“በዚህም ለዳዊት ቀንድ አበቅላለሁ፤ ለቀባሁትም ሰው መብራት አዘጋጃለሁ። ጠላቶቹን ኀፍረት አከናንባቸዋለሁ፤ እርሱ ግን በራሱ ላይ የደፋው ዘውድ ያበራል።” (መዝሙር 132፥17-18)
እግዚአብሔር ለዳዊት ከገባው ኪዳን ተጠቃሚ የሚሆነው ማነው?
መዝሙር 132፥17-18 በድጋሚ ይኸውና፦ “በዚህም ለዳዊት ቀንድ አበቅላለሁ፤ ለቀባሁትም ሰው መብራት አዘጋጃለሁ። ጠላቶቹን ኀፍረት አከናንባቸዋለሁ፤ እርሱ ግን በራሱ ላይ የደፋው ዘውድ ያበራል” ይላል።
አሁን ደግሞ ይህንን ከኢሳይያስ 55፥1-3 ጋር አገናኙት፦ “እናንት የተጠማችሁ ሁሉ ኑ፤ እናንት ገንዘብ የሌላችሁ፣ ወደ ውሆች ኑ፤ ኑና ግዙ፤ ብሉም፤ ኑና ያለ ገንዘብ፣ ያለ ዋጋ፣ የወይን ጠጅና ወተት ግዙ።… ለዳዊት በገባሁት በጽኑ ፍቅሬ፣ ከእናንተም ጋር የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ።”
ከመስቀሉ ታሪክ በዚህኛው በኩል ላለን ለእኛ፣ ይህ ቃል ኪዳን በሌላ መልኩ እንዲህ ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፦ ማንም ሰው እግዚአብሔር ለእኛ በክርስቶስ የሆነውን ተጠምቶ፣ በራሱ ማንነት ወይም በሥራው ሳይደገፍ፣ ወደ እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ቢመጣ፣ እግዚአብሔር ከዚያ ሰው ጋር ቃል ኪዳንን ይገባል።
በራእይ 22፥17 ላይ የመጨረሻዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ምን እንደሆኑ ታስታውሳላችሁ? “የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግም ሁሉ የሕይወትን ውሃ በነፃ ይውሰድ።” ይህ በኢሳይያስ ዘመን ለነበሩ አይሁዶች ብቻ አይደለም። ይህ ጥሪ የተደረገው የነፍሱን ጥማት ለማርካት ወደ ክርስቶስ ለሚመጣ ሁሉ ነው። “[ከእርሱ ጋር] ዘላለማዊ ቃል ኪዳኔን አደርጋለሁ” ይላል።
የምን ቃልኪዳን? እግዚአብሔር ለ“ዳዊት ባለው ጽኑ ፍቅር” የተወሰነና የተረጋገጠ ቃል ኪዳን። ኢሳይያስ 55፥3 እንዲህ ይላል፦ “ጆሮአችሁን ከፍታችሁ ወደ እኔ ቅረቡ፤ ነፍሳችሁም እንድትኖር አድምጡኝ። ለዳዊት በገባሁት በጽኑ ፍቅሬ፣ ከእናንተም ጋር የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ” ይላል። ይህ ማለት እኔም በዳዊት ቃል ኪዳን ውስጥ ተካትቻለሁ ማለት ነው። ዳዊት የሚያገኘውን ሁሉ እኔም ደግሞ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል አገኛለሁ።
ታዲያ ያ ምንን ያካትታል?
ቀንድ ይበቅልልኛል። ይህም ማለት የብርታት ሁሉ ምንጭ የሆነው ጌታ ለእኔ ይዋጋልኛል፤ እኔንም ይጠብቀኛል ማለት ነው። በእግዚአብሔር የተዘጋጀ መብራት ይኖረኛል። ይህም ማለት ብርሃን ይከበኛል፣ ጨለማም አያሸንፈኝም ማለት ነው። ለራሴ ዘውድ ይኖረኛል። ይህም ማለት ከዳዊት ልጅ ጋር እገዛለሁ፤ በእርሱም ዙፋን ላይ ከእርሱ ጋር እቀመጣለሁ። “ድል የሚነሣውንም ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ” (ራእይ 3፥21)።
ለዳዊት ከተገባው ቃል ኪዳን እኛ መጠቀም መቻላችን በጣም የሚያስገርም ነገር ነው። እግዚአብሔር እንድንገረም ይፈልጋል። የጥሞና ጊዜያችን ድንቅ ፍቅሩን በማሰላሰል የተሞላ እንዲሆን ይሻል። በእርሱ የተወደድንበትን ኀይል፣ ወደር የለሽ ሥልጣኑን እና የፍቅሩን እርግጠኝነት እያሰብን በመገረም እንሞላ።