ከሚያዳምጡትም ሴቶች መካከል ልድያ የምትባል አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም እግዚአብሔርን የምታመልክና ከትያጥሮን ከተማ የመጣች የቀይ ሐር ነጋዴ ነበረች። ጌታም፣ ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል ትሰማ ዘንድ፣ ልቧን ከፈተላት። (ሐዋሪያት ሥራ 16፥14)
ጳውሎስ በሰበከባቸው ቦታዎች ሁሉ አንዳንዶች የሰሙትን የወንጌል ቃል አምነው ሲቀበሉ፣ ሌሎች ደግሞ አያምኑም። በኃጢአታቸው እና በበደላቸው ሙታን ከሆኑት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ በንስኀ ሲመለሱ፣ ሌሎቹ ግን ያላመኑበትን እና በዐመጻቸው የጸኑበትን ምክንያት እንዴት እንረዳዋለን? (ኤፌሶን 2፥1፣ 5)
“አንዳንዶች ለምን አላመኑም?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ፣ “ስለናቁት ነው” የሚል ነው (ሐዋሪያት 13፥46)። ምክንያቱም የወንጌሉ መልእክት ለእነርሱ ሞኝነት ነው፣ ሊረዱትም አይችሉም (1 ቆሮንቶስ 2፥14)። “ለኀጢአት የተገዛ አእምሮ ከእግዚአብሔር ጋር ጠበኛ ነው፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛም፤ መገዛትም አይችልም” (ሮሜ 8፥7)።
ወንጌልን ሰምቶ የማይቀበለው፣ “ብርሃንን ይጠላል፤ አድራጎቱም እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም” (ዮሐንስ 3፥20)። “እነርሱ ከልባቸው መደንደን የተነሣ ስለማያስተውሉ ልቦናቸው ጨልሞአል” (ኤፌሶን 4፥18)። ይህ አለማወቅ ራሱ በደል ነው። እውነቱ የተገለጠ ነው። ነገር ግን “በክፋታቸው እውነትን ዐፍነው” ይይዛሉ (ሮሜ 1፥18)።
ግን ታዲያ ሁሉም በበደላቸው ሙታን ከሆኑና በልብ ድንዳኔ ውስጥ ካሉ፣ ለምን አንዳንዶች ያምናሉ? የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ቢያንስ በሦስት የተለያዩ መንገዶች ለዚህ መልስ ይሰጠናል። አንደኛው መንገድ ለማመን የተቀጠሩ ናቸው የሚል ነው። ጳውሎስ በጲሲዲያ ውስጥ ባለችው አንጾኪያ በሰበከ ጊዜ፣ አህዛብ ደስ አላቸው፤ “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁትም ሁሉ አመኑ” (ሐዋሪያት 13፥48)።
አንዳንዶች ብቻ እንዴት ያምናሉ ለሚለው ጥያቄ ሌላ መልስ መስጠት የሚቻልበት መንገድ ደግሞ፣ ራሱ እግዚአብሔር ንስሓን ይሰጣል የሚል ነው። በኢየሩሳሌም የነበሩ ቅዱሳን፣ አይሁድ ብቻ ሳይሆኑ አህዛብም ለወንጌል ምላሽ እየሰጡ እንደሆነ በሰሙ ጊዜ፣ “ይህማ ከሆነ፣ አሕዛብም ወደ ሕይወት ይመጡ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ንስሓን ሰጥቷቸዋል ማለት ነዋ” አሉ (ሐዋሪያት 11፥18)።
ከሁሉም በላይ ግን፣ አንድ ሰው ወንጌልን ለምን ያምናል ለሚለው ጥያቄ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ያለው ግልጽ መልስ፣ እግዚአብሔር ልብን ስለሚከፍት ነው የሚል ነው። ለዚህም ደግሞ ልዲያ በጣም ጥሩ ምሳሌ ናት። ለምን አመነች? ሐዋሪያት ሥራ 16፥14 እንዲህ ይላል፦ “ጌታም፣ ጳውሎስ የሚናገረውን በማስተዋል ትሰማ ዘንድ፣ ልቧን ከፈተላት።”
እናንተም በኢየሱስ የምታምኑ ከሆናችሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሆነውላችኋል፦ እንድታምኑ ተወስናችኋል፣ ንስሓ ተሰጥቷችኋል፣ ደግሞም ጌታ ልባችሁን ከፍቷል። ይህ ሁሉ የሆነው ከእርሱ እንጂ ከእናንተ አይደለም። ቀሪ ዘመናችሁን ሁሉ፣ የዚህ አስደናቂ ተዓምር ተካፋይ በመሆናችሁ እየተደነቃችሁና እያመሰገናችሁ፣ በአምልኮና በመሰጠት ልትኖሩ ይገባል።