መንፈስ ቅዱስ፣ ጸሎት እና ስብከት

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ አንድ እምነት አለኝ። ይሄም፣ የዛሬዋን ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋት አዲስ እና ዘላቂ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ መሆኑ ነው። ይህ ጽኑ እምነት፣ ለእኔ ቢያንስ፣ መንፈስ ቅዱስ እንዲወርድ እና እንዲያንሰራራ ወይም እንዲያበረታን ያለው የቤተ ክርስቲያን ፍላጎት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህ እምነት የኢየሱስ ክርስቶስን አገዛዝ ለሌሎችም ሆነ ለእኛ እንዲገልጥልን ካለን ፍላጎት ጋር የተያያዘ ነው። ልክ እንደ እኔ፣ ይህ አስተሳስብ በልባችሁ እና በአምሮአችሁ ውስጥ በአዲስ ጉልበት እና ኅይል እየሞላ ከሆነ፣ እንዲህ ብሎ መጠየቅ ጥሩ ሊሆን ይችላል፦ “ይህ አስተሳስብ በውስጣችን መስረጹን እንዴት እናውቃለን?” ማለትም “በእርግጥ እንደተቀበልነው፣ እንዳመንበት የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?”

ለጸሎት መሰጠት
በቅርብ ጊዜ፣ በእነዚህ ዐይነት ጥያቄዎች ላይ እያሰላሰልኩ ነበር፤ እናም ቢያንስ ሁለት ምልክቶች የሚታዩ ይመስለኛል። በመጀመሪያ፣ ይህ እምነት ለጸሎት ቁርጠኝነት በሚኖርበት ጊዜ ራሱን ይገልጻል። የሚጸልየው ሰው “ያገኘዋል።” በእውነቱ ከሆነ፣ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ፊት የሚሄዱት ብቻ እምነቱን በእውነት ይጎናጸፋሉ ብዬ አስባለሁ። በጸሎታቸው፣ በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የመታደስ ሥራን ማከናወን የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ማመናቸውን ያሳያሉ። እኛ የማንጸልይ ሰዎች ከሆንን ሥራውን በራሳችን እንደምናሳካ ማሰባችንን ያመለክታል።

ትክክል ከሆንኩ፣ ማለትም ጸሎት የእኛ ጽኑ እምነት ግልጽ ማስረጃ ከሆነ፤ እግዚአብሔር በዘመናችን አዲስ የወንጌል ሥራ እንዲሠራ የሚመኙ ሰዎች የሚጸልዩ ሰዎች ናቸው ማለት ነው።

የሚገርመው፣ በሉቃስ ወንጌል ሐተታ ዋና ነጥቦች ውስጥ፣ ይህ ዐይነቱ ቁርኝነት ተጽፏል። ቢያንስ አራት ጊዜ ሰዎች ኢየሱስን ማን እንደሆነ ሲለዩት ከሚጸልይ ሰው ጋር አያይዞት ነበር።
-ጴጥሮስ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ከመቀበሉ በፊት ኢየሱስ ብቻውን ሲጸልይ ነበር (9፥18-20)።

  • ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ለመጸለይ ወደ ተራራ ወጡ። ከዚያም ኢየሱስ ማን እንደሆነ ብቻ ሳይሆን   ተከታዮቹም ከዚህ እውቀት አንጻር ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመግለጥ ከሰማይ የእግዚአብሔር ድምጽ መጣ (9፥28-36)።
  • ኢየሱስ በተጠመቀበት ወቅት፣ ሰማያት ሲከፈቱ፣ መንፈስ ቅዱስ ሲወርድ፣ እና ከሰማይ የመጣ ድምፅ ኢየሱስን ልጁ መሆኑን ሲያረጋግጥ እየሱስ እየጸለየ ነበር (3፥21-22)። 
  • አረጋውያኑ ቅዱሳን ስምዖን እና ሐና ኢየሱስን በማንነቱ ያወቁት በመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት እና በመደበኛው የጸሎት ጊዜ ነበር።

እነዚህ አራት ሁነቶች አስፈላጊ ናቸው። እንደ ንድፍ ተሰጥተውናል ብዬ አምናለሁ። ሰዎች ወደ ክርስቶስ ሲመጡ እና እሱን መከተል የሚጅምሩት በአዲስ እና ቀጣይነት ባለው የመንፈስ ቅዱስ ስራ ነው፣ ይሄንንም በጸሎት በኩል እንደሚደረጉት ያስተምሩናል።
መንፈስ ቅዱስ እንደሚያስፈልገን ከልብ ከተቀብልን ፣ እራሳችንን ለጸሎት እንሰጣለን። 

ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ገለጭ አስተምሮ መገዛት
ሁለተኛ፣ ለአዲስ እና ለዘላቂ የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት እምነት እና መሻት ሲኖረን ጸሎት ብቻ አይደለም መታወቂያው። ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ገላጭ ስብከት ያለ ቁርጠኝነትም አብሮ ብቅ ይላል። ቤተ ክርስቲያን ለታላቁ መሻታችን መልስ እየሰጠች ስትሄድ ሰዎችም ሆኑ ሰባኪዎች ለእግዚአብሔር ቃል መገለጥ እየተራቡ ይመጣሉ። በሌላ መንገድ፣ በጸሎት እየተጋ ያለው ያ ሰው ራሱ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊው ገላጭ ስብከትም በውዴታ ይሰጣል።

መንፈስ ቅዱስ እና ስብከት አብረው የሚሠሩ ናቸው
ብዙ አንባቢዎች ፣ በመንፈስ ቅዱስ እና ስብከት መካከል ያለው ግንኙነት አልተረዱም። ደግሞም ብዙዎቻችን ለመንፈስ ቅዱስ መሰጠትን ወይም ለእግዚአብሔር ቃል መሰጠትን መምረጥ አለብን ተብለን በስሕተት ተነግሮናል። አንድ ሰው “የአስተምሮ ሰው” ወይም “መንፈሳዊ ሰው” መሆን መፈልግ ይችላል ነገር ግን ሁለቱንም በአንዴ መሆን አይችልም ይባላል።

እንዲህ የሚሉት ሰዎች “በመንፈስ የሚመራ ቤተ ክርስቲያን” ወይም “ቃል-ማዕከል ያደረገች ቤተ ክርስቲያን፣” መምረጥን እንዲያምን ይፈልጋሉ። ነገር ግን አንድ ሰው በሁለቱም በአንዴ መገኘት አይችልም ይላሉ። ይህ አይነቱ አስተሳሰብ እኛ መካከል ሥር ሰዷል።  ነገር ግን የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው።

እውነቱን ለመናገር፣ ለዚህ ዐይነቱ ክርክር ዝያለሁ። መንፈስ እና ቃል እርስ በርሳቸው የተጋጩ አስመስለው ውይይቱን በዚህ መንገድ ከሚያካሄዱት ጋር መነጋጋር አድካሚ ስራ ነው። ይህ አይነቱ መነጣጠል ውሸት ነው።  እናም ይሄን ችግር እንዴት ማለፍ እንዳለብን የምንማርበት ጊዜ ነው።

በዚህ ምትክ እኔ የምከራከረው የመንፈስ ቅዱስን አዲስ እና ዘላቂ ስራ በቤተ ክርስቲያን እንዲሆን የሚፈልግ ሰው ለጸሎት ብቻ ሳይሆን ለቃለ እግዚአብሔርም ራሱን የሰጠ ሰው ነው የሚል ይሆናል። ምክንያቱም የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ምንጊዜውም ሰንሰለታዊ በሆነ መልኩ ከቃሉ አገልግሎት ጋር የተያያዘ ነው።

ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደ ምሳሌ መውሰድ

ምንም እንኳን ብዙ ሊመረጥ ይችል የነበረ ቢሆንም ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት አንድ ጽሑፍ በቂ ነው። ዕብራውያን 3፣ በተለይም ቁጥር 7ን ተመልከት፣ በዚህ መንገድ ነው የሚጀምረው፦ “ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል….” በእነዚህ አራት ቃላት ውስጥ ሁለት አስደናቂ ነገሮች አሉ። በመጀመሪያ፣ ይህን አስተውል! ጸሐፊው መዝሙር 95ን ሲጠቅስ የመንፈስ ቅዱስን ደራሲነት በማመልከት ነው። እርሱ “መጽሐፍ እንደሚለው” ወይም “መዝሙረኛው እንዳለው” ወይም  “ጽሑፉ እንዳለው” አላለም። ይልቁንስ “መንፈስ ቅዱስ እንደሚል” ሲል ጽፏል።

ይህ ትልቅ ቁምነገር ነው።  የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ ለመስማት ከፈለጋችሁ፣ ይህ ድምጽ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ጋር ይዛመዳል። ያም ማለት፣ መንፈስ ቅዱስ ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የገለጸው ቃል እንዳለ ያሳያል። እንዲህ ብሎ በትዊተር የለጠፈው ጆን ፓይፐር ይመስለኛል፣  “ዛሬ እግዚአብሔር ሲያናግርህ መስማት የምትፈልግ  ከሆነ ክፍልህ ውስጥ ግባ፣ በሩን ዝጋ፣ እና መጽሐፍ ቅዱስን ጮክ ብለህ አንብብ።” እኔም እስማማለሁ። የእግዚአብሔር ቃል የመንፈስ ቅዱስ ድምፅ ነው። ስለዚህ፣ የእኛ እምነት እና ፍላጎት የቤተ ክርስቲያን አዲስ እና ዘላቂ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስብከት ላይ እኩል ቁርጠኝነት ማድረግ ያስፈልገናል።

በዕብራውያን 3፥7 ላይ ያለው ሁለተኛው አስገራሚው ነገር የጥቅሱ የሰዋሰው መድብ ግሥ አሁን ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑ ነው! እንዲህ ይነበባል፦ “መንፈስ ቅዱስ እንደሚል…” የዚህም ጠቀሜታ ሊታለፍ አይገባም። መዝሙር 95፣ ቀድሞ በተለየ ዘመን ይኖሩ ለነበሩ ጥንታውያን ሕዝቦች የተሰጠው የእግዚአብሔር ቃል፣ ሕያው ቃል ሆኖ ለኋለኛው ትውልድም እንዲሁ ነው ተብሏል። ዛሬም ቢሆን ለእኛ እንዲሁ ነው። ዕብራውያን 3፥7 በአሁን ጊዜ ባለው የመንፈስ ቅዱስ አገልግሎት እና በተገለፀው የእግዚአብሔር ቃል መካከል ቀጣይ እና ሰንሰለታዊ ግንኙነት ይመሠረታል።

ማጠቃለያ

ለተሃድሶሃዊው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ጽኑ እምነት ያስፈልጋል። እናም የጸሎት እና የቃለ እግዚአብሄር ስብከት በሚገኙበት ጊዜ ይህ ጽኑ እምነት በአጥንታችን ዘልቆ እንደገባ እናውቃለን። በቅርብ ቀናት ውስጥ፣ ይህ ጽኑ እምነት በአዲስ ኅይል እና ጉልበት ወደ ነፍሴ ውስጥ እየገባ ነበር። ይህ እምነት ትክክለኛ መሆኑን ተረዳሁ ምክንያቱም ጸሎት እና ስብከት ከጊዜ ወደ ጊዜ በህይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ውጤት እያመጡ ስላየሁ ነው። ለአንተም/ ለአንቺም እንዲሁ እንዲሆን እመኛለሁ።

ዴቪድ ሄልም