ካለብን የኀጢአት እስራት ለማምለጥ በክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር ክብር ልንቀርብ ይገባናል። ብቸኛው ተስፋችን እርሱ ነው።
በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የነገረ መለኮት ምሁሩ ጆናታን ኤድዋርድስ የተካነ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ ውስጥ የእግዚአብሔርን ክብር እና ውበት አስተዋለ፤ ይህንንም ስለ ክርስቲያናዊ ሕይወት ያለው መረዳት ማዕከል አደረገው።
ኤድዋርድስን በተለምዶ ኀጥአንን በገመድ አስሮ በእግዚአብሔር የሚነድድ ቁጣ አፋፍ ላይ የሚያንጠለጥል ስለ ሲኦል እሳት ብቻ የሚሰብክ ሰባኪ አድርጎ መረዳት ስለ አገልግሎት ዘመኑ ሚዛናዊ ያልሆነ ምስል መያዝ ነው። በመለኮታዊ ቁጣ ሰዎች ከሲኦል እንዲያመልጡ በማስፈራራት የታወቀ ሊሆን ቢችልም፣ አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፈው በወንጌል ውስጥ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ውበት በማወጅ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማይ እንዲገቡ በመማረክ ነበር። ዴን ኦርትለንድ፣ “ኤድዋርድስ እና የክርስትና ኑሮ፦ ለእግዚአብሔር ውበት ሕያው መሆን” በሚል መጽሐፉ ላይ ስለዚህም ጉዳይ ጽፏል።
ለእግዚአብሔር ውበት ያለን ይህ ጥልቅ መሻት የክርስትና ኑሮን እሳት እንዲንቦገቦግ ያደርገዋል። በየዕለቱ የምንጠይቀው አንድን ነገር ነው፤ ይኸውም የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አናይ ዘንድ” ነው (መዝሙር 27፥4)። ደግሞም አብረን፣ “የሕዝብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ። ክብርና ግርማ በፊቱ ናቸው፤ ብርታትና ውበትም በመቅደሱ ውስጥ አሉ” (መዝሙር 96፥5-6) በማለት እንመሰክራለን።
የእግዚአብሔር ውበት ያስፈልገናል።
ታዲያ አሁን ላይ የእግዚአብሔር ግርማ ከዕለት ተለት ሕይወቴ ጋር ምን ያገናኘዋል? በሥራ መባተሌ ውስጥ፣ በፈተናዎቼ ውስጥ፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ ድርቀቴ ውስጥ ምን ስፍራ አለው? በክሮስዌይ መጽሐፍ ቅዱስ ህትመት ዳይሬክተርነት ከሚያገለግለው ዴን ኦርትለንድ ጋር በቅርቡ ለቃለ ምልልስ ተቀምጬ ነበር።
ውበት እና ባተሌነት
በመጀመሪያ የእግዚአብሔር ውበት ባተሌ እና የተጨነቀ ልባችንን ያሳርፋል።
“የእግዚአብሔር የጣፋጭ ምሕረቱ ውበት ርጋታን ይሰጠኛል፤ መልሼ እንድተነፍስና ተጨንቃ የምትራውጠው ልቤ እንድትረጋጋ ያደርጋታል” ይላል ዴን። “እንደ አንድ ግብረገባዊ ሰው ስንኖር ብዙ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች አሉት። በጭንቀቴ ሁሉ ውስጥ ልጁ ያደረገኝ እና ያጸደቀኝ ከቶ የማይጥለኝ ገር የሆነ አባቴ ነው።” ኤድዋርድስ ይህ በሚገባ ተሰምቶት ነበር። በተለይም ስብከቶቹን ወይም ደብዳቤዎቹን ስታነብብ የምታሸተው የሆነ ዐይነት መአዛ አለ። እግዚአብሔር እንደ አባት ለእርሱ ከነበረው ሩኅሩኅ እንክብካቤው የተነሣ የተወደደ እና በእርሱ የተጠበቀ እንደሆነ ይሰማው ነበር።
ውበት እና ፈተና
በሁለተኛነት ደግሞ የእግዚአብሔር ውበት የልባችንን መሻት ይሞላል። ይህም ደግሞ የኀጢአትና የፈተና ጠላቶቻችንን የምንፋለም ከሆነ አስፈላጊ ይሆናል። ዴን፣ “ደስታ የሚገኘው በምኞት ውስጥ በመረስረስ ነው እያለች ዓለም ትነግረኛለች” ሲል ይናገራል። በተቃራኒው ኤድዋርድስ በእግዚአብሔር ውበት በጸጥታ ስለ መደሰትና እንደ እኔ ያሉ ኀጢአተኞችን ወዳጅ በሆነው በኀያል ልጁ አማካኝነት ከእርሱ ጋር ኅብረት ስለማድረግ በተደጋጋሚ ይጽፋል። ኤድዋርድስ በደስታ ከሚለው ነገር ውስጥ አንዱ በእግዚአብሔር ደስ መሰኘት፣ ደስተኞች ያደርገናል የሚል ነው።
የክርስትና ኑሮ ዋነኛው ፍልሚያ የኀጢአትን እውነተኛ አስቀያሚነት ማወቅና አጥፊነቱንም መረዳት ነው። “ኀጢአት ሊገላችሁ ላለው ነገር ማባበያ መሣሪያ ነው” በማለት ዴን ይናገራል። “ወደ ኀጢአት ባሕር ዘልዬ ከመግባትና ከፍርድ እና ሲኦል እንዲሁም የሞት ዐለት ጋር ከመጋጨት ራሴን መከልከል አልችልም። ለማቆም ምንም ቆራጥነት የለኝም። ራሴን ላስቆመው አልችልም። ከዚህ የሚልቅ ጣፋጭ ነገር፣ ርቱዕ የሆነ ውበት ያስፈልገኛል። የማደርገውም የምወድደውን ነገር ብቻ ነው፤ ለዘላለም የምሆነው እንዲሁ ነው። በሌላ መልኩ ልኖር አልችልም። ምንም ይሁን ምንም ላረካው የሚገባኝ የውበት ጥማት አለብኝ።”
ሁላችንም አለብን። “ወጣት ሴት ፍለጋ ሚስቱን የተወ የሥልሳ ዓመት ሰውዬ ይሁን፣ ፖርኖግራፊ የሚያየው ወጣት፣ አሊያም የባንክ ሒሳቡን በየሰዓቱ የሚያየው የባንክ ሠራተኛ፣ ወይም የጉባኤው ሙገሳ ለነፍሱ የሚመግባት መጋቢ፣ እነዚህ በሙሉ በእውነት ሊወድዳቸው የሚፈልግ ትክክለኛው ሰው በቀጣዩ ክፍል እያለ፣ አሻንጉሊት ወስደው ሜካፕ በመቀባት እንደ ትዳር አጋራቸው እየቆጠሩና እንደ ትዳር አጋራቸው እንዲወድዷቸው እየጠበቁ ነው።”
ውበት እና ድብርት
የእግዚአብሔር ውበት ጭንቀታችንን እና ፈተናዎቻችንን ተቃውሞ እንደሚቆም ሁሉ የድብርታችንን መንፈሳዊ አደጋንም ተቃውሞ ይቆማል።
ከአንድ ዓመት በፊት አንድ የስፖርት ሚዲያ፣ ክርስቶፈር ሌን ስለ ተባለ አንድ የኮሌጅ ቤዝ ቦል ተጫዋች አሳዛኝ ታሪክ አጋርቶ ነበር። ይህ ተጫዋች በዳንክን ኦክላሆማ በአንድ መንገድ ላይ ሲሮጥ ሦስት ዕድሜያቸው በዐሥራዎቹ ውስጥ ያሉ ልጆች ከጀርባው በመኪና በመምጣት ያለ ርኅራኄ ተኩሰው ገደሉት። እነዚህ ልጆች ኋላ ላይ ይህንን ድርጊታቸውን እንዲያብራሩ ሲጠየቁ ድርጊቱን የፈጸሙት “ደብሯቸው” ስለነበር እንደሆነ ተናገሩ።
ማርቲን ሎይድ ጆንስ እንዳለው “በአንድ መልኩ ኀጢአት ሁልጊዜ የድብርት ሕይወት ነው።”
ዴን ይህንን ሲያብራራ፣ “ኀጢአት የሚወስደን ወደዚያ ነው። ከብዙ ምክንያቶች መካከል ሲኦልን ሲኦል ያደረገው በድብርት የተሞላ ቦታ ስለሆነ ነው።” አዎን በድብርት የተሞላ ነው። ምክንያቱም ሲኦል ከውጪ ላለው ውበት ዐይኑ በታወረ፣ ውሰጡ እርካታ በሌለው፣ ውጪው ደስታ አልባ በሆነ ራስ ወዳድነት ለዘላለም እየደቀቀ ስላለ ነው።
ይሁን እንጂ በሌላ በኩል “ቅድስና አዝናኝ ነገር ነው” ይላል ዴን በጥንቃቄ። “እንደዚያ ማለት እችላለሁ? ቅድስና አዝናኝ ነው። ንጹሕ ነው። ወደ ሥላሴ ፍቅር ስለተሻገርን ቅድስና ብሩህ ነው ጨለማ አይደለም። ጸድቀናል። ዳግም ሰዎች ሆነናል።”
ይህ የቅድስና ምስል ከተለመደው ተጻራሪ ነው።
“ቅድስና የሚለውን ቃል ስንሰማ ቶሎ ወደ አዕምሯችን የሚመጣልን ነገር ምንድን ነው?” በማለት ዴን ይጠይቃል። ኮስታራ፣ ጨምዳዳ፣ አስፈሪ ፊት። ከቀደምት ስብከቶቹ ውስጥ በአንዱ ላይ ኤድዋርድስ እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ቅድስና በጣም ውብ የሆነ ጣፋጭ ነገር ነው። ብዙ ጊዜ ሰዎች ስለ ቅድስና ሲያስቡ መራር እና አስከፊ ነገር እንደሆነ የመሳሰሉ ግር የሚሉ አመለካከቶችን ከልጅነታቸው ወራት የመቅዳትና የመጋት ዝንባሌ አላቸው። ነገር ግን ቅድስና ውስጥ ጣፋጭ እና አስደሳች ነገር እንጂ ሌላ ምንም የለም ይላል ኤድዋርድስ። ኀጢአት ረመጥ እና ቆሻሻ ነው። ቅድስና ጣፋጭ፣ ደስ የሚያሰኝ፣ ሰላም ያለው እና የተረጋጋ ነው። ይህ እኔን ያርመኛል። ቅድስና እርጋታን የሚሰጥ ነው። ሕይወቴን ደስ ላሰኝበት የምችለው ብቸኛ መንገድ ነው። ምክንያቱም ዓለም በምትሰጠው የውሸት የደስታ መንገዶች ደስ ስለማልሰኝ ነው። ቅድስና በዝምታ ጮቤ የሚያስረግጥ ነው። ከቅድስና ደማቅ ብርሀን ውጪ የት መኖር ትሻላችሁ?
ውበት እና ዘላለም
እውነተኛ ደስታ የሚለካው የመዝናኛ መንገዶችን ተጠቅሞ ከድብርት በመውጣት አይደለም። ለአንድ ጥሩ ምክንያት ይህ የሚሠራ መንገድ አይደለም። “ያለ ደስታ የክርስትና ኑሮ በትክክል አይሠራም” ይላል ዴን በሙሉ ልብ። ይሁን እንጂ አስቂኝ የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች የበለጠ መመልከት አለባችሁ ማለት አይደለም። ሳቅ ትክክለኛ የደስታ መለኪያ አይደለም። ቴሌቭዥን ላይ የሚታዩትን ሁሉንም የኮሜዲ ፕሮግራሞች ተመልክታችሁ ብታሟጥጡ፣ ደስታችሁ ግን የእናንተ ባልሆነ ስፍራ እንደ ተቀበረ ይቆያል።
ይሁን እንጂ ዴን መናኝ አይደለም። በመጽሐፉ ላይ እንዲህ በማለት ይጽፋል “የደስታ ቀመር፦ ደስታ የሚገኘው ከእግዚአብሔር ሲደመር ‘ልትጠቅሷቸው በምትችሉት የእናንተ ነገሮች ’ ውስጥ ሳይሆን እግዚአብሔር ነው በ’እናንተ ነገሮች’ ውስጥ ደስታን የሚሰጠው” (ገጽ 77)። ቀጥሎም ሲያብራራ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ከእግዚአብሔር እና ሥራ፣ ቤተሰብ፣ ወሲብ፣ ጓደኞች፣ ዕረፍት፣ ጥሩ መኪና ከመንዳት፣ ቤት ከመግዛት፣ መጽሐፍ ከማንበብ፣ ቡና ከመጠጣት አይደለም። ይልቁንም እውነተኛ ደስታ የሚገኘው በእነዚህ ነገሮች ውስጥ ከእግዚአብሔር ነው።… ከፏፏቴው ጩኸት እስከ ወፎቹ ዜማ፣ ከእውነተኛ ወዳጅነት ግርማ እስከ አስደናቂ ወሲባዊ ልምምድ፣ በዚህ ዓለም ውስጥ የምንቀምሰው እያንዳንዱ ውበት ከመለኮታዊ የውበት ውቅያኖስ ጠብ ያለ ነው። እያንዳንዱ ፍስሓ ወደ ራሱ ወደ እግዚአብሔር መልሶ የሚጠቁም ነው። ደስታ የሚገኘው ከእግዚአብሔር እና በመጨረሻም በእግዚአብሔር ውስጥ ብቻ ነው” (ገጽ 79)።
ባደረግነው ቃለ ምልልስ ላይ ዴን ረገጥ አድርጎ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ምናልባት ርኅራኄ የጎደለው ሊመስል ቢችልም የምንወዳቸው ሰዎች ሲሞቱ የምናዝንበት ምክንያት የለንም ይላል ኤድዋርድስ። ምክንያቱም ደግሞ በምንወዳቸው ሰዎች ውስጥ እንወደው የነበረውን ነገር በሙሉ በሰማይ ለዘላለም በክርስቶስ ውስጥ ስለምናገኘው ነው። ክርስቶስ ራሱ ሁሉንም ደስታዎች አጠቃልሎ የያዘ ነው። ክርስቶስ ካላችሁ ሁሉም ደስታ አላችሁ።”
በሰማይ ከጓደኞቻችን እና ቤተሰቦቻችን ጋር ጣፋጭ የሆኑ መልሶ የመገናኛ ጊዜዎች የሉም እያለ አይደለም። ነገር ግን እያለ ያለው፣ በእነዚህ ዳግም የመገናኘት ወቅቶች ውስጥ ሳይቀር ደስ የሚያሰኙ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው የምንወዳቸው ሰዎች ሲደመር እግዚአብሔር ሳይሆን በምንወዳቸው ሰዎች ውስጥ ከእግዚአብሔር ውበት ጋር ስለምንገናኝ ነው።
ውበት እና ድባቴ
ይሁን እንጂ ስለ ውበት ያወራነው ይህ ሁሉ ወሬ ክርስቲያኖችን ከሰቆቃ እና ድባቴ አይጋርዳቸውም። ከዴን ጋር በነበረን የቃለ ምልልሳችን መቋጫ ላይ በድባቴ ውስጥ ላሉና የእግዚአብሔርን ውበት መመልከት ላቃታቸው፣ በመንፈስ ድርቀት ወራቶች ውስጥ እያሳለፉ ላሉ ሰዎች ምን ዐይነት ምክር ሊሰጣቸው እንደሚችል ጠይቄው ነበር። እንደዚህ ላሉ ሰዎች ኤድዋርድስ ቢሆን ምን ይላቸው ነበር?
ዴን ስድስት ምክሮችን አቅርቧል።
የመጀመሪያው ጤነኛ ያልሆናችሁ አይደላችሁም። ስለዚህ ተረጋጉ። ሁላችንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በዚህ ነገር ውስጥ እናልፋለን።
ሁለተኛ፣ የደነዘዘ እና የማይንቀሳቀስ ሁኔታችሁ እናንተን እስካሳሰባችሁ ድረስ ኤድዋርድስን አያሳስበውም። እያሳሰባችሁ ያለው ጥያቄዎችን እየጠየቃችሁ ስለሆነ ነው። በሌላ አገላለጽ፣ ኤድዋርድስ ስለ ዳግም ውልደት እና ስለ ተቀየረ ልብ የበለጸገ መረዳት ነበረው። ያልተለወጠ ልብ እንደዚህ ላሉ ነገሮች ግድ እንደማይለው ያውቃል (ምናልባትም ይህንን ቃለ ምልልስ ጭምር አያነብም)።
ሦስተኛ፣ እግዚአብሔር በሕይወታችሁ ላይ የሚያሳልፈው ፍርድ በእግዚአብሔር ውበት መደሰታችሁ ታላቅነት ላይ ተመሥርቶ አይጠነክርም፤ ወይም ማነሱ ላይ ተመሥርቶ አይላላም። ይልቁንም የእግዚአብሔር ውበት አንደኛው መልክ፣ የአባትነት እንክብካቤው እና ፍቅሩ ይህንን ውበት መለማመዳችን ላይ የተመሠረተ አለመሆኑ ነው።
አራተኛ፣ በኀጢአት ውስጥ ስለምትኖሩ መንፈሳችሁ እንደ ደረቀ እና ባዶ እንደሆናችሁ ከተሰማችሁ እና ካወቃቸሁት ሕይወታችሁ ምን እንዲመስል ነው የምትጠብቁት?
አምስተኛ፣ በክርስቶስ ከሆናችሁ አንድ ቀን ወደዚህ ደረቅ እና ባዶ የሆነ በመከራ የተሞላ ሕይወት መለስ ብላችሁ ተመልክታችሁ የዚህ ዓለም መከራ በሙሉ (አሁን ያለንበት አንዳንዴም ደግሞ የሚያደቅቀን) ያበቃና በመጨረሻም ለመክበራችን እና ማንጸባረቃችን እንዲሁም ግርማ ለመልበሳችን አካል እንደሆነ ታያላችሁ። ስለዚህ ጽኑ።
ስድስት፣ በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ውስጥ ቆዩ። እነዚህ መዝሙሮች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተቀመጡት ሕይወታቸው ለደረቀባቸው እና ባዶ ለሆነባቸው ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚሉትን ነገር ለማቀበል ደግሞም አዕምሯቸውን ለመመለስ ነው። ምክንያቱም ለራሳቸው ከተተዉ ማድረግ የሚፈልጉት ብቸኛው ነገር ወይ አልጋ ውስጥ ተጠቅልሎ መተኛት፣ ወይ ሄዶ መስከር አሊያም ራሳቸውን ማጥፋት ስለሆነ ነው። ምክንያቱም የሕይወት ሥቃይ እጅጉን ታላቅ ነውና።