገባውን ቅጣት ጨምሮ፣ ስለ ሁሉም ቅጣት እንድናስብ የሚፈልገው፣ በዚህ መንገድ ነው። እንዲያውም፣ ቅጣትን ለመግለጽ ብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥና አዲስ ኪዳን በግሪክ ጥቅም ላይ የሚያውላቸው መሠረታዊ ቃላት፣ “ቅጣት” የማቅናት ሐሳብ ያለው በውጤቱም ትምህርት የሚያስገኝ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ቅጣት፣ ቀናና ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ጥረት ነው።
ዛሬ ለበርካቶች ቅጣት ጽዩፍ ቃል ነው። የቅጣትን ሐሳብ በሙሉ አሉታዊ፣ ገዳቢ በሆነ ዕይታ ለጥፋት ከሚከፈል ቅጣት፣ ከህመም፣ ከችግርና ዕጦት ጋር አያይዘው ይመለከቱታል። እነዚህ እውነታዎች በሆነ መንገድ ሊካተቱ የሚችሉ ቢሆንም፣ እውነተኛ ቅጣት ሁሉ፣ በፍጹም ራሱ መዳረሻ ወይም ግብ አይደለም። ሁሌም ወደሚፈለገው መዳረሻ የሚታለፍበት መንገድ ነው። ዕብራውያን 12፥11 እንደሚያስረዳው፣ “ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጂ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም፥ ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል።”
ቅጣት በአንድ ወቅት የሚከወን ተግባር ሲሆን፣ ሁሌም ግን የሚደረገው “ለበኋላ” ተብሎ ነው። ገበሬው የማረስ፣ የመትከልና የመኮትኮት ተግባሩን የሚያከናውነው፣ እነዚህን ድርጊቶች ለማድረግ ያህል ሳይሆን፣ በውጤቱ ለሚገኘው አዝመራ ሲል ነው።
እግዚአብሔርም ከሚወድዳቸው ሰዎች ቅጣትን የማይከለክለው፣ በርግጥም ለሚገኘው በጎ ውጤት ሲል ነው። ይህ ክርስቲያኖች በፈተናና በችግር ውስጥ በሚያልፉበት ጊዜ ሊያስታውሱት የሚገባ ወሳኝ እውነት ነው። የዕብራውያን ጸሓፊም ምሳሌ 3፥11-12ን በመጥቀስ እዚህ ሐሳብ ላይ አጽንኦት በመስጠት፣ ተደራሲያኑ በሚያልፉበት መከራ ውስጥ በነፍሳቸው ዝለው ተስፋ እንዳይቈርጡ ያበረታታቸዋል። “ልጄ ሆይ፤ የጌታን ተግሣጽ አታቃልል፤ በሚቀጣህም ጊዜ ተስፋ አትቍረጥ ምክንያቱም ጌታ የሚወድደውን ይገሥጻል፤ እንደ ልጅ የሚቀበለውንም ይቀጣል።” በማለት እግዚአብሔር ልጆቼ ብሎ የሚጠራቸው መሆኑን እንዲያስታውሱ ያሳስባቸዋል (ያሳስበናል)(ዕብራውያን 12፥5-6)።
በተመሳሳይ መንገድ፣ እግዚአብሔር ወላጆች ልጆቻቸውን በአግባቡ ለመቅጣት በሚያስችል ፍቅር በመውደድ እርሱን እንዲመስሉ ጥሪ ያቀርባል። ይህንም ሲያደርግ ልጆች ሲቀ’ጡ’ የሚጨመሩትን በጎ ጠቀሜታዎች በማቅረብ ነው። “ልጅህን ቅጣ ዕረፍትንም ይሰጥሃል፤ ለነፍስህም ተድላን ይሰጣታል” (ምሳሌ 29፥17)። ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ልጁም ይጠቀማል። “ስንፍና በሕፃን ልብ ታስሮአል፤ የተግሣጽ በትር ግን ከእርሱ ያርቃታል (ምሳሌ 22፥15)። በአግባቡ የተቀጣ ልጅ ስንፍናው በተደጋጋሚና ወጥ በሆነ መልኩ ስለሚጋለጥና ስለሚስተካከል የጥበብ ውበትና መልካምነት በላቀ መልኩ እየሳበው ይሄዳል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ልጆችን የመቅጣትን ኀላፊነት የሚሰጠው በቀጥታ ለወላጆች በተለይም ለአባት ነው። ጳውሎስ በኤፌሶን 6፥4 ላይ ለዚህ እጅግ ቀጥተኛና ቅልብጭ ያለ መግለጫ ሲሰጥ፣ “አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው።” ይላል። ይህ ክፍል የወላጅን የኀላፊነት ድርሻን በሙሉ የሚያካልል ነው።
ልጆቻቸውን እንዳያስቈጡ ካስጠነቀቃቸው በኋላ፣ ጳውሎስ በመሠረታዊነት ወላጆችን፣ በተለይም አባቶችን፣ የገዛ ልጆቻቸውን እንዲያሳድጕ ምክር አዘል ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል። ይህ ግልጽ፣ ያልተወሳሰበ ትእዛዝ በጣም ጥልቅ ከመሆኑ የተነሣ እያንዳንዱ ወላጅ ቢረ’ዳ’ውና ቢታዘዘው፣ ከታዳጊ ወጣቶች ጋራ በተያያዘ የሚነሡ አብዛኞቹ ማኅበራዊ ችግሮች ይቀረፉ ነበር።
ልጆችን የማሳደግ ሥራ በቀጥታ የትምህርት ቤት፣ የማኅበረ ሰብ፣ የቤተ ክርስቲያን ወይም የወጣቶች ኅብረት አይደለም። የወላጆች ሥራ ነው። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ከሆነ፣ ልጅን ማሳደግ የሚጠይቀው፣ መንደር ሳይሆን አባት ነው።
ኤፌሶን 6፥4ን እንደ ወላጆች የትጥቅ ሳጥን ብናስበው፣ እግዚአብሔር ወላጆች እንዲጠቀሟቸው የፈለገው ሁለቱ ዋነኛ መሣሪያዎች የጌታ “ቅጣት”[1]ና የጌታ “ምክር” መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርብናል። እነዚህ ቃላት ሁለት ወሳኝ የወላጅ ተግባራትን የሚያሳዩ ናቸው። የመጀመሪያው አካላዊ ሲሆን ኋለኛው በንግግርና በቃል የሚገለጥ ነው። የጌታ ቅጣት ልጁ ላይ የሚደረግ ሲሆን፣ የጌታ ምክር ደግሞ ለልጁ የሚነገር ነው። ልጆች በዚህ ዓለም ለመልካም ኑሮ እንዲሠለጥኑ፣ እነዚህ ሁለቱ መሣሪያዎች በአንድነት ጥቅም ላይ ሊውሉ ይገባል።
እዚህ ክፍል ውስጥ ታሳቢ የተደረገው ቅጣት፣ በእግዚአብሔር ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት የሚሰጡትን ተገቢ ምክር ዐውቆ ያልታዘዘን ልጅ ማቅናትን የሚያካትት ነው (6፥1-3)። ይህ ማቅናት አካላዊ ቅጣትን ሊያካትት የሚችል ነው (ለዚህም ነው ምሳሌ 22፥15 ላይ “የተግሣጽ በትር” ተብሎ የተጠቀሰው)።
አካላዊ ቅጣት፣ ለበርካቶቹ ዘመናውያን ኋላ ቀርና ጥቃት የሚያደርስ ሆኖ ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ቤት ውስጥ የሚተገበር ቅጣት ክፍል አድርጎ ሲነግረን ፈራ ተባ አይልም። ”ልጅን ከመቅጣት ወደ ኋላ አትበል፤ በአርጩሜ ብትገርፈው አይሞትም” (ምሳሌ 23፥13)። እዚህ ክፍል ላይ ታሳቢ የተደረገው ቅጣት፣ ሆን ተብሎ በትርን በመጠቀም የተወሰነ ሕመም የሚያስከትል ዐይነት ቅጣት ነው።
እንዲህ ያለው ቅጣት ልጅ ላይ ጥቃት ማድረስ አይደለም። በቍጣ ተነሣሥቶ ከሚደረግ ጥቃት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም። እንዲህ ያለው የተበላሸ የልጆች አያያዝ አስጸያፊ ነው፤ ደግሞም ትንሽ እንኳ ጤናማ አመለካከትና ምግባር ባለው እያንዳንዱ ሰው ሊወገዝ የሚገባው ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊው ቅጣትና የልጆች ጥቃት፣ ሁለቱ ፈጽመው የተለያዩ ጕዳዮች ናቸው። ኋለኛው፣ እስከ ጥግ ከገፋንበት፣ ውጤቱ ሞት ነው። በአንጻሩ፣ በትር ወይም አርጩሜ ተጠቅሞ የተወሰነ ምቾት መንሳትን ትኩረቱ ያደረገው መጽሐፍ ቅዱሳዊው ቅጣት፣ ጭራሽ እዚያ ሰፈር የሚያደርሰው መስመር የለም። መጽሐፍ ቅዱስ የሚደግፈውን ዐይነት ቅጣት የሚቀበል ልጅ በውጤቱ “ከሞት ያመልጣል”።
እግዚአብሔር የሰጠው የቅጣት ዐይነት በጭራሽ ወደ ጥቃት ማድረስ እንዳያሽቆለቁል አስፈላጊውን መከላከያ ሰጥቷል፣ ይኸውም፣ ሁለተኛውን መሣሪያ መጠቀም ነው፤ ምክር። ወላጆች አስተማሪዎች ናቸው፤ ለልጆቻቸው የሚሰጡትም ምክር መናገርን ይጠይቃል። ብዙ ንግግር። መጽሐፈ ምሳሌ ሙሉውን፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በየጊዜው የእግዚአብሔርን ጥበብ በተለያዩ በጎም መጥፎም የሕይወት ልምዶችና ሁኔታዎች ውስጥ ሊያስተምሯቸው የሚገባው እንዴት እንደ ሆነ ያሳያል።
ይህ የማቅናት ጊዜን የሚያካትት መሆኑ ርግጥ ነው። ወላጅ በትር መጠቀሙ በቂ አይደለም፤ ቃላትንም ደግሞ ሊጠቀም ይገባዋል። የጌታን ምክር እንዲሁም የጌታን ቅጣት መስጠት አለበት። በትር በተግባር ላይ ሲውል፣ ልጁ ሁኔታውን በእግዚአብሔር ቃል እውነት ብርሃን እንዲመለከተው መማር ይገባዋል።
ልጅዎ ኀጢአት ስታደርግ፣ ሊገባት በሚችል ቀለል ያለ አገላለጽ ያደረገችውን ያስረዷት። ማድረግ ይገ’ባ’ት የነበረውንም ግልጽ ያድርጉላት። በቀጥታም (“በሐሰት አትመስክር” በሚለው ዐይነት) ይሁን በተዘዋዋሪ (“ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ” በሚለው ዐይነት) ስለ ሁኔታው እግዚአብሔር ምን እንደሚል በመንገር፣ የእግዚአብሔርን ሥልጣን እንድትረዳ ያድርጉ። ለኀጢአቷ የሚቀጧት፣ እርሷን ለማቅናትና እጅግ ስለሚወድዷት እንደ ሆነ (ምሳሌ 13፥24) ደግሞም ጌታን እጅግ ስለሚወዱትና መታዘዝ ስለሚፈልጉ መሆኑን (ዮሐንስ 14፥15) ያስተምሯት።
በመቀጠልም፣ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሞተው እንዲህ ላሉ ኀጢአቶች [የሚገ’ባ’ውን የቅጣት ዋጋ] ለመክፈል መሆኑን ቀለል ባለ መልኩ ያብራሩ። ይህን ማስታወስ፣ ወላጆች ማንኛውንም ጠንከር ያለ የቅጣት ጊዜ ስለ ወንጌል ለመነጋገር እንደ ዕድል እንዲጠቀሙበት ይረዳቸዋል። “አንቺና እኔ አባትሽ ኀጢአተኞች ነን። ነገር ግን ይቅርታን ማግኘት እንድንችል ኢየሱስ እንደ እኛ ላሉ ኀጢአተኞች ሞቶልናል። እግዚአብሔር በኢየሱስ የሚያምነውን ሁሉ ይቅር ይላል። አሁን እግዚአብሔር ኀጢአትን የሚጠላ አዲስ ልብ እንዲሰጥሽና በኢየሱስ አምነሽ ይቅርታን እንድታገኚ እጸልይልሻለሁ።”
ከዚያ ያድርጉት። በተቻለ ጊዜ ሁሉ ደጋግመው ያድርጉት።
ወላጆች እነዚህን ጉዳዮች በግልጽ ሲያስተውሉና ልጃቸውን በወጥነት በጌታ ቅጣትና ምክር ለማሠልጠን ሲሠሩ፣ ያንን ልጅ በእምነት የሰጣቸውና በቅዱስ መጽሐፍ ጥበብ እንዲያሳድጉት ዐቅም የሚሆናቸው ጌታ፣ በጸጋው እንደሚያድነውና መንግሥቱንም በልጃቸው ልብ አጽንቶ እንደሚተክለው ተስፋ እያደረጉ ለመጸለይ ምክንያት ይኖራቸዋል።
በቶም አስኮል