ስብከት ለምን አስፈለገ?

ባለፈው ሳምንት የቤተ ክርስቲያናችንን የእሁድ ጠዋት መልእክት ለማዘጋጀት 25 ሰዓታት ገደማ ወስዶብኝ ነበር። በ1ኛ ሳሙኤል 9-11 ላይ ስለተመሠረተ፣ መልእክት ከምለው ስብከት ብለው ይሻላል። ሙሉውን ጥቅስ አንብቤ ለ40 ደቂቃ ያህል ተናገርኩ፤ ትርጉሙን በማብራራትና በተሰብሳቢዎቹ ልብ ውስጥ የሚቀር ተግባራዊ ነገር ለማቅረብ ሙከራ አድርጌያለሁ። ስለዚህ ምናልባትም ገላጭ ስብከት ልንለው ይገባል።

እኔ የምኖረው በቅድመ-አብርሆት ዘመን (pre-enlightment) ባለች እንግሊዝ ውስጥ አይደለም፤ ወይም በፕዩሪታንስ ዘመን እንደ ነበረው ዓመታዊ የቤተ ክርስቲያን የስብከት ዕቅድ ቤተ ክርስቲያኔን አትጠቀምም። ይህን ሁሉ ሰዓት የእግዚአብሔርን ቃል ለመስበክ መዘጋጀት ለምን አስፈለገ? ለምን አንድ ጉባኤ የእኔን ንግግር ለአንድ ሰዓት ያክል በመስማት ያሳልፋሉ? ከዚህ በፊት እንደዚህ ዐይነት ጥያቄዎች ቀርበውልኛል። ጥሩ መካሪ የሆኑ ጓደኞቼ በርጋታ ወቅሰውኛል። ጥያቄዎቻቸው እንዲህ ዐይነት ይዘት አላቸው፦ “ስብከትን ከሌሎች የአምልኮ ዐይነቶች ለይተህ ለምን ትመለከታለህ? ይህ ለአመክንዮአዊ ደግሞም በሥርዐት ለተሞሉ ንግግሮች ያላችሁን የምዕራባውያን ባሕል ጫና የሚያንፀባርቅ አይደለምን? ለማንኛውም አንተ ከተናገርከው ነገር 95%ቱን ማንም አያስታውሰውም። በሌላ አነጋገር፣ የእኛንም ሆነ የራስህን ጊዜ ማባከን አቁም” እያሉ ነው!

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በእሁድ አምልኮ ላይ የቅዱሳት መጻሕፍትን ስብከት ለመዝናኛ ፕሮግራሞች አሳልፈህ ከመስጠትህ በፊት፣ ስብከት እንዲያው መኖር ያለበት ነገር ብቻ ሳይሆን በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት የሚያስረግጡ ጥቂት ምክንያቶች ልስጥህ።

የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሚሰበሰቡት የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ነው

ብታምኑም ባታምኑም፣ አንድ ሰው ብቻውን ሲያወራ ቁጭ ብዬ መስማት አልወድም። ይልቁንስ ፊልም በማየት እነቃቃለሁ፤ ወይም የጥበብ ሥራ በመታደም ምቾት ይሰማኛል። ነገር ግን በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የምናየው ወጥ የሆነ ልምምድ፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በእግዚአብሔር ቃል ስብከት ዙሪያ መሰባሰባቸውን ነው። የእግዚአብሔርን ቃል እንዲሰሙ ሰባኪው ሲናገር፣ ጉባኤው ደግሞ ያደምጣል።

የእስራኤል ሕዝብ ከግብጽ በሚወጣበት ወቅት፣ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ያለውን የቃል ኪዳን ግንኙነት ሲመሠርት፣ ሕዝቡ እንዲሰበሰቡና እነዚያን ትዕዛዛት እንዲሰሙ አዘዛቸው (ዘጸአት 24፥7)። እስራኤል ወደ ተስፋይቱ ምድር በምታደርገው ጉዞ ጠላቶቿ ከኋላ እያሳደዷት ሳለ፣ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከጉዞ አቁሞ በሰሜን ወደ 32 ኪ.ሜ. ርቆ ባለ፣ ሁለት ተቃራኒ ቋጥኞች ወዳለው ቦታ እንዲጓዙ አዘዛቸው። በዚያ የነበሩት ገደላማ ተራሮች እንደ ቲያትር መሰባሰብያ ስፍራ አገልግሏቸው፦ “ከዚህ በኋላ ኢያሱ፣ የሕጉን ቃላት በሙሉ ማለትም በረከቱንና መርገሙን ሁሉ፣ ልክ በሕጉ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው አነበበ፤ ኢያሱ በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ሴቶች፣ ሕፃናትና በመካከላቸው የኖሩ መጻተኞች ባሉበት ያነበበው፣ ሙሴ ያዘዘውን ቃል አንድም ሳይቀር ሙሉ በሙሉ ነበር” (ኢያሱ 8፥34-35)።

በደቡብ በኩል እየመጣባቸው ባለው ድንገተኛ ጥቃት መካከል፣ ኢያሱ እንዲያ ማድረጉ የሚያስገርም ነገር ነው። ሆኖም ተራ ጦርነት አልነበረም። ሕዝቦቹም ተራ ሕዝቦች አልነበሩም። የሚገልጻቸው ቃል የፈጠራቸው ቃል ነው። ከዓመታት በኋላ፣ ኢዮስያስ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር ሲመራ፣ “በእግዚአብሔር ቤት የተገኘውን የኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ አነበበላቸው” ይላል (2ኛ ዜና መዋዕል 34፥30)። የእግዚአብሔር ሕዝብ ከስደት በኋላ አንድ ሆነው ሲሰበሰቡ ነህምያ ሌላ ያስቀደመው ተግባር አልነበረም። ዕዝራን በእንጨት መድረክ ላይ እንዲቆም አደረገ (ነህምያ 8፥4)። ሕዝቡ በየስፍራቸው ሲቆሙ (8፥7)፣ ዕዝራና ጸሓፍትም፣ “ሕዝቡ የሚነበበውን መረዳት እንዲችሉ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ካነበቡላቸው በኋላ ይተረጕሙላቸውና ይተነትኑላቸው ነበር” (8፥8)።

በሉቃስ ወንጌል ውስጥ የኢየሱስ የአደባባይ አገልግሎት የሚጀምረው ወደ ምኩራብ በመግባት፣ የኢሳይያስን ጥቅልል በማንሳት፣ በማንበብና ከመጽሐፉ በማስተማር ነው (ሉቃስ 4፥14-22)። በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2 ላይ ያሉት ሰዎች የዳኑት በሚያዝናና ነገር ወይም በሌላ ውዥንብር ሳይሆን፣ በአደባባይ በጴጥሮስ በተደረገው የኢዩኤል ምዕራፍ 2 ገላጭ ስብከት ነው። በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 6 ዲያቆናት ያስፈለጉት ሐዋርያት የእግዚአብሔርን ቃል ለመስበክ ነፃ እንዲሆኑ እንጂ ለሌላ ጉዳይ አልነበረም (የሐዋርያት ሥራ 6፥2)። ጳውሎስም ጢሞቴዎስን ቃሉን እንዲሰብክ አጥብቆ አሳስቦታል (2ኛ ጢሞቴዎስ 4፥2)።

መቀጠል እችል ነበር። የሚታይ ነገር ሊያንጸባርቅ ይችል ይሆናል፤ የሚሰማ ነገር ግን ለልብ የተሻለ ቅርብ ነው። የገነት በሮች እና የገሃነም ነበልባል የሚያሳዩ ትዕይንቶች አያስፈልጉንም። የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ዙሪያ መሰብሰብ አለባቸው።

የእግዚአብሔርን ቃል ለምዕመኑ መስበክ፣ ቃሉን እንዴት ማንበብ እንዳለባቸው ያስተምራል

በአንድ ወቅት ዴቪድ ዌልስ የተባለ ሰው፣ ወንጌላውያን እንዴት ፕሮቴስታንት ለመሆን ድፍረት እንደሌላቸው ተናግሯል። ዛሬ ዛሬ ታሪካዊ ክርስቲያን የመሆን ድፍረትን ለማግኘት እንታገላለን። የፆታዊ እና ባሕላዊ ማዕበል በላያችን ላይ ሲከደን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ አሻሚነት የሚናገረው ነገር እንደሌለ ስለምናስብ፣ ወይም የሚናገረውን ስለማናውቅ ወይም ከቁም ነገር ስለማንቆጥረው እና መጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ታሪኮች ስብስብ፣ ወይም ባሕላዊ ተረት እና ሃይማኖታዊ ትዝታዎችን የያዘ ነገር ስለሚመስለን የምንናገረው ነገር የለንም።

ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ዋና ነገር ማድረግ፣ በተለይም የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎችን በተከታታይ መስበክ፣ ሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ማንበብ እንዳለባቸው ያስተምራቸዋል። ይህንን ለማግኘት የሥነ አፈታት ኮርስ ሥልጠና የግዴታ መውሰድ ላያስፈልጋቸው ይችላል። የሚያስፈልጋቸው ታማኝ ስብከት ነው። የሚፈጥረውን የእግዚአብሔርን ቃል ኅይል፣ የመጀመሪያው የአዳም ውድቀት፣ የመሥዋዕት አስፈላጊነት፣ የሁለተኛው አዳም እና የአዲሲቷ ዔደን ተስፋን የሚናገር ስብከት ማለቴ ነው። እግዚአብሔር በእስራኤል በኩል ያደረገውን ከኢየሱስ እና ከአዲሱ የእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር በሚገባ የሚያገናኝ ስብከት ማለቴ ነው።

በቀድሞ የክርስትና ሕይወቴ የእግዚአብሔርን ቃል በሚወዱ አብያተ ክርስቲያናት አሳልፌያለሁ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናት፣ የወርቅ ቦታን እንደ መቆፈር አድርገው አያዩትም ነበር። በልበ ሙሉነት ብሉይ ኪዳንን ማንበብ የጀመርኩት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጭብጦችን በጥንቃቄ በማገናኘት እና ሁሉም ክፍሎች እንዴት ወደ ክርስቶስ እንደሚጠቁሙ በማሳየት፣ ቃሉን እንደ ወርቅ ፍለጋ በሚዝቁ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አባል ከሆንኩ በኋላ ነበር። በስብከትህና በትምህርትህ ውስጥ የአምላክን ቃል ዋና ማዕከል አድርገህ መያዝ፣ ሰዎች እንዴት ማንበብ እንዳለባቸው እንዲያውቁ መርዳት ብቻ ሳይሆን ለራሳቸው ጠልቀው እንዲገቡ እና እንዲያነቡ ማበረታቻ ይሠጣቸዋል።

የእግዚአብሔርን ቃል መስበክ፣ በየሳምንቱ ሕይወታቸውን ለመለወጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው

የሰማናቸውን አብዛኞቹን የስብከት ይዘቶች ወዲያው የምንረሳ ከሆነ ስብከቶች ምን ይፈይዳሉ? በእውነቱ ከሆነ የምንሰማውን ሁሉ አንረሳውም። አብዛኞቻችን ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ትዳር፣ ስለ ገንዘብ፣ ወዘተ እንዴት ማሰብ እንዳለብን ያሳሰቡንን እና ለዘላለም የተለወጥንባቸውን ስብከቶችን ማስታወስ እንደምንችል አምናለሁ። ስለዚህ ሁሉን ነገር በአንዴ አንደምስሰው። ከዚህ ባለፈ ግን የእሁድ መልእክት የሚተላለፈው፣ ወደ መጪው እሁድ እንዲያደርሰን ብቻ ነው! በቤተ ክርስቲያን ሳምንታዊ ዑደት፣ የሚመጣውን እሁድ ተርበን እንመጣለን። ስለዚህም በየሳምንቱ እንደገና በቃሉ መሞላት አለብን።

ስብከቶቼ፣ ስብከቶቻችሁ፣ ለዘላለም ከሕዝባችን ጋር መቆየት የለባቸውም። በዚህ መልኩ የምዕመናን ሕይወት ለመለወጥ የታሰቡ አይደሉም። የሳምንት ቀለብ ሊሆናቸው ይችላል። እንዲህ እያልን መንግሥቱ እስኪመጣ ድረስ እንቀጥላለን። በዚያም ሥጋ የለበሰው የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ ጋር ለዘላለም ይኖራል፤ ያኔ ስብከት አያስፈልገንም።

ብራድ ዊለር