የሕማማት ማክሰኞ ምሽት
“የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል” (ማርቆስ 10፥33)
ወደ ቀራንዮ የሚወስደው መንገድ ለእነዚያ የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት የመተማመን ሳይሆን ግራ የመጋባት መንገድ ነበር።
ኢየሱስ ለርሱ መሲሕ መሆን ምን ማለት እንደ ሆነ ሦስት ጊዜ ለእነዚህ ሰዎች አስረድቷቸው ነበር። አስከፊ፣ ሆኖም በተስፋ የተሞላ ታሪክ ነበር፦ የተስፋው ንጉሥ ግድያ፣ እናም ከዚያ በኋላ የሚያስገርምና ታይቶ የማይታወቅ ትንሣኤ። ይህ ግን የሩቁን ለማያዩት ክብር ለተጠሙት ለጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስ፣ እና ለሌሎቹም አእምሮ እጅግ ከባድ ነበር።
የእነርሱ አለማወቅና የተሳሳቱ ምላሾች በሰው ልብ ውስጥ ያሉትን ክፉ ዝንባሌዎች (ungodly grooves) ያጐላሉ። ስሕተቶቻቸው በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ለነበሩ ዓሣ አጥማጆች ብቻ የተወሰኑ አልነበሩም። በፍጹም፣ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያንኑ ያህል የተለመዱና ጐጂ ናቸው። የዐርብ ስቅለትን አሠቃቂነትና የትንሣኤን ድል ስንጠባበቅ፣ ይህን ጥያቄ እንደ ገና መጠየቅ አለብን፣ ይህን ኢየሱስ ማን ነው እንለዋለን? (ማርቆስ 8፥29)። እርሱ (በእግዚአብሔር መንገድ) ክርስቶስ ነውን? ወይስ እርሱ ለሌላ ነገር ወይም ለሌላ ሰው የምንጠቀምበት ሁሉን ዐዋቂ፣ ሁሉን ቻይ ቊልፍ ብቻ ነው?
የምቾት ሰው ሳይሆን መከራ ተቀባይ
ድራማው፣ “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” በሚለው ጥያቄ ይጀምራል። “አንተ ክርስቶስ ነህ” (ማርቆስ 8፥29)። ጴጥሮስ በአንድ ጊዜ በጣም ትክክልና በጣም ስሕተት ነበር። ክርስቶስ የሚለው ቃል በሁሉም ረገድ ተስማሚ ነበር። ትክክለኛ መልስ ነበር።
ነገር ግን ጴጥሮስ ለተስፋው አዳኝ የሰጠው ስያሜ ትክክል ቢሆንም፣ መረዳቱ ግን በሚያስደነግጥ ሁኔታ ጐዶሎ ነበር።
ኢየሱስ ስለ ክርስቶስ ይበልጥ ዝርዝር የሆነ ሥዕል ይሥላል፣ በታሪክ ውስጥ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ሰው የሥራ ድርሻ፦
“ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፣ በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፣ እንደሚገደል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር።” (ማርቆስ 8፥31)
ጴጥሮስ (እንዲሁም ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት) የመከራ ተቀባዩን ክርስቶስን ሐሳብ ናቁት። ወዲያውኑ ኢየሱስን የተጋፈጠው ከዚህ የተነሣ ነው (ማርቆስ 8፥32)። እርሱ ክርስቶስ መሆኑን በትክክል ዐውቆ፣ ከዚያም እርሱን የማረም አመለካከትና ሥልጣን እንዳለው ዐሰበ። ትክክል ነበር፣ ነገር ግን በአሳዛኝ ሁኔታ ስሕተት ነበር።
በእውነት የሚያድነው ብቸኛው አዳኝ፣ የሚያድነው በመከራ በኩል ብቻ ነው። ኀጢአተኞች የሆንን እኛ በቅዱስ አምላክ ፊት ጻድቅ የምንሆንበት ብቸኛ መንገድ መስቀል ነበር። ድነታችን የተገዛው በመከራ ነው፤ የታተመውና የተጠበቀውም በመከራ ነው (ያዕቆብ 1፥2-4) እንጂ በምቾት አይደለም። በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ውስጥ የመጽናናት ተስፋ ተሰጥቶናል (2 ቆሮንቶስ 1፥4)፤ ነገር ግን ይህ በዘመናዊው ዓለም የለመድነው ዐይነት ርካሽ፣ ጊዜያዊ የኩረጃ ምቾት አይደለም።
ሕይወታችንን ቀላልና ይበልጥ ምቹ እንዲያደርግልን በመጠበቅ ወደ ተሰቀለው ጌታ የምንመጣ ከሆነ፣ እርሱን እያዳመጥነው አይደለም። ኢየሱስ፣ “ሊከተለኝ የሚወድድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” ይላል (ማርቆስ 8፥34)።
የሚሞት ከዚያም ሕይወትን የሚያገኝ
ኢየሱስ የቀራንዮን ታሪክ ከመፈጸሙ በፊት በድጋሚ ይነግራቸዋል፦
“ከዚያም ተነሥተው በገሊላ በኩል ዐለፉ፤ ኢየሱስም ያሉበትን ስፍራ ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም፤ ለደቀ መዛሙርቱ፣ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም ይገድሉታል፤ ከሦስት ቀንም በኋላ ይነሣል” እያለ ያስተምራቸው ነበር። እነርሱ ግን የሚላቸው አልገባቸውም፤ እንዳይጠይቁትም ፈሩ።” (ማርቆስ 9፥30–31)
ብዙዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች፣ ኢየሱስ አሁን ሊታደጋቸውና ንጉሥ ሊሆን እንደ መጣ ዐስበው ነበር። ከሮማውያን ጨቋኝ አገዛዝ አካላዊና ፖለቲካዊ ነጻነትን ተስፋ አድርገው ነበር። ክርስቶስ ለእነርሱ፣ ለወቅታዊው የአሁኑ ዓለም ችግሮቻቸው መፍትሔ ነበር። ሕይወት አሁን። ነጻነት አሁን። ኀይል አሁን። ወደ መስቀል የሚጓዘው ኢየሱስ ግን፣ ጠብቁ ይላል። ታገሡ።
እኔን በመከተልና በእኔ ውስጥ ሕይወትን በማግኘት የሚገኘው ዋጋ፣ ዛሬ ላይ በሙላት ላይመጣ ይችላል፤ ነገር ግን እናንተ ተስፋ ካደረጋችሁት ከማንኛውም ነገር እጅግ የላቀ ይሆናል። በዚህ የሕይወት፣ የተስፋ የነጻነት ታሪክ ውስጥ፣ ሞት መጀመሪያ ይመጣል፣ ከዚያም ሕይወት። ጨለማ፣ ከዚያም ነጻ የሚያወጣ፣ ታላቅ፣ የማይመረመር ብርሃን።
ተቀባይነትን የሚያገኝ ሳይሆን የሚገፋ
ለሦስተኛ ጊዜ ኢየሱስ ስለ ሞቱ ያዘጋጃቸዋል (እኛንም ያዘጋጀናል)፦
“ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ከሕዝቡ ለይቶ ምን እንደሚደርስበት ነገራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል፤ ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል፤ እርሱ ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።” (ማርቆስ 10፥32–34)
በዚህ መልኩ አይደለም እንጂ፣ ደቀ መዛሙርቱ በኢየሩሳሌም ውስጥ ተቃውሞ እንደሚኖር በርግጥ ዐስበው ነበር። ከጠላቶቻቸው ጋራ አደገኛ ግጭት ውስጥ እንደሚገቡ ጠብቀው ነበር፤ ይጐዳል ብለው የጠበቁት ግን ሮምን እንጂ ንጉሡን አልነበረም። ተቃውሞ የሚገጥመው ንጉሥ በማግኘታቸው ደስተኞች ነበሩ፤ ይሁን እንጂ በሚገፋ፣ በተለይም ታልፎ በሚሰጥ፣ በሚሠቃይና በሚገደል ንጉሥ ግን ደስተኞች አልነበሩም።
ኢየሱስ የሌሎችን ተቀባይነት (approval) ለመግዛት አልመጣም። በፍጹም፣ እርሱ፣ “በሰዎች የተናቀና የተጠላ፣ የሕማም ሰውና ሥቃይ ያልተለየው ነበር። ሰዎች ፊታቸውን እንደሚያዞሩበት ዐይነት፣ የተናቀ ነበር” (ኢሳይያስ 53፥3)። ለምን? ምክንያቱም እኛ በእጅጉ የሚያስፈልገን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን (approval) ማግኘት ነው። በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የሚመጣው ደግሞ፣ በብዙኀኑ አስተያየት ሳይሆን በመለኮታዊ ጣልቃ ገብነት፣ የገዛ ልጁን በእኛ ቦታ በመተካት ነው። የዳንነው በመገፋት አማካይነት (ኢሳይያስ 53፥3) ነው፤ በእግዚአብሔር ጸጋም ወደ ድነት የተሸጋገርነው በርሱ መገፋት አማካይነት ነው (ማቴዎስ 10፥22)።
የቀራንዮ ጥሪ፣ ኢየሱስን የመከተል ጥሪ፣ የመሞትና የመነሣት ጥሪ ነው። ጊዜያዊው በሆነው የዚህ ሕይወት ኪሣራ ዘላለማዊ የሆነውን የቀጣይ ሕይወት ትርፍ የማግኘት ጥሪ ነው። ድነት በዚህ ምድር ላይ ያሉ ልዩና ራስ ወዳድ ምኞቶቻችንን የማግኚያ መንገድ አይደለም፤ ይልቁንም፣ ለእግዚአብሔር ክብርና እኛ በርሱ ለምናገኘው ርካታ ተብሎ በተሠራች አዲስ ፍጥረት ውስጥ ነፍሳችንን ለሌላ ዓለም የማዘጋጃና የመጠበቂያ መንገድ ነው።
በእውነት ለመኖር፣ በምናባችን ራሳችን ለፈጠርነው ንጉሥ ሳይሆን፣ በርግጥም ለሚያስፈልገን ንጉሥ መገዛት አለብን።