ለምን ተውኸኝ?

የስቅለት ዐርብ ማታ

በዘጠኝም ሰዓት ኢየሱስ፣ “ኤሎሄ፣ ኤሎሄ፣ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ (ማርቆስ 15፥34)።

እስከዚህ ነጥብ ድረስ፣ የስቅለቱ ትረካ ያተኰረው በኢየሱስ አካላዊ ሥቃዮች ላይ ነበር። እነርሱም ግርፋቱ፥ የእሾህ አክሊሉና በመስቀል ላይ መሞቱ ናቸው። ምስማሮቹ ከተመቱ አሁን ስድስት ሰዓታት ዐልፈዋል። ሕዝቡ አፌዘ፤ ጨለማ ምድሪቱን ሸፈነ፤ አሁን ደግሞ በድንገት ከረጅም ጸጥታ በኋላ፣ ከአዳኙ ነፍስ ውስጥ ይህ የጭንቀት ጩኸት ወጣ።

ቃላቱ ከመዝሙር 22 የተወሰዱ አራማይክ ነክ ጥቅሶች ናቸው። ማቴዎስና ማርቆስ ለአሕዛብ አንባቢዎች ሲሉ ትርጕሙን ቢያቀርቡም፥ ኢየሱስ የተናገራቸውን ትክክለኛ ቃላት እንድንሰማ በግልጽ ፈልገዋል። እጅግ በደከመበት ሰዓት፣ አእምሮው በደመ ነፍስ መዝሙራትን ይተነፍሳል፤ ከነርሱም ውስጥ አሁን የሥጋውን ሳይሆን የነፍሱን ጭንቀት የሚገልጹትን ቃላት ይዋሳል።

ካልቪን እንደ ጻፈው፣ በነፍሱ ውስጥ “የተፈረደበትንና የጠፋን ሰው ከባድ ሥቃዮች” ተሸከመ። ነገር ግን በዚህ ቅዱስ ስፍራ የበለጠ ግልጽነትን ለመፈለግ እንደፍር ይሆን?

ተስፋ በሌለበት ተስፋ ማድረግ

በርግጥ አንዳንድ በጣም ግልጽ የሆኑ አሉታዊ እውነታዎች አሉ። ለምሳሌ መተው ማለት በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለው ዘላለማዊ ኅብረት ተቋረጠ ማለት ሊሆን አይችልም። እግዚአብሔር ሥሉስ አሐዱነቱን ሊያጣ አይችልም።

እንዲሁም፣ አብ ወልድን መውደዱን አቆመ ማለት ሊሆን አይችልም፤ በተለይም ወልድ አብ ከተቀበለው ሁሉ የላቀውን የታዛዥነትና የፍቅር መሥዋዕት እያቀረበ ባለበት በዚህ ጊዜና ስፍራ ላይ።

በተጨማሪም፣ መንፈስ ቅዱስ ወልድን ማገልገል አቆመ ማለት ሊሆን አይችልም። በጥምቀቱ ጊዜ የወረደው በርሱ ለመኖር እንጂ ለአንድ ዐጭር ቅጽበት ብቻ አይደለም (ዮሐንስ 1፥32)፥ እንዲሁም ወልድ ራሱን ለእግዚአብሔር ባቀረበበት በዘላለም መንፈስ በኩል እስከ መጨረሻው ድረስ በዚያ ይኖራል (ዕብራውያን 9፥14)።

በመጨረሻም፣ ቃላቱ የተስፋ መቊረጥ ጩኸት አይደሉም። ተስፋ መቊረጥ ኀጢአት ይሆን ነበር። በጨለማ ውስጥ ቢሆንም እግዚአብሔር “አምላኬ” ነበር፤ ምንም እንኳ የርሱ ምልክት ባይኖርም፤ እንዲሁም ሥቃዩ ተስፋዎቹን ቢያደበዝዛቸውም፣ በነፍሱ ጥልቀት ውስጥ እግዚአብሔር እንደ ያዘው የሚያሳይ ማረጋገጫ ቀርቶ ነበር። ለአብርሃም እውነት የነበረው፣ ለኢየሱስም ይበልጥ እውነት ነበር፤ ምንም ተስፋ በሌለበት ተስፋ አድርጎ አመነ (ሮሜ 4፥18)።

በእውነት የተተወ

ሆኖም ከእነዚህ ሁሉ ማብራሪያዎች ጋራ፣ ይህ እውነተኛ መተው ነበር። ኢየሱስ የተተወ እንደ ሆነ እየተሰማው ብቻ አልነበረም። እርሱ ተትቷል፤ ያውም የተተወው በደቀ መዛሙርቱ ብቻ ሳይሆን፣ በእግዚአብሔርም ጭምር ነበር። እርሱን ለይሁዳ፣ ለአይሁድ፣ ለጲላጦስና በመጨረሻም ለመስቀሉ አሳልፎ የሰጠው አብ ነበር።

አሁን ደግሞ በጮኸ ጊዜ እግዚአብሔር ጆሮዎቹን ዘጋ። ሕዝቡ ማፌዙን አላቆመም፤ አጋንንት መሳለቃቸውን አልተዉም፤ ሥቃዩም አልቀነሰም። ከዚህ ይልቅ፣ እያንዳንዱ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ቊጣ የሚያሳይ ነበር፤ ምንም ዐይነት ተቃራኒ ድምፅም አልነበረም። በዚህ ጊዜ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅና እጅግ የተወደደ መሆኑን የሚያስታውስ ምንም ቃል ከሰማይ አልመጣም። የመንፈስን መገኘትና አገልግሎት ለማረጋገጥ ምንም ርግብ አልወረደም። ሊያበረታውም የመጣ መልአክ አልነበረም። ሊያመሰግነው የሰገደ የዳነ ኀጢአተኛ አልነበረም።

ርግማኑን መሸከም

እርሱ ማን ነበር? በአራማይክ ቋንቋ ይጮኻል፤ ነገር ግን ከአራማይክ ቃላት ሁሉ የላቀውን “አባ” የሚለውን ቃል አልተጠቀመም። በጌቴሴማኔ ጭንቀት ውስጥ ሆኖ፣ እጅግ ተረብሾና ታውኮ በነበረ ጊዜ እንኳ ያን ቃል መጠቀም ችሎ ነበር (ማርቆስ 14፥36)። እዚህ ጋር ግን አልተጠቀመውም።

አብርሃምና ይስሐቅ ወደ ሞሪያ ተራራ እንደ ወጡ ሁሉ፣ እርሱና አብ ዐብረው ወደ ቀራንዮ ወጥተው ነበር። አሁን ግን “አባ” እዚያ የለም። እዚያ ያለው “ኤል” ብቻ ነው፤ ሁሉን ቻይ አምላክ፤ ፍጹም ቅዱስ የሆነ አምላክ። እርሱም አሁን በተወዳጅ ልጅነቱ ሳይሆን የዓለም ኀጢአት ሆኖ በ”ኤል” ፊት ቆሟል። ማንነቱ ይህ ነው፤ በፍጹም ጽድቅ ፊት የሚቆምበት ባሕርይው ይህ ነው።

ከኀጢአተኞች ጋራ ያለው ዝምድና አወዛጋቢ አይደለም። እርሱ ከእነርሱ አንዱ ነው፤ ከዐመፀኞች ጋራ ተቈጥሯል። እንዲያውም እርሱ ሁሉንም ይወክላል። እርሱ ኀጢአት ሆኗል (2 ቆሮንቶስ 5፥21)፤ ርግማኑን ሊሸከም ተፈርዶበታል፤ ከዚህ የሚከለልበት ምንም መንገድ የለውም። ማንም ጠበቃው ሆኖ ሊያገለግል አይችልም። ለማስተስረያ የሚቀርብ ምንም ነገር የለም። ሁሉንም መሸከም አለበት። እንዲሁም “ኤል” የቤዛነቱን ዋጋ ሙሉ በሙሉ እስኪከፈል ድረስ ሊራራለት አይችልም፤ አይፈቅድምም። ተልእኮው ይሳካ ይሆን? ቢከሽፍስ?

የጥንት የነገረ መለኮት ሰዎች እንደሚሉት፣ የነፍሱ ሥቃዮች የሥቃዩ ዋና ክፍሎች ነበሩ። ወደዚያች ነፍስ ደግሞ እኛ ማየት የምንችለው በድንግዝግዝ ብቻ ነው። ጩኸቱ በአደባባይ ቢሆንም፣ ኀጢአትን በተሸከመው ወልድና በሰማይ አባቱ መካከል ያለውን እጅግ ግላዊ የሆነ የጭንቀትን ውጥረት የሚገልጽ ነበር። የኀጢአት ዐውሎ ነፋስ እጅግ በሚያስፈራ መልኩ የተገለጠበትና እግዚአብሔር በእግዚአብሔር የተተወበት ሁኔታ ነበር።

የነፍሱ ጭንቀት

ነገር ግን በኢየሱስ ነፍስ ውስጥ ከነበረው ሥቃይ ባልተናነሰ ፈታኝ የሆነው “ለምን?” የሚለው ጥያቄው ነው።

ይህ የተቃውሞ “ለምን” ነው? ማለትም ንጹሕ የሆነ ሰው ኢፍትሓዊ በሆነ ሥቃይ ላይ የሚያሰማው ጩኸት ነው? መሠረታዊ ጕዳይ  በርግጥ ትክክል ነው። እርሱ ንጹሕ ነው። ነገር ግን ኀጢአትን የሚሸከም መሆኑንና ለብዙዎች ቤዛ ሆኖ መሞት እንዳለበት በማወቅ ሕይወቱን ሙሉ ኖሯል። ታዲያ አሁን ያንን ረሳው?

ወይስ እዚህ ለምን እንዳለ እንዳልተገነዘበ የሚያሳይ ያለመረዳት “ለምን” ነው? ዘላለማዊውን ኪዳን ረሳው? ምናልባት። አእምሮው እንደ ሰው በሁሉም እውነታዎች ላይ በአንድ ጊዜ ሊያተኲር አይችልም፤ እናም ለጊዜው ሥቃዩ፣ መለኮታዊው ቊጣና የዘላለም ጥፋት ፍርሀት (መስቀሉ የእግዚአብሔር የመጨረሻ ቃል በመሆኑ) ሐሳቦቹን ሁሉ ተቈጣጥረዋቸዋል።

ወይስ ፈጽሞ ያልጠበቀውን አስፈሪነት ሲጋፈጥ የሚመጣ የመገረም “ለምን” ነው? ከጅምሩ አሠቃቂ ሞት እንደሚሞት ያውቅ ነበር (ማርቆስ 10፥33-34)፤ በጌቴሴማኔም ፊት ለፊት ተመልክቶት ተንቀጥቅጦ ነበር። አሁን ግን በመላው መራራነቱ እየቀመሰው ነው፤ እውነታውም ከጠበቀው በእጅጉ የከፋ ነው።

ከዚህ በፊት በርሱና በአባቱ መካከል ምንም ነገር ገብቶ አያውቅም፤ አሁን ግን የዓለም ሁሉ ኀጢአት በመካከላቸው ገብቷል። እርሱም በዚህ አስፈሪ በሆነ የርግማን ዐውሎ ነፋስ ውስጥ ተይዟል። “አባ” እዚያ የለም ማለት አይደለም፤ ነገር ግን እዚያ ያለው፣ ምንም ነገርን በቸልታ ሊያልፍ የማይችልና የገዛ ልጁን እንኳ ሊራራለት የማይችል የመላው ምድር ፈራጅ ሆኖ ነው (ሮሜ 8፥32)።

ጽዋዋ ተጠጣች

አሁን የኢየሱስ አእምሮ ከዚህ በላይ መከራን መቀበል የማይችልበት ገደብ ላይ ደርሷል። እኛ በታሪክ መድረክ ላይ ተቀምጠን፣ ውጤቱን በርግጠኛነት እናውቃለን። በሰብአዊ ተፈጥሮው የገሃነምን ቊጣ እየተሠቃየ ያለው እርሱ ግን አያውቅም። ከዚህ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ ማንም ቆሞበት በማያውቅ ስፍራ ላይ ቆሟል፤ በአንድ ውስን ስፍራና የጊዜ ቅጽበት፣ ኀጢአት የሚገባውን ሁሉ ቅጣት ማለትም ሙሉ ለሙሉ ርግማኑ በርሱ ላይ ሆነ።

ነገር ግን በድንገት፣ ተፈጸመ። መሥዋዕቱ ተጠናቀቀ፤ መጋረጃው ተቀደደ፤ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደውም መንገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተከፈተ። አሁን ደግሞ የኢየሱስ ደስታ በሌላ መዝሙር ይኸውም በመዝሙር 31፥5 ቃላት መግለጫውን አገኘ። በዋናው ጽሑፍ ውስጥ “አባ” የሚለውን ቃል አልያዘም ነበር፤ ኢየሱስ ግን አስገባው፣ “አባት ሆይ፤ መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ” አለ (ሉቃስ 23፥46)።

በሁለቱ ጩኸቶች መካከል ምን እንደ ገባ የምናውቅበት ምንም መንገድ የለንም። የምናውቀው ጽዋዋ መጠጣቷንና ርግማኑ ማለቁን እንዲሁም አሁን አብ ለተወዳጅ ልጁ ነፍስ እጆቹን በኲራት መዘርጋቱን ብቻ ነው።