የሕማማት ማክሰኞ ጠዋት
አሁን ማክሰኞ ጠዋት፣ መጋቢት 31 (March 31) 33 ዓ.ም. ነው። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በትላንትናው ዕለት የረገማትንና አሁን የደረቀችውን የበለስ ዛፍ ጠቈሙት። ኢየሱስ ከርሷ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ ቀላል የሆነ ትምህርት ሰጣቸው፤ በእግዚአብሔር እመኑ። በተለይም፣ ጥርጥር የሌለው እምነት ካላቸው ተራሮችን እንኳ ወደ ባሕር መጣል እንደሚችሉ ነገራቸው።
ደቀ መዛሙርቱ የሚሰማ ጆሮ ቢኖራቸው ኖሮ፣ ኢየሱስ ዛፎችን ስለሚረግምና ተራሮችን ስለሚያፈርስ አስማታዊ ኀይል ሳይሆን ከዚያ በላይ ስለ ሆነ ነገር እየተናገረ እንደ ሆነ ይገነዘቡ ነበር። ከዚህ የሚበልጡ እውነታዎችን እየተናገረ ነው።
ይህን ተራራን ስለሚያንቀሳቅሰውና ጥርጣሬ ስለሌለው እምነት የሚያስተምረውን ዐጭር ትምህርት ሲያጠቃልል እንዲህ እንዳለ አስተውሉ፦ “እንዲሁም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ፣ የሰማዩ አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲልላችሁ፣ እናንተም በሰው ላይ ያላችሁን ሁሉ ይቅር በሉ” (ማርቆስ 11፥25)። ኢየሱስ ይቅር አለማለት ከተራራ ይልቅ ለጸሎት ትልቅ እንቅፋት እንደ ሆነ እያስታወሳቸው ነው። ደቀ መዛሙርቱ በቅርቡ በእምነታቸውና ይቅር ለማለት ባላቸው ችሎታ ላይ ታላላቅ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል። በቢታንያ መንገድ ላይ ያዩዋትን ይህችን የደረቀች ዛፍ ያስታውሱ ይሆን?
ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ሲቃረቡ፣ በትላንትናው ዕለት የተፈጸሙት ክሥተቶች ከአእምሯቸው የራቁ ሊሆኑ አይችሉም። ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ግቢ ሲገባ፣ ሕዝቡ ትምህርቱን ለመስማት ተሰበሰበ (ሉቃስ 21፥38)፤ ነገር ግን የካህናት አለቆች፣ ጻፎችና ሽማግሌዎች የራሳቸውን ርምጃ ለመውሰድ ጊዜ አላጠፉም። ተቀናቃኛቸውን ለማጥመድ አራት ወጥመዶችን ለማስቀመጥ ይሞክራሉ።
ወጥመድ አንድ፦ በማን ሥልጣን?
ትናንትና ያደረጋቸውን ድርጊቶች በማን ሥልጣን እንዳደረገ ወዲያውኑ እንዲነግራቸው ጠየቁት (ማርቆስ 11፥28)። ኢየሱስ በወጥመዳቸው አልተያዘም። ከዚህ ይልቅ፣ በራሱ ጥያቄ ወጥመዱን ወደ እነርሱ አዞረው፦ “የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው?” (ማርቆስ 11፥30)። “ከሰማይ” ብለው ከመለሱ፣ የሚቀጥለው ጥያቄ ግልጽ ነው፦ ታዲያ ዮሐንስ ስለ መሰከረለት ሰው ለምን አላመናችሁም? “ከሰው” ብለው ከመለሱ፣ ዮሐንስን እንደ ነቢይ አድርጎ የሚያከብረውን ሕዝብ ሊያስቈጡና ሊያጡ ይችላሉ።
ከዚያም ኢየሱስ ሦስት ምሳሌያዊ ታሪኮችን አቀረበ (ስለ ሁለቱ ልጆች፣ ስለ ነፍሰ ገዳዮቹ ገበሬዎችና በሠርግ ድግስ ላይ ስለ ተጠሩት እንግዶች)፤ እነዚህ ሁሉ ታሪኮች የሚያስተላልፉት ዋና መልእክት፣ እነርሱ በግብዝነት ራሳቸውን ጻድቅ ለማድረግ ሲሉ ጸጋንና እውነትን እየተቃወሙ መሆናቸውን ነው።
ወጥመድ ሁለት፦ ታማኝ መሆን ?
መሪዎቹ አዲስ ስልት ሞከሩ። ፈሪሳውያንን (በሕግ ቅንዓታቸው የሚታወቁ የአይሁድ ቡድኖች) እና ሄሮድሳውያንን (ለሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ታማኝ የሆኑ ቡድኖች) ጥያቄ እንዲጠይቁት ላኩ፦ “ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” (ማቴዎስ 22፥15-22፤ ማርቆስ 12፥13-17፤ ሉቃስ 20፥20-26)። “አዎ” ብሎ ከመለሰ፣ የሮማውያንን አገዛዝ የሚገለብጥ መሲሕ ነው ብለው የጠበቁትን የሕዝቡን ተስፋ ያደክማል። “አይሆንም” ብሎ ከመለሰ ደግሞ፣ ዐመፅን በማነሣሣት ሊታሰር ይችላል።
ነገር ግን ኢየሱስ ከሁለት አንዱን መምረጥን (either-or dilemma) በብልሃት አስወገደ። ዲናሩ የቄሣር መልክ አለበት፤ ስለዚህ ቄሣር በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ፣ ለርሱ ግብር መክፈል ተገቢ ነው። እኛ ደግሞ የእግዚአብሔር የሆኑትን ነገሮች ለእግዚአብሔር መስጠት አለብን። በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠርን ስለ ሆንን፣ ያለን ሁሉ ማለትም ያለን ነገርና ማንነታችንን ሁሉ፣ የርሱ ነው። ግብራችሁን ክፈሉ፤ እግዚአብሔርንም አምልኩ።
ወጥመድ ሦስት፦ በትንሣኤ የማን ሚስት ትሆናለች?
ኢየሱስ ፈሪሳውያንንና ሄሮድሳውያንን ዝም ካሰኘ በኋላ፣ ሰዱቃውያን (የመጨረሻውን የሙታን ትንሣኤ የሚክዱ የአይሁድ ቡድኖች) በሰማይ ስለሚኖር ጋብቻ የሚያደናግር ጥያቄ በመጠየቅ ኢየሱስ በትንሣኤ ላይ ያለውን እምነት ለማፌዝ ሞከሩ (ማቴዎስ 22፥23-33፤ ማርቆስ 12፥18-27፤ ሉቃስ 20፥27-40)። ኢየሱስ ቅዱሳት መጻሕፍትን (በሰማይ ጋብቻ የለም) ወይም የእግዚአብሔርን ኀይል (በዘፀአት 3፥6፣ 15-16 ላይ እግዚአብሔር ስለ ራሱ የሰጠው ማረጋገጫ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አለመሆኑን ያሳያል) እንደማያውቁ ነገራቸው። እንደ ሌሎቹ ሁሉ፣ የእነርሱም ፌዝ ወደ መደነቅ ተቀይሮ ዝም አሉ።
ወጥመድ አራት፦ የትኛው ትእዛዝ?
አሁን ፈሪሳውያን አንድ የሕግ ዐዋቂ ኢየሱስን እንዲጠይቀው ላኩ። ከእግዚአብሔር ትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው (ማቴዎስ 22፥34-40፤ ማርቆስ 12፥28-34)? ኢየሱስ ምላሹን በአንድ ቃል አጠቃለለው፦ ፍቅር (ለእግዚአብሔርና ለባልንጀራ ዘዳግም 6፥4-5፤ ዘሌዋውያን 19፥18)። ነገር ግን ኢየሱስ በዚህ ጠያቂ ውስጥ ከሌሎቹ የተለየ ነገር አስተዋለ፤ ስለዚህ አደነቀውና በተዘዋዋሪ ጋበዘው፤ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” (ማርቆስ 12፥34)።
አሁን ደግሞ ሊያጠምዱት የሚሞክሩትን ሰዎች ጥያቄዎችን የመጠየቅ ተራ የኢየሱስ ሆነ። ስለ መዝሙር 110፥1 እና መሲሑ እንዴት የዳዊት ጌታ ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ ባቀረበላቸው ጊዜ፣ “አንድ ቃል ሊመልስለት የቻለ ወይም ከዚያ ቀን ጀምሮ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም” (ማቴዎስ 22፥46)። ከዚያም ኢየሱስ በጻፎችና በፈሪሳውያን ላይ ረጅምና ከባድ ትችት ሰነዘረ፤ በእነዚህ “ግብዞች” እና “ዕውር መሪዎች” ላይ ሰባት የፍርድ ወዮታዎችን ዐወጀ (ማቴዎስ 23፥1-39፤ ማርቆስ 12፥38-40፤ ሉቃስ 20፥45-47)።
ይህ አጠቃላይ የቃላት ጥቃት፣ ስለ ኢየሱስ ዐላማዎች፣ አጀንዳዎችና ግቦች የነበረውን ጥርጣሬ ሁሉ ያስወግዳል። እርሱ አሁን ካለው አመራር ጋራ የመተባበር ምንም ፍላጎት የለውም። የእነርሱን ሥልጣን ሊገለብጥ መጥቷል። በዚህ እየተባባሰ በመጣው ግጭት ውስጥ ሁለቱም ወገኖች ሊተርፉ የሚችሉበት ምንም መንገድ የለም። ወይ ኢየሱስ ሥልጣኑን ይይዛል፤ ወይም መሞት አለበት።
በእያንዳንዱ ወጥመድ ውስጥ ጸጋና እውነት
ሌላ ውጥረት የተሞላበት ቀን ካለፈ በኋላ፣ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቢታንያ መመለስ ጀመሩ። ለማረፍ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ቆሙ፤ ይህ ስፍራ ፀሓይ በስተምዕራብ ኢየሩሳሌም ጀርባ ስትጠልቅ ከተማዋን በሚገባ ለማየት የሚያስችል አስደናቂ እይታ ይሰጣቸዋል። ደቀ መዛሙርቱ በእነዚህ አስደናቂ ሕንጻዎች ስፋትና ግርማ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን፣ አንድም ድንጋይ በድንጋይ ላይ የማይቀርበት ቀን በቅርቡ እንደሚመጣ ነገራቸው። በመቀጠልም፣ ተከታዮቹ እስከ መጨረሻው የፍርድ ቀን ድረስ እየጨመረ የሚሄድ ስደትና መከራ እንደሚገጥማቸው አብራራላቸው። የእነርሱ ኀላፊነት ግን ነቅቶ መጠበቅና በእምነት መጽናት ነው።
ማክሰኞ አሁን ተጠናቅቋል። ዐርብ ግን እየመጣ ነው። ይህ አንዳንዶቻችን በልጅነታችን የተማርነው ያ ምስኪኑ (flannel-board) ኢየሱስ አይደለም። ይህ እውነተኛው፣ ታሪካዊው ኢየሱስ ነው። በሁሉም አቅጣጫ ለሚመጡ ወጥመዶች በጸጋና በእውነት ምላሽ ሲሰጥ ነገሮችን ሙሉ በሙሉ ተቈጣጥሮ ነው። ምን እያደረገ እንዳለ ያውቃል። ምን እየመጣም እንዳለ ያውቃል። እያንዳንዱ ቃልና እያንዳንዱ ርምጃ የአባቱን ስም ለማክበርና መስቀላቸውን ተሸክመው ከርሱ ጋራ ለመሞት ፈቃደኛ የሆኑትን ለማዳን ነው።