እንዲያው ሳይቸግረኝ መንገድ ስቼ ሄድሁ፤ አሁን ግን ቃልህን እጠብቃለሁ። (መዝሙር 119፥67)
ይህ ቁጥር የሚያሳየው እግዚአብሔር መከራን የሚልክብን ቃሉን እንድንማር ለመርዳት እንደሆነ ነው። ይህ እንዴት ይሰራል? መከራ የእግዚአብሔርን ቃል እንድንማር እና እንድንታዘዘው ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
ለዚህ ታላቅ የሆነ ምህረት ስፍር ቁጥር የሌላቸው መልሶች አሉ። አምስቱን እንመልከት፦
- መከራ የሕይወትን እርባና ቢስነት በማስወገድ ይበልጥ ቁምነገረኛ እንድንሆን ያደርገናል። በዚህም ደግሞ አስተሳሰባችን በእግዚአብሔር ቃል አስፈላጊነት የተቃኘ ይሆናል። በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እንዲያው በዋዛ የተጻፈ አንድም ገጽ እንደሌለ ልብ በሉ።
- መከራ ዓለማዊ ቁሳዊነትን ከውስጣችን በማጥፋት ይበልጥ በእግዚአብሔር ላይ እንደንደገፍ ያደርገናል። ይህም ደግሞ ከቃሉ ዓላማ ጋር በይበልጥ እንድንጣጣም ይረዳናል። የቃሉ ዓላማ በእግዚአብሔር እንድናምን፣ በእርሱም ላይ ተስፋ እንድናደርግ ነው። “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና” (ሮሜ 15፥4)። “ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ፣ የእግዚአብሔርም ልጅ እንደሆነ ታምኑ ዘንድ፣ አምናችሁም በስሙ ሕይወት እንዲኖራችሁ ይህ ተጽፎአል” (ዮሐንስ 20፥31)።
- መከራ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሕይወታችን ሩቅ አድርገን ከመመልከት ይልቅ፣ እርዳታን ለማግኘት በከፍተኛ ተስፋ እንድንመረምራቸው ያግዘናል። “እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፣ በፍጹም ልባችሁም ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ” (ኤርምያስ 29፥13)።
- እኛ ላይ የሚደርስ መከራ የክርስቶስን መከራ ወደመካፈል ያቀርበናል። በዚያም ከክርስቶስ ጋር የቀረበ ሕብረትን በማድረግ ዓለምን እርሱ በሚያይበት እይታ ማየት ይሆንልናል። የጳውሎስ የልቡ ምኞትና ታላቅ መሻቱ ይህ ነበር፦ “ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኀይል እንዳውቅ፣ በሥቃዩ ተካፋይ እንድሆንና በሞቱም እርሱን እንድመስል እመኛለሁ” (ፊልጵስዩስ 3፥10)።
- መከራ በውስጣችን ያሉ አሳሳች እና አዘናጊ ስጋዊ መሻቶችን በመግደል፣ ወደ በሰለ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያመጣናል። መንፈሳዊ ለሆነው የእግዚአብሔር ቃልም ንቁ ያደርገናል። “እንግዲህ ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ እናንተም በዚሁ ዐላማ ታጥቃችሁ ተነሡ፤ ምክንያቱም በሥጋው መከራን የሚቀበል ሰው ኀጢአትን ትቶአል” (1ኛ ጴጥሮስ 4፥1)። መከራ ኀጢአትን የመግደል ባሕርይ አለው። እኛም የበለጠ እየጸዳን እና እየጠራን ስንመጣ፣ እግዚአብሔርን ይበልጥ አጥርተን ማየት እንችላለን (ማቴዎስ 5፥8)።
በዚህ ሁሉ ውስጥ፣ በእግዚአብሔር የመከራ ትምህርት ቤት በምናልፍበት ከባድ ወቅት፣ አጉረምራሚዎች እና ቂም የሚይዙ እንዳንሆን መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን ይስጠን።