5 የብልጽግና ወንጌል ስሕተቶች

ቻርለስ ስፐርጅን፣ ከአንድ ክፍለ ዘመን ገደማ በፊት፣ ትልቅ ጉባኤ ለነበረው አጥቢያው ሲናገር፦

ለማንኛውም ክርስቲያን ቢሆን፣ ሀብት የማከማቸትን ግብ ይዞ መኖር ጸረ ክርስትና እና ርኩስ ነው ብዬ አምናለሁ። “የምንችለውን ያህል ገንዘብ ለማግኘት፣ የምንችለውን ሁሉ ጥረት ልናደርግ አይገባንምን?” ትል ይሆናል። እንዲህ ማድረግ ትችላለህ። አለመስማማት አልችልም! እንዲህ በማድረግ፣ ለእግዚአብሔር አገልግሎት ልታውሉት ትችላላችሁ። ነገር ግን እኔ ያልኩት ሀብት የማከማቸት ግብ ይዞ መኖር፣ ፀረ ክርስትና ነው። [1]

ይሁን እንጂ፣ ባለፉት ዓመታት በዓለም ውስጥ ባሉ ትልልቅ አብያተ ክርስቲያናት የሚሰበከው መልእክት ተቀይሯል። በአሁኑ ጊዜ በርግጥ አብዛኞቹ ጉባኤዎች አዲስ ወንጌል እየተማሩ ነው። ይህ ወንጌል ብዙ ስሞች ይሰጠዋል፤ ለምሳሌ፦ “ጥራው! የእኔ ነው በለው!” ወንጌል፣ “ንጠቅና ያዘው” ወንጌል፣ “የጤና እና ሀብት” ወንጌል፣ “የብልጽግና ወንጌል” እና “የአዎንታዊ አዋጅ አስተምህሮ” ይባላል።

በየትኛውም ስም ቢጠራ የዚህ አዲስ ወንጌል ፍሬ ነገር ግልጽ ነው። በቀላል አነጋገር፣ ይህ ራስ ተኮር “የብልጽግና ወንጌል” የሚያስተምረው፣ አማኞች በአካል ጤናማ፣ በቁስ ባለጠጋ እና ሁሌ ደስተኛ እንዲሆኑ እግዚአብሔር መፈለጉን ነው። የብልጽግና ወንጌል ታዋቂ ተናጋሪዎች ከሆኑት አንዱ የሆነው ሮበርት ቲልተንን ቃል አድምጡ፦ “ሁሉም እንዲበለጽጉ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ አምናለሁ። ይህም በቃሉ ውስጥ ስላየሁት እንጂ ለሌላ ሰው በኅይል ስለሠራ አይደለም። ዓይኖቼን በሰዎች ላይ አላደርግም፤ ነገር ግን ሀብት ለማግኘት ኃይልን በሚሰጠኝ አምላክ ላይ እንጂ።”[2] የብልጽግና ወንጌል አስተማሪዎች ተከታዮቻቸውን በቁሳዊ ሀብት እንዲበለጽጉ ወደ እግዚአብሔር በይገባኛል መንፈስ እንዲጸልዩ እና እንዲጠይቁ ያበረታታሉ።

የብልጽግና ወንጌል አምስት ሥነ መለኮታዊ ስሕተቶች

በቅርቡ፣ እኔና ራስል ዉድብሪጅ የተባለ ሰው የብልጽግና ወንጌል አስተማሪዎችን አቋም ለመመርመር ጤና፣ ሀብት እና ደስታ የሚል መጽሐፍ ጻፍን።[3] የመጽሐፋችን ሙሉ ሐሳብ ለዚህ አምድ በጣም ሰፊ ቢሆንም፣ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በመጽሐፋችን ውስጥ የጠቀስናቸውን አምስት አስተምህሮዎችን ለመከለስ እፈልጋለሁ። ይህም ማለት ስለ የብልጽግና ወንጌል ደጋፊዎች የሚሳሳቱባቸውን አስተምህሮዎች ይመለከታል። መሠረት በሆኑ አስተምህሮዎች በተመለከተ እነዚህን ስሕተቶች በማስተዋል፣ የዚህ ጽሑፍ አንባቢዎች የብልጽግና ወንጌልን አደጋዎች በግልጽ እንደሚመለከቱ ተስፋ አደርጋለሁ። የምዳስሰውም አስተምህሮዎች የአብርሃም ቃል ኪዳን፣ ስርየት፣ መስጠት፣ እምነት እና ጸሎት ናቸው።

1. የአብርሃም ኪዳን ቁሳዊ በረከት የማግኛ መንገድ ነው።

የምንመረምረው የመጀመሪያው ስሕተት፣ የብልጽግና ወንጌል የአብርሃምን ኪዳን ለቁሳዊ በረከት ማግኛ መብት እና መጠቀሚያ መንገድ አድርጎ መመልከቱ ነው።

የአብርሃም ኪዳን (ዘፍ 12፣ 15፣ 17፣ 22) ከብልጽግና ወንጌል ሥነ መለኮታዊ መሠረቶች መካከል አንዱ ነው። የብልጽግና አስተማሪዎች ቅዱሳት መጻሕፍት በአብዛኛው የአብርሃም ቃል ኪዳን ፍጻሜ መሆናቸውን መገንዘባቸው ጥሩ ሆኖ ሳለ፣ በዚህ ኪዳን ላይ ቀጥተኛውን አስተምህሮ አለመያዛቸው ግን ስሕተት ነው። ስለ ኪዳኑ ታሪካዊ ዳራ የተሳሳተ አመለካከት አላቸው፤ በይበልጥ ደግሞ፣ የኪዳኑን አፈጻጸም በተመለከተ የተሳሳተ ፍቺ አላቸው።

ኤድዋርድ ፑሰን በአብርሃም ኪዳን አተገባበር ላይ ያለውን የብልጽግና አመለካከት በሚገባ ገልጾታል፦ “ክርስቲያኖች የአብርሃም መንፈሳዊ ልጆች እና የእምነት በረከቶች ወራሾች ናቸው . . . ይህ የአብርሃም ወራሽነት በዋነኛነት ከቁሳዊ በረከቶች አንፃር የሚብራራ ነው”[4] ይላል። በሌላ አነጋገር፣ የብልጽግና ወንጌል እንደሚያስተምረው ከሆነ የአብርሃም ኪዳን ዋና ዓላማ፣ እግዚአብሔር አብርሃምን በቁሳዊ ነገሮች እንዲባርክ ነው። ስለሆነም አማኞች አሁን የአብርሃም መንፈሳዊ ልጆች ስለሆኑ፣ እነዚህን የሀብት በረከቶች ወርሰዋል።

የብልጽግና አስተማሪው ኬኔት ኮፕላንድ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የእግዚአብሔር ኪዳን ስለተመሠረተ እና ብልጽግና የዚህ ቃል ኪዳን መግቦት ስለሆነ፣ ብልጽግና አሁን ያንተ መሆኑን መገንዘብ አለብህ!”[5]

ይህን ለመደገፍ የብልጽግና አስተማሪዎች ገላትያ 3፥14ን “በክርስቶስ ኢየሱስ በአሕዛብ ላይ ሊመጡ የሚችሉትን የአብርሃም በረከቶች” ይጠቅሳሉ። የሚገርመው ግን ገላትያ 3፥14ን ሲጠቅሱ የብልጽግና አስተማሪዎች “…የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል” የሚለውን የጥቅሱን ሁለተኛ አጋማሽ ችላ ይሉታል። በዚህ ጥቅስ ጳውሎስ የገላትያ ሰዎችን የሚያሳስባቸው ስለ ድነት መንፈሳዊ በረከት እንጂ ስለ ቁሳዊ በረከት አይደለም።

2. የኢየሱስ የስርየት ሥራ፣ የቁሳዊ ድህነትን “ኃጢአት” ያካትታል።

ሁለተኛው የብልጽግና ወንጌል ሥነ መለኮታዊ ስሕተት፣ ስለ ስርየት ያለው የተሳሳተ አመለካከቱ ነው።

የሥነ መለኮት ምሑር ኬን ሳርልስ “የብልጽግና ወንጌል በስርየት ሥራ ውስጥ አካላዊ ፈውስም ሆነ የገንዘብ ብልጽግና እንደተዘጋጀ ይናገራል” በማለት ጽፈዋል።[6] ይህ ትክክለኛ ምልከታ ይመስላል፤ ኬኔት ኮፕላንድ “የክርስትና ሕይወት መሠረታዊ መርህ እግዚአብሔር ኃጢአታችንን፣ ደዌያችንን፣ በሽታዎቻችንን፣ ሀዘናችንን እና ለቅሶአችንን፣ እና ድህነታችንን በቀራንዮ በኢየሱስ ላይ እንዳስቀመጠው ማወቅ ነው” ይላል።[7] ይህ የስርየትን አድማስ በትክክል አለመረዳት፣ የብልጽግና ወንጌል ደጋፊዎች ከሚያደርጓቸው ሁለት ስሕተቶች የመነጨ ነው።

በመጀመሪያ፣ የብልጽግና ሥነ መለኮት ተከታዮች ስለ ክርስቶስ ሕይወት መሠረታዊ የሆነ የተሳሳተ ግንዛቤ አላቸው። ለምሳሌ፣ አስተማሪው ጆን አቫንዚኒ፣ “ኢየሱስ ጥሩ ቤት፣ ትልቅ ቤት ነበረው፣”[8]  “ኢየሱስ ብዙ ገንዘብ ያስተዳድር ነበር”[9] እንዲያውም “የዲዛይነር ልብስ ነበር የሚለብሰው”[10] በማለት ተናግሯል። ስለ ክርስቶስ ሕይወት እንዲህ ያለው የተዛባ አመለካከት ስለ ክርስቶስ ሞት ምን ያህል የተሳሳተ ግንዛቤ ሊኖር እንደሚችል በቀላሉ ያመለክታል።

ሁለተኛው ስለ ስርየት ሥራ ወደ ተሳሳተ አመለካከት የሚያመራው የአተረጓጎም ስሕተት በ2ኛ ቆሮንቶስ 8፥9 ላይ ይገኛል። “የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ።” ይህን ጥቅስ ጥልቀት በሌለው መንገድ ከተነበበ አንድ ሰው ጳውሎስ ስለ ቁሳዊ ሀብት መጨመር እያስተማረ ልመስለው ይችላል። በምዕራፉ ዐውድ ውስጥ ግን ጳውሎስ በቀጥታ የሚያስተምረው ተቃራኒውን ሐሳብ እንደሆነ ማየት ይቻላል። በርግጥም፣ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ክርስቶስ በማስተሰረያ ሥራው በኩል ብዙ ስላደረገላቸው፣ ለወንጌል አገልግሎት ሀብታቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ እያስተማራቸው ነበር። ለዚህም ነው ከአምስት አጫጭር ቁጥሮች በኋላ ጳውሎስ የቆሮንቶስ ሰዎች ሀብታቸውን ለተቸገሩ ወንድሞቻቸው እንዲሰጡ ያሳሰባቸው፣ “የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ።” (2ኛ ቆሮንቶስ 8፥14)

3. ክርስቲያኖች የሚሰጡት ቁሳዊ ትርፍ እና ካሳ ከእግዚአብሔር ለማግኘት ነው።

ሦስተኛው የብልጽግና ወንጌል ስሕተት፣ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ቁሳዊ ካሳ ለማግኘት መስጠት አለባቸው ማለቱ ነው። የብልጽግና አስተማሪዎች በጣም አስደናቂ ከሆኑት ባሕሪያት አንዱ ለመስጠት ያላቸው ቁርጠኝት ነው። የብልጽግና ወንጌል ተከታዮች በልግስና እንዲሰጡ፣ “እውነተኛ ብልጽግና የእግዚአብሔርን ኃይል በማንኛውም የሕይወት ዘርፍ የሰውን ልጅ ፍላጎት ለማሟላት ማስቻል ነው”[11] እና “እኛ የተጠራነው በዓለም ሁሉ ለወንጌል ሥራ የገንዘብ ድጋፍ ለመስጠት ነው” በሚሉ ቃላተ ያሸበረቁ ናቸው።[12] እነዚህ አባባሎች ሊመሰገኑ የተገባቸው ቢመስሉም፣ ይህ መስጠት ላይ ያለው ትኩረት ከቅን ልቦና ሳይሆን በሌላ ምክንያቶች ላይ የተመሠረተ ነው። ከዚህ የልግስና ትምህርት በስተጀርባ ያለውን አንቀሳቃሽ ኃይል የብልጽግና መምህር ሮበርት ቲልተን “የማካካሻ ሕግ” ሲል ይጠቅሰዋል። በዚህ ሕግ መሠረት፣ ከማርቆስ 10፥30 [13] ጋር ለማያያዝ እየሞከሩ፣ ክርስቲያኖች ለሌሎች በልግስና መስጠት ያለባቸው ምክንያት እግዚአብሔር በምላሹ ብዙ ስለሚሰጠን ነው ይላሉ። ይህ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደ ወለድ እየጭመረ ይሄዳል ማለት ነው።

ግሎሪያ ኮፕላንድ እንዳለችው፣ “10 ዶላር ስጥ እና 1,000 ዶላር ተቀበል፤ 1,000 ዶላር ስጥ እና 100,000 ዶላር ተቀበል… በአጭሩ፣ ማርቆስ 10፥30 አዋጭ ቁማር ነው።”[14] እንግዲያውስ የብልጽግና ወንጌል የመስጠት አስተምህሮ የተገነባው በተሳሳተ መነሣሣት ላይ እንደሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ምንም ተስፋ ሳታደርጉ ስጡ” (ሉቃስ 10፥35) ብሎ አስተማረ፤ የብልጽግና የሥነ መለኮት አስተማሪዎች ደግሞ ደቀ መዛሙርቶቻቸው ታላቅ ትርፍ ስለሚያገኙ እንዲሰጡ ያስተምራሉ።

4. እምነት ወደ ብልጽግና የሚመራ ከራ የሚመነጨ መንፈሳዊ ኃይል ነው።

አራተኛው የብልጽግና አስተምህሮ ስሕተት፣ እምነት ወደ ብልጽግና የሚመራ ኃይል ነው የሚለው ትምህርት ነው። በአንጻሩ ትክክለኛው የክርስትና እምነት በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ላይ መታመን ሲሆን፣ የብልጽግና አስተማሪዎች ግን ከዚህ የተለየ ትምህርትን ይሰጣሉ። ኬኔት ኮፕላንድ The Laws of Prosperity በተሰኘው መጽሐፋ “እምነት መንፈሳዊ ጉልበት፣ መንፈሳዊ ኃይል፣ መንፈሳዊ አቅም ነው። የመንፈስ ዓለም ሕግጋትን ተግባራዊ የሚያደርገው ይህ የእምነት ኅይል ነው። . . . በአግዚአብሄር ቃል ውስጥ የተገለጡ ብልጽግናን የሚቆጣጠሩ አንዳንድ ሕጎች አሉ። እምነት እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል”።[15] ይህ በግልጽ የተሳሳተ፣ መናፍቃዊ፣ የእምነት ግንዛቤ ነው።

እንደ ብልጽግና አስተምህሮ፣ እምነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ፣ እግዚአብሔርን ያማከለ የፈቃድ ተግባር አይደለም። ይልቁን በእግዚአብሔር ላይ ያነጣጠረ በሰው የተሠራ መንፈሳዊ ኃይል ነው። በርግጥም፣ በእግዚአብሔር ፊት ከመጽደቅ ይልቅ እምነትን እንደ ቁሳዊ ጥቅም ማግኛ ብቻ የሚመለከት ማንኛውም አስተምህሮ የተሳሳተ እና የተዛባ ተብሎ ሊፈረጅ ይገባል።

5. ጸሎት እግዚአብሔር ብልጽግናን እንዲሰጥ የሚያስገድድ መሣሪያ ነው።

በመጨረሻም፣ የብልጽግና ወንጌል እግዚአብሔር ብልጽግናን እንዲሰጥ ለማስገደድ ጸሎትን እንደ መሣሪያ አድርጎ ይቆጥረዋል። የብልጽግና ወንጌል ሰባኪዎች “ስላልጠየቅን የለንም” የሚለው ጥቅስ ላይ በአብዛኛው ያተኩራሉ (ያዕቆብ 4፥2)። የብልጽግና ወንጌል አስተማሪዎች፣ አማኞች በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ለግል ስኬት እንዲጸልዩ ያበረታታሉ። ክሪፍሎ ዶላር እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የምንጸልይውን እንደተቀበልን በማመን ስንጸልይ፣ እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንዲፈጸም ከማድረግ በቀር ሌላ ምርጫ የለውም . . . ይህ እንደ ክርስቲያን ውጤት ለማምጣት ቁልፍ ነው።” [16]

በርግጥ ለግል በረከት የሚቀርቡ ጸሎቶች በራሳቸው የተሳሳቱ አይደሉም፤ ነገር ግን የብልጽግና ወንጌል በሰው ላይ ያለው ከልክ ያለፈ ትኩረት፣ ጸሎት ለአማኞች አምላክ ፍላጎታቸውን እንዲሰጣቸው ለማስገደድ ሊጠቀሙበት ወደሚችሉት መሣሪያነት ይለውጠዋል።

በብልጽግና ወንጌል ውስጥ፣ እግዚአብሔር ሳይሆን ሰው የጸሎት ዋና ትኩረት ይሆናል። የሚገርመው፣ የብልጽግና ሰባኪዎች በጸሎት ላይ የያዕቆብን ትምህርት ሁለተኛ አጋማሽ ማለትም “ትለምናላችሁ፥ በምቾቶቻችሁም ትከፍሉ ዘንድ በክፉ ትለምናላችሁና አትቀበሉም” (ያዕቆብ 4፥3) የሚለውን ክፍል ችላ ይሉታል። እግዚአብሔር ስሙን የማያከብሩ የራስ ወዳድነት ጸሎቶችን አይመልስም።

በርግጥ ሁሉም ልመናዎቻችን በእግዚአብሔር ዘንድ መቅረብ አለባቸው (ፊልጵስዩስ 4፥6)፤ ነገር ግን የብልጽግና ወንጌል በሰዎች ፍላጎት ላይ ያተኮረ ከመሆኑ የተነሣ ሰዎች ለእግዚአብሔር ክብር የማያመጡ ራስ ወዳድ፣ ጥልቀት የሌላቸው፣ ግብዝ ጸሎቶችን እንዲጸልዩ ይመራቸዋል። በተጨማሪም፣ ይህ የብልጽግና ትምህርት ከእምነት አስተምህሮ ጋር ተዳምሮ ሰዎች የሚፈልጉትን ለማግኘት እግዚአብሔርን ለማዘዝ እንዲሞክሩ ሊያደርጋቸው ይችላል። ይህ ደግሞ ከንቱ ጥረት ነው። ይህ ዐይነቱ ልምምድ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲፈጸም ከሚጸለየው ጸሎት በጣም የራቀ ልምምድ ነው።

የውሸት ወንጌል

ከቅዱሳት መጻሕፍት አንፃር ስናየው፣ የብልጽግና ወንጌል በመሠረቱ ስሑት ነው። ከመሠረቱ የብልጽግና ወንጌል የተሳሳተ ወንጌል ነው፤ ምክንያቱም በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል ስላለው ግንኙነት ያለው ምልከታ ስሕተት ነው። በቀላል አነጋገር፣ የብልጽግና ወንጌል እውነት ከሆነ፣ ጸጋ ከንቱ ነው። እግዚአብሔር የማይጠቅም ነው። እናም ሰው የሁሉም ነገር መለኪያ ነው። ስለ አብርሃም ኪዳን፣ ስለ ስርየት፣ ስለ መስጠት፣ ስለ እምነት፣ ወይም ስለ ጸሎት ሲያወሩ የብልጽግና አስተማሪዎች በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ተራ የግብይት ግንኙነት ይለውጣሉ። ጄምስ አር ጎፍ እንደተናገረው፣ እግዚአብሔርን “የፍጥረቱን ፍላጎቶች እና መሻቶች ወደሚያሟላ የፍጥረቱ ታዛዥ አድርገው ያወርዳሉ።”[17] ይህ በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል ስላለው ግንኙነት የተዛባ እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ አመለካከት ነው።

በዴቪድ ጆንስ


[1] Tom Carter, ed., 2,200 Quotations from the Writings of Charles H. Spurgeon (Grand Rapids: Baker Book House, 1988), 216.

[2] Robert Tilton, God’s Word about Prosperity (Dallas, TX: Word of Faith Publications, 1983), 6.

[3] David W. Jones and Russell S. Woodbridge, Health, Wealth, and Happiness: Has the Prosperity Gospel Overshadowed the Gospel of Christ? (Grand Rapids: Kregel, 2010).

[4] Edward Pousson, Spreading the Flame (Grand Rapids: Zondervan, 1992), 158.

[5] Kenneth Copeland, The Laws of Prosperity (Fort Worth, TX: Kenneth Copeland Publications, 1974)51.

[6] Ken L. Sarles, “A Theological Evaluation of the Prosperity Gospel,” Bibliotheca Sacra 143 (Oct.-Dec. 1986): 339.

[7] Kenneth Copeland, The Troublemaker (Fort Worth, TX: Kenneth Copeland Publications, 1996), 6.

[8] John Avanzini, “Believer’s Voice of Victory,” program on TBN, 20 January 1991. Quoted in Hank Hanegraaff, Christianity in Crisis (Eugene, OR: Harvest House, 1993), 381.

[9] Idem, “Praise the Lord,” program on TBN, 15 September 1988. Quoted in Hanegraaff, 381.

[10] Avanzini, “Believer’s Voice of Victory.”

[11] Kenneth Copeland, The Laws of Prosperity, 26.

[12] Gloria Copeland, God’s Will is Prosperity (Fort Worth, TX: Kenneth Copeland Publications, 1973)45.

[13] Other verses that the “Law of Compensation” is based upon include Eccl. 11:1, 2 Cor. 9:6, and Gal. 6:7.

[14] Gloria Copeland, God’s Will, 54.

[15] Kenneth Copeland, The Laws of Prosperity, 19.

[16] Creflo Dollar, “Prayer: Your Path to Success,” March 2, 2009, http://www.creflodollarministries.org/BibleStudy/Articles.aspx?id=329 (accessed on October 30, 2013).

[17] James R. Goff, Jr., “The Faith That Claims,” Christianity Today, vol. 34, February 1990, 21.