በ11ኛው ሰዓት ጥሶ መውጣት | የካቲት 8

“ኢየሱስ ሆይ፤ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ” አለው። (ሉቃስ 23፥42)

ተስፋን ከሚገድሉ ነገሮች መካከል ትልቁ፣ ለረጅም ጊዜ ለመለወጥ ሞክራችሁ ሳይሳካላችሁ ሲቀር ነው።

ወደ ኋላ ዞር ብላችሁ፣  “ታዲያ ምን ጠቀመኝ?” ብላችሁ ታስባላችሁ። “ያንን ኀጢአት ጥሶ መውጣት እንኳን ቢሆንልኝ፣ ከባከኑት ዓመታት አንጻር፣ ይህንን አዲስ ሕይወት ለመኖር ያለኝ በጣም ጥቂት ጊዜ ስለሆነ ምንም ለውጥ አይኖረውም” ትሉም ይሆናል።

በመስቀል ላይ ከኢየሱስ አጠገብ የተሰቀለው ወንበዴ የነበረው ሰው፣ ኢየሱስን አምኖ ከተለወጠ በኋላ ወደ አንድ ሰዓት ገደማ ያህል በሕይወት ቆይቷል። ከዚያም በኋላ ሞተ። የቀረውን ዕድሜ በመስቀል ላይ እንደ አዲስ ሰው በአዲስ ባሕርይ እና ድርጊት (ስድብ ትቶ) ኖረ። ነገር ግን የሕይወቱ 99.99 በመቶው ባክኖ ነበር። ታዲያ እነዚያ ጥቂት የመጨረሻዎቹ የመታደስ ሰዓታት ፋይዳ ይኖራቸው ይሆን?

እጅጉን ፋይዳ ነበራቸው። ይህ ቀድሞ ወንበዴ የነበረው ሰው፣ ልክ እንደሁላችንም፣ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ቆሞ ስለራሱ ሕይወት መልስን ይሰጣል። “ሁላችንም በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለንና፤ እያንዳንዱም ሰው በሥጋው ለሠራው በጎ ወይም ክፉ ሥራ ተገቢውን ዋጋ ይቀበላል” (2ኛ ቆሮንቶስ 5፥10)። ሕይወቱ ከክርስቶስ ጋር አንድ ስለመሆኑ እና ዳግም ስለመወለዱ እንዴት ይመሰክራል? እንዴትስ በክርስቶስ በኩል ያገኘውን አዲስነትስ እንዴት ያረጋግጣል?

የመጨረሻዎቹ ሰዓታት የእርሱን ታሪክ ይናገራሉ። ይህ ሰው አዲስ ሆኖ ነበር። እምነቱም የእውነት ነበር። በእውነት ከኢየሱስ ጋር አንድ ሆኗል። የክርስቶስ ጽድቅ የእርሱ ጽድቅ ሆኗል። ኀጢአቶቹም ተሰርየውለታል።

በሚመጣው የፍርድ ወንበር ፊት የመጨረሻዎቹ ሰዓታት የሚያውጁት ይህንን ነው። ይህ ሰው ተለውጧል! ለውጡም ፋይዳ አለው። ለእግዚአብሔር ጸጋ ኃይል፣ ለእምነቱም እውነተኛነት፣ እንዲሁም ከክርስቶስ ጋር አንድ ስለ መሆኑ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር ውብ ምስክርነት ይሰጣል።

አሁን ትኩረታችንን ከለውጥ ጋር ወዳለን ትግል እንመልስ። ድካም ያለባቸው እውነተኛ አማኞች እንደ ወንበዴው ሰው አልዳኑም እያልኩ አይደለም። እያልኩ ያለሁት የሕይወት የመጨረሻዎቹ ዓመታት እና ሰዓታት እጅግ ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው ነው።

በሕይወታችን የመጨረሻው 1% ጊዜ ላይ፣ ለረዥም ጊዜ የቆየ የኀጢአት ልምምድን ማሸነፍ ወይም መጥፎ ባሕርይን መጣል፣ ለእግዚአብሔር ጸጋ ጉልበት ውብ የሆነ ምስክርነት ነው። በመጨረሻው ፍርድ ጊዜም በክርስቶስ ስላለው እምነታችን እና ከእርሱ ጋር አንድ ለመሆናችን ተጨማሪ ምስክር ይሆናል።

ስለዚህም እናንተ ደካሞች፣ ልባችሁ ይበርታ። ልመናችሁን፣ ፍለጋችሁን እና ማንኳኳታችሁን ቀጥሉ። ወደ ክርስቶስ መመልከታችሁን እንዳታቆሙ። ወንበዴን በ11ኛው ሰዓት ላይ በማዳን እግዚአብሔር የሚከብር ከሆነ፣ በእርግጥ ለእናንተም ለዓመታት ስትጓጉለት የነበረውን ጥሶ መውጣት ያልሰጠበት ምክንያት አለው።