ዐውዳዊነት ለምን ያስፈልጋል?

ለዐውዳዊነት ዐራት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረቶች

በዘመናችን ሚስዮናዊነት ውስጥ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዪች ውስጥ አንዱ ዐውዳዊነት ነው። በቀላል አነጋገር፣ ዐውዳዊነት ወንጌልንና ቤተ ክርስቲያንን በተቻለ መጠን በአንዳች የባህል ዐውድ ውስጥ ቅቡል የማድረግን ሂደት ለመግለጽ የምንጠቀምበት ቃል ነው።

የአሜሪካ ክርስቲያኖች፣ ዐውዳዊነት ሚስዮናውያን “የሆነ ስፍራ” የሚያደርጉት ነገር ነው ብለው ያስባሉ፤ እናም በምዕራቡ ዓለም ያሉ ብዙ ቁም ነገረኛ ክርስቲያኖች፣ ምዕራባውያን ያልሆኑ አብያተ ክርስቲያናት ዐውዳዊ ለመሆን በሚደረገው ጥረት ምን ያህል እንደሚሄዱ ያሳስባቸዋል። እውነታው ግን፣ ዛሬ በሕይወት ያለ እያንዳንዱ ክርስቲያን በዐውዳዊነት ውስጥ በንቃት ይሳተፋል። እያንዳንዱ አሜሪካዊ ክርስቲያን ዐውዳዊ በተደረገ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያመልካል። ጥያቄው ዐውዳዊ እናደርገዋለን ወይስ አናደርገውም የሚለው አይደለም። የአንደኛው ክፍለ ዘመን ፍልስጤማውያን አይሁዶች እስካልሆንን ድረስ፣ በሰሜን አሜሪካም ሆነ በደቡብ እስያ ያለ እያንዳንዱ አማኝ፣ በበርካታ መንገዶች ወንጌልንና ቤተ ክርስቲያንን ለባህላቸው ዐውዳዊ ያደርጋሉ። ስለዚህ እያንዳንዱ ምእመንና ቤተ ክርስቲያን የሚጋፈጠው ጥያቄ፣ በጥሩ ሁኔታ ዐውዳዊ ያደርጋል ወይስ አያደርግም የሚለው ነው። ዐውዳዊ እያደረገ መሆኑን ያልተገነዘበ ሰው በጥንቃቄና መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መንገድ ማሰብ ይሳነዋል፤ በቀላሉም ጥሩ ላልሆነ ዐውዳዊነት ይጋለጣል። ቅይጣዊነት በኢንዶኔዥያ ወይም በኢንዲያና ወይም በአዮዋ ውስጥ በቀላሉ ሊከሰት ይችላል!

ከሁሉም በላይ በቀዳሚነት፣ ሁሉም ነገሮች የሚገመገሙበት መመዘኛ ቅዱሳት መጻሕፍት እንጂ የእኛ ተሞክሮ አለመሆኑን መቀበል አለብን። ቅዱሳት መጻሕፍት ስሕተት አልባ፣ ባለ ሥልጣንና በቂ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ወይም ክልከላ ወይም አስገዳጅ ሞዴል በሰጠበት፣ ጉዳዩ እልባት ያገኛል። ቅዱሳት መጻሕፍት ድንበር ሲያበጁ፣ መተላለፍ የለብንም። በእነዚያ ወሰኖች ውስጥ ስለ ባህላዊ የአሠራር መንገዶቻችን፣ በተለየ ሁኔታ የተቀደሰ ነገር የለም። በዘመናትና በዓለም ዙሪያ፣ ልክ እንደ እኛ ለቅዱሳት መጻሕፍት ታማኝ የሆኑ ሌሎች የክርስትና ባህላዊ መግለጫዎች ነበሩ። ዋናው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ዳኛ እንዲሆን መፍቀድና ዓለም ዓቀፋዊው የክርስቶስ አካል የእግዚአብሔርን ቃል እኛ ልናስተውለው በማንችለው ጉዳያችን ላይ እንዲናገር መፍቀድ ነው።

የዐውዳዊነት ሂደት የሚጀምረው በራሱ በአዲስ ኪዳን ነው። ምናልባት በዚህ ርዕስ ላይ በሰፊው የሚጠቀሰው የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍል 1ኛ ቆሮንቶስ 9 ነው። የዚህ አምድ ቀሪው ክፍል ከዚያ ምንባብ ለታማኝ ዐውዳዊነት አራት መሠረታዊ ምልከታዎችን ያወጣል።

1. ጳውሎስ ትክክለኛ መብቶቹን ተወ

የምንባቡ ቁልፍ የሚገኘው ቁጥር 12 ላይ ነው፤ “እኛ ግን በዚህ መብት አልተጠቀምንም፤ ይልቁንም ለክርስቶስ ወንጌል ዕንቅፋት እንዳንሆን ሁሉንም ነገር እንታገሣለን።” የጳውሎስ ናፍቆት የወንጌል መስፋፋት ነበር። በዚህ መስፋፋት ላይ ምንም አላስፈላጊ ነገር እንዲቆም አልፈለገም። የራሱን ሕጋዊ መብቶች አለመጠቀምን ጨምሮ ወንጌልን በብቃት እንዲሠራጭ የሚያስችለውን ማንኛውንም ድሎት ማጣት ወይም የግል ችግር ለመቋቋም ፈቃደኛ ነበር። ለምሳሌ፣ ሥጋ የመብላት፣ አማኝ ሚስት በዐብሮነት የመውሰድና የገንዘብ ድጋፍ የማግኘት መብት ነበረው። ከእነዚህ ነገሮች ውስጥ የትኛውንም በማድረጉ ኀጢአት ባልሠራ ነበር። በርግጥ ሌሎች ሐዋርያት አድርገዋቸዋል። ምንም እንኳ በሂደቱ ውስጥ የትኛውንም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ወይም ትእዛዝ ለመጣስ ፈቃደኛ ባይሆንም፣ በወንጌል መንገድ ላይ ምንም ዐይነት እንቅፋት እንዳይኖር ሲል መብቱን በፈቃደኝነት ዐሳልፎ ሰጥቷል።

እኛ እንደ አሜሪካውያን ከዚህ ጋር እንታገላለን። መብታችንን እንድንጠይቅ ተደርገን አድገናል። እንደ ነጻ አሜሪካዊ፣ ባለሁበት በአዲሱ የባህል ዐውድ ውስጥ የሚያስቆጡ ብዙ ነገሮችን የመሥራት “መብት” አለኝ፤ ጫማዬን ቤት ውስጥ መጫማት፣ በግራ እጄ መብላት ወይም የሆነን ሰው መንካት፣ የአካባቢዬ ማኅበረ ሰብ መሪን ፈቃድ ሳልጠይቅ በራሴ ግቢ ውስጥ ዐጥር የማቆም፣ ወይም ሩዝ ከመቅረቡ በፊት የልደት ድግስ ጥሎ መውጣት። እንደ ፈለግሁት የመልበስ፣ የፈለግሁትን የመብላትና ቤቴን እንደ ፈለግሁት የማስጌጥ “መብት” አለኝ። በተመሳሳይ ጊዜ፣ እነዚህን ነገሮች ለማድረግ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ የለኝም። እነዚህን መብቶች የመተግበር ጉዳይ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ሳይሆን የራሴ ምቾትና ምቾት ነው። እኔ የማደርገው ማንኛውም ነገር፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ካዘዙኝ ነገሮች ውጭ ለሙስሊሞች፣ ለሂንዱዎች ወይም ለኢ-አማንያን ከእኔ ወንጌልን ለመስማት አስቸጋሪ ካደረገባቸው፣ በፈቃዴ ለመተው ፈቃደኛ መሆን አለብኝ።

2. ጳውሎስ ለማያምኑት አገልጋይ ነበር።

ሁለተኛ፣ ጳውሎስ ለማያምኑት የአገልጋይነት ልብ ነበረው። በቁጥር 19 እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እኔ ነጻ ሰው ነኝ፤ የማንም ባሪያ አይደለሁም፤ ነገር ግን ብዙዎችን እመልስ ዘንድ ራሴን ለሰው ሁሉ ባሪያ አደርጋለሁ።” እዚህ ላይ ላልዳኑት ስለሚያደርገው አገልግሎት እየተናገረ ስለ ሆነ፣ ክርስቲያኖችን ስለ ማገልገል እየተናገረ አይደለም። መብቱን ዐሳልፎ መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ ጳውሎስ ዐልፎ በመሄድ፣ በወንጌል ሊደርሳቸው ከሚሞክረው ሰዎች በታች ራሱን አገልጋያቸው አድርጎ ማስቀመጥን መረጠ።

በባህል ግጭት ውስጥ ስንሆን ብዙውን ጊዜ ሰዎችን ለማገልገል ሳይሆን ለማቅናት እንፈልጋለን። ኢየሱስ ግን ለመገልገል ሳይሆን ለማገልገል ነው የመጣው። የተሳሳቱትን፣ በእርሱ ላይ የሚያምፁትንና በመጨረሻ የሚገድሉትን ሰዎች አገልግሏል። ጳውሎስ በዚህ ጊዜ የጌታውን ልብ በሚገባ ተረድቷል። የአገልጋይነት ልብ የክርስቶስን ባሕርይ ያሳያል። የተዛቡ አመለካከቶችን ያፈርሳል፤ እንቅፋቶችንም ያስወግዳል። የአገልጋይነት ልብ ለባህል ተሻጋሪ አገልግሎት አስፈላጊ ባሕርይ ነው፤ ደግሞም ተቃርኖ በሚመስል፣ በክርስቶስ ያለንን ነጻነት እንዴት መጠቀም እንዳለብን ይገልጻል።

3. ጳውሎስ ወንጌልን እንደ ሰበከላቸው ስዎች ኖሯል።

ሦስተኛ፣ ጳውሎስ ሊደርሳቸው ከሚፈልጋቸው ሰዎች ጋር ራሱን ለማመሳሰል ሞክሯል፤ የክርስቶስን ሕግ ሳያመቻምች በሚችለው መጠን ከአኗኗራቸው ጋር ተላምዷል፦

እኔ ነጻ ሰው ነኝ፤ የማንም ባሪያ አይደለሁም፤ ነገር ግን ብዙዎችን እመልስ ዘንድ ራሴን ለሰው ሁሉ ባሪያ አደርጋለሁ። አይሁድን እመልስ ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፣ ከሕግ በታች ያሉትን እመልስ ዘንድ ከሕግ በታች እንዳሉት ሆንሁ። እኔ ራሴ ከእግዚአብሔር ሕግ ነጻ ያልሆንሁና፣ ለክርስቶስ ሕግ የምገዛ ብሆንም፣ ሕግ የሌላቸውን እመልስ ዘንድ፣ ሕግ እንደሌለው ሰው ሆንሁ። ደካሞችን እመልስ ዘንድ፣ ከደካሞች ጋር እንደ ደካማ ሆንሁ። በሚቻለኝ ሁሉ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር ሆንሁ። ይህን ሁሉ የማደርገው፣ ከወንጌል በረከት እካፈል ዘንድ፣ ስለ ወንጌል ብዬ ነው (1 ቆሮንቶስ 9፥19-23)።

ከየትኛውም ባህል፣ ከሌሎች ሁሉ ይልቅ ራሱን መንፈሳዊ አድርጎ የመቁጠር መብት ቢኖረው፣ በዚህ ረገድ የአይሁድን ባህል የሚስተካከለው የለም። ጳውሎስ የአይሁድ ባህላዊ ውርሱን የመጠበቅ ‘መብት’ እንደ ነበረው ምንም ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይ ጊዜ፣ ጳውሎስ ከሕግ ሸክም ነጻ ወጥቷል። ነገር ግን ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆነ፤ ከአሕዛብም ጋር እንደ አሕዛብ ሆነ። ከደካሞች (ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ተጨማሪ ቀንበርና ማንጠልጠያ ካላቸው) ጋር በቀንበራቸው መካከል ኖረ። አንዳንዶችን ያድን ዘንድ በሁሉ መንገድ ስለ ሁሉም ሰዎች ሲል ሁሉን ነገር ሆነ። ሊያገኛቸው ከሚፈልጋቸው ሰዎች ጋራ ራሱን አመሳስሏል። ወንጌልን እንዳይሰሙ በሚያደናቅፍ በማንኛውም የአኗኗር ዘይቤው ከእነርሱ ጋራ ተመሳስሏል። ከራሱ መብት፣ ከራሱ ምቾት፣ ከባህሉም በላይ ለወንጌሉ ዋጋ ሰጥቷል። ወንጌልን በሚያቀርብ ጊዜ ማናቸውም የሚያስቆጣ ወይም የሚያሰናክል ነገር ቢኖር፣ መስቀሉ እንጂ ሌላ እንዳይሆን ፈልጎ ነበር።

4. ጳውሎስ በመጽሐፍ ቅዱስ የታሰረ ነበር።

ዐራተኛ፣ ጳውሎስ በቅዱሳት መጻሕፍት ወሰን ውስጥ ራሱን ገድቧል። በመመሳሰልና በማላመድ ላይ በሰጠው መግለጫ መካከል፣ በጣም አስፈላጊ የሆነ ማብራሪያ አስገብቷል፦ “እኔ ራሴ ከእግዚአብሔር ሕግ ነጻ ያልሆንሁና፣ ለክርስቶስ ሕግ የምገዛ ብሆንም፣” (ቁ. 21) የሚል። ምንም እንኳ የሥርዐት ሕጉን መጠበቅ ከሚጠይቀው መስፈርትም ሆነ የአምላክን ሕግ ፍጹም ባለማድረግ ከሚያስከትል ቅጣት ነጻ ቢሆንም፣ ጳውሎስ አሁንም ራሱን በቃሉ ውስጥ በተገለጠው የአምላክ ሥልጣን ሥር እንደ ሆነ አድርጎ ይመለከት ነበር። ሊደርሳቸው ከሚፈልጋቸው ሰዎች ለመላመድ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት (በነገረ መለኮታቸው፣ በንጽረተ ዓለማቸው፣ በትእዛዛትና በመርሖቻቸው) ድንበር ሆነውታል።

ይህ ለእኛም ይሠራል። ማንኛውም የሰው ባህል፣ የጋርዮሽ ጸጋን[1] ያንጸባርቃል፤ ነገር ግን እያንዳንዱ ባህል ውድቀትንም ያንጸባርቃል። ስለዚህ ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ከሚቃረነው ባህል ጋር አንላመድም። ጳውሎስ ስለዚህ መርሖ ያለው ግንዛቤ ግልጽ ነው። በዙሪያው ያለውን ታዋቂውን የሄለናዊውን ንጽረተ ዓለም “ጥበብ” ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም፤ ምክንያቱም ምንም ያኽል የተራቀቀ ቢመስልም፣ ከሥር መሠረቱ ወንጌልን እንደሚቃረን ስለ ተገነዘበ ነው። በርግጥም ጳውሎስ በአስተምህሮ ጉዳዮች ላይ ልዩነትን ወይም አካታችነትን ፈጽሞ አልፈቀደም። የዘመኑ ተጓዥ አስተማሪዎች ልምምዶችን አላስተናገደም። በርግጠኝነት የቆሮንቶስ ማኅበረ ሰብ “ተቀባይነት ያለው” ምግባረ ብልሹነትን አልተቀበለም። የሰው ባህልና የሰው ወግ ለድርድር የሚቀርቡ ናቸው፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይደለም። መቼም።

መደምደሚያ

ዐውዳዊነት መወገድ የማይችልም መልካምም ነው። ወንጌሉ በሁሉም ባህል ቤተኛ መሆን ይችላል፤ መሆንም አለበት። ምንም ዐይነት ምቾት ቢያሳጣን፣ ልንደርስባቸው ከምንሞክራቸው ሰዎችና ከባህላቸው ጋር መመሳሰል አለብን። ነገር ግን፣ ወንጌል እያንዳንዱን ባህል (የራሳችንን ጨምሮ) በአንዳንድ ጉዳዮች ይሞግታል ያወግዛልም። መጽሐፍ ቅዱስ መስመር ሲያበጅ፣ እኛም መስመር ማበጀት አለብን። የዐውዳዊነት ዐላማ ምቾት ሳይሆን ግልጽነት ነው። ወንጌል፣ ለወደቀ ለማንኛውም ማኅበረ ሰብም ሆነ ለማንኛውም ኀጢአተኛ ሰው በፍጹም አይመችም። ግባችን እኛው ራሳችን በወንጌሉ መንገድ ላይ ምንም ዐይነት እንቅፋት እንዳንፈጥር፣ ነገር ግን ብቸኛው ማሰናከያ የመስቀሉ ማሰናከያና የዚያ መስቀልም ትርጉም ለሁሉም ግልጽ እንዲሆን ማድረግ ነው።

ዜን ፕራት

የአርታዒ ማስታወሻ፦ ይህ ዐምድ በሳውዝ ኢስተርን ሴሚናሪየም በታይምስ ጦማር ሊነበብ የሚችል ተከታታይ ትምህርት እጣሪ ነው።


[1] Common Grace