እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ አማካኝነት ከእርሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረን፣ ዕድሉን ለእኛ አቅርቧል። የእግዚአብሔር ጥሪ ከእርሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረን ነው። ይህ ጥሪ ከምንም ነገር በላይ በእርሱ ላይ ያለንን እምነት የሚፈትን ነው (ያዕቆብ 1፥2-4)።
የጠበቀ ግንኙነት ማዕከል
ከአንድ ሰው ጋር ቅርብ የሆነ ግንኙነት አለን የምንለው፣ ያንን ሰው የእውነት ስናውቀው እና በዚያም ሰው ደግሞ ስንታወቅ ነው። ብዙ ጊዜ ይህንን ተሞክሮ ለመግለጽ፣ ከስፍራ ጋር የተያያዘ አነጋገር እንጠቀማለን። የቅርብ ጓደኛ የምንለው ሰው፣ ለልባችን ቅርብ የሆነና በጠለቀ መንገድ የሚያውቀን ሰው ነው። ከጓደኛችን ጋር ያለንን የጠበቀ ግንኙነት የሚጎዳ ነገር ከተፈጠረ ደግሞ፣ ልባችን ከዚያ ሰው ይርቃል። ወይም ለልባችን ቅርብ በሆነ መንገድ የማያውቀን ሰው፣ በጠለቀ መንገድ አያውቀንም።
ነገር ግን ከሰው ጋር ያለን የጠበቀ ግንኙነት፣ በአንጻራዊ ቦታ ላይ ሳይሆን በግንኙነት ላይ የተመሠረተ ነው። ሁላችንም ከጎናችን ከተቀመጠው ሰው ልባችን ርቆ፣ ስድስት ሺህ ኪሎ ሜትር ርቆ ካለው ሰው ጋር የቀረበ ግንኙነት ሊኖረን ይችላል።
ከሌላ ሰው ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለን እንዲሰማን የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው? በርግጥ በደንብ ለመቀራረብ አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ ነገሮች ቢኖሩም፣ ለሁሉም የጋራ የሆነው ግን እምነት ነው። ከማናምነው ሰው ጋር የጠበቀ ግንኙነት ሊኖረን አይችልም።
እምነት ከሰው ጋር ላለን የጠበቀ ግንኙነት ማዕከል ነው። አንድ ሰውን ባመንነው ቁጥር፣ ይበልጥ ወደ ልባችን እናስጠጋዋለን። እምነታችን በሚሸረሸርበት ልክ ደግሞ፣ ቅርበታችንም በዚያው ልክ ይቀንሳል።
ከእግዚአብሔር ጋር ላለን የቀረበ ግንኙነት ማዕከል
ይህ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት እውነት እንደሆነ ሁሉ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነትም እንደዚሁ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር አለን ብለን የምናስበው ቅርበት ወይም ርቀት፣ ከእርሱ ጋር ያለንን እውነተኛ ቅርበት አይገልጽም። ቅዱሳት መጻሕፍት፣ እግዚአብሔር ከሚያምኑት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው ይናገራሉ። እግዚአብሔርን ይበልጥ ባመንነው ቁጥር፣ ይበልጥ እናውቀዋለን። ከእግዚአብሔር የሚያርቀን፣ በእርሱ ላይ ያለንን እምነት የሚሸረሽር ነገር ነው፤ ይኸውም ኀጢአት ነው። ይህንን መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው። እንደ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረን እንፈልጋለን። ከዘማሪውም ጋር አብረን እንዲህ እንላለን፤ “ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል” (መዝሙር 73፥28)። የያዕቆብን ምክር እና በምክሩ ውስጥ የሚገኘውን ተስፋ ወራሾች መሆን እንፈልጋለን። “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” (ያዕቆብ 4፥8)። ነገር ግን ይህንን ቅርበት በማይፈጥሩ መንገዶች እንፈልገዋለን።
የጠበቀ ግንኙነት ከዕውቀት በላይ ነው
አንዱ የተለመደው ስሕተት፣ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ የሚቻለው በዕውቀት ክምችት እንደሆነ ማሰብ ነው። በርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረን፣ ስለ እግዚአብሔር ማወቅ ያለብን አስፈላጊ ነገሮች አሉ። ኢየሱስ እንዲህ ይላል፦ “እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም ነፃ ያወጣችኋል” (ዮሐንስ 8፥32)። ኢየሱስ ብዙዎች የማያውቁትን እንደሚያመልኩ ይናገራል (ዮሐንስ 4፥22)።
ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ እንደ አሁኑ ጊዜ ነገረ መለኮታዊ ዕውቀት ለብዙ ሰዎች የተዳረሰበት ዘመን የለም። የአሜሪካ ቤተ ክርስቲያን የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሆናለች። በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ በጽሑፎች፣ በሚያንጹ መጻሕፍት፣ በመንፈሳዊ ፊልሞች፣ በመዝሙሮች፣ በዘጋቢ ፊልሞች፣ በተቀዱ ስብከቶች ተሞልታለች። ይህ እጅግ መልካም ነው። ለዚህም ማመስገን አለብን።
ነገር ግን አሜሪካ፣ እንደ ሄኖክ አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ባደረጉ እና ከእርሱም ጋር የጠበቀ ግንኙነት ባላቸው ሰዎች አልተሞላችም (ዘፍጥረት 5፥24፤ ዕብራውያን 11፥5)። ለምን? ዕውቀት እና እምነት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ለዚህም ነው ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩ፣ የላቀ ዕውቀት ለነበራቸው የሃይማኖት መሪዎች እንዲህ ያለው፣ “በእነርሱ የዘላለም ሕይወትን የምታገኙ እየመሰላችሁ፣ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ እነዚሁ መጻሕፍት ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ እናንተ ግን፣ ሕይወት እንዲኖራችሁ ወደ እኔ መምጣት አትፈልጉም” (ዮሐንስ 5፥39-40)።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕውቀት፣ በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት ለመጨመር ስንጠቀመው ከወርቅ ይልቅ የከበረ ይሆናል (መዝሙር 19፥10)። ነገር ግን ይህ ዕውቀት፣ በእግዚአብሔር ላይ ያለንን እምነት ከተካ፣ ትዕቢትን ያመጣል (1ኛ ቆሮንቶስ 8፥1)።
ውበት የተላበሱ ሰው ሠራሽ ልምምዶች፣ ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት የማያመጡት ለምንድን ነው?
ሌላው የተለመደ ስሕተት፣ ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረን፣ ግላዊና ውበት የተላበሱ ሰው ሠራሽ ልምምዶችን መለማመድ ነው። ይህንን “የሕልም መስክ” አካሄድ ልንለው እንችላለን። ይህ አካሄድ (ትክክለኛውን ስፍራ እና ሁኔታ ማዘጋጀት ከቻልን) እግዚአብሔር “ይመጣል” የሚል ነው።
አንዳንዶች ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት የላቀ እና ሚስጥራዊ እንደሆነ እንዲሰማቸው ከፍ ያሉ የአምልኮ ስፍራዎችን ይመርጣሉ። ሌሎች ደግሞ ውስጣዊ ስሜቶችን ለማነሣሣት የተዘጋጁ መንፈሳዊ ኮንፍረንሶች ላይ ይሳተፋሉ። ሌሎችም ወደ እግዚአብሔር ኀይል መቅረብ፣ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንደሆነ በማሰብ መንፈሳዊ ሪቫይቫል ያሳድዳሉ። እነዚህ ሁሉ እውነተኛ እምነት ካለን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ሊያጠነክሩ ይችላሉ። ነገር ግን አንዳቸውም በራሳቸው ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረን የማድረግ አቅም የላቸውም።
“እግዚአብሔር የሚደነቀው፣ በእምነታችን እንጂ ባስመዘገብነው ድል አይደለም።”
እንዲህ ብላችሁ አስቡ፣ በሻማ የታጀበ የራት ግብዣ እና የፍቅር ሙዚቃ፣ በባልና በሚስት መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያጠነክር ይችላል። ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው በሁለቱም መካከል የጋራ መተማመን እና ፍቅር ካለ ብቻ ነው። በመካከላቸው አለመተማመን ካለ ግን የቦታው ውበት በመካከላቸው ያለውን ክፍተት ሊሞላ አይችልም። የዚህ ብቸኛው አማራጭ፣ እምነትን ወደ ነበረበት ስፍራ መመለስ ብቻ ነው።
ወደ እግዚአብሔር እንዴት እንቅረብ?
ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት እና እርሱም ወደ እኛ የሚቀርብበት ምስጢር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በግልጽ ተቀምጦልናል። ወደ እግዚአብሔር ልንቀርብ የምንችለው በእምነት በኩል፣ በክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር ስንጠጋ ብቻ ነው (ዕብራውያን 4፥14-16፣ 7፥25፤ ፊልጵስዩስ 3፥9)። በክርስቶስ ስለምናገኘው “እጅግ ታላቅና ክቡር የሆነውን ተስፋ” እንተማመናለን (2ኛ ጴጥሮስ 1፥4፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 1፥20)።
እግዚአብሔር የሚደነቀው፣ በእምነታችን እንጂ ባስመዘገብነው ድል አይደለም። እምነታችን ሲጎድል እግዚአብሔር በዕውቀታችን ብዛት እና በምናዘጋጀው ውብ ስፍራዎች አይደሰትም።
ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት (ዕብራውያን 11፥6)።
በፍጹም ልባቸው የእግዚአብሔርን ተስፋ ለሚተማመኑ እና በእነርሱም ለሚኖሩ ቅዱሳን የእግዚአብሔር እርዳታ ይከተላቸዋል (2ኛ ዜና 16፥9)፤ ለእነርሱም ራሱን ይገልጣል።
“የሚወድደኝ ትእዛዜን ተቀብሎ የሚጠብቅ ነው፤ የሚወድደኝንም አባቴ ይወድደዋል፤ እኔም እወድደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ” (ዮሐንስ 14፥21)።
ወደ ጠበቀ ግንኙነት የእግዚአብሔር ግብዣ
እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረው ይፈልጋል። ለዚህ የሚያስፈልገውን ሥራ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ጨርሶታል። ከአንተ የሚፈልገው በእርሱ እንድታምን ብቻ ነው (ዮሐንስ 14፥1)። በፍጹም ልብህ እንድታምነው ይፈልጋል (ምሳሌ 3፥5)። ይህ ማለት ከእርሱ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖርህ ያቀረበው ግብዣ ክምንም ነገር በላይ እምነትህን የሚፈትን የእግዚአብሔር መግቦት ነው። እግዚአብሔርን አሁን ልታምነው የሚያስፈልገው፣ እርሱ ለአንተ ያለው ሐሳብ ወደ እርሱ እንድትጠጋ ስለሆነ ነው።
ሥጋህ ይህንን ግብዣ እንድትቀበል አይፈልግም። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስህን ስታነብ፣ እንደ ደመና በዙሪያችን የከበቡን ብዙ ምስክሮች (ዕብራውያን 12፥1)፣ ከያዕቆብ እና ከጴጥሮስ ጋር በመስማማት የእምነት መፈተን ወደ ላቀ ደስታ የሚያመራ መንገድ እንደሆነ ይናገራሉ (ያዕቆብ 1፥2-4፤ 1ኛ ጴጥሮስ 1፥8-9)። ከጳውሎስስ ጋር ክርስቶስን ከማወቅ እና ከሚመጣው ክብር ጋር ሊነጻጸር እንደማይችል ይስማማሉ (ፊልጵስዩስ 3፥8፤ ሮሜ 8፥18)።
እግዚአብሔርን ማመን እጅግ የሚያስፈልጉን ቦታዎች፣ ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት የሚኖረን ቦታዎች ናቸው። በምድር ላይ ያለ ሰማያዊ ሕይወት ማለት፣ በእግዚአብሔር ላይ በፍጹም ልብ በመታመን ከማስተዋል በላይ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሰላም እና ሊገለጽ የማይችለውን ደስታ ስናገኝ ነው (ፊልጵስዩስ 4፥6-7)። የድሮው የመዝሙር ጸሐፊ እንዳለው፣ “በእርሱ በፍጹም ልባቸው የሚታመኑት፣ ፍጹም እውነተኛ ሆነው ያገኙታል።”
በ ጆን ብሉም