ወንጌል ስብከት | ወንጌልን ለማሳመን ዒላማ አድርጎ ማስተማር

ወንጌልን እየሰበክን መሆኑን በምን እናውቃለን? መልሱ ስለ ወንጌል ስብከት ባለን መረዳት ላይ ይወሰናል። ወንጌል ስብከትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መንገድ ማብራራት፣ የወንጌል ስብከት ልምምዳችንን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ላይ ማድረግ እንድንችል ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወንጌል ስብከት ምን እንደሆነ በግልጽ ማስቀመጥ ካልቻልን፣ በርግጥ ትክክለኛ ወንጌል እየሰበክን ላይሆን ላይሆን ይችላል።

ለምሳሌ፦ አንዲት የቤት እመቤት ጓደኛዋን አግኝታት ቡና እየጠጡ የምታደርገው ወንጌል ስብከት ሆኖ፣ በአንፃሩ ግን አንድ እጅግ ጎበዝ ክርስቲያን አቃቤ እምነት፣ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰብስበው ላሉ ሺዎች የሚያደርገው ንግግር ወንጌል ስብከት ላይሆን ይችላል። ብዙዎቻችን የተሳሳተ የወንጌል ስብከት መረዳት ስላለን፣ ጥቂቶች ናቸው በእንደዚያ መንገድ የሚያዩት። እምነትን ማስጠበቅ እና መከላከል መልካም ነገር ሆኖ ሳለ፣ ወንጌልን ሳያብራሩ መተው ቀላል ነው፤ ያለ ወንጌል ደግሞ ወንጌል ስብከት ሚባል ነገር የለም።

እኔን ለብዙ ዓመታት ያገለገለኝን ማብራሪያ ከዚህ በታች አስቀምጣለሁ፦

ወንጌል መስበክ፣ ወንጌልን ለማሳመን ማስተማር ነው።

በጣም ቀላል አተረጓጎም ነው አይደል? ይመስለኛል ብዙ ሰዎች ከእንደዚህ ዐይነት ሥነ መለኮታዊ አገላለጽ ብዙ ነገር ይጠብቃሉ። ነገር ግን ይህ አፈታት ምንም እንኳ ትንሽ ቢሆንም፣ ምን ያህል ሰዎች ለተማጽኖ ምላሽ ሰጡ ከሚለው በጣም የተሻለ የወንጌል ማካፈል ልምምዶቻችንን የምንመዝንበት ሚዛን ያቀርባል።

ከላይ ያለውን ወንጌልን የማካፈል አተረጓጎም እንዲህ አድርጎ የበለጠ ማብራራት ይቻላል፦ ወንጌል መስበክ ወንጌልን (ወደ ድነት የሚመራ ከእግዚአብሔር የሆነ መልእክት) ለማሳመን (ማግባባት፣ መለወጥ) በማለም (ተስፋ ማድረግ፣ መፈለግ፣ ግብ ማድረግ) ማስተማር (ማብሰር፣ ማወጅ፣ መስበክ) ነው።

ማብራሪያው ወዲያውኑ የሚሆን ውጪያው ምላሽን እንደማያጠቃልል አስተውሉ። ወደ መድረክ መምጣት፣ እጅን ማንሳት፣ ጸሎት መጸለይ ወንጌል ስብከት እንደተካሄደ እንደሆነ ሊጠቁሙን ቢችሉም፣ እነዚህ ድርጊቶች ራሳቸው ግን ወንጌል ስብከት አይደሉም። ተጨማሪ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ፣ ከአራቱ ክፍሎች አንዱ ከጎደለ ምናልባት እያደረግን ያለነው ነገር ወንጌልን ስብከት ላይሆን ይችላል።

ቤተ ክርስቲያናት ወንጌል ማካፈል ያልሆኑ ነገሮችን ናቸው ብለው በማለታቸው ምክንያት ብዙ በሽታ በዓለም ዙሪያ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አለ።  ስለዚህም ወንጌል ምን እንደሆነ እና ከአንድ ግለሰብ “ወደ ክርስቶስ ዘወር ለማለት” ምን እንደሚጠበቅ በግልጽ ማስተማር አለብን።

ለማሳመን ማለም አለብን፤ ነገር ግን የማሳመን ጥረታችን ማምታታት ሊኖርበት አይገባም። ምንም እንኳ አጓጊ ቢሆንም ስለክርስትና ሕይወት ከባድ የሆኑ ነገሮችን አስቀርተን መሆን የለበትም፤ የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ከሰው ምላሽ ጋር ማምታታት የለብንም፤ በተለይም ደግሞ ስለሚያስከትላቸው ነገሮች መዋሸት የለበትም። ሰዎች የእውነት የተለወጡ ተከታዮች መሆናቸውን የሚያሳይ ነገር ሳይኖራቸው ክርስቲያኖች ብለን ከመጥራትም መጠንቀቅ አለብን።

ለውጤት ወይም የሆነ ”ስኬት” ለማግኘት በማሰብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆችን መሠዋት ልክ አይደለም። በዙሪያዬ ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ የወንጌል ስብከት ልምምዶችን አያለሁ። ወንጌሉ ለሰዎች ሳይደርስ ይቀርና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ቃላት፣ ዘልቆ የሚገባዉን የኅጢአት፣ ሞት እና ገሃነም ትርጉምን ይበርዙታል፤ ወይንም ከልብ እዉነትን የሚፈልጉትን ግራ ያጋባሉ።

የጤና እና የሀብት ተስፋዎች እንደ ድሆች፣ የተጎዱ እና የታመሙ ያሉትን ተጋላጭ የሆኑትን ያስታሉ። እናም ብዙ አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የትም ጋር የማይገኝ እጅግ ውድ፣ ምቾት የሞላበት እና ጥቅም አምጪ “ወንጌል” ያቀርባሉ። እንዲያውም ወንጌሉ ጳውሎስ በገላቲያ 1፥6–7 ላይ “የተለየ ወንጌል” በሚለው ተተክቷል። ቤተ ክርስቲያናት የሰዎችን ፍላጎት ለሟሟላት በሚል ትኩረታቸውን የእግዚአብሔርን ክብር ሕዝቦቹ በሚያደርጉት አምልኮ ውስጥ በማሳየት ፈንታ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች እንደሆኑ አድርገው እየተንቀሳቀሱ ነው።

ከዚህም የተነሣ በአብዛኛው ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚደረጉ አገልግሎቶች ከአምልኮ ይልቅ መዝናኛ ይሆናሉ። ኢየሱስ አሳታፊ ነበር፤ ነገር ግን መቼም አዝናኝ አልነበረም። በዚህ ዘመን ባለችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጠፍቶ ሊሆን የሚችል ታላቅ ልዩነት አለ። በፊት ከባድ የነበረው የሽያጭ ሥራ አሁን ቀለል ባለው ራስን መርዳት የሚባለውን በመሸጥ ተተክቷል።

እንዲህ ዐይነት ነገሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወንጌል ማካፈልን አቃልለው የሚያዩ ዓለማዊ ፈተናዎች ውጤት ናቸው።

ነገር ግን ለእንደዚህ ዐይነት ፈተናዎች መልስ አለ። በጳውሎስ ጊዜ ከነበረው የተለየ አይደለም። መፍትሔው እንደ መጽሐፍ ቅዱስ መርሆ የሆነ እና ወንጌልን ማዕከላዊ ያደረገ ወንጌል ስብከት በአእምሮአችንና ልባችን መካከል ማድረግ ነው። ወንጌልን በሐቀኝነት ማስተማርንና እውነተኛ መለወጥን ዓላማ ማድረግ መጠበቅ መማር ነው።

ስለዚህም በሚቀጥለው ጽሑፍ ውስጥ በጥንቃቄ “ማስተማር፣” “ወንጌል፣” “ማለም፣” እና “ማሳመን” የሚሉትን ክፍሎች አብራርተን እናያለን።

ጄ. ማክ ስቲልስ