የእግዚአብሔርን ድምጽ የሰማሁባት ማለዳ

ከዕለታት በአንዱ ሰኞ ማለዳ 12 ሰዓት አካባቢ መጋቢት 19፣ 2007 ዓ.ም. እ.ኤ.አ. የገጠመኝን ድንቅ ነገር ልንገራችሁ። እግዚአብሔር ራሱ ተናገረኝ። የተናገረኝ እግዚአብሔር ለመሆኑ ምንም ጥርጥር አልነበረውም። ከሆነ ሰው ጋር የነበራችሁን ውይይት ጥርት ብሎ በኅሊናችሁ ሲንሸራሸር እንደሚሆነው ዓይነት፣ በጭንቅላቴ ውስጥ ንግግሩን ሰማሁ። ንግግሩ በእንግሊዘኛ ቢሆንም በውስጡ ግን የሚያስተጋባ እውነትን የያዘ ነበር። ዛሬም እግዚአብሔር እንደሚናገር ያለ ምንም ጥርጥር አውቃለሁ።

በሆነ ምክንያት መተኛት አልቻልኩም ነበር። የቤተ ክርስቲያናችን ሠራተኞች ከትዳር አጋሮቻችን ጋር ጉዞ አድርገን ሰሜናዊው የሚኖሶታ ክፍል ውሰጥ በሚገኝ አንድ ቤት አርፈን ነበር። ሊነጋጋ 11፥30 አካባቢ ነበር። ከእንቅልፌ ልነሣ ወይስ መልሶ እስኪወስደኝ ልጠብቅ ብዬ እያሰብኩ ነበር። እግዚአብሔር በምሕረቱ ከአልጋዬ እንድነሣ አደረገኝ። ጨለማ ቢሆንም ልብሴን ፈላልጌ ለበስኩና ባለቤቴ ኖኤልን ሳልቀሰቅሳት ቦርሳዬን ይዤ ከክፍሉ ወጣሁ። ዋናው ክፍል ውስጥ እጅግ ጸጥ ያለ ነበር። ሌላ ከእንቅልፉ የተነሣ ማንም አልነበረም። ስለዚህ በሶፋው አንድ ጥግ ላይ ለመጸለይ ተቀመጥኩ።

“ኑና እዩ”

በሐሳብ ተውጬ እየጸለይኩኝ ሳለ በድንገት ነገሩ ተከሰተ። እግዚአብሔርም “ና! ያደረግኩትንም እይ” አለኝ። እነዚህ ቃላት የእግዚአብሔር እንደነበሩ ምንም ጥርጥር አልነበረኝም። በዚያች ስፍራ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እግዚአብሔር በፍጹም ሥልጣን እና ግልጽ በሆነ እውነታ እየተናገረኝ ነበር። ይህን ነገር ለማገናዘብ ቆም ብዬ አሰብኩ። አንዳች የሚማርክ ነገር አለው። ጊዜው አላስጨነቀኝም። እግዚአብሔር ቅርብ ነበር። በእርሱ እይታ ውስጥ ነበርኩ። የሚናገረኝ ነገር ነበረው። እግዚአብሔር ወደ እናንተ ሲቀርብ ሩጫው ይረጋጋል፤ ጊዜው ፍጥነቱን ይቀንሳል።

“ዛሬም እግዚአብሔር እንደሚናገር ያለ ምንም ጥርጥር አውቃለሁ።”

“ና እና እይ” ሲል ምን ማለቱ ነው ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። ልክ ጳውሎስን ወደ ሰማይ ወስዶት በሰው አንደበት ሊነገር የማይገባውን ነገር እንዳሳየው (2ኛ ቆሮንቶስ 12፥3-4) እኔንም የሆነ ቦታ ሊወስደኝ ይሆን? “እይ” ያለኝ ማንም ያላየውን የእግዚአብሔርን ሥራ በራዕይ ልመለከት ይሆንን? “ና! ያደረግኩትንም እይ” በሚለው እና ቀጥሎ በተናገረው መካከል ምን ያህል ጊዜ እንዳለፈ አላውቅም። ብዙም ፋይዳ የነበረው ነገር አይደለም። ከእኔ ጋር በግል ባደረገው የግንኙነት ፍቅሩ ተከብቤ ነበር። የዓለም ፈጣሪ እየተናገረኝ ነበር።

ቀጥሎም ወደ አእምሮዬ መጥተው የሚያውቁ ቃላት መጥተው በሚያውቁት ግልጽነት ልክ እንዲህ አለኝ፦ “በሰዎች መካከል ሥራዬ አስፈሪ ነው።” ልቤ ዘለለች። “አዎን ጌታ ሆይ! ሥራህ አስፈሪ ነው! ሰዎች ቢያዩትም ባያዩትም ሥራህ አዎን አስፈሪ ነው!” አልኩ። ቀጥዬም “አሁን ምን ልታሳየኝ ነው?” ብዬ ጠየቅሁ።

ቃላቱ እንደገና መጡ። ከዚህ በፊት እንደነበረው ግልጽ ቢሆኑም በይበልጥ ግን ስለአንድ ውስን ነገር የሚናገሩ ነበሩ። “ባሕሩን የብስ አደረግሁት፣ ወንዙን በእግር ተሻገሩ። እነርሱም በኀይሌ ለዘላለም በምገዛው በእኔ ደስ አላቸው” አለኝ። ቀይ ባህርን እና የዮርዳኖስ ባህርን ወዳደረቀበት ብዙ ሺህ ዘመን ወደኋላ እየወሰደኝ እንደሆነ አስተዋልኩኝ። እነዚያን ታላላቅ ሥራዎች ወዳደረገባቸው ዘመናት በቃሉ ይዞኝ ነጎደ። “ና እና እይ” ማለቱ ይህ ነበረ። በሰዎች ዘንድ ወዳደረጋቸው እነዚያ ሁለት ታላላቅ ሥራዎቹ በቃሉ አማካኝነት እየወሰደኝ ነበር። “ሥራዬ አስፈሪ ነው” ያለው እነዚህን ነበር። የእግዚአብሔርን አስፈሪ ሥራ ራሱ እግዚአብሔር እየተረከው ነበር። ለእኔ ለራሴው እየተረከልኝ ነበር። ይህንንም ሲያደርግ በጭንቅላቴ ውስጥ እያስተጋቡ ባሉ ቃላት ነበር።

ቅዱስ ጊዜ

በላዬ ላይ ታላቅ ፍርሀት ወደቀ። የሚዳሰስ ሰላም በላዬ ወረደ። ጊዜው ለእኔ የተቀደሰ በዓለም ላይ ካሉ ቦታዎች ሁሉ ደግሞ ቅዱስ ነበር። ሁሉን ቻዩ እግዚአብሔር ወደ እኔ መጥቶ ድምጹን እንድሰማ መረጋጋቱን እና ፍቃዱን እየሰጠኝ ነበር። ባህርን እና ወንዝን በሚያደረቅ ኃይሉ ስገረም ሳለ እንደገና ተናገረኝ። “ዐይኖቼ ሕዝቦችን ይመለከታሉ፤ እንግዲህ ዐመጸኞች ቀና ቀና አይበሉ።”

የሚደንቅ ነገር ነው። ደግሞም የሚያስፈራ። ልክ እንደ ተግሳጽ ነበር። ወይም እንደ ማስጠንቀቂያ። የቲሸርቴን ኮሌታ ባንድ እጁ ጨምድዶ ይዞ ከመሬት አንሥቶኝ በሚያስፈራ፣ ነገር ግን ፍቅር በተሞላ መልኩ “መቼም ይሁን መቼም ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ። መቼም ቢሆን በእኔ ላይ እንዳታምጽ” ብሎ ቢናገረኝ ብላችሁ አስቡት።

ፈዝዤ ቁጭ አልኩ። አእምሮዬ ስለ እግዚአብሔር ክብር በማሰብ ተሞላ። “ዐይኖቼ ሕዝቦችን ይመለከታሉ” ብሎ ተናገረኝ። አንዲህ ብሎ መናገሩ ብቻ አልነበረም። እርግጥ ነው የከበረ ነገር ነው። ነገር ግን እኔን መናገሩ እጅግ የከበረ ሆነልኝ።  የእግዚአብሔር የራሱ ቃል በአእምሮዬ ውስጥ ነበር። ልክ አሁን ይህንን ስጽፍ ቃላቱ በአእምሮዬ ውስጥ እንዳሉት፣ እግዚአብሔርም የተናገረው ቃል እንዲሁ በአእምሮዬ ውስጥ ነበር። ባለቤቴ እራት አዘጋጅታ “እራት ደርሷል ሥራህን ስትጨርስ ና” በምትለኝ መልክ በግልጽ ነበር የተሰማኝ። አነዚያ ቃላት የሚስቴ እንደሆኑ አውቃለሁ። እነዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃላት እንደሆኑ አውቃለሁ።

ዛሬም ይናገራል

ይህን አስቡ። በዚህ ተደነቁ። በዚህ ጉዳይ መገረም ይሙላባችሁ። ልክ ሰዎች ዓይኖቻቸውን በሚጠብቋቸው ከብቶች ላይ ወይም ንግዳቸው ላይ፣ አሊያም ሕንፃ ሥራ ላይ እንደሚያደርጉት ዓይኖቹን በሕዝቦቹ ላይ ያደረገው ይህ አምላክ ዛሬም ይናገራል። እኔ የእርሱን ቃላት ሰምቻለሁ። ለእኔ በግሌ ተናግሮኛል።

 “እግዚአብሔር ወደ እናንተ ሲቀርብ ሩጫው ይረጋጋል፤ ጊዜው ፍጥነቱን ይቀንሳል።”

ይህ ነገር በእኔ ላይ ምን ዓይነት ውጤት ነበረው? የእግዚአብሔር ሕልውና በአዲስ መልኩ እንዲሰማኝ አድርጓል። እግዚአብሔር በታሪክም ውስጥ ሆነ በዘመናችን የሚሠራ እንደሆነ የበለጠ አረጋገጠልኝ። እግዚአብሔር ከጎኔ እንደቆመና ለእኔ እንደሚያስብልኝ፣ እንዲሁም እኔን ለመጠበቅ ኃይሉን እንደሚጠቀም እምነቴን አጠነከረልኝ። አለበለዚያማ እነዚህን ነገሮች ለእኔ መጥቶ ለምን ይነግረኛል?

የእግዚአብሔር ቃል እንደመሆኑ ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለኝን ፍቅር ጨምሮልኛል። ምክንያቱም እነዚህን መለኮታዊ ቃላት የሰማሁት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለነበር ነው። ደግሞም ይህንኑ የሚመስሉ ልምምዶች በየዕለቱ በሚባል ደረጃ የኖሩኝ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ስለሆነ ነው። የዓለማችን ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ገጽ ላይ ለአእምሮዬ ይናገራል። እንዲሁም ለእናንተም አእምሮ ይናገራል። የምናደምጠው የራሱን ቃላት ነው። “እግዚአብሔር ራሱ ያደረገው ድንቅ ነገር ብዙ ነው፤ ለእኛ ያቀድኸውን፣ ሊዘረዝርልህ የሚችል ማንም የለም፤ ላውራው ልናገረው ብል፣ ስፍር ቍጥር አይኖረውም” (መዝሙር 40፥5)።

ከሁሉም በላይ ድንቅ የሚያደርገው ለሁሉም ሰው ቅርብ መሆናቸው ነው። ሚኖሶታ ሶፋው ላይ ሆኜ የሰማኋቸውን ቃላት መስማት የምትፈልጉ ከሆነ መዝሙር 66፥5-7ን አንብቡ። እኔ የሰማኋቸው እዚያ ላይ ነው። አቤቱ! መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ያለ ዕንቁ ነው! የእግዚአብሔር የራሱ ቃል ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመንም እግዚአብሔር በቅዱሱ መጽሐፍ ውስጥ ይናገራል። ይህ የእግዚአብሔር የራሱ ድምጽ ነው። በዚህ ድምጽ በፍጹም እውነት እና ኃይል ይናገራል። በዚህ ድምጽ ከሁሉ የሚልቀው ውበቱን ይገልጻል። በዚህ ድምጽ የልባችንን የተሰወሩ ሚስጥሮች ይገልጻል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደሰማነው፣ የእግዚአብሔር ድምጽ ጥልቅ ሊወርድ ወይም ከፍታን ሊወጣ አሊያም ርቀትን ተሸክሞ ሊሄድ የሚችል ድምጽ፣ በየትኛውም ስፍራ ይሁን ጊዜ የለም።

ዛሬም እግዚአብሔር ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ያሉ ድምጾች በሰዎች ነፍስ ውስጥ ሊደመጥ ከሚችለው በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት በታላቅ ኃይል እና በታላቅ ክብር፣ በታላቅ ዋስትና እንዲሁም ድንቅ ጣዕም፣ በታላቅ ተስፋ እና ታላቅ ምሪት፣ ለውጥን በሚያመጣ ታላቅ ኃይል እና ክርስቶስን በሚያከብር እውነት መናገሩ በጣም የሚደንቅ ነገር ነው።

አቅጣጫውን የሳተ አድናቆት

ለዚህ ነው “ክርስቲያኒቲ ቱደይ” ያወጣው አንድ ጽሑፍ አሳዛኝ እንደሆነ የተሰማኝ። የጽሑፉ ርዕስ “ከእግዚአብሔር ጋር የነበረኝ ውይይት” ይሰኛል። በጣም በሚታወቅ አንድ የክርስቲያን ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚያስተምር ስሙ ያልተጠቀሰ ፕሮፌሰር ነበር የጻፈው። በጽሑፉ ላይ የእግዚአብሔርን ድምጽ ስለሰማበት አጋጣሚ ያወራል። እግዚአብሔር ለጸሐፊው የተናገረው ከሚጽፈው አዲስ መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን የሽያጭ መብት ለአንድ የተቸገረ ተማሪ ትምህርት ክፍያ እንዲያውል ነበር።

በጽሑፉ ያዘንኩበት ምክንያት እውነት ስላልሆነ ወይም ያልተከሰተ ጉዳይ በመሆኑ አልነበረም። አሳዛኝ ያደረገው ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ከእግዚአብሔር ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶች በሚልቅ ሁኔታ ድንቅ የሆኑ እና እምነትን የሚያጠነክሩ ናቸው የሚል አንድምታ ስለሚሰጥ ነው። ይህ ሲሆን የሚቀበል ልብ ባላቸው ዘንድ በየዕለቱ ለግላቸው እንዲሁም በኃይል እና በሚለውጥ ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሚቀጣጠለው ከሕያው አምላክ ጋር የሚደረገው የከበረ ግንኙነት በጸጥታ ይዘለላል።

ይህ የሥነ መለኮት ፕሮፌሰር እንዲህ ማለት አስቦ እንዳይደለ እርግጠኛ ብሆንም የተናገረው ግን እንዲህ ነበር፦ “ለዓመታት እግዚአብሔር አሁንም ይናገራል ባስተምርም ራሴ ግን በግሌ ልመሰክረው የምችለው ነገር አልነበረም። አሁን ግን ማንነቴን ግልጽ ሳላደርግ መመስከር እችላለሁ። ምክንያቱ ግልጽ ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” (የተወሰነ አጽንዖት ጨምሬበታለሁ)። እያለ ያለውን ነገር አንድምታ እንደማያምን እርግጠኛ ነኝ። አንድምታውም “ከመጽሐፍ ሽያጩ የሚመጣው ገንዘብ ያንተ አይደለም” የሚል ዓይነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የሆነ ድምጽ ሲሰማ፣ ያኔ ነው እግዚአብሔር አሁንም እንደሚናገር መመስከር የሚቻለው የሚል ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን በኃይል እና በእውነት፣ በጥበብ እና በክብር፣ በደስታ እና በተስፋ፣ በድንቅ እና በሚጠቅም ሁኔታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ልንሰማ ከምንችላቸው ማናቸውም ነገሮች ዐሥር ሺህ እጥፍ አብልጦ ዛሬም ድረስ በአለቅነት የሚናገረውን የእግዚአብሔርን ድምጽ ለማሳነስ አስቦ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ። 

በዚያ ጽሑፍ ላይ እየተላለፈ ያለው መልዕክት ያሳዝናል። ለጊዜያችን የሚያስፈልገን ነገር ሕያው የሆነውን የእግዚአብሔርን እውነት ሰዎች እንዲለማመዱት በግላቸው እንዲሁም ሊለውጣቸው በሚችል ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔርን ድምጽ መስማት ነው።

ከመዝሙረኛው ጋር አብረን “ልቤን ወደ ምስክርነትህ አዘንብል. . . ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ ዐይኖቼን ክፈት” እያልን ልንጮህ ያስፈልገናል (መዝሙር 119፥18)። አቤቱ! እግዚአብሔር ሆይ ጆሮዎቻችን ለቃልህ የተደፈኑ ሆነውብን በውበቱ እና በግርማው ከመደመም ይልቅ ትንንሽ ነገሮችን የምናከብር እንድንሆን አታድርግ። ይባስ ብለን፣ የአድናቆታችንን አቅጣጫ ስተን፣ እንዲህ የመሰለ ጽሑፍ በአገር ደረጃ በሚታተም መጽሔት ላይ ከማውጣት ጠብቀን።

ጆን ፓይፐር