ደስታ አማራጭ አይደለም

እግዚአብሔር ስለ ደስታችሁ ግድ ይለዋል

ደስታ ለክርስትና ሕይወት መሠረታዊ የሆነ ነገር ነው። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሐሤትን እንዲያደርጉ እንደታዘዙ፣ ያም ደግሞ መገለጫቸው ሊሆን እንደሚገባ ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ ይናገራሉ።

ደስታችንን በተመለከተ የሰማዩ አባታችን ግድ የለሽ አይደለም። ደስታ — እንደ ምግብ ማባያ አዋዜ — የክርስትና ሕይወታችንን ማጣፈጫ አይደለም። ወይም ዳቦ ላይ ሰሊጥ እንደምንነሰንሰውም አይደለም። ይልቁንም የሊጡ መሠረታዊ ውህድ ነው።

ይህ ማለት ግን፣ ሁል ጊዜ በሕይወታችን ደስታና ፌሽታ ብቻ ነው ያለው ማለት አይደለም። ይልቁንም፣ አስከፊ በሆኑ ሐዘኖቻችን እና መከራዎቻችን ውስጥ እንኳ፣ የክርስቲያኖች ደስታ ምን ያህል ጥልቅ ከሆነ ጎተራ እንደሚፈልቅ እንረዳለን። እንዲህ ባለ ከባድ እና ጨለማ ሁኔታ ውስጥ ብቻ ነው፣ የዚህን ደስታ መሠረታዊ ምንነት መቅመስ የምንችለው። ይህም ደስታ ከላይ ከላይ የሆነ፣ ባዶ እና ሚዛን የማይደፋ አይደለም። ይልቁንም በተቃራኒው፣ ስር የሰደደ፣ የተትረፈረፈ እና ትርጉም ያለው ነው።

ደስታን ማግኘት ይቻላል

‘ደስታ አማራጭ አይደለም’ የሚለውን ንግግር መስማት ለአንዳንዶች ተስፋን የሚሰጥ ነው። ደስታ መሠረታዊ የሆነ ነገር ነው ካልን፣ ያ ማለት ደስታን ማግኘት ይቻላል ማለት ነው። ኀጢአት እና መከራ በሞላባት፣ ውጥንቅጧ በወጣ እና ችጋር በበዛባት ዓለም ውስጥ፣ ደስታን ማግኘት እንደሚቻል መስማት እጅግ መልካም የሆነ ዜና ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያዩ ስፍራዎች ደስታ እንደ ትእዛዝ ተቀምጧል። የእግዚአብሔር የመጀመሪያ የቃል ኪዳን ሕዝቦች የሆኑት እስራኤላውያንም ይህንን ታዘዋል — በተለይም በመዝሙር መጽሐፍ። «እስራኤል በፈጣሪው ደስ ይበለው፤ የጽዮንም ልጆች በንጉሣቸው ሐሤት ያድርጉ» (መዝሙር 149፥2)። «ያዕቆብ ደስ ይበለው፤ እስራኤልም ሐሤት ያድርግ» (መዝሙር 14፥7)። «በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ» (መዝሙር 97፥12)። «እግዚአብሔርን በደስታ አገልግሉት» (መዝሙር 100፥2)። «ጻድቃን ሆይ፤ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤትም አድርጉ፤ ቅን ልብ ያላችሁም ሁሉ እልል በሉ» (መዝሙር 32፥11)። በብሉይ ኪዳን መጽሐፍት ውስጥ እንደ እነዚህ ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ትእዛዞች አሉ።  

ከእስራኤል በተጨማሪም፣ ዓለም ሁሉ በፈጣሪው ደስ እንዲለው እግዚአብሔር ያዝዛል። «ሕዝቦች ደስ ይበላቸው፤ በእልልታም ይዘምሩ» (መዝሙር 67፥4)። እንዲሁም፣ ፍጥረታዊው ዓለም እንኳ ሳይቀር ይህንን ደስታ እንዲቀላቀል ታዝዟል። «ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ ምድርም ሐሤት ታድርግ» (መዝሙር 96፥11)።

እንዲሁም በአዲስ ኪዳን ውስጥ፣ እግዚአብሔር ራሱ በፍጹም ሰውነቱ፣ በዚህች በወደቀችው ዓለማችን ውስጥ “የሕማም ሰው” ቢሆንም፣ ስለ ደስታ ያለውን አቋም ግን ለደቂቃ አልለወጠም (ኢሳይያስ 53፥3)። ይልቁንም ደስተኞች እንድንሆን ከማንም በላይ ያዝዘናል፤ ጨምሮም ደስተኞች የምንሆንበትን ምክንያት ይሰጠናል። «በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴት አድርጉ»(ማቴዎስ 5፥12)። «ደስ ይበላችሁ፤ ፈንድቁም» (ሉቃስ 6፥23)። «ስማችሁ ግን በሰማይ ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ» (ሉቃስ 10፥20)። አዎን፣ ደስታን ማግኘት ይቻላል። እውነተኛ የሆነን እና የተትረፈረፈን ደስታን ስናገኝም፣ ወደ ወዳጆቻችን እና ወደ ጎረቤቶቻችን በመዞር «ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ» እንላለን (ሉቃስ 15፥69)።

እያልኩ ያለሁት ነገር በሚገባ ግልጽ ካልሆነላችሁ፣ ጳውሎስ ለአብያተ ክርስቲያናት በሚጽፈው መልእክቱ ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል። «በተስፋ ደስተኞች ሁኑ . . . ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ» (ሮሜ 12፥1215)። «በተረፈ ወንድሞች ሆይ፤ ደኅና ሁኑ» (2ኛ ቆሮንቶስ 13፥11)። «ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ» (1ኛ ተሰሎንቄ 5፥16)። ከዚያም የፊልጵስዩስ መልእክቱን በደስታ ማዕበል ያጥለቀልቀዋል፦ «ከእኔ ጋር ደስ ልትሰኙና ሐሤት ልታደርጉ ይገባል» (ፊልጵስዩስ 2፥18)። «በጌታ ደስ ይበላችሁ» (ፊልጵስዩስ 3፥1)። «ምንጊዜም በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ» (ፊልጵስዩስ 4፥4)። ይህ ማለት ታዲያ፣ በዚህ ዘመን ለሚገጥሙን ፈርጀ ብዙ የሕይወት ህመሞች እንደነዝዛለን ማለት አይደለም። ይልቁንም፣ በታላቅ መከራ ውስጥ እንኳ እያለፍን፣ በክርስቶስ ግን ጥልቅ የሆነንና የላቀን ደስታ እናገኛለን። «ሐዘንተኞች ስንሆን ሁል ጊዜ ደስተኞች ነን» (2ኛ ቆሮንቶስ 6፥10)።

መጽሐፍ ቅዱስ ደስተኞች እንድንሆን ያለማቋረጥ ከሚጎተጉትበት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የእግዚአብሔር መልካምነት ነው። ደስተኞች ሁኑ የሚለው ትእዛዝ በእርሱ መልካምነት ላይ የተመሠረተ ነው። «አምላክህ እግዚአብሔር ለአንተና ለቤትህ በሰጠው በጎ ነገር ሁሉ ደስ ይበላችሁ» (ዘዳግም 26፥11)። በፍጥረት ልብ ውስጥ ያለው ደስታ፣ በፈጣሪ ልብ ውስጥ ካለው መልካምነት ጋር ተያያዥ ነው። ደስታ ለሰጪው መልካምነት ተቀባዩ የሚያቀርበው ተገቢ ምላሽ ነው።

ይሁን እንጂ ደስተኛ አይደለሁም

‘ደስተኞች ሁኑ’ የሚለውን ትእዛዝ፣ አንዳንዶች ‘ይቻላል’ በሚል ስሜት ሲቀበሉት፣ ሌሎች ግን ችግር ሆኖ ይታያቸዋል። ሁለቱም ምላሾች ግን በምክንያት የተደገፉ ናቸው። እኛ ከፍጥረታችን የሞትን ኀጢያተኞች ነን (ኤፌሶን 2፥1-3)። አብዛኛውን ጊዜም፣ ስሜታችን የሚዋዥቅና ለመንፈሳዊ ነገር የደነዘዝን ነን። በክርስቶስ ውስጥ ሆነን እንኳ እያለ፣ ዥዋዥዌ ላይ እንዳለ ሰው፣ በየዕለቱ፣ ከደደነዘዘ ልብ ወደ ተነቃቃ መንፈስ፣ ከዚያም መልሰን ወደ ድርቀት በመሄድ እንዋዥቃለን። 

ራሳችንን የምናውቅና እውነታን ተቀብሎ መኖርን እየተማርን ያለን ሰዎች ከሆንን፣ ከልብ ደስተኞች የምንሆንባቸው ጊዜያት ምን ያህል ጥቂት እንደሆኑ በማመን፣ አባታችንን ደግመን ደጋግመን፣ «የማዳንህን ደስታ መልስልኝ» እያልን እንማጸናለን (መዝሙር 51፥12)።

እንደነዚህ ላሉ ሰነፍና ራሳቸውን ለሚያውቁ ሰዎች፣ ደስታ አማራጭ እንዳልሆነ መስማት፣ ‘ይቻላል’ ከሚል ስሜት ይልቅ ኩነኔን ይፈጥርባቸዋል። በብዙ ሸክም ተዳክሞ ባለ ትከሻ ላይ ሌላ ተጨማሪ ቀንበርን እንደመጫን ነው።

ነገር ግን፣ ደስታን ያጡ ሰዎች መሆናችን የታሪኩ መደምደሚያ አይደለም። በስሌቱ ውስጥ አንድ ከመጠን በላይ ዋጋ ያለው ነገር ይቀራል።

እግዚአብሔር ለደስታችሁ ፈጽሞ ይተጋል

ማብቂያ የሌላቸውን ውድቀቶቻችንን ስናስብ፣ እግዚአብሔር ራሱ፣ በርሱ ለዘላለም ደስተኞች እስክንሆን ድረስ እንደሚተጋ መስማት፣ እጅግ ድንቅ የሆነ መልካም ዜና ነው። እንደውም በአንድ መልኩ፣ በአጽናፈ ዓለማችን ውስጥ ላለው የመግነን እና የመክበር ዓላማው ተሰጥቶ እንደሚሠራው ሁሉ፣ ልክ በዚያው መጠን፣ እኛም በእርሱ እንደሰት ዘንድ ተሰጥቶ ይሠራል ማለት እንችላለን። ምክንያቱም፣ የእኛ ደስታ እና የእርሱ ክብር አብረው የተሰፋ ነገሮች ናቸው። በሌላ አገላለጽ፣ ጆን ፓይፐር እንደሚለው፦ “እግዚአብሔር ከመቼውም ይልቅ በእናንተ የሚከብረው፣ እናንተ ከምንም በላይ በእርሱ ስትረኩ ነው።”

እግዚአብሔር ጻድቅ ስለሆነ ስለ ክብሩ ግድ የለሽ አይደለም። የልጁን ደም እና ጽድቅ የሙጥኝ ላልን ለእኛ ደግሞ፣ እግዚአብሔር ስለ ደስታችን ግድ የለሽ አለመሆኑ እጅግ መልካም የሆነ ዜና ነው። እርሱ ሊሰጠን የሚሻው ደስታ፣ የወደቀው ዓለም የሚሰጠውን ዐይነት ውጫዊ፣ ጊዜያዊ እና ባዶ የሆነ አይደለም። ይልቁንም፣ ትርጉም ያለው፣ ጥልቅ የሆነ፣ የተትረፈረፈ እና በዚህ ሕይወት ካሉ ደስታን ሊያሳጡ ከሚችሉ ሁኔታዎች በላይ ሞልቶ የሚፈስስ ነው።

ከእንግዲህ ወዲህ፣ በክርስቶስ አማካይነት፣ እግዚአብሔር በአስፈሪ ቁጣው ከእኛ ተቃርኖ አይቆምም፤ ይህ ብቻ ግን አይደለም፤ አሁን ላይ በሁሉን ቻይ ፍቅሩ ጥልቅ እና ዘላቂ ለሆነ ደስታችን ለእኛ ወግኖ ይሠራል። እግዚአብሔር በኤርምያስ በኩል የገባው ተስፋ በክርስቶስ በኩል አሁን የእኛ ሆኗል፦ «ለእነርሱ መልካም በማድረግ ደስ ይለኛል፤ በፍጹም ልቤና በፍጹም ነፍሴ በእውነት በዚህች ምድር እተክላቸዋለሁ» (ኤርምያስ 32፥41)።

በዚህች ዓለም እያለን ደስታችን ፍጹም አይሆንም፤ ሁልጊዜም ትግል እና ተግዳሮት ይገጥመናል። ስጋት እና ጭንቀትም ይኖሩብናል። በከፍታዎች እና በዝቅታዎችም እናልፋለን። ነገር ግን በዚህም ውስጥ እንኳ ደስታን መቅመሳችን አይቀርም። እውነታው ታላቅ ደስታ እየመጣ መሆኑ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን አሁንም እንኳ ሳይቀር ጣፋጭነቱን እናጣጥማለን — በተለይ በተለይ በመከራ ውስጥ ስናልፍ። «እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በእርሱ ታምናላችሁ፤ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሎአችኋል» (1ኛ ጴጥሮስ 1፥8)።

በክርስትና ሕይወት ውስጥ ደስታ አማራጭ አለመሆኑ መልካም የሆነ ዜና ነው፤ ምክንያቱም፣ ዋናው ሸክም በደካማው ጀርባችን ላይ ሳይሆን፣ በራሱ በኀያሉ በእግዚአብሔር ትከሻ ላይ ስለሚያርፍ ነው።

በዴቪድ ማቲስ