የመለወጥ ውበት

ለብዙ ሰዎች፣ ክርስቲያናዊው የመለወጥ[1] አስተምህሮ (the doctrine of Conversion) ውብ ወይም ማራኪ አይደለም። አስገዳጅ ወይም ስሜት የሚረብሽ ነው ይላሉ፤ “ማንም ሰው እምነቱን በግድ አያሰርጽብኝም!” ወይም “እምነቴና አካሄዴ ስሕተት እንደሆነ የምትነግረኝ አንተ ማን ነህ!?” ሲሉ ይስተዋላሉ።

በርግጥ በዚህ አመለካከት መሠረት ውበት እንደ ተመልካቹ ነው ሊባል ይችላል። ነገር ግን የክርስትና አስተምህሮ ዋናው አንኳር ማራኪ ወይም አስቀያሚ የመሆኑ ጉዳይ ሳይሆን፣ እውነት ወይም ሐሰት መሆኑ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ እውነተኛው የክርስትና የመለወጥ አስተምህሮ እጅግ ውብ ነው።

በአንድ በኩል፤ የክርስትና መለወጥ ልክ እንደ የትኛውም ለውጥ ውብ ነው። ልጆች በትምህርት ቤት ውስጥ ስለ አባ ጨጓሬ ወደ ቢራቢሮ መቀየር፣ ወይም የእንቁራሪት እጭ ወደ እንቁራሪት የሚቀየርበትን መንገድ (Metamorphosis) ይማራሉ። በሰንበት ትምህርት ቤት ደግሞ ይህንኑ ምስል በመጠቀም፣ ሰው “በኅጢአት ሙት ከመሆን” ወደ “አዲስ ፍጥረትነት” እንዴት እንደሚቀየር ይማሩበታል። አበባ ይፈነዳል፤ እንቁላል ይፈለፈላል፤ ጫጩትም ክንፏን ለመጀመሪያ ጊዜ ዘርግታ ትበርራለች። እነዚህ ለውጦች በየራሳቸው መንገድ ውብ ናቸው፤ በተመሳሳይ መንገድም ውብ ናቸው። በእግዚአብሔር ፍጥረት ውስጥ ያሉትን የለውጥ ምሳሌዎች በመመልከት፣ ከመንፈሳዊ ሞት ወደ ዘላለማዊ ሕይወት በመለወጥ ውስጥ የታየውን የክብሩን መገለጥ መረዳት እንችላለን።

ከተፈጥሯዊው ዓለም ሕግጋቶች መካከል አንዱ፣ ለራሳቸው የተተው ነገሮች ወደ ኋላ ይመለሳሉ እንጂ አያድጉም የሚል ነው። ሁሉም ይሞታል። ሆኖም ግን እግዚአብሔር በዚህ ግዛት ውስጥ ለተሻለ ዓላማ የለውጥን ውበት እዚህም እዚያም ሰውሯል። እነዚህ ሁሉ የድነት ድንቅ ምልክቶች አይደሉምን?

በርግጥ መለወጥ ከዚህም ይበልጣል። ለመረዳት ከባድ ባለመሆኑ (ሮሜ 10፥9) ደግሞም በውስብስብነቱ (ኤፌሶን 2፥1-10) ውብ ነው።

ነገር ግን የመዳንን ውበት በጥልቀት ለማድነቅ ተጨማሪ ነገሮችን እንመልከት።

አሰራሩ ውብ ነው

መለወጥ የተለያዩ ክስተቶችን በውስጡ ያካተተ ውብ አሰራር ነው። መለወጥን መለወጥ የሚያሰኘው አንድ ቅጽበት አለ። የሆነ ወቅት ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እና እግዚአብሔር ከሙታን እንዳስነሣው አናምንም ነበር፤ የሆነ ወቅት ላይ ደግሞ አምነን ተገኘን፣ ከአለማመን ወደ ማመን ተሻገርን።

በራሱ ጉዳይ ተጠላልፎ የነበረው ኅጢአተኛው ሰው ለማመንና ክርስቶስን በባዶ እጁ ለመያዝ የመጀመሪያውን የእምነት ውሳኔ ሲያደርግ፣ በዚያ ቅጽበት ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በታቀደለት የድነት ሰንሰለት ውስጥ ይታሰራል። ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር አነጣጥሮበት ነበር፤ እናም አሁን ጊዜውን ጠብቆ ውጤታማው ጥሪ በተወሰነለት ጊዜ ተፈጽሟል። በሰው የታቀዱት እርምጃዎች፣ በእግዚአብሔር መሪነት አቅጣጫ ቀይረዋል (ምሳሌ 16፥9)።

በአንድ ጎኑ ከተመለከትነው፣ መለወጥ የእግዚአብሔር ዕቅድ ስኬት እና የመንገዱ መነሻ ነጥብ ነው። መሰረታዊ የሆነ ውሳኔ ነው፤ ከጀርባው ግን በብዙ የታቀደለት ውሳኔ ነው። በሮሜ 8፥30 ላይ በብዙ ጥንቃቄ ስለተደረገው ውሳኔ ግልጽ ዝርዝር እናገኛለን፦ “አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውን አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን አከበራቸው።” ዐይኖቻችን ሰዎች ንስሓ ሲገቡ እና በክርስቶስ ላይ እምነት ሲያሳርፉ ሊመለከቱ ይችላል፤ ነገር ግን መጨረሻ የሚሆነውንና መዳረሻ የሆነውን ዘላለማዊ ክብር ሊቋቋሙ ይሳናቸዋል።

በሮሜ 8፥30 ላይ ስለ ተጠቀሰው ስለ እያንዳንዱ ደረጃ ብዙ ገጽ ሊጻፍ ይችላል። ውበት ውስጥ ያለ ውበት ነው። የሰናፍጭ ቅንጣት የምታክል እምነት፣ ልቡ በተሰበረ ደካማ ኅጢአተኛ ውስጥ ተቀብሯል፤ ይህም በኅጢአተኛው ውስጥ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የተኮተኮተ የእግዚአብሔር ጥልቅ እውቀት ነው። ከዘላለም ዘመናት በፊት፣ እግዚአብሔር በጸጋው የዚህን ኅጢአተኛ ግለሰብ ጽኑ ዐመፃ አስቀድሞ በመመለከት፣ የታደለ ልጅ እንዲሆን በፍቅር አስቀድሞ ወስኖታል። ደግሞ እግዚአብሔር ለግለሰቡ ኅጢአት፣ እንከን አልባ መሥዋዕት ይሆን ዘንድ አንድያ ልጁን ልኮታል፤ የዚያ ሰው ደንዳና ልብ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ዳግም ተወልዶ የክርስቶስም ጽድቅ ተሻግሮለታል፤ ጻድቅ መባል ችሏል። ልብ ሰርጾ የሚገባ አይደለምን? ይሄ የሚያጸድቅ የእምነት ዘር፣ በእግዚአብሔር ታማኝነት አማካይነት የሚቀድስ እምነት ወደ መሆን ያድጋል። ይሄ አሁንም በመንፈስ ቅዱስ ሥራ አማካይነት እስከ ክብር ተስፋ ያደርሳል፤ ይህ ልብ ሰርጾ የሚገባ አስደናቂ እውነት ነው።

በቃል ኪዳኑ ውስጥ ያለ ውበት

መለወጥ በቃል ኪዳን ውስጥ ውበት ነው። ኦ፣ ያ ቃል ኪዳን! ይሄ በርግጥ ሁላችንም ማግኘት የምንፈልገው አይደለምን? ቅዱሱ እና ኅጢአተኛው በምን ዐይነት ተስፋ ሊመሳሰሉ ይችላል? ሁሉም ሰው ለውጥ ይፈልጋል። ሁሉም ሰው መጥፎው ጥሩ እንዲሆን፣ ስሕተትም መስመር እንዲይዝ ይፈልጋል። ይህ ስለሚሳካበት መንገድ ሁላችንም የተለያዩ ሐሳቦች አሉን፤ በአጭሩ ግን ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ነገር ይፈልጋል፦ ሕይወት።

እግዚአብሔር ዘላለማዊነትን በልባችን አኑሯል (መክብብ 3፥11)። ከዚህ የተነሣ እያንዳንዱ የንቃት ቅጽበት፣ ለአንድ ወይም ለሌላ አምላክ የሚቀርብ አምልኮ መገለጫ ነው፤ ይህም የትክክለኛው፣ የእውነተኛው፣ የተወዳጁ እና የተሻለው የውስጥ ተስፋችን ምኞት መገለጫ ነው። ብሩስ ማርሻል ታዋቂ አባባል አለው፦ “በግልሙትና ቤት ውስጥ የሚያዘወትር ወጣት፣ ባይገባውም አምላክን እየፈለገ።”[2] ይሄ ለሁሉም ዐይነት ጣዖት አምላኪ ተመሰሳይ ነው። ሁሉንም የሚያያይዘው እውነት ግን እግዚአብሔርን የሚፈልግ አንድም አለመኖሩ ነው (ሮሜ 3፥11)። እውነታው ግን እኛ እያሰስን ያለው፣ በርግጥ ፈጽሞ እንዲወገድልን የምንፈልገውን ብቸኛ አምላክ ነው።

ስለዚህ “እግዚአብሔርን የሚፈልጉት” በርግጥ እግዚአብሔር የፈለጋቸው ናቸው። የሚያጽናናው መንፈስ፣ ለሕይወት ያስነሣቸው ዘንድ ምድርን እያሰሰ ነው። እግዚአብሔር ሁላችንም ወደ ንስሓ እንድንገባ እንጂ ማናችንም እንድንጠፋ አይፈልግም፤ ከዚህ የተነሣ አስቀድሞ የሚያውቃቸውን ጣዖት አምላኪዎች ይታገሣል። መንፈሱ በልባችን ውስጥ ብርሃንን ያበራል፤ ከመቃብራችንም “ውጡ” ብሎ ይጣራል፤ የማይታመነው የሚታመን ይሆናል። የተለየ መሆን እችላለሁ! መለወጥ እችላለሁ! እግዚአብሔርን ማወቅ እና በዚያም ሕይወትን ማወቅ እችላለሁ! መዝሙሩ እንደሚለው፣ “በሕይወት ውስጥ ወቀሳ የለም፤ እንዲሁም የሞት ፍርሀት— በእኔ ያለው የክርስቶስ ኅይል እንዲህ ነውና!”

ወንጌል ለእኔ እና ለዚች ዓለም የሚያስፈልገውን እውነተኛ ተስፋ ይገልጣል። ሁሉም የፍጥረት ውበት ቢሆን ሥነ ጥበብ፣ ለእድገትና ለአብርሆት የሚደረገው የሰው ልጅ ትግል ሁሉ ተጠቅልሎ ሰው በሆነው፣ በተሰቀለው፣ በተቀበረው፣ በተነሣው እና በከበረው ኢየሱስ ውስጥ ይገኛል። እርሱ የትንሣኤው በኩራት እንደሆነ ሁሉ (1ኛ ቆሮንጦስ 15፥20-23)፣ ወደ መዳን እምነት የሚያመጣው የእኛም መለወጥ፣ ለማይጠፋ ሕይወት የሚያበቃ የመለወጥ ተስፋ ነው— “ሁላችንም እንለወጣለን” (1ኛ ቆሮንጦስ 15፥50-53)።

በእልፍ አእላፍ ሥራዎች ውስጥ ያለ ውበት

መለወጥ በእልፍ አእላፍ ሥራዎች ውስጥ የሚታይ ውበት ነው። የሰዎች በክርስቶስ ወደ ሚያድን እምነት መለወጥ፣ ውበቱ ከሚያካትታቸው ወሳኝ ነገሮች ሁሉ ቀዳሚው ነው። በእኔ ትውልድ ያሉ ብዙዎች “የሚድኑት” ወደ መድረክ በመምጣት፣ እጅ በመዘርጋት፣ ወይም ቀመራዊ ጸሎት በመጸለይ ነው። እናም በእኔ ትውልድ ያሉ አብዛኞቹ መጋቢዎች፣ ሰዎች ለወንጌል ምላሽ እንዲሰጡ የሚደረገውን መሰል ልዩ ጥሪ አያስተናግዱም። መጽሐፍ ቅዱሳዊው ወንጌል መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ መንገድ መሰበኩን ሁላችንም በጥንቃቄ ማረጋገጥ ይገባናል። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የሚሳሳቱ ሰዎችን፣ እንከን ያለበትን መንገድ ተጠቅሞ፣ ኅያል የሆነውንና እንከን አልባውን የኢየሱስ ክርስቶስን የምሥራች ማስተላለፉ እንዴት ያለ ተአምር ነው!

እኔ የዲስፔንሴሽናል ቅድመ መከራ ንጥቀት (dispensational pretribulational rapturist) አማኝ አይደለሁም፤ ሆኖም ግን መንፈስ ቅዱስ በጥበቡ እንደ “Left Behind” ዐይነት የ1970ቹ ጣፋጭ ፊልም ተጠቅሞ፣ ለምሕረት እና ጥበቃ ኢየሱስን እንድፈልግ ልቤን አለሰለሰ። ዛሬ መሰል ዘዴዎችን አልጠቀምም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ልጆቹን ወደ ሕይወት ስለሚያመጣበት መንገድ ቸልተኛ ባለመሆኑ አመስጋኝ ነኝ። ደካማ በሆነው የወንጌል ስብከታችን፣ እንዲያውም እንከን ባለበት ስብከታችንና ልመናችን ፍጹም የሆነው ኅይሉ ይፈጸማል። እግዚአብሔር በወንጌል አገልግሎታችንና ከዚያም አልፎ የሚሠራበት መንገድ ሁልጊዜም ያስደንቀኛል።

ወደ ክርስቶስ የተደረጉ መለወጦች ሁሉ የመነጩት፣ በመጨረሻ እርሱን እንደ ድነታችን መባ ይዞ በመቅረብ ነው። የዚህ ግልጽ ምሳሌ ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ የሳውል መለወጥ ነው። ያ ቅጽበት በጣም አስደናቂ ነው። ለአንዳንዶች ክስተቱ እዚህ ግባ ማይባል ነው። በልጆች ቤተ ክርስቲያን (የሰንበት ትምህርት ቤት) ውስጥ አንድ ልጅ  ጸሎትን ይጸልያል። አንድ ሰው በሰንበት አገልግሎት ማጠናቀቂያ ወደ መድረክ ይሄዳል። አንድ የማውቀው ሰው ደግሞ የመለወጥ ልምምድ በእርሱ ላይ ከመከሰቱ በፊት፣ በየሰንበቱ ለሦስት ዓመታት ያህል በቤተ ክርስቲያን ይመላለስ ነበር፤  በስተ መጨረሻ እንዲህ አለ፦ “መዳን አለብኝ። ማመን አለብኝ።

That Hideous Strength” በተሰኘው ልብ ወለድ ውስጥ፣ ሲ. ኤስ. ሌዊስ በማይታበል መንገዱ፣ የአንዲትን ሴት መለወጥ መደበኛነቱን እና ክብደቱን እንዲህ አስቀምጦታል፦

እርሷን እዚያ የሚጠብቃት፣ ከሐዘን እና ከዚያም ያለፈ ነው። ድምጽም ሆነ ቅርፅ አልነበረም። ከቁጥቋጦው በታች ያለው ሻጋታ፣ በመንገድ ላይ ያለው ሙዝ እና ትንሽ የጡብ ድንበር በሚታይ መንገድ አልተለወጡም፤ ግን ለውጥ ነበር። የድንበር ሽግግር ነበር። ወደ አንድ ሌላ ዓለም፣ ወይም ወደ አንድ አካል፣ ወይም አንድ አካል መገኘት ቀርባለች። የሚናፈቅ፣ ታጋሽ፣ ፈጽሞ የማይቆም፣ ያለ አንዳች መጋረጃ ወይም ከለላ ተገናኛት...

በዚህ ከፍታ፣ ጥልቀት እና ስፋት ውስጥ “እኔ” የሚለው የራሷ ትንሽ ሐሳብ ወድቃ ጠፋች፤ ልክ አየር በሌለበት ቦታ እንዳለ ወፍ ሆነች። “እኔ” የሚለው የፍጡር ሕልውና መጠሪያ፣ እስካሁን ሙሉ በሙሉ ያልነበረ ነገር ግን የሚፈለግ ፍጡር ስም መሆኑን አልጠረጠረችም ነበር።  አካል ነበር (እርሷ ያሰበችው ዐይነት ባይሆንም)፤ ግን ደግሞ የተፈጠረ መሣሪያም ነበር። ሌላን (እግዚአብሔርን) ለማስደሰት እና ሌሎችን በእርሱ በኩል ደስ ለማሰኘት የተፈጠረ መሣሪያ ነበር። ያለ ምርጫው እና ባልተጠበቀ መንገድ በዚህ ወሳኝ ቅጽበት የተበጀ ነበር። ሸክላ በሚያበጁ እጆች ይሁን በመውቀጫ በየትኛው እንደሆነ እርግጠኛ ባትሆንም፣ የመፍጠር ሥራው በክብር እና በሐዘን በሁለቱ መካከል ተከናወነ።

ጊዜ ተብሎ ለመጠራት በጣም አጭር በሆነ ቅጽበት ውስጥ ትልቅ ነገር እርሷ ዘንድ ስፍራ ያዘ። እጇ ከትውስታ በቀር ምንም አልያዘም። በእጇ እንደተያዘ፣ ያለ ቅጽበት እረፍት፣ ከሰውነቷ ከእያንዳንዱ ክፍል ሐሴት ጠል የሆኑ ድምጾች ያንሾኳሽኩ ጀመር።

"ተጠንቀቂ። ወደ ኋላ ተመለሽ። ራስሽን ጠብቂ። ራስሽን አትስጪ” ይላሉ። ይበልጥ ደግሞ በስውር ከሌላ አቅጣጫ፣ “ሃይማኖታዊ ልምምድ ነበረሽ። ይሄ ደስ ይላል፤ ምክንያቱን ሌላው ሰው የለውም። አሁንማ የዐሥራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ገጣሚዎችን በተሻለ ሁኔታ መረዳት ትችያለሽ!”

. . .ሆኖም ግን መከላከያዎቿ አሁን በቁጥጥር ሥር ውለዋል፤ እናም እነዚህ መልሶ የማጥቃት ሙከራዎች አልተሳኩም።[3]

አጋንንቱ እርሷን ይቃወማሉ፤ አንዳንድ ጊዜ በቀጥታ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የልምምዷን ትርጉም ይለውጣሉ። ነገር ግን መላእክትም ሆኑ አጋንንቶች፣ ጄንን ከእግዚአብሔር ፍቅር መለየት አይችሉም። ስለዚህ ጸጥ ባለው የእንግሊዝ አትክልት ስፍራ፣ በተቀደሰ መሠዊያ ላይ በሚቀርቡ ጸሎቶች፣ ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ወንበር ላይ ሆኖ በሚያነብ ብቸኛ ነፍስ፣ ዘላለማዊነት ይወርዳል።

እግዚአብሔር ሙታንን ወደ ሕይወት የሚያመጣባቸው እልፍ አእላፍ መንገዶች ውብ ናቸው፤ አንዳንዶች አዲስ እውነታዎችን በቅጽበት ይገነዘባሉ፤ ሌሎች ደግሞ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በጊዜ ሂደት ይገነዘባሉ። አንዳንዶች መልእክቱን ለመጀመሪያ ጊዜ ሰምተው በእምነት ምላሽ ይሰጣሉ። ሌሎች መልእክቱን በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ቢሰሙም መንፈሳዊ ‘የሚሰማ ጆሮ’ የላቸውም። ይህ በጥበብ የተሞላ ነው። እግዚአብሔር ብዙ በሆነው የሰው ልጅ ልምምድ እና የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ፣ በሚያስደንቅ እና ለየት ባለ ሁኔታ፣ ትንሣኤን እየደጋገመ አለ። የተለመደው የመለወጥ መንገድ እንኳ ያልተለመደ ነው። መላእክት ከጥቂት ዓመታት በፊት ለልጄ ለመጀመሪያ ጊዜ በመኝታ ክፍልዋ ውስጥ ላሳየችው የሚያድን እምነት ያሳዩት ደስታ፣ ለጳውሎስ ከ2,000 ዓመታት በፊት ካደረጉት አያንስም። እያንዳንዱ መለወጥ ተአምር ነው። እናም ታላቁ የክርስቶስ የክብር ነጸብራቅ እኛም ውስጥ የክብር ነጸብራቅ ይፈጥራል (2ኛ ቆሮንጦስ 3፥18)።

ከምንጩ ያለ ውበት

መለወጥ ከምንጩ ውብ ነው። ፈጣሪ ክቡር ነውና የሚሠራው ሁሉ የከበረ ነው። እናም ከዚህ ወሳኝ እውነት የተነሣ “ውበት እንደተመልካቹ ነው” ማለት ብቻውን ልክ አይሆንም። ሟች በሆኑት ውስጥ ቢኖርም ባይኖርም፣ ውበት ፍጹም በሆነ መንገድ ሥሉስ አምላክ ውስጥ ተሰውሯል። ዳዊት በጌታ ቤት እንዲኖር እና የጌታን ውበት ያይ ዘንድ ጠየቀ (መዝሙር 27፥4 ይመልከቱ)። ነገር ግን ጌታ እንደነዚህ ያሉትን ጸሎቶች ባይመልስ እንኳ፣ ውበቱ ቅንጣት ታክል አይቀንስም።

በሌላ በኩል፣ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ውበት (አብዛኛውን ጊዜ ክብሩ ተብሎ የሚጠራው) ይንጸባረቃል፤ እንዲያውም እየጨመረ ይሄዳል። ስለዚህ እግዚአብሔር ሙታንን ለአዲስ ሕይወት ካስነሣባቸው ውበቶች አንዱ፣ በስብከትና በመዝሙር ውበቱን ለማንፀባረቅ ምስጋና በተሞላ ልብ መምጣታቸው ነው (ቆላስይስ 3፥16)። ጴጥሮስ የክርስቶስን መከራና ትንሣኤ ከተመለከተ በኋላ፣ ራሱን “ሊገለጥ ባለው ክብር ተካፋይ” እንደሆነ አድርጎ መጥራት ችሏል (1ኛ ጴጥሮስ 5፥1)። በሚያድን እምነት ለወንጌል ጥሪ ምላሽ መስጠትን በሌላ መልኩ ካየነው፣ ያንን ውበት ማግኘት እና ያንን ማድመቅ ነው። ጳውሎስ በ2ኛ ተሰሎንቄ 2፥14 ላይ “የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር እንድታገኙ በወንጌላችን ጠራችሁ” በማለት ጽፏል።

መለወጥ ውብ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ውብ ነው። እርሱ በክብሩ ታላቅነት እና በግርማው፣ በማንነቱ መገጫዎች ሁሉ እና በባሕሪያቱ ውብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ውበት የሚናገርበት መንገድ ራሱ ዉብ ነው። ይህም በአምስቱ የሙሴ መጽሐፍት ትረካዎች ከቀረቡት ቅድስናዎች አንሥቶ እስከ መዝሙራት  ድረስ፣ እግዚአብሔር ለኢዮብ ከመለሰለት አስደናቂ መልስ አንሥቶ እስከ ነቢያት ድንቆች፣ ከወንጌላት አንሥቶ በመልእክቶች እስካሉት የላቁ መደነቆች፣ ከመለኮታዊ ማወደሶች በዮሐንስ እስካሉት አወዛጋቢ ራእዮች ድረስ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር ጥልቅ እና አስደናቂ ውበቶች ተውቧል።

እናም ይሄ አስደናቂ፣ ቅዱስ እና ከአእምሮ በላይ የሆነው እግዚአብሔር፣ አወቀን፤ ወደደን፤ መረጠን፤ ጠራን፤ እናም አዳነን። “በክርስቶስ ፊት እግዚአብሔር የክብሩን ዕውቀት ብርሃን ይሰጠን ዘንድ፣ “በጨለማ ብርሃን ይብራ” ያለው እግዚአብሔር ብርሃኑን በልባችን አብርቶአልና” (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥6)። የመለወጥ ውበት (ገና ደግሞ ለዘላለም የምንመረምረው) ሁሉ፣ ከራሱ ከእግዚአብሔር የመነጨ እና የእርሱ ጥላ ነው፤  ክብሩንም እንድናየው እና ኢየሱስን በማወቅ ለዘላለም እንድንቀየር፣ ክብሩ በጊዜ ሳይገደብ ይገለጣል።

በጃሬድ ዊልሰን


[1] Conversion ለሚለው የእንግሊዘኛ ቃል አቻ ትርጉም ስላልተገኘ፣ “መለወጥ” (‘መ’ ትጠብቃለች) በሚለው አማርኛ ቃል መተካቱን ልብ ይበሉ።  

[2] Bruce Marshall, The World, The Flesh and Father Smith (Boston: Houghton Mifflin, 1945), 108.

[3] C.S. Lewis, That Hideous Strength (New York: Macmillan, 1970), 318-319.