እንዴት ሁሉም ነገር እንደ ጉድለት ይቆጠራል?

ስለ ክርስቶስ ሲባል ሁሉን እንደ ጉድለት መቁጠር ምን ማለት ነው? ስለ ክርስቶስ ስንልስ ያለንን ነገር ሁሉ መካድ ምን ማለት ነው?

ጳውሎስ ይህን እንደሚያደርግ ተናግሯል። “… ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት እቆጥረዋለሁ፤” (ፊልጵስዩስ 3፥8)።  ከጥቂት ጥቅሶች በኋላም እንዲህ ይላል፤ “ወንድሞች ሆይ፤ የእኔን አርኣያነት በመከተል … ” (ፊልጵስዩስ 3፥17)።

ስለዚህ ይህ ለአማኞች ሁሉ የቀረበ ትዕዛዝ ነው።

መሠረታዊ ክርስትና

ክርስቲያን መሆን ማለት ይህ ነው፤ የላቀ ደቀ መዝሙርነት ሳይሆን መሠረታዊ ክርስትና። ኢየሱስም ይህንን አስረግጦ ተናግሯል፤ “ከእናንተ ማንም ያለውን ሁሉ የማይተው፣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም” (ሉቃስ 14፥33)። ያለንን ሁሉ መተው “ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት ከመቁጠር” ጋር አንድ ነው። ስንለወጥ (at conversion) የሚሆነውም ይህ ነው። ያለ እርሱ ደቀ መዝሙር መሆን አይቻልም። ይህንንም ኢየሱስ በምሳሌ እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተደበቀ ሀብት ትመስላለች፥ አንድ ሰው ባገኛት ጊዜ መልሶ ሸሸጋት፤ ከመደሰቱም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ በመሸጥ ያንን የእርሻ ቦታ ገዛ” (ማቴዎስ 13፥44)። የመንግሥቱን ጥሪት ለማግኘት ያለንን ሁሉ በደስታ መሸጥ ስንል፣ ክርስቶስን ለማግኘት ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት መቍጠር የሚለውን ሃሳብ በምሳሌ እየገለጽን ነው።

ስለዚህ ክርስቲያን መሆን ከመንፈሳዊ ሞት መታወር መንቃት እና ኢየሱስን በቂ እና ሁሉን የሚያረካ ሆኖ ማግኘት ማለት ነው፤ ያን ጊዜም፣ (1) ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት እንቆጥራለን፤ (2) ንብረታችንን ሁሉ እንተዋለን፤ በምሳሌው አገላለጽ ደግሞ (3) የክርስቶስን ሀብት ለማግኘት ያለንን ሁሉ እንሸጣለን።

እንዴት ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት ይቆጠራል?

በዕለት ተዕለት ተግባራዊ አገላላጽ፣ ይህንን ማድረግ ምን ማለት ነው? ቢያንስ እነዚህን አራት ነገሮች ማለት ነው።

  1. ሁሉን መካድ (ሁሉንም እንደ ጉድለት መቁጠር) ማለት፣ ከክርስቶስ እና ከሌላ ከምንም ነገር መምረጥ ቢኖርብንክርስቶስን እንመርጣለን ማለት ነው።

ይህ ማለት፣ ምንም እንኳን እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ይሄ-ወይስ-ይሄ እያለ የምርጫ ቀውስ ውስጥ ባያስገባንም፣ ምርጫ ማድረግ ካለብን ግን፣ ክርስቶስን ለመምረጥ በልባችን ዝግጁ ሆነን ወስነናል ማለት ነው።

  1.  ሁሉን መካድ (ሁሉንም እንደ ጉድለት መቁጠር) ማለት ወደ ሕይወታችን የሚመጡትን ማንኛውንም ነገሮች፣ ወደ ክርስቶስ ለመቅረብ እና የበለጠ ክርስቶስን እንድናተርፍ፣ በእርሱም እንድንደሰት እንዲረዱን እንጠቀምባቸዋለን ማለት ነው።

ማለትም፣ ደስ የሚያሰኝን ነገር ሁሉ ክርስቶስን በማመስገን እንቀበላለን፤ እንዲሁም ሊጎዳንን የሚችልን ነገር ሁሉ በክርስቶስ በኩል በመታገስ እንቋቋማለን።

  1. ሁሉን መካድ (ሁሉንም እንደ ጉድለት መቁጠር) ማለት፣ የዚህ ዓለም ነገሮች የእኛ ሀብት እንዳልሆኑ፣ ይልቁንም ክርስቶስ ውዱ ሀብታችን መሆኑን በሚያሳይ መንገድ ለመያዝ ከልብ እንጥራለን ማለት ነው።

ማለትም፣ ነገሮችን ሳንጨነቅ እንይዛለን፤ በልግስና እናካፈላለን፤ ደግሞም ከክርስቶስ ጋር ለተያያዙ ነገሮች ዋጋ እንሰጣለን። በ1ኛ ቆሮንቶስ 7፥30-31 እንደተጻፈው ለመኖር እንተጋለን፦ “[ክርስቲያኖች] ዕቃ የሚገዙም የገዙት ነገር የእነርሱ እንዳልሆነ ይቁጠሩ፤ በዚህ ዓለም ነገር የሚጠቀሙም እንደ ማይጠቀሙበት ይሁኑ።”

  1. ሁሉንም መካድ (ሁሉንም እንደ ጉድለት መቁጠር) ማለት፣ ይህ ዓለም ሊሰጥ የሚችለውን ማንኛውንም ወይም ሁሉንም ነገር ብናጣ ደስታችንን፣ ጥሪታችንን፣ ወይም ሕይወታችንን አናጣም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ የእኛ ጥሪት፣ የእኛ ሐሴት እና ሕይወታችን ስለሆነ።

ይኸውም በትንንሽ ኪሳራ አናጉረምርም (ፊልጵስዩስ 2፥14)፤ ምናልባት በታላላቅ ኪሳራዎች ልናዝን እንችላለን፤ ነገር ግን ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች አንሆንም (1ኛ ተሰሎንቄ 4፥13)።

የተረጋጋ፣ ደስታ የሞላበት፣ ወሳኝ መፍትሔ

በእኔ እምነት ኢየሱስን ፍጹም በቂ እና ፈጽሞ የሚያረካ ሆኖ ማግኘት ማለት፦ (1) ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት  እንቆጥራለን (ፊልጵስዩስ 3፥8)፣ (2) ንብረታችንን ሁሉ እንተዋለን (ሉቃስ 14፥33) እና፣ (3) የክርስቶስን ሀብት ለማግኘት ያለንን ሁሉ እንሸጣለን ማለት ነው (ማቴዎስ 13፥44)።

ማናችንም ብንሆን ክርስቶስን እንደዚህ ፍጹም በሆነ መንገድ አንወደውም፤ ወይም በዘላቂነት እንዲህ አንኖርም። ነገር ግን እውነተኛ ክርስቲያን፣ የኢየሱስ ተከታይ መሆን ማለት፣ እነዚህ አራት “ከሁሉም ነገር” ጋር የተቆራኙ መንገዶች ለህይወታችን የተረጋጉ፣ ደስታ የሞላባቸው፣ ወሳኝ መፍትሔዎች እንዲሆኑ እናደርጋለን ማለት ነው።

ከጳውሎስ ጋር “ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋር ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጉድለት እቆጥረዋለሁ” ስንል ይህንን ማለታችን ነው።

ጆን ፓይፐር