ይህንን ስጽፍ የፕሮስቴት ቀዶ ጥገና የሚደረግልኝ ቀን ዋዜማ ላይ ሆኜ ነው። በተአምራትም ይሁን በመድኀኒት የሚሠራውን የእግዚአብሔርን የፈውስ ኀይል አምናለሁ። ስለ ሁለቱም ዐይነት የፈውስ መንገዶች መጸለይ ትክክለኛ እና መልካም እንደሆነ አምናለሁ። እግዚአብሔር ሲፈውሰው ካንሰር ያልባከነ ይሆናል። ክብሩን እርሱ ይወስዳል። ካንሰር ያለው ለዚሁ ነው። ስለዚህም ፈውስ እንዲሆንላችሁ አለመጸለይ ካንሰራችሁን ሊያባክነው ይችላል። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ፈውስን ለሁሉም ያቀደው ነገር አይደለም። እንዲሁም ካንሰራችሁን ልታባክኑ የምትችሉባቸው ሌሎች ብዙ መንገዶች አሉ። ይህንን ሕመም እንዳናባክነው፣ ለግሌም ሆነ ለእናንተ ጸሎቴ ነው።
- እግዚአብሔር ለእናንተ ያቀደው ነገር እንደሆነ ካላመናችሁ ካንሰራችሁን ታባክኑታላችሁ
እግዚአብሔር ካንሰራችንን ይጠቀመዋል፤ ነገር ግን አላቀደውም ብሎ ማለት አዋጭ አይደለም። እግዚአብሔር የፈቀደውን ነገር የሚፈቅደው በምክንያት ነው። ይህም ደግሞ የእርሱ ዕቅድ ነው። ሕዋሶቻችን ወደ ካንሰርነት ሲለወጡ እግዚአብሔር አስቀድሞ ቢመለከት፣ ሊያስቆመውም ላያስቆመውም ይችላል። ባያስቆመው ዓላማ ስላለው ነው። ወደር የሌለው ጠቢብ ስለሆነ ይህንን አሠራሩን የታቀደ ነው ብሎ ማለት ተገቢ ነው። ሰይጣን ብዙ ፍሰሓዎችን እና ሕመሞችን የሚያደርስ ቢሆንም ነገር ግን የበላዩ እርሱ አይደለም። ስለዚህ ሰይጣን ኢዮብን በክፉ ቁስል ሲመታው (ኢዮብ 2፥7) ይህንን በዋነኛነት ያደረገው እግዚአብሔር እንደሆነ ኢዮብ ያስባል (ኢዮብ 2፥10)። የመጽሐፉም ጸሐፊ ከዚህ ጋር በመስማማት “እግዚአብሔርም ካመጣበት መከራ ሁሉ አጽናኑት” ይላል (ኢዮብ 42፥11)። ካንሰራችሁን እግዚአብሔር ለእናንተ ያቀደው ነገር እንደሆነ ካላመናችሁ ታባክኑታላችሁ።
- ካንሰራችሁ ስጦታ ሳይሆን መርገም እንደሆነ ካመናችሁ ታባክኑታላችሁ
“ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም” (ሮሜ 8፥1)። “ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል” (ገላትያ 3፥13)። “በያዕቆብ ላይ የሚሠራ አስማት የለም፤ በእስራኤልም ላይ የሚሠራ ሟርት አይኖርም” (ዘኁልቁ 23፥23)። “እግዚአብሔር አምላክ ፀሓይና ጋሻ ነውና፤ እግዚአብሔር ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን፣ መልካም ነገር አይነፍጋቸውም” (መዝሙር 84፥11)።
- ከእግዚአብሔር ይልቅ በሕክምና ውጤት ከሚኖር ተስፋ መጽናናትን ስትሹ ካንሰራችሁን ታባክኑታላችሁ
እግዚአብሔር ለካንሰራችሁ ያለው ዕቅድ በህክምና የሚገኙ ውጤቶችን የማስላት አመክንዮ ሊያለማምዳችሁ አይደለም። ዓለም መጽናናቷን የምታገኘው የነገሩን የመሆን ዕድል በማስላት ነው። ክርስቲያኖች ዘንድ ግን ይህ አይደለም። እነዚህ በሰረገላ (የመትረፍ ዕድል)፣ እነዚያ በፈረስ (የሕክምና የጎንዮሽ ጉዳት) ይመካሉ፤ “እኛ ግን ትምክሕታችን የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም ነው” (መዝሙር 20፥7)።
ከ2ኛ ቆሮንቶስ 1፥9 ላይ የእግዚአብሔር ዕቅድ ግልጽ ነው። በርግጥም የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደብን ይሰማን ነበር፤ ይህም የሆነው ሙታንን በሚያስነሣ በእግዚአብሔር እንድንታመን እንጂ፣ በራሳችን እንዳንታመን ነው። እግዚአብሔር በካንሰራችን ውስጥ ያለው ዓላማ (ከሌሎች ሺህ በጎ ነገሮች ውስጥ) በእርሱ ላይ ፈጽሞ መታመን እንድንችል በልባችን ውስጥ ያሉትን ነገሮች ለማፈራረስ ነው።
- ስለ ሞት ለማሰብ አሻፈረኝ ካላችሁ ካንሰራችሁን ታባክኑታላችሁ
ኢየሱስ የመምጫውን ጊዜ ካራዘመው ሁላችንም እንሞታለን። ይህንን ሕይወት ጥሎ መሄድ እና ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ምን እንደሚመስል አለማሰብ ከንቱነት ነው። መክብብ 7፥2 እንዲህ ይላል፤ “ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ፣ ወደ ሐዘን ቤት (ቀብር) መሄድ ይሻላል፤ ሞት የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፤ ሕያው የሆነም ይህን ልብ ማለት ይገባዋል።” ካላሰባችሁበት እንዴት አድርጋችሁ ልብ ልትሉት ትችላላችሁ? መዝሙር 90፥12 “ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረን ዘንድ፣ ዕድሜያችንን መቍጠር አስተምረን” ይላል። ዕድሜን መቁጠር ማለት፣ ዘመናችን ምን ያህል ትንሽ እንደሆኑና በቶሎ እንደሚያበቁ ማሰብ ነው። ይህንን ለማሰብ አሻፈረኝ ካላችሁ ጥበብን የተሞላ ልብ እንዴት ሊኖራችሁ ይችላል? ስለ ሞት የምናስብ ካልሆንን እንዴት ያለ ማባከን ነው የሚሆነው።
- ካንሰርን ማሸንፍ ክርስቶስን ዕንቁ አድርጎ መያዝ ሳይሆን በሕይወት መቀጠል እንደሆነ የምታስቡ ከሆነ ካንሰራችሁን ታባክኑታላችሁ
ሰይጣን እና እግዚአብሔር በካንሰራችሁ ውስጥ ያላቸው ዕቅድ ተመሳሳይ አይደለም። ሰይጣን ዓላማው ለክርስቶስ ያላችሁን ፍቅር ማጥፋት ነው። እግዚአብሔር ዓላማው ለክርስቶስ ያላችሁን ፍቅር ጥልቅ እንዲሆን ማድረግ ነው። ካንሰር የሚያሸንፈው ብትሞቱ አይደለም። ክርስቶስን ዕንቁ አድርጎ ከመያዝ ብትጎድሉ ግን ያሸንፋል። የእግዚአብሔር ዓላማ የዓለምን ወተት ከመጋት አስጥሎ የክርስቶስን በቂነት ድግስ እንድትታደሙ ነው። “ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጕድለት እቈጥረዋለሁ” (ፊልጵስዩስ 3፥8) ማለት እንድትችሉ እና እንዲሰማችሁ የታለመ ነው። ስለዚህም ደግሞ፣ “መኖር ክርስቶስ ፤ ሞትም ማትረፍ እንደሆነ” (ፊልጵስዩስ 1፥21) እንድታውቁ ነው።
- ስለ ካንሰር ለማንበብ ረጅም ጊዜን የምታጠፉ ነገር ግን ስለ እግዚአብሔር ለማንበብ በቂ ጊዜ የሌላችሁ ከሆነ ካንሰራችሁን ታባክኑታላችሁ
ስለ ካንሰር ማወቅ ስሕተት አይደለም። አለማወቅ የሚበረታታ ባሕርይ አይደለም። ይሁን እንጂ የበለጠ ለማወቅ የመጣጣር ፈተና እና እግዚአብሔርን የበለጠ ለማወቅ ቅንዓት ማጣት ያለማመን ምልክት ነው። ካንሰር የታለመው የእግዚአብሔርን እውነታ ለማንቃት ነው። “እግዚአብሔርን እንወቀው፤ የበለጠ እናውቀውም ዘንድ እንትጋ” (ሆሴዕ 6፥3) ከሚለው ትእዛዝ ጀርባ ስሜትን እና ጉልበትን ማስታጠቅ ነው። “አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ግን ጸንተው ይቃወሙታል፤ ርምጃም ይወስዳሉ” (ዳንኤል 11፥32) ለሚለው እውነታ እንዲያነቃን የታለመ ነው። የማይናወጡ እና የማይወድቁ ዛፎች ሊያደርገን የታለመ ነው። “ነገር ግን ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል። እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” (መዝሙር 1፥2-3)። ስለ ካንሰር ቀን እና ሌሊት እያነበብን ስለ እግዚአብሔር ችላ የምንል ከሆነ፣ ካንሰራችንን ምንኛ ማባከን ነው!
- ከሰዎች ጋር የሚኖራችሁን ወዳጅነት በሚታይ ፍቅር ስር እንዲሰድድ ከማድረግ ይልቅ ወደ ብቸኝነት የሚመራችሁ ከሆነ ካንሰራችሁን ታባክኑታላችሁ
በፊልጵስዩስ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ለጳውሎስ የላከችውን ስጦታ አፍሮዲጡ ይዞ ሲመጣ እጅግ በጣም ታምሞ ለመሞት ታቃርቦ ነበር። “እርሱ ሁላችሁንም ይናፍቃልና፤ መታመሙን ስለ ሰማችሁም ተጨንቋል።” (ፊልጵስዩስ 2፥26)። እንዴት ድንቅ የሆነ ምላሽ ነው! ስለ ታመመ ተጨነቁ አይደለም የሚለው። ይልቁንም መታመሙን ስለ ሰሙ ተጨነቀ ይላል። እግዚአብሔር በካንሰር ውስጥ ሊሠራ የሚያልመው እንዲህ ያለውንና ለሰዎች ጥልቅ የሆነ ፍቅር ያለውን ሩኅሩኅ ልብ ነው። እራሳችሁን በማግለል ካንሰራችሁን አታባክኑት።
- ተስፋ እንደሌላቸው የምታዝኑ ከሆነ ካንሰራችሁን ታባክኑታላችሁ
ጳውሎስ ይህንን የሚናገረው ወዳጆቻቸው ከሞቱባቸው ሰዎች ጋር በተያያዘ ነበር። “ወንድሞች ሆይ፤ አንቀላፍተው ስላሉ ሰዎች ሳታውቁ እንድትቀሩ አንፈልግም፤ ደግሞም ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ሰዎች እንድታዝኑ አንሻም” (1 ተሰሎንቄ 4፥13)። በሞት ጊዜ ሐዘን አለ። የሞተው አማኝ ሳይቀር ለጊዜው የሚያጣው ነገር አለ። ሥጋውን ያጣል፣ እዚህ ያሉትን ወዳጆቹን ያጣል፣ የምድር አገልግሎቱን ያጣል። ይሁን እንጂ ሐዘኑ የተለየ በተስፋ የተከበበ ነው። “ከሥጋ ተለይተን ከጌታ ጋር መኖርን እንደምንመርጥ ርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ” (2 ቆሮንቶስ 5፥8)። ይህ ተስፋ እንደሌላቸው በማዘን ካንሰራችሁን አታባክኑት።
- ኀጢአትን ድሮ በምትመለከቱበት መንገድ የምትመለከቱት ከሆነ ካንሰራችሁን ታባክኑታላችሁ
ስር የሰደዱ ኀጢአቶቻችሁ ካንሰር ከመያዛችሁ በፊት እንደ ነበሩት የሚማርኳችሁ ናቸው? ከሆነ ካንሰራችሁን እያባከናችሁት ነው። ካንሰር የታቀደው ለኀጢአት ያላችሁን ፍላጎት ለማጥፋት ነው። ትዕቢት፣ ስስት፣ ምኞት፣ ጥላቻ፣ ይቅር አለማለት፣ ትዕግሥት ማጣት፣ ስንፍና፣ መዘግየት የመሳሰሉት ካንሰር እንዲያጠቃቸው የታለሙ ጠላቶች ናቸው። ካንሰርን መፋለም ብቻ አታስቡ። ይልቁንም ከካንሰር ጋር አብራችሁ መፋለምንም አስቡ። እነዚህ ነገሮች ከካንሰር የባሱ ጠላቶች ናቸው። ካንሰር እነዚህን ነገሮች ለማድቀቅ ያለውን ኀይል አታባክኑት። የዘላለም መኖር በጊዜ ውስጥ ያሉ ኀጢአቶች ከንቱ በሆኑበት ልክ እንዲታዩ ይሁን። “ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ጥቅሙ ምንድን ነው” (ሉቃስ 9፥25)።
- የክርስቶስን እውነት እና ክብር ለመመስከር ካልተጠቀማችሁበት ካንሰራችሁን ታባክኑታላችሁ
ክርስቲያኖች የሚደርሱበት ስፍራ አጋጣሚ ሆኖ አያውቅም። የደረስንበት ስፍራ የደረስንበት ምክንያት አለው። ስላልተጠበቁ የመከራ ሁኔታዎች ኢየሱስ ያለውን ልብ በሉ። “ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ግን ሰዎች ይይዟችኋል፤ ያሳድዷችኋል፤ ወደ ምኵራብና ወደ ወህኒ ቤት ያስገቧችኋል፤ በነገሥታትና በገዥዎች ፊት ያቀርቧችኋል፤ ይህም ሁሉ በስሜ ምክንያት ይደርስባችኋል። ይህም ለመመስከር ጥሩ ዕድል ይሆንላችኋል” (ሉቃስ 21፥12-13)።
በካንሰርም ቢሆን እንዲሁ ነው። ምስክርነት ለመስጠት ጥሩ አጋጣሚ ነው። ክርስቶስ ተመን የሌለው ዕንቁ ነው። ከሕይወት እንደሚልቅ ለማሳየት ወርቃማ ዕድል ነው።
አስታውሱ! ለብቻችሁ የተጣላችሁ አይደላችሁም። የሚያስፈልጋችሁን ዕርዳታ ታገኛላችሁ። “አምላኬም እንደ ታላቅ ባለጠግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ይሞላባችኋል” (ፊልጵስዩስ 4፥19)።