አሁንም አልረፈደም! ከፖርኖግራፊ ሱስ ጋር ለምናደርገው ውጊያ የሚሆኑ ተስፋዎች

በዐይኖቹ ላይ ሕመሙ እና ፍርሀቱ ይታየኝ ነበር።

ጥያቄው መዳኑን በተመለከተ እርግጠኛ ካለመሆኑ ጋር የተያያዘ ነበር። ለመፈላሰፍ ወይም ለጠቅላላ ዕውቀት የተጠየቀ ጥያቄ እንዳልነበረ ከሁኔታው በግልፅ መረዳት ይቻላል። ይልቁንም ጥያቄው የመነጨው፣ በውስጡ ጸንቶ የቆየ አንድ ኀጢአት ነፍሱን ስላደከመው ነበር።

ምንጩ ምን እንደሆነ አጣርቶ ለማወቅ፣ አንድ ጥያቄ ብቻ መጠየቅ በቂ ነበር። ይኸውም በተደጋጋሚ ወደ ፖርኖግራፊ መመለሱ ነበር። ቀጥዬ ሳናግረው ወቀሳ ተሰማው፤ ይህ ደግሞ የእግዚአብሔር ጸጋ ምልክት ስለሆነ ጥሩ ነገር ነው።

አሁን ላይ በዩንቨርስቲ አገልግሎት ውስጥ እንዲህ ያለ ነገር ሲገጥም የሚያስደንቅ አይደለም። በክርስቲያን ዩንቨርስቲዎች ውስጥ ለመጋቢዎች በተደጋጋሚ ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል ዋነኛው፣ የመዳንን እርግጠኝነት ማጣት ነው። መጀመሪያ ላይ ጥቂት ግራ መጋባት ይኖርና ከዚያ ውይይቱ በጥልቀት ሲደረግ፣ ችግሩን እያመጣ ያለው ፖርኖግራፊ እና ግለ ወሲብ እንደሆነ ፍንትው ብሎ ይታያል።

የዚህ ትውልድ ወረርሽኝ

የኢንተርኔት ተደራሽነት መስፋፋትን ተከትሎ እየተዛመተ ባለው የፖርኖግራፊ ወረርሽኝ ምክንያት፣ በክርስቲያኖች ዘንድ ያለው የመዳን እርግጠኝነት ከምንጊዜውም በላይ ዝቅተኛ ሳይሆን አይቀርም። አንዳንድ ጊዜ በሕልውና ሰቆቃ እና በሥነ ልቦና ቀውስ የሚገለጽ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ጊዜ ግን የመዳንን እርግጠኝነት ማጣት፣ ሥር የሰደደ ኀጢአት ውጤት ነው። በድጋሚ ላላደርገው በጣም ብዙ ጊዜ ቃል ከገባሁበት ኀጢአት ጋር ደጋግሜ የምመለስ ከሆነ፣ በእርግጥ ልድን እችላለሁ?

በቅርቡ 8,000 የሚሆኑ የዲዛየሪንግ ጋድ (desiringGod.org) አንባቢዎች ላይ ዳሰሳ ሠርተን ነበር። በጥናታችን መረዳት እንደቻልነው፣ በሚያሳዝን ሁኔታ ፖርኖግራፊ መጠቀም በብዙዎች ዘንድ የተለመደ ብቻ ሳይሆን በወጣቶች ዘንድ ቁጥሩ ከፍ ያለ መሆኑም ነው። ዕድሜያቸው ከስልሳ ዓመት በላይ ከሚሆኑት ወንዶች ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት ፖርኖግራፊን በተደጋጋሚ እንደሚጠቀሙ ሲመሰክሩ፣ ዕድሜያቸው በሀምሳዎቹ ከሆኑት ውስጥ 20 በመቶዎቹ፣ ዕድሜያቸው አርባዎቹ ገደማ ከሆኑት 25 በመቶዎቹ፣ እናም ዕድሜያቸው ሠላሳዎቹ አካባቢ ከሆኑት መካከል 30 በመቶዎቹ ይጠቀማሉ። ይሁን እንጂ ክርስቲያን እንደሆኑ ከሚናገሩና ዕድሜያቸው ከ18-29 ከሆኑ ወጣት ወንዶች ውስጥ 50 በመቶ የሚጠጉት ፖርኖግራፊን በተደጋጋሚ እንደሚጠቀሙ መስክረዋል (ምንም እንኳ ቁጥሩ ያነሰ ቢሆንም፣ በሴቶችም ዘንድ ተመሳሳይ ዝንባሌ እንዳለ የጥናት ዳሰሳው አመላክቷል። ዕድሜያቸው ከ18-29 የሚሆኑ ሴቶች 10 በመቶዎቹ፣ ዕድሜያቸው ሠላሳዎቹ ውስጥ ካሉት ደግሞ 5 በመቶ የሚሆኑት ሲሆን ዕድሜያቸው በአርባዎቹ፣ ሀምሳዎቹ እና ስልሳዎቹ አካባቢ በይበልጥ ዝቅተኛ ነው)።

ዛሬ ድምፁን ስሙ

ለዚህ ትውልድ በኢንተርኔት ላይ ፖርኖግራፊን በቀላል የማግኘቱ ጉዳይ አዲስ ነገር ቢሆንም (ደግሞም ለዚህ ነገር በለጋ ዕድሜያቸው የተጋለጡ ላይ ጉዳቱ ቢከፋም) ጸንቶ ለቆየ ኀጢአት የቀረበው የንስሓ ጥሪ ግን ብዙ ዘመንን ያስቆጠረ ነው። ዛሬ ላይ ላሉ ተግዳሮቶች ምናልባትም ከዕብራውያን ምዕራፍ 3 እና 4 የበለጠ ወሳኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም።

ከተጻፈ 2,000 ዓመት ያስቆጠረው የዕብራውያን መልእክት፣ ይበልጥ ወደ ኋላ በመሄድ እግዚአብሔር በመዝሙር 95፥7-8 ላይ ወደሚያቀርበው የንስሓ ጥሪ ይጠቁማል። ”ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፤ ልባችሁን አታደንድኑ” (ዕብራውያን 3፥7-813154፥7)። ምንም እንኳ ይህ የዕረፍት ጥሪ ለብዙ ዘመናት የቆየ ቢሆንም፣ ለእያንዳንዱ አማኝ ተግባራዊ የሚሆነው ግን ባለማመን ልባቸውን ላላደነደኑ እና በንስሓ ለሚመለሱ ሰዎች ብቻ ነው።

የዕብራውያን መልእክት የተጻፈው በስደት ላይ ለነበሩ አይሁድ ክርስቲያኖች ነው። ኢየሱስን እንደ መሲሕ ማምለካቸው የስደት ምክንያት የሆነባቸው እነዚህ አይሁዶች፣ እምነታቸውን ትተው በአንድ ወቅት ያለ ኢየሱስ ይኖሩ ወደ ነበረበት ይሁዲነት ለመመለስ ተፈትነዋል። እንዲህ ያለው አካሄድ ነገረ መለኮታቸውን ማለትም እግዚአብሔርንና መገለጡን የሚረዱበትን መንገድ ይጎዳል፤ እንዲሁም ዘላለማቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ነው። እነዚህ ቀደምት ክርስቲያኖች ተመሳሳይ የልብ ድንዳኔ ገጥሟቸው ነበር። ይህም ደግሞ ልክ የዚህ ዘመን ክርስቲያኖች እንደሚገጥማቸው የኀጢአት ልምምድ እና ያልተዋጉት አለማመንን ተከትሎ የሚመጣ ነው።

እንደዚህ ባለ ዐውድ ውስጥ የዕብራውያን መልእክት ወደ መዝሙር 95 በመጠቆም እንዲህ ያለ ማጽናኛውን ይሰጠናል፦ “ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፤ ልባችሁን አታደንድኑ።” ይህን ቃል ትውልዳችን በእጅጉ ሊሰማው የሚያስፈልገው ቃል ነው።

አሁንም ድረስ ድምጹን እየሰማችሁ ከሆነ

“ዛሬ” የሚለው ላይ ያለው አጽንዖት እጅግ አስፈላጊ ነው። ነገ በእጃችን አይደለም። ያላችሁ አሁን ነው።

”ዛሬ ወደ ክርስቶስ እና ወደ ቅድስናው የሚጠራችሁን የእግዚአብሔርን ድምፅ ብትሰሙ፣ ከዚያም ይህን ድምፅ ሳትቀበሉ ብትቀሩ ልባችሁ በተወሰነ መልኩ እየደነደነ ይመጣል። በሚቀጥለው ሳምንት ወይም ወር እና የዛሬ ዓመት ንስሓ እገባለሁ ብላችሁ እርግጠኞች አትሁኑ።

የሚወቅሰንን የጸጋ ድምጽ ችላ ባልን ቁጥር አንድ እርምጃ ወደ ፍርድ እየቀረብን እንሄዳለን። እያወቅን በጽድቅ ላይ የምናደርገው እያንዳንዱ ዐመፅ ነፍሳችንን እያጨለመ ልባችንን ያሻክረዋል። ከዚያም በአንድ ወቅት በልባችን ምንም ዓይነት ሙቀት ይሁን መለሳለስ አይቀርልንም። ልክ እንደ ዔሳው ለንስሓ ስፍራ እንዳላገኘው ማለት ነው (ዕብራውያን 12፥17)። ጊዜው የረፈደ ይሆንብናል።

ነገር ግን ዛሬ፣ ዛሬ! በመንፈሱ ማነሣሣት ድምፁን ብትሰሙ፣ ዛሬም ጸጸት የሚሰማችሁ ከሆነ፣ አሁንም ድረስ ማፈር የሚሰማችሁ ከሆነ፣ ስለ ኀጢአት ቆሻሽነት አሁንም ጥላቻ የሚሰማችሁ ከሆነ ዛሬን የለውጣችሁ መጀመሪያ አድርጉት። “ለሚናገረው እምቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ” (ዕብራውያን 12፥25)።

በተደጋጋሚ ስለ ምትፈጽሙት ኀጢአት መጥፎ ስሜት የሚሰማችሁ መሆኑ ጥሩ ነገር ነው። ይህም የሚሆነው ጸጋ ሲዳስሳችሁ ነው። ከሚያደነዝዘው ኀጢአት ወደሚሞቀው ይቅር ባዩ ጌታ ዘወር የማለት ዕድል አላችሁ። ልባችሁ መጠገን እስካይችል ድረስ ደንድኖ ቢሆን ኖሮ፣ ኀጢአት ምንም ባልመሰላችሁ ነበር። እየተሰማችሁ ያለው ጸጸት ከእርሱ መልካምነት የተነሣ ነው።

“ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ”

በምታደርጉት ውጊያ ውስጥ ዛሬ አዲስን መነሣሣት አድርጉ። ዛሬ ልባችሁን የማነሣሣት አቅም ኖሯችሁ ሳለ ኀጢአታችሁን ጣሉ። በዚህ ትግላችሁ ውስጥ በዕብራውያን 3፥12-13 ላይ ያለውን በዋጋ የማይተመን ጸጋ በተግባር ሊጋራችሁ የሚችል ጓደኛ አካትቱ።

“ወንድሞች ሆይ! ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኀጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ” (ዕብራውያን 3፥12-13)።

ዛሬ ጽድቅን ምረጡ። ቅድስናን ለመምረጥ የምንወስዳት እያንዳንዷ ተጨባጭ እርምጃ ወሳኝ ነች። ክፋትን የመቃወም እያንዳንዱ ውሳኔ፣ ደግሞም በልባችን እና በአእምሯችን ብሎም በሰውነታችን የምንወስደው እያንዳንዱ የጽድቅ እርምጃ ወሳኝ ነው። እያንዳንዱ ኀጢአትን እምቢ የማለት ውሳኔ በቀጣይነት ጽድቅን እንድትመርጡ በመጠኑም ቢሆን ያዘጋጇችኋል። “ወደ ፊት የምንሆነውን በየዕለቱ እየሆንነው ነው” (Joe Rigney, Live Like A Narnian, 52)። ስለዚህም ዛሬ ወሳኝነት አለው። የአሁኗ ጊዜ ወሳኝነት አላት።

የተስፋችን መገኛ

ከምንም በላይ ደግሞ “በድካማችን የሚራራልን” እንዲሁም “እንደ እኛ በማንኛውም ነገር የተፈተነ ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአትን ያልሠራው” ጠበቃችን እና ሊቀ ካህናችን ላይ ዛሬም ዐይናችሁን እንደ አዲስ ትከሉ (ዕብራውያን 4፥15)። በሚያስፈልገንም ጊዜ ምሕረትን ሊሰጠን ጸጋንም ሊልክልን ዝግጁ ነው (ዕብራውያን 4፥16)። ኀጢአትን እምቢ የምንለው፣ በእርሱ ላለው ደስታ እሺ በማለት ነው።

ታላቁ ተስፋችን በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል። ይህ ተስፋ በእኛ ተጠያቂነት፣ ወይም በቆራጥነታችን እንዲሁም በእኛ መነሣሣት ላይ ያረፈ አይደለም። ይህ ተስፋ በቀደመው ጊዜ በነበረን ታሪክ ላይ ወይም አሁን ባለን አቋም ላይ አሊያም ወደፊት በሚኖረን እምቅ ችሎታ ላይ የተመሠረተ እይደለም። ታላቁ ተስፋችን ያለው ከእኛ ሳይሆን ድል በነሣውና በእርሱ ሆነን ድል በምንነሣበት በክርስቶስ ነው።

ዴቪድ ማቲስ