ኢየሱስ ጠረጴዛውን ገለበጠ

የሕማማት ሰኞ ማታ

ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤  (ማርቆስ 11፥15)

ይህ የተለየ ሰኞ በዘመናዊው ምዕራባዊ ዓለም እንደሚታወቀው፣ ወደ መደበኛው የሥራ ጫና (grind) እንደምንመለስበት እንደ ማንኛውም ሰኞ ጠዋት ሆኖ ሊሰማን ይችላል። ኢየሱስ በርግጥም የሥራ ኀላፊነቱን ለመወጣት (to take care of business) ወደ ኢየሩሳሌም ገባ።

ብዙ የዘመናችን ሰዎች የሚመርጡት፣ ሁሉን ተቀባይ የሆነው (progressive “tolerance”) ያ የዋሁና ለስላሳው የኢየሱስ ምስል፣ እርሱ የገንዘብ ለዋጮችን ዕቃ ባተራመሰ ጊዜ ፈጽሞ ሊታይ አይችልም። ኢየሱስ ልክ እንደ ኤርምያስ በእስራኤል ላይ ብርቱ ፍርድን ሲያውጅ፣ ምንም ዐይነት ልስላሴና ገርነት አልታየበትም።

ያለ ምንም አሻሚ ቋንቋ፣ የርሱ ተግሣጽ በአምልኳቸው ላይ ወደቀ።

ርግቦች! ርግቦቻችሁን ግዙ!

እኔ ያደግሁበት የክርስቲያን ባህል (Christian tradition)፣ ጕብኝት የሚያደርጉ የሙዚቃ ቡድኖች ኮንሰርቶችን ሲያቀርቡ ማስተናገድ የተለመደ ነበር። እንደምትገምቱት፣ እነዚህ ቡድኖች አልበሞቻቸውንና ሌሎች የንግድ ዕቃዎቻቸውን ይዘው በመዞር ያስተዋውቃሉ። ነገር ግን በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ እንዲሸጡ አይፈቀድላቸውም ነበር፤ ቢያንስ ብዙ ተሰብሳቢዎች በሚገቡበት የቤተ ክርስቲያኑ መግቢያ (foyer) ውስጥ። ለዚህም እንደ መነሻ የሚቀርበው ማርቆስ 11፥15-19 ላይ ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን ያነጻበት ታሪክ ነው። ኢየሱስ ሰዎች በቤተ መቅደስ ዙሪያ ዕቃዎቻቸውን ሲሸጡ በግልጽ ስላልወደደው፣ እኛም በመቅደሱ ዙሪያ ዕቃዎችን መሸጥ የለብንም የሚል ነው።

በርግጥ፣ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የአይሁድ እምነት የአምልኮ ስፍራና በአሜሪካ ገጠራማ አካባቢ የሚገኝ የመጥምቃውያን ቤተ ክርስቲያን አዳራሽ ሙሉ በሙሉ አንድ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን የኢየሱስን ንግግር በመከተል፣ የእኔ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ስፍራ ወደ ንግድ ስፍራነት እንዲቀየር አልፈለገችም። ያ ደግሞ ትክክል ነበር።

በኢየሱስ ዘመን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከነበሩት ችግሮች አንዱ ይህ ነበር። በምናባችሁ ለመሣል ከሞከራችሁ፣ ከተማዋ በፋሲካ ምክንያት በመንገደኞች ተጨናንቃ ነበር። መሥዋዕት ለማቅረብም ወደ ቤተ መቅደስ ይመጣሉ፤ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የርግብ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን በዚያ ከፍተው ነበር። ይህ ዛሬ በስፖርት ውድድሮች ላይ ላብ ያጠመቃቸው ሻጮች በመተላለፊያዎች ላይ እየተዘዋወሩ ፋንዲሻ ከሚሸጡበት ሁኒታ ጋራ ብዙም ላይለይ ይችላል፤ ነገር ግን እነዚህ መሥዋዕት የሚሆኑ አዕዋፍ ነበሩ፤ የነጋዴዎቹ ዐላማ ክፉ ነበር፤ ዋጋውም ምናልባት በጣም የተወደደ ነበር። “ርግቦች! ርግቦቻችሁን ግዙ!” እያሉ ይጮኹ ይሆናል።

ያለ ጥርጥር፣ ይህ የአምልኮ ስፍራ መሆን ከነበረበት ሁኔታ በጣም የራቀ ነበር። ኢየሱስም፣ ይህን አልተቀበለውም። በሥልጣኑ የሰዎችን ትኲረት በመሳብ፣ ኢየሱስ እግዚአብሔርን ወክሎ ተናገረ፤ ገበታዎቻቸውን ገለበጠ። ለዚህ ሁሉ ማዕከል የሆነው ከብሉይ ኪዳን፣ ይኸውም ከኢሳይያስና ከኤርምያስ የጠቀሰው ቃል ነበር፦

“ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት” [ኢሳይያስ 56፥7-8ኤርምያስ 7፥11]።

ከመስመር የወጣ

የንግዱ መሰባሰብ ችግር ነበር፣ ነገር ግን ያ ብቻ አልነበረም፤ ወይም ደግሞ ኢየሱስ ያተኰረበት ዋናው ነገር ያ አልነበረም። እውነተኛው ውድቀት የእስራኤል አምልኮ፣ ኢሳይያስ ከተነበየው ታላቁ የመጨረሻ ዘመን ራእይ ጋራ ዐብሮ የማይሄድ፣ ከመስመር የወጣ መሆኑ ነበር። ይህም ኢየሱስ ሊያስጀምረው የመጣው አዲሱ ዘመን ነው።

ኢየሱስ በኢሳይያስ 56 ላይ ካለው ራእይ አንድ ክፍል ይጠቅሳል፦ “ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች።”

ኢሳይያስ 56 ዐውድ የበለጠ ይነግረናል። እንደ ኢሳይያስ ራእይ፣ ጃንደረቦች የእግዚአብሔርን ኪዳን ይጠብቃሉ (ኢሳይያስ 56፥4)፣ ባዕዳን ራሳቸውን ከርሱ ጋር ያያይዛሉ (ኢሳይያስ 56፥6)፣ እናም የተገለሉት (the outcasts) ከሕዝቡ ጋራ ይሰበሰባሉ (ኢሳይያስ 56፥8)። ነገር ግን ኢየሱስ ያየው ቤተ መቅደስ በመግዛትና በመሸጥ ግርግር የተሞላ ነበር። ለአሕዛብ ሁሉ፣ ለባዕዳን እንዲሰበሰቡበት፣ ሕዝቦች ጌታን እንዲፈልጉበት የተዘጋጀው የአሕዛብ አደባባይ (The court of the Gentiles)፣ ትርፍ ለማግኘት በሚራወጡ ስግብግቦች ተወርሮ ነበር። የአይሁድ መሪዎች ደግሞ፣ ይህ እንዲሆን ፈቅደው ነበር።

የእነርሱ የኢኮኖሚ ግፊትና ቤተ መቅደሱን የበረከት ምልክት (ኤርምያስ 7፥3-11) አድርገው በመውሰድ የነበራቸው ሐሰተኛ የደኅንነት ስሜት፣ ሕዝቦች የሚቀርቡበትን ስፍራ አጣብቦት ነበር። ስለዚህም ኢየሱስ እያባረራቸው ነበር። የዚህ ትዕይንት ታላቅ ሐዘን የምርቶቹ መደርደርና የዋጋ ንረቱ ሳይሆን፣ ይህ ሁሉ ለአሕዛብና ለተገለሉት ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንዲመጡ ምንም ቦታ ስለማይሰጣቸው ነበር። ይህ የአምልኮ ስፍራ የእግዚአብሔርን የታደሰ ፍጥረት ተስፋ አስቀድሞ ሊያሳይ ይገባ ነበር። ይህም፣ “ሕዝቦችም ሁሉ ወደዚያ ይጐርፋሉ። ብዙ አሕዛብ መጥተው እንዲህ ይላሉ፤ “ኑ፤ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤” (ኢሳይያስ 2፥2-3) የሚሉበት ቀን ነው።

በሌላ አነጋገር፣ በእግዚአብሔር ስፍራ ላይ ያለው የእግዚአብሔር ሕዝብ የላቀው ራእይ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እግሩን ሲያነሣ ከነበረው ይልቅ የተለያየና የተደባለቀ መልክ ሊኖረው ይገባ ነበር። አምልኳቸው ከዚህ ራእይ በጣም የራቀ ስለ ነበር፣ ኢየሱስ በቃኝ አለ። የእግዚአብሔር ሕዝብ አምልኮ ከእግዚአብሔር ዐላማዎች ጋራ በጣም የተፋለሰ ስለ ነበር፣ የእግዚአብሔርን መሲሕ ቅንዓት በላው። ማብቃት ነበረበት።

እኛስ?

በዚህ የሕማማት ሰኞ ለእኛ የሚሆነው ትምህርት ይህ ነው፤ ወይም ጥያቄው ይህ ነው፤ አምልኳችን የአዲሱን ፍጥረት ትንቢታዊ ራእይ ምን ያህል አስቀድሞ ያሳያል? የእኛ ግንኙነቶችና የጋራ ስብሰባዎቻችን፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን፣ የተገለሉትን የሚሰበስበውን የእግዚአብሔርን ልብ ያንጸባርቃሉ?

ይህ ጥያቄ በተለይም አብያተ ክርስቲያኖቻችን እጅግ ውብ ሆነው ለመታየት ከሚሞክሩበት ከትንሣኤ በዓል ጊዜ የበለጠ ፈያጅነት ያለው ጊዜ የለም። በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለአምልኮ ስንሰበሰብ፣ ማንም ሰው ምንዛሬ ለመቀየር ጠረጴዛዎችን አያዘጋጅም፤ ማንም ሰው ለመበልጸግ ዐስቦ በሬዎቹን እየነዳ አያመጣም፤ ማንም ሰው ዋጋቸው የተወደደ ርግቦችን በረት አይሸከምም። ነገር ግን ማስጌጫዎቻችን የተንቈጠቈጡ ሊሆኑ ይችላሉ፤ አለባበሳችን ያማረ ሊሆን ይችላል፤ ሙዚቃችን የላቀ ደረጃ ያለው ሊሆን ይችላል። በእነዚህ ነገሮች ላይ ከፍተኛ ጕልበት አውጥተን፣ አስደናቂ ትዕይንት ልናደርገው እንችላለን። ነገር ግን ኢየሱስ ቢመጣ፣ በዚህ እሑድ ወደ አብያተ ክርስቲያኖቻችን ጕዞውን ቢያደርግ ኖሮ፣ ዝቅተኛ የሆኑትን፣ የተገለሉትን፣ በማኅበረ ሰቡ የተገፉትን ይፈልግ ነበር። የተረሱት፣ በማኅበረ ሰቡ የተገፉት፣ የተገለሉት የት አሉ?

ከምቾቶቻችን፣ ከቡድኖቻችንና ከተዋቡ የሰንበት ልብሶቻችን ዐልፈን እንድንወጣና ከሁሉ ያነሱትን አጥብቀን እንድንፈልግ የሚገፋፋን በቂ ሕይወት በትንሣኤ ደም ሥሮች ውስጥ ይገኛል።