ወንጌል-ተኮር ስብከት | ወንጌል ደምቆ የሚያበራበት ስብከት  

ዘ ፕሪንሰስ ብራይድ የሚለው ፊልም ከምንጊዜውም ምርጥ ፊልሞች ጎራ ይመደባል ብላቹ ታስባላቹ? ፊልሙ ላይ ያሉት ታዋቂዎቹ ንግግሮችን ካሰብን ከምርጥ ሥራዎች ጎራ ሊመደብ ይችላል። አንዱ ታዋቂ ንግግር ከፊልሙ ኢንዲጎ ሞንታያ በቪዚኒ “ሊታሰብ የማይችል!” በሚለው ንግግር ግራ ተጋብታ የተናገረቸው ነው። ፊልሙ ላይ ቪዚኒ ይህን ቃል ሲደጋግምው “ይህን ቃል በተደጋጋሚ ስትጠቀመው እሰማለሁ፤ ነገር ግን ቃላቶቹ አንተ ያሰብከው ትርጉም የላቸውም” ብላ ትመልስለታለች።

“ወንጌል-ተኮር” ወይም “የወንጌል ማዕከላዊነት” የሚሉትን ተደጋጋሚ የስብከት ገላጭ ዐረፍተ ነገሮችን ስሰማ ኢንዲጎ ሞንታና ያለችው ነገር አዕምሮዬ ላይ ይመጣብኛል። በተደጋጋሚ ቃላቶቹን ብንጠቀምም ቃላቶቹ ግን ያሰብነውን ትርጉም የያዙ አይመስለኝም። ስለዚህ እስቲ ይሄን ሐሳብ አብረን ለመረዳት እንሞክር።

ወንጌል-ተኮር ስብከትን በተመለከተ ያሉ ክህደቶች

የተወሰኑ ወንጌል-ተኮር ስብከት ያልሆኑ ነገሮችን ማንሣት ወንጌል-ተኮር ስብከት ምን እንደሆነና እንዳልሆነ ለመረዳት መስመሩን ያሰምርልናል፦

  • አንድ ስብከት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ብቻ ወንጌል-ተኮር ስብከት ሊባል አይችልም። አንዳንድ ስብከቶች መጽሐፍ ቅዱስን መስመር በመስመር እየተከተሉ የሚያስተምሩ ሆነው፣ እርሱ ብቻም ሳይሆን ስለ ኢየሱስ ሚናገር ክፍል እየሰበኩ ነገር ግን ስሑት አስተምህሮ ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ሌዋውያኑና ካህናቱ የእግዚአብሔር ቃል ልህቃን ነበሩ፤ ሆኖም ግን የኢየሱስ የመጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ-ተኮር ምስክርነትን ስለሣቱ ሲገሥጻቸው እንመለከታለን (ዮሐንስ 5፥39-40)።
  • አንድ ስብከት ጸጋን በማሳየት ሰዎችን ስላጽናና ብቻ ወንጌል-ተኮር ስብከት ሊባል አይችልም። የወንጌል ጸጋ ማጽናናት ብቻ ሳይሆን ለመታዘዝም ያነቃቃል፤ ያጸድቃልም። ደግሞም ለቅድስና ያነሣሳል (ይቀድሳል)። የተደረገልን ላይ ተመሥርተን አድርጉ የተባልነውን ወደ ማድረግ ያሳድገናል፤ “ኅጢአትህ ተሰርዮልሃል፤ ደግመህ ኅጢአትን አትሥራ ይለናል።”
  • አንድ ስብከት ኢየሱስ ለኅጢአተኞች የሞተውን ሞትና ትንሣኤውን እንደ ማመሳከሪያ ስለጠቀሰ ብቻ ወንጌል ተኮር ስብከት ሊባል አይችልም። በርግጥ ኢየሱስ ለኅጢአተኞች መሞቱ እና ትንሣኤው የወንጌል መልእክት ማዕከል ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥1-4)። ሆኖም ግን ይህን መልእክት እንደ ግዴታ ጠቅልለን የስብከታችን የሆነ ቦታ ብንሸጉረው፣ ወይም ልክ እንደ ግርጌ ማስታወሻ የስብከታችን የሆነ ቦታ ብናስቀምጠው፣ ወንጌል-ተኮር ስብከት ሆነ ማለት አይደለም።

የወንጌል ተኮርነት ምስል

“ተኮር” ወይም “ማዕከላዊነት” የሚለው ቃል ለብዙ ግርታዎች ምንጩ ነው። ከኢየሱስ መልካም ዜና ስብከት ጋር “ተኮር” ወይም “ማዕከላዊነት” የሚሉት ቃላቶች ምን ግንኙነት አላቸው? እስቲ ይህን በተመለከተ የሆነ ምስል ልስጣችሁ። ፀሓይ የሥርዓተ ፀሓይ ማዕከል እንደሆነች ሁሉ ወንጌልም የስብከታችን ማዕከል እንዲሆን መፈለግ አለብን። በእኛ ሥርዓተ-ፀሓይ ሁሉም ነገር በፀሓይ ዙሪያ ይዞራል፤ ደግሞም ሙቀትም ሆን ብርሃን ከፀሓይ ያገኛል። የፀሓይ ከፍተኛ ስበት ኅያል ሁሉንም ነገር ወደ ራሱ በመሳብ በሥርዓተ-ፀሓይ ውስጥ ያሉ አካላትን አያይዞ ዑደቱ እንዲቀጥል ያደርጋል። የፀሓይ ብርሃን እና ሙቀት በምህዋሩ ውስጥ ወዳለው እያንዳንዱ ነገር ይደርሳል።

ስለዚህ ወንጌል በስብከታችን ውስጥ እንዲሁ መሆን አለበት። ክርስቶስ ፀሓያችን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ሥርዐተ ፀሓያችን። የትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፣ የትኛውም አስተምህሮ፣ የትኛውም ሐሳብ የኢየሱስን የማዳን ሥራ ላይ መዘወር አለበት። የእግዚአብሔር ሙሉ መገለጥ ላይ፣ የሚሰሙን ሕዝቦች ላይ፣ እንዲሁም ሰባኪው ላይ የኢየሱስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ ብርሃንና ሙቀት መስጠት አለበት። ስብከት እነዚህን እውነቶች ባንጸባረቀበት መጠን ነው ስብከቱ ወንጌል ተኮር ነው ወይም ወንጌልን ማዕከል ያደረገ ነው ማለት የምንችለው።

በወንጌል ተኮር ስብከት ውስጥ ወንጌል ልክ እንደ ፀሓይ ሁሉንም የስብከት አካላትን ወደ ምህዋሩ እየሳበ ብርሃንና ሙቀት ይሰጣቸዋል። ወንጌል ተኮር ስብከት ወንጌል ደምቆ የሚያበራበት ስብከት ነው።

የመመርመሪያ ጥያቄዎች

ስብከትን ከሥርዐተ ፀሓይ ጋር ማስተያየት በሐሳብ ደረጃ ጠቃሚ ነው፤ ነገር ግን ከላይ ያልነውን ነገር መሬት አውርደን ማየት አለብን። ስብከታችን በምን ያህል ደረጃ ወንጌል-ተኮር እንደሆነ የምንመዝንበት መንገድ ይኖር ይሆን? ቀጥሎ የምናያቸው ሦስት የመመርመሪያ ጥያቄዎች ስብከታችንን ለመመዘን ያግዙናል። እነዚህ ጥያቄዎች ከላይ ካነሣናቸው ጋር ካስተያየናቸው እነዚኛዎቹ አዎንታዊ ናቸው። 

(1) ለስብከታችን በተጠቀምነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ወንጌል እንደ ፀሓይ አብርቷል ወይ?

ጥያቄው፣ የክፍሉ ዋና ሐሳብ በወንጌል ብርሃን ተነግሯል ወይ የሚል ነው። ስለ ፍጥረት፣ ጾታ፣ ኪዳን፣ ቤተ-መቅደስ፣ መሥዋዕት፣ ቅድስና፣ ፍርድ፣ በረከት፣ እርግማን፣ ንጽህና፣ ጸሎት፣ ትዳር፣ ላጤነት፣ አንድነት፣ ፍትሕ፣ ተልዕኮ፣ አብ፣ መንፈስ ቅዱስ ወዘተ ስለ መሳሰሉት ጉዳዮች ምንም ብንሰብክም ዋና ጥያቄው የሚሆነው የስብከታችን ዋና ሐሳብ ግልጽ በሆነ በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ፍጻሜን አግኝቷል? ቅርጽ ሰጥቶታል? እና በወንጌል ኅይል አግኝቷል ወይ ነው? በአጭር አገላለጽ የክፍሉ ዋና ሐሳብ ግልጽ በሆነ መንገድ ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ጋር ባለው ግንኙነት በደንብ መታየት አለበት።

(2) ወንጌል በአድማጮች ሕይወት ላይ እንደ ፀሓይ አብርቷል ወይ?

ወንጌል በክፍሉ ዋና ሐሳብ ላይ ብቻ ሳይሆን በአድማጮች ሕይወትም ላይ ያበራል። የወንጌል ማዕከላዊነት ወይም ተኮርነት በቃሉ ትርጉም ላይ ብቻ ሳይሆን በተዛምዶአችንም ላይ ያበራል። ክርስቲያኖች ጥሪያቸው ለወንጌል ምላሽ እንዲሰጡ ነው። በክርስቶስ ባለው የእግዚአብሔር ጸጋ በክርስቶስ ያላመኑ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ፣ በክርስቶስ እንዲያምኑና እንዲድኑ አጥብቆ መነገር አለበት። በክርስቶስ ባለው የእግዚአብሔር ጸጋ አማኞች አሮጌውን ማንነት አውልቀው እንዲጥሉ፣ በአዕምሮቸው መታደስ እንዲለወጡና አዲሱን ሰው እንዲለብሱ መበረታታት አለባቸው። ሕይወት ቀያሪው ጸጋ በእውነተኛ ወንጌል-ተኮር ስብከት ላይ ብርሃኑን ያበራል። በወንጌል እንድንሆናቸውና እንድናደርጋቸው የተነገሩን ነገሮች በወንጌል ከተደረጉልን ነገሮች ይነሣሉ፤ ስለዚህም ከሁለቱ አንዱን ለይተን መተው የለብንም።  

(3) የወንጌል ብርሃን በሰባኪው ልብ ላይ አብርቷል ወይ?

ለወንጌል ክብር ሲባል በጨረፍታ ወንጌልን በስብከት መሃል ለአመል ጣል ከማድረግ ጭራሹኑ ባይደረግ ሳይሻል አይቀርም። ሆኖም ግን በእውነተኛ ወንጌል-ተኮር ስብከት፣ ሰባኪው ራሱ በመጽሐፍ ክፍሉ ውስጥ ባለው የወንጌል ተዛምዶ ልቡ ይያዛል። ሰባኪው ራሱ በፀሓዩ ሙቀትና ብርሃን ስለተጎበኘ ህዝቡ ፊት ሲቆም እንደ ቀዛቃዎቹ ፕላኔቶች ፕሉቶና ሜርኩሪ መሆን አይችልም። ምክንያቱም እርሱ ራሱ በክርስቶስ ውስጥ ባለው ወደር የሌለው ደስታ ውስጥ ነው። ወንጌልን ሲሰብክ እንደ መግቢያ የሚያደርገው ሳይሆን፣ ዋና ርዕሱም ዝርዝሩም ወንጌል ነው።

ሊታሰብ የማይችል!

ወንጌል-ተኮር ስብከት በጥሩ ሁኔታ ሲደረግ፣ ወንጌል ከሚሰበከው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደ ፀሓይ በሰሚዎቹ እና በሰባኪው ላይ ደምቆ ያበራል። ሊታሰብ የማይቻለው ነገር የወንጌል ማዕከላዊነት ወይም ወንጌል-ተኮርነት ከዚህ ባነሰና በረከሰ ትርጉሞች መቀመጡ ነው። ስለዚህ ከላይ ያነሣሁትን ወንጌል-ተኮርነት ያልሆኑ ነገሮችን አስቧቸው። ደጋግማቹ የመመርመሪያ ጥያቄዎቹን አሰላስሏቸው። መዝሙረኛው በመዝሙር 19፥6 ላይ ስለ ጀምበር እንዲህ እንደሚል “መውጫው ከሰማያት ዳርቻ ነው፤ ዑደቱም እስከ ሌላኛው ዳርቻ ነው፤ ከትኵሳቱም የሚሰወር የለም።’’ እንደዚሁ ስብከታችን እንደ ጀንበር ፀሓይ እንዲሆን መማር አለብን። ወንጌል-ተኮር ስብከት ወንጌል ደምቆ የሚታይበት ስብከት ነው።

ዴቪድ ኪንግ