ከ1400 ዓመታት በኋላ የሚፈጸም የሕይወት ዓላማ እግዚአብሔር ያዘጋጀልህ ይመስልሃል?
አዎ! እኔም አንተም ተዘጋጅቶልናል።
ከ1400 ዓመታት በኋላ አዲሱ ሰማይና አዲሱ ምድር በዚህ ሊሆኑ ይችላሉ። እንደዚያ ከሆነ አሁን በሕይወትህ ውስጥ እየደረሱ ያሉ ነገሮች በሙሉ ለበጎ ነገር ተያይዘው እየሠሩ ነው ማለት ይቻላል።
ይህንን በድፍረት እንድል ያስቻለኝ ጳውሎስ በመልእክቱ፣ “ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል” በማለቱ ነው (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥17)። ጳውሎስ “ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን” ሲል በሕይወታችን ያሳለፍነው ሁሉንም በሕመም የተሞሉ የሕይወት ክፍሎቻችንን ነው። በሮሜ 8፥18 ጳውሎስ ይህንኑ “የአሁኑ ዘመን ሥቃያችን” በማለት ይገልጸዋል።
ጳውሎስ በሕይወታችን ሙሉ የሚያጋጥመንን መከራ “ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል” ሲል፣ አሁን በምናሳልፈው መከራ እና ስንከብር በሚኖረው ሕይወት መካከል ግንኙነት እንዳለ ይነግረናል። ይህ ግንኙነት ወደ ክብር እንደምንሄድ ያረጋግጥልናል።
ጳውሎስ፣ “እኔ የጀርባ ሕመምን የምቀበልበት መንገድ እና አንገቱን በመቆረጥ የተሠዋ ሰው፣ መከራን የተቀበለበት መንገድ የዘላለማዊውን ክብር እንደምናገኝ ያረጋግጥልናል” ማለቱ ብቻ ሳይሆን፣ “ያስገኝልናል” (katergazetai) የሚለው ቃል አንገቱን በመቆረጥ የተሠዋ ሰው የሚያገኘው ዘላለማዊ ክብር፣ እኔ የጀርባ ሕመምን በተቀበልኩበት መንገድ ከሚያስገኘው የዘላለማዊ ክብር ጋር ሲነጻጸር የተለየ ግንኙነት እንዳለው የሚያሳይ ነው። በዚህም ለእርሱ በሚኖረው የተለየ የክብር ሽልማት ደስተኛ ነኝ።
ሁሉም ነገር እርስ በእርሱ የተያያዘ ነው
ከ1400 ዓመታት በኋላ ክርስቶስ ዳግም ባይመጣስ? በሚኖረው ዓለም አሁን ያለው ሕይወታችሁ ልዩነት የሚያመጣ ይመስላችኋል? አዎን ያመጣል። እግዚአብሔር በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥ ሁሉም ነገር እርስ በእርሱ የተጋመደና የተያያዘ ነው።
ይህንን ምሳሌ ተመልከቱ፦
ባለፈው ሕዳር ኢትዮጵያ በነበርኩበት ወቅት፣ አንድ ኢትዮጵያዊ ለሚሲዮናዊ አገልግሎት ወደ ፓኪስታን እንደተጓዘ ሰምቼ ነበር። ምንም እንኳን ፓኪስታን ለዚህ አገልግሎት በሮቿ ዝግ ቢሆኑም፣ ይህ ሚሲዮናዊ ወንጌል ለመስበክና ቤተ ክርስቲያን ለመትከል ወደዚያ አቅንቶ ነበር። ነገር ግን የከተማው መሪዎች ከኢትዮጵያ እንደመጣ ሲሰሙ፣ ወደ እነርሱ ጠርተው “ልትሠራ ያሰብከውን መሥራት ትችላለህ። ሕዝብህ ከ1400 ዓመታት በፊት ለመሐመድ ጥገኝነት ስለሰጡ፣ አሁን ደግሞ አንተን የመቀበልና የማስተናገድ ዕዳ አለብን” በማለት ለወንጌል በር ከፍተውለታል።
የፍትሕ ምድር
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ ከዚህ አስገራሚ ንግግር ጀርባ ያለውን ታሪክ ለማጣራት ሞክሬ ነበር። በ2008 እ.ኤ.አ ስለዚሁ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም እና የተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ምሑራን፣ አዲስ በተገኙ ታሪካዊ ግኝቶች ላይ ተወያይተዋል።
በእስልምና ታሪክ እና ትውፊት ውስጥ ኢትዮጵያ(አቢሲንያ፣)ለእስልምና እምነት ተከታዮች “የመጀመሪያው ስደት መጠለያ” በመባል ትታወቃለች። መሐመድ በሕይወት በነበረበት ወቅት(570-632 ዓ.ም.)ተከታዮቹ በመካ ዙሪያ በአረማውያን ጎሳዎች ይሰደዱ ነበር።
በሩትጀርስ የአፍሪካ ታሪክ ጥናት ፕሮፈሰር የሆነው ዶ/ር ሰይድ ሳማታር፣ ይህንን ታሪክ እንዲህ አብራርቶታል፦ “ንጉሥ አርማህ(ነጋሽ) ከአረማውያን አሳዳጆቻቸው ሸሽትው አክሱም የደረሱትን የመሐመድ ቤተሰቦች ጥገኝነት ሰጥተዋል። ንጉሥ አርማህ(ነጋሽ) ክርስቲያን የነበረ ንጉሥ ሲሆን፣ በጉቦ የማይታለልና ለሙስሊሞች በአክሱም የሚያርፉበት ቦታ የሰጠ ንጉሥ ነበር። መሐመድም ይህንን የነጋሽን ለጋስነት እንደማይዘነጋ ሐዲስ ላይ ‘አቢሲንያ(ኢትዮጵያ) ማንም የማይጨቆንበት የፍትሕ ምድር ነው’ በማለት መስክሯል።”
ስለዚህም ዛሬም ከ1400 ዓመታት በኋላ ለብዙ ሙስሊሞች “ኢትዮጵያ ከስደት እና ከፍርሃት ነጻ የመውጣት ምሳሌ ናት።”
ልትፈጥር የምትችለውን ተጽዕኖ አስብ
ከ1400 ዓመታት በፊት የነበሩት ክርስቲያኖች ያደረጉት ነገር ዐሥራ አራት ምዕተ ዓመታትን ተሻግሮ፣ የፓኪስታንን ከተማ ከንቲባ ለሚሲዮናዊው በር እንዲከፍት እና የክርስቶስ ክብር እንዲበራ ምክንያት እንደሚሆኑ የሚያውቁ ይመስልሃል?
ስለዚህ ክርስቶስን በመታዘዝ የተኖረ ሕይወት፣ በምንም ዐይነት ሁኔታ የባከነ ሊሆን አይችልም። የምናደርገው ነገር ሁሉ በታሪክ ኩሬ ውስጥ እንደተጣለ ጠጠር ነው። ምንም ያህል የጣልነው ጠጠር ኢምንት ቢሆን፣ ኩሬው እስከምን ልክ ድረስ መሙላት እንዳለበት የሚወስነው እግዚአብሔር ነው።
ጠጠሮችህ ያስፈልጋሉ። በየዕለቱ በእግዚአብሔር ታምነህ ወደ ኩሬው ጣላቸው፤ እግዚአብሔር እስከየት ድረስ መሙላት እንዳለበት ይወስናል።
በጆን ፓይፐር