የስቅለት ዐርብ ጠዋት
ዕለተ ዐርብ ሚያዝያ 3፣ 33 ዓ.ም. ነው። አብዛኛው የሰው ልጅ ስለዚህ ጕዳይ ምንም ፍንጭ የለውም። ይሁን እንጂ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ ጨለማን የተሞላ ቀን ነው። በሮም፣ ጢባርዮስ ግዛቱን የማስተዳደር ከባድ ሥራውን እያከናወነ ነው። በመላው ዓለም፣ ሕፃናት ይወለዳሉ፣ ሰዎች ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፤ ያገባሉ፣ ይጋባሉ፤ በገበያ ይነግዳሉ፤ የንግድ መርከቦችን ያንቀሳቅሳሉ፤ እንዲሁም ጦርነቶችን ይዋጋሉ። ልጆች ይጫወታሉ፤ አረጋውያን ስለ ሌሎች ሰዎች ያወራሉ፤ ወጣቶች በፍትወት ይመኛሉ፣ ሰዎችም ይሞታሉ።
ነገር ግን በዛሬው ዕለት፣ አንድ ሞት፣ አንድ እጅግ ጭካኔን የተሞላበትና ዘግናኝ የሆነ ሞት፣ ከሰው ልጆች ሞት ሁሉ የከፋውና ከሁሉ የተሻለው ሞት በሰው ልጅ ታሪክ ሸራ ላይ በጥቁር ቀለም ይመዘገባል። በኢየሩሳሌም፣ የሁሉ ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር ወልድ የሞት ቅጣት ይፈጸምበታል (ዮሐንስ 1፥3)።
የአትክልት ስፍራው
የአይሁዳውያን ቀን የሚጀምረው በምሽት ነው፤ ሰዓቱ ስለ ደረሰና የጨለማ ሥልጣን ስለ መጣ ከዚህ ይበልጥ ተስማሚ ጊዜ አልነበረም (ሉቃስ 22፥53)። ኢየሱስ በጌቴሴማኔ ውስጥ ነበር፤ በዚያም በብርቱ ጩኸትና በእንባ ሲጸልይ ቈይቶ ፈቃዱ በሚፈጸምለት አባቱ ተሰምቷል (ዕብራውያን 5፥7)። ኢየሱስ ጫጫታዎችን ሰምቶ ቀና ብሎ አየ። ችቦዎችና ሹክሹክታዎች የአሳሪዎቹን መምጣት ጠቈሙ።
ኢየሱስ ወንድማቸው ይሁዳ መምህሩን በመሳም አሳልፎ ሲሰጥ በማየታቸው የደነገጡትን የሚያንቀላፉ ወዳጆቹን ቀሰቀሳቸው። ወታደሮችና አገልጋዮች ኢየሱስን ከበቡት። ጴጥሮስ በቊጣ ተሞልቶ ሰይፉን መዘዘና ከኢየሱስ አጠገብ በነበረው ሰው ላይ ሰደደው። ማልኮስ አፈገፈገ፣ ነገር ግን በቂ አልነበረም። ከባድ ሕመም ተሰማው፤ ጆሮውም ከነበረበት ስፍራ ላይ ደም ፈሰሰ። በዙሪያው የነበሩ ሰዎች ቢያወሩም፣ ማልኮስ ግን የሚሰማው በሁለት እጆቹ ይዞት የነበረው የቈሰለው ጆሮው ከባድ ሕመም ነበር። አንድ እጅ፣ እጆቹን ሲነካ ተሰማው፣ ሕመሙም ጠፋ። በእጆቹ ሥር ጆሮው ነበር። ደንግጦ፣ እየተወሰደ ያለውን ኢየሱስን ተመለከተ። ደቀ መዛሙርቱ ተበታትነዋል። ማልኮስ በደም ወደ ተጨማለቁት እጆቹ አቀረቀረ።
ሸንጎው
ኢየሱስ ተጐትቶ የቀድሞው ሊቀ ካህናት ወደ ነበረው ወደ ሐና ቤት ተወሰደ፤ እርሱም ስለ ትምህርቱ ጠየቀው። ይህ መደበኛ ያልሆነ ምርመራ፥ እርሱን አደናግሮና ሳይዘጋጅ በወጥመድ ለመጣል ታስቦ የተደረገ መሆኑን ኢየሱስ ያውቃል። ኢየሱስ አልተደናገረም፤ አልተታለለምም፤ ለዚህ ተንኰለኛ መሪ ምንም ዕድል ፈንታ አልሰጠውም። ከዚህ ይልቅ ሐናን ወደ ሰሚዎቹ መለሰው፤ በዚህም ምክንያት ክብር ነስተሃል ተብሎ በአንድ የአይሁድ አገልጋይ በጥፊ ተመታ። የተበሳጨው ሐና፣ ኢየሱስን አማቹ ወደ ሆነው ሊቀ ካህናት ወደ ቀያፋ ላከው።
በቀያፋ ቤት ችሎቱ በፍጥነት ተጀመረ። ማለዳው በፍጥነት ይመጣል። ሸንጎው በጠዋት ከባድ ውሳኔ ማስተላለፍ አለበት። እንቅልፍ ያጡት የሸንጎ አባላት እየገቡ ምርመራው ቀጥሏል።
ችሎቱ በችኰላ የተሰበሰበ በመሆኑ ምስክሮቹ በሚገባ አልተመረመሩም ነበር። ምስክርነታቸውም አልተጣጣመም። የሸንጎው አባላት ግራ የተጋቡ ይመስሉ ነበር። ኢየሱስ ግን እንደ በግ ዝም አለ። የተበሳጨውና ትዕግሥት ያጣው ቀያፋ ጕዳዩን አቋርጦ፣ “በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ ንገረን” አለው (ማቴዎስ 26፥63)።
ሰዓቱ ደርሷል። በአባቱ ስም እንዲመልስ የተጠየቀው ኢየሱስ፣ ሊሸከመው የመጣውን መከራ የሚያትመውን ቃል ተናገረ (ዮሐንስ 12፥27)፣ “አንተው ራስህ ብለኸዋል፤ ነገር ግን ለሁላችሁም ልንገራችሁ፤ ወደ ፊት የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” (ማቴዎስ 26፥64)።
ሕግን በመጣስ (ዘሌዋውያን 21፥10) በተደረገ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ድራማ፣ ቀያፋ የሐሰት ቊጣውን በማሳየትና እርሱን ለመክሰስ በኢየሱስ ስድብ ያገኘውን ደስታ ለመደበቅ ሲል ልብሱን ቀደደ። “ከእንግዲህ ሌላ ምስክር ምን ያስፈልገናል? ራሳችን ከገዛ አንደበቱ ሰምተናልና” በማለት ችሎቱን ደመደመ (ሉቃስ 22፥71)።
ከኢየሩሳሌም ምሥራቃዊ ሸንተረር ላይ ፀሓይ ስትወጣ፣ ይሁዳ በራሱ ቀበቶ ታንቆ ተንጠለጠለ፤ ጴጥሮስ በውድቀቱ ሐዘን ተሠቃየ። የኢየሱስ ፊት ደግሞ፣ ሌሊት በነበረው የቤተ መቅደሱ ፖሊሶች ፌዝ በደረቀ ደምና ምራቅ ተበላሸ። የሸንጎው ፍርድ፣ እግዚአብሔርን በመስደብ ጥፋተኛ ነው የሚል ነበር። ቅጣታቸውም ሞት ነበር። ነገር ግን ይህን ቅጣት በራሳቸው ማከናወን አይችሉም። ሮም የሞት ቅጣትን አሳልፋ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረችም።
ገዢው
ገና ጎህ ሳይቀድ፣ ሸንጎው ባደረገው ያልተጠበቀ ጣልቃ ገብነት፣ የጲላጦስ ስሜት አስቀድሞ ተበላሽቶ የነበረ ሲሆን፣ ሁኔታውን ሲረዳ ይበልጥ ተበሳጨ። የገሊላውን ነቢይ እንዲገድለው ፈልገው ነበር። ደመ ነፍሱ አንድ የተሳሳተ ነገር እንዳለ ይነግረው ነበር። ኢየሱስን መርምሮ ለሸንጎው፥ “እኔ በዚህ ሰው ላይ ምንም ወንጀል አላገኘሁበትም” አላቸው (ሉቃስ 23፥4)።
ጲላጦስና ሸንጎው የፖለቲካ ዳማ ጨዋታ ጀመሩ፤ ሁለቱም ወገኖች ንጉሥ ሳይሆኑ ተራ ወታደር መሆናቸውን አላወቁም ነበር።
ጲላጦስ የመጀመሪያውን ርምጃ ወሰደ። ኢየሱስ የገሊላ ሰው እንደ መሆኑ በርሱ ላይ የመፍረድ ሥልጣን ያለው ሄሮድስ አንቲጳስ ነው። ስለዚህም፣ ሄሮድስ ይፍረድ። ሄሮድስ በመጀመሪያ ተአምር ለማየት በማሰብ ኢየሱስን በደስታ ተቀበለው። ነገር ግን ኢየሱስ እርሱን ለማዝናናትም ሆነ መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። ቅር የተሰኘው አንቲጳስ፥ ኢየሱስን ወደ ጲላጦስ በመመለስ የጲላጦስን ርምጃ አከሸፈ።
ጲላጦስ ሌላ ርምጃ ወሰደ። ኢየሱስን የዓመቱ በፋሲካ የሚፈታ እስረኛ አድርጎ ሊፈታው አቀረበ። ሸንጎው ግን “የለም፤ እርሱን አይደለም! በርባንን ፍታልን!” ብለው ጮኹ (ዮሐንስ 18፥40)። ጲላጦስ ተገረመ። ሸንጎው ከዚህ ምስኪን ነቢይ ይልቅ ሌባና ነፍሰ ገዳይ እንዴት መረጠ?
ጲላጦስ ሌላ ሙከራ አደረገ። የሸንጎውን የደም ጥማት ለማርገብ በማሰብ ኢየሱስን በከፍተኛ ሁኔታ አሳስሮ አስገረፈው፤ አዋረደውም። ሆኖም የሸንጎው አባላት ኢየሱስ፣ “ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ስላደረገ” ሊሰቀል ይገባዋል ብለው አጥብቀው ሲጠይቁ ርምጃው በድጋሚ ከሸፈ (ዮሐንስ 19፥7)። የጲላጦስ ፍርሀት ጨመረ። ኢየሱስ መለኮት መሆኑን መናገሩ ሮምን ሥጋት ውስጥ ሊጥል ይችላል። ከዚህም የከፋው፣ ይህ እውነት ሊሆን መቻሉ ነው። የሮማውያን አማልክት በሰው አምሳል ሊገለጡ እንደሚችሉ ይታመናል። ለኢየሱስ ያቀረበው ተጨማሪ ጥያቄ ይበልጥ አሸበረው።
አንድ የመጨረሻ ርምጃ። ጲላጦስ ሸንጎውን አሳምኖ ኢየሱስን ለመፍታት ሞከረ። አንድ የመጨረሻ ክልከላና ወጥመድ። “ይህን ሰው ብትፈታው የቄሳር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ የቄሳር ተቃዋሚ ነው” (ዮሐንስ 19፥12)። ሸንጎው ጲላጦስን በሚፈልጉበት አጣብቂኝ ውስጥ ከተቱት።
ነገር ግን ሥሉስ አሐዱ የሆነው እግዚአብሔር ሸንጎውን፣ ጲላጦስንና ሰይጣንን ለዕቅዱ በሚፈልገው ቦታ ላይ አስቀምጧቸዋል። ከላይ ካልተሰጣቸው በቀር በወልድ ላይ ምንም ሥልጣን አልነበራቸውም (ዮሐንስ 19፥11)። የወደቁ አይሁዳውያን፣ አሕዛብና መንፈሳዊ ኀይላት ለጥፋተኛው ሕይወትን ሊሰጥ የሚችለውን ብቸኛው የንጹሕን ሰው ሞት ለማስፈጸም ሳያውቁት ተባበሩ።
መስቀሉ
ኢየሱስ እጅግ ተደብድቦና ብዙ ደም እየፈሰሰው ከገዢው ግቢ ሲወጣ ጠዋቱ እያለፈ ነበር። ሮማውያን ወታደሮች ሰዎችን በሚያሠቃዩበት የፈጠራ ጭካኔያቸው እጅግ አረመኔዎች ነበሩ። የኢየሱስ ራስ በእሾህ ተወግቷል፤ ጀርባውም የቈሰለና በደም የተሞላ ነበር። ቀራንዮ በአትክልት ስፍራው በር በኩል ግማሽ ኪሎ ሜትር ብቻ የሚርቅ ቢሆንም፣ ኢየሱስ 18 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን የመስቀሉን ዕንጨት ለመሸከም ዐቅም አልነበረውም። የቀሬናው ስምዖን ከሕዝቡ መካከል ተገድዶ ተጠራ።
ከሃያ ዐምስት ደቂቃዎች በኋላ፣ ኢየሱስ የሰው ልጅ ከፈጠራቸው በጣም ዘግናኝ ከሆኑት የሥቃይ መሣሪያዎች በአንዱ ላይ ተሰቅሎ እጅግ አሠቃቂ ሥቃይ ውስጥ ነበር። በእጆቹ አንጓዎች ላይ ምስማሮች ተመትተው ነበር (ይህንም ማወቅ የቻልነው ቶማስ ከጥቂት ቀናት በኋላ በሚገልጸው ጥርጣሬ ምክንያት ብቻ ነው፤ ዮሐንስ 20፥25 ይመልከቱ)። ከኢየሱስ በላይ የተለጠፈው ጽሑፍ በግሪክ፣ በላቲንና በአራማይክ ቋንቋዎች የርሱን ማንነት ያውጃል፤ የአይሁድ ንጉሥ።
ንጉሡ በሁለቱም ጐኖች በወንበዴዎች ተከብቧል፤ በዙሪያውም የሚመለከቱና የሚያፌዙ ሰዎች አሉ። አንዳንዶቹ፣ “በእግዚአብሔር የተመረጠው ክርስቶስ እርሱ ከሆነ፣ እስኪ ራሱን ያድን” እያሉ ይጮኻሉ (ሉቃስ 23፥35)። ሟች ከሆኑት ወንበዴዎች አንዱ በፌዙ ተባበረ። ንጉሡ ራሱን ካዳነ፣ ብቸኛው የድነት ተስፋቸው እንደሚጠፋ አልተረዱም ነበር። ኢየሱስ ይቅር እንዲላቸው አባቱን ጠየቀ። ሌላኛው የተሰቀለው ወንበዴ ግን በአጠገቡ ባለው የተጐዳ ሰው ውስጥ መሲሑን ተመለከተ፤ ደግሞም መሲሑን እንዲያስበው ጠየቀው። የኢየሱስ ጸሎት መመለስ ጀምሯል። በመቶ ሚሊዮኖች የሚቈጠሩም ይከተሉታል።
ጊዜው ከሰዓት በኋላ ቢሆንም፣ የወደቀው አስፈሪ ጨለማ ሁሉንም ሰው ጭንቀት ውስጥ ጥሎታል። ለኢየሱስ ግን ጨለማው ከዚህ በፊት አይቶት የማያውቀው አስፈሪ ነገር ነበር። ከምስማሮቹ፣ ከእሾሁና ከግርፋቱ ይልቅ በአትክልቱ ስፍራ ደም እንዲያልበው ያደረገው ይህ ነበር። የአብ ቊጣ በሙሉ ኀይሉ እየመታው ነው። በዚያች ቅጽበት እርሱ የተባረከ ሳይሆን የተረገመ ሆኗል (ገላትያ 3፥13)። እርሱ ኀጢአት ሆኗል (2 ቆሮንቶስ 5፥21)። ከአባቱና ከሰዎች ሁሉ ተለይቶ እጅግ በሚያስፈራ ብቸኝነት ውስጥ፣ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ?” እያለ ጮኸ፤ ትርጕሙም “አምላኬ፤ አምላኬ፤ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው (ማቴዎስ 27፥46፤ መዝሙር 22፥1)። ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር (ዮሐንስ 15፥13)፣ ትሕትና (ፊልጵስዩስ 2፥8)፣ ወይም መታዘዝ (ዕብራውያን 5፥8) ታይቶ አያውቅም፤ ወደ ፊትም አይታይም።
ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ገደማ፣ ኢየሱስ በደከመ ድምፅ የሚጠጣ እንዲሰጡት ጠየቀ። በፍቅር፣ የአባቱን የቊጣ ጽዋ እስከ መጨረሻው ጠጥቶታል። የእኛን ርግማን ሙሉ በሙሉ ተሸክሟል። የሚከፈል ምንም ዕዳ አልቀረም፤ ሊሰጥ የሚገባ የቀረ አንዳች ነገር አልነበረም። ወይኑ አፉን በማርጠብ አንድ የመጨረሻ ቃል እንዲናገር አስቻለው፤ “ተፈጸመ” (ዮሐንስ 19፥30)። እግዚአብሔር ወልድም ሞተ።
ይህ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከሁሉ የከፋውና ከሁሉ የተሻለው ሞት ነው። ምክንያቱም በዚህ ዕንጨት ላይ ኀጢአታችንን በሥጋው ተሸክሟል (1 ጴጥሮስ 2፥24)፤ “ወደ እግዚአብሔር ያቀርባችሁ ዘንድ ጻድቅ የሆነው እርሱ ስለ ዐመፀኞች ሞተ” (1 ጴጥሮስ 3፥18)። አሁን ደግሞ ተፈጽሟል።
መቃብሩ
በዚህ እጅግ ጨለማ በሆነ ቀን ውስጥ የሚታየው አስገራሚው ምጸት፣ የክርስቶስን አስከሬን ለመቅበር የጠየቁት ሰዎች የቤተ ሰብ አባላት ወይም ደቀ መዛሙርት አለመሆናቸው ነው። ይልቁንም እነርሱ የሸንጎው አባላት ነበሩ፤ የአርማትያሱ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ። ይህ በዚህ የቤዛነት ታሪክ ውስጥ የተሸመነ ሌላኛው ያልተጠበቀ የጸጋ ክር ነው። የኢየሱስን አስከሬን በፍጥነት በበፍታ ከፍነው በአቅራቢያው ባለ መቃብር ውስጥ አኖሩት። ምሽት እየመጣ ስለ ነበር፣ አካሉን በሽቱ ሙሉ በሙሉ በመቀባት ለቀብር ለማዘጋጀት ጊዜ አልነበራቸውም።
መግደላዊት ማርያምና የዮሳ እናት ማርያም ዐብረዋቸው ነበሩ፤ የመቃብሩንም ስፍራ በጥንቃቄ ተመለከቱ። ከሰንበት በኋላ፣ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን፣ ሁሉ ነገር መፈጸሙን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ሽቱ ይዘው ለመመለስ ዐቅደዋል።