5 ቅደም ተከተሎች፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብን ጭብጥ እንዴት ማግኘት እችላለሁ?

“የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብን ጭብጥ እንዴት ማግኘት እችላለሁ?”

ይህ ጥያቄ በማገለግልባት ቤተ ክርስቲያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን መሪዎች እና ከተማሪ ሕብረት መሪዎች በተደጋጋሚ የምሰማው ጥያቄ ነው። ለእነርሱም ሆነ ለዚህ ጽሑፍ አንባቢያን፣ ከመጽሐፉ ክፍል በቀጥታ ወደ ዋናው ነጥብ፣ ወይም በተሻለ ሁኔታ ወደ ተግባራዊ ተዛምዶው የሚወስዳቸው አስማታዊ ቀመር እንዳለኝ እነግራቸዋለሁ።

ሆኖም ግን ያ አስማታዊ ቀመር የለኝም! ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ የትኛውም ክፍል ውስጥ ብትሆኑ፣ ጭብጡን ለማግኘት የሚረዱ ውስን ነገሮች እንዳሉ አስባለሁ።

1. መዋቅር እና አጽንዖት

በመጀመሪያ፣ የምንባቡን መዋቅር እና አጽንዖት ግምት ውስጥ አስገባ። እኔ በመዋቅር መጀመር እወዳለሁ፤ ወይም ምንባቤ እንዴት ወደ ተለያዩ ቁጥሮች እንደሚከፋፈል ለማየት እሞክራለሁ።

በርግጥ መዋቅር የምናገኝበት መንገድ በጥቂቱም ቢሆን በምንባቡ ዐይነት ላይ ይወሰናል። የትረካ ምንባብ እየተመለከትኩ ከሆነ፣ ግጭት እና ገፀ ባሕሪያት ጥናት አጋዥ ነገር ናቸው። መቼቱ፣ ጡዘቱ እና መፍትሔው ላይ ትኩረት እሰጣለሁ። ንግግር ወይም ደብዳቤ እየተመለከትኩ ከሆነ ደግሞ፣ ምክንያታዊ ነጥብ ያለው የሐሳብ ፍሰት እፈልጋለሁ። ግጥምን እያየሁ ከሆነ፣ የተለያዩ አንጓዎችን ለመለየትና እነርሱን ለማጠቃለል (ለማያያዝ) እሞክራለሁ።

እና በየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ብሆን፣ የተደጋገሙ ቃላትን እና ሐሳቦችን እፈልጋለሁ። የቃል በቃል ትርጉም እዚህ ላይ ይረዳል። ዋና ጥያቄዬ፦ “ጸሐፊው ይህንን ክፍል እንዴት አዘጋጀው?” የሚለው ነው። እና አንድ ጊዜ መዋቅር መሳል ከጀመርኩ በኋላ፣ በዚህ መዋቅር ምን አጽንዖት እየተሰጠ እንደሆነ ራሴን እጠይቃለሁ።

2. ዐውድ

ሁለተኛ፣ ዐውዱን ተመልከት። አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ብቻውን አልቆመም። ይልቅ እያንዳንዱ ጽሑፍ በጸሐፊው ሆን ተብሎ የተቀናበረ የሙግት፣ የታሪክ ወይም የምንባቦች ስብስብ አካል ነው።

ከምንባቤ በፊት እና ከምንባቤ ቀጥሎ የሚመጣው ነገር አስፈላጊ ነው። የመረጥኩትን ምንባብ በደንብ እንድረዳው ያግዘኛል። እንዲሁም ጸሐፊው የሚናገረውን ርዕስ ለመገንዘብ፣ ደግሞም የመጽሐፉን ትልቅ ክፍል እንዳይ ሊረዳኝ ይችላል። በምንባቤ ውስጥ በተሳሰተ መንገድ ያነበብኩት ነገር ላይ ጠቃሚ እርማት ይሰጣል። እንዲያውም የመጀመሪያዎቹ ተደራሲያንን ታሪካዊ ዳራ ለመረዳት ይጠቅመኛል።

ዐውድ ቁልፍ ነው። ሆኖም የምርመራ ጥያቄዬ፦ “በዚህ የመጽሐፉ ቦታ፣ ጸሐፊው ይህን ክፍል ለምን እዚህ አስቀመጠው?” የሚለው ነው።

3. የመጽሐፉን አንኳር ሐሳቦች

ስለ ዐውድ የጠቀስኩትን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ስሜት የሚሰጠው ቀጣይ ጥያቄ እይታችንን ጎላ በማድረግ እና በማስፋት ስለ መጽሐፉ ይዘት ጥያቄ መጠየቅ ነው። የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ዋና አጀንዳ ምንድን ነው?

በርግጥ የአንድን ሙሉ መጽሐፍ ጭብጥ በትክክል ለመረዳት የተወሰነ ሥራ ይጠይቃል። ቢሆንም፣ “የእኔ ምንባብ (በተለይም በመዋቅር ውስጥ ያገኘሁት አጽንዖት) ከዚህ አጠቃላይ የመጽሐፉ ጭብጥ ጋር እንዴት ይዛመዳል?” ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ እርምጃ ይመስለኛል።

4. ሥነ መለኮታዊ እይታ

በሉቃስ 24፥13-49 ላይ ኢየሱስ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት በሙሉ ሞቱንና ትንሣኤውን እንደሚጠቁሙ፣ እነዚህም የወንጌል ውጤቶች ንስሓ እና የኃጢአት ስርየት መሆናቸውን ያስተምራል። ይህን ሳንረዳ፣ አንድን ክፍል ከግብረ ገብ አንጻር ብቻ ወይም በሆነ መንገድ ከወንጌል ነጥለን የመተርጎም አደጋ ያጋጥመናል።

ስለዚህ፣ “ይሄ ክፍል ከወንጌል ጋር እንዴት ይዛመዳል?” ብሎ ለመጠየቅ ሁሉንም የነገረ መለኮት መሣሪያዎች (በተለይ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የሥነ መለኮት ስልት) መጠቀም አስፈላጊ ነው። በርግጥ ይህን መጥፎ በሆኑ መንገዶች ለማድረግ ብዙ አማራጮች አሉ። ስለዚህ በምንባባችን እና በወንጌል መካከል ተገቢ ግንኙነት ማድረጋችንን መፈተን አስፈላጊ ነው።

5. ሁሉንም ማያያዝ

በመዋቅር፣ በዐውድ፣ በመጽሐፉ አንኳር እና በሥነ መለኮት ውስጥ ማድረግ የሚገባህን ሥራ ስትጨርስ፣ ሁሉንም ነጥቦች ምታገናኘው አሁን ነው። ይህንን ዋና ነጥብ፣ የምንባቡ ዋና ጭብጥ ወይም ትልቅ ሐሳብ ብለህ ብትጠራውም፣ ወደ መጨረሻው ደረጃ መቀጠሉ አስፈላጊ ነው። እኔ ራሴን መጠየቅ የምፈልገው ጥያቄ፦ “ጸሐፊው የመጀመሪያ አድማጮቹን ለማስተማር እየሞከረ ያለው ምንድን ነው?” የሚለው ነው። ምን እያለ ነው? የእርሱ ዋና ነጥብ ምንድን ነው?

ራስህን አታሞኝ! ይህ ቀላል ሂደት አይደለም። አነስ ላለ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን፣ የአንድ ወይም ሁለት ሰዓት ዝግጅት ያስፈልገዋል። ለስብከት ደግሞ ምናልባት የ12 ሰዓታት ዝግጅት! ነገር ግን ምንም ያህል ጊዜ ቢኖርህ፣ በዚህ መንገድ መሥራት ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ።

በርግጥ ዋናውን ሐሳብ ከተረዳህ፣ ስለ ተግባራዊ ምልከታዎች ማሰብ አለብህ። አሁንም ቢሆን፣ ምንባቡን ለመረዳት የምጀምረው በእነዚህ ቅደም ተከተሎች ነው፦

1. ጸሐፊው ይህንን ክፍል እንዴት አዋቀረው?

2. ጸሐፊው ይህንን ክፍል በዚህ ቦታ፣ በዚህ መንገድ ለምን አስቀመጠው?

3. ምንባቤ ከመጽሐፉ አንኳር ነጥቦች ጋር እንዴት ይገናኛል?

4. ምንባቤ ከወንጌል ጋር እንዴት ይገናኛል?

5. ጸሐፊው የመጀመሪያ ተደራሲያኑን ለማስተማር እየሞከረ ያለው ምንድን ነው?

ሮበርት ኪኒ


  • ጥቂት ለመጨመር፣ የዴቪድ ሄልም Expositional Preaching: How We Speak God’s Word Today (Crossway, forthcoming April 2014) የሚለውን መጽሐፍ ይመልከቱ።