መለወጥ ምን ማለት ነው?

መለወጥ[1] የአቅጣጫ ለውጥ ማድረግ ማለት ነው። አንድ ሰው ከኅጢአት መንገድ ተመልሶ ለድነት ወደ ክርስቶስ ሲሄድ ማለት ነው። ይህም ከጣዖት አምልኮ እግዚአብሔርን ወደ ማምለክ፣ ራስን ከማጽደቅ ወደ ክርስቶስ ጽድቅ መሻገር ማለት ነው። ከራስ አገዛዝ ወደ እግዚአብሔር አገዛዝ መመለስ ማለት ነው።

መለወጥ ሊከሰት የሚችለው፣ ራሱ እግዚአብሔር በኅጢአት የሞተውን ግለሰብ ለንስሓ ሲያበቃና በክርስቶስ እንዲያምን ሲያስችለው ነው።

  • ኢየሱስ ንስሓ እንድንገባና እንድናምን ሲጠራን፣ መለወጥ እንዲሆንልን ጥሪ እያደረገ ነው። ይህም እምነታችንና ድርጊታችን ላይ ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ ነው። (ማርቆስ 1፥15)
  • ኢየሱስ መስቀል ተሸክመን እንድንከተለው ሲጠራን፣ መለወጥ እንዲሆንልን ጥሪ እያደረገ ነው። (ሉቃስ 9፥23)
  • በንስሓ ለመቅረብ እግዚአብሔር አዲስ ሕይወት፣ አዲስ ልብን እና እምነትን ሊሰጠን ይገባል። (ሮሜ 6፥17፣ ቆላስያስ 2፥13፣ ሕዝቅኤል 36፥26፣ ኤፌሶን 2፥8፣ 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥25)

መለወጥ ያልሆናቸው ነገሮች

  1. መለወጥ ምንም ትርጉም የሌለው የአንድ ጊዜ ክስተት አይደለም። መለወጥ በአንድ ቅጽበት ሊከሰት ይችላል። ቅጽበቱም ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ ነው። ከዚያ በኋላ ሕይወት የተለየ መልክ ሊኖረው ይገባል። አዲስ የጦርነት ገድል መንገድም ይጀመራል።
  2. መለወጥ መዳረሻ የሌለው ጉዞ አይደለም። መለወጥ ለአንዳንዶች ረዘም ያለ ሂደትን ሊጠይቅ ይችላል፤ ነገር ግን ሁሌም ንስሓና እና በክርስቶስ መታመንን ያካትታል። ይህም ራሱ እግዚአብሔር በመንፈስ ለሞተው ለኅጢአተኛው ሰው የሚሰጠው ሕይወት ነው።
  3. መለወጥ አማራጭ አይደለም። በሐዋርያት ሥራ 17፥30 ላይ እንደምናነበው፣ እግዚአብሔር በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ ያዛል። መለወጥ በግድ እንዲከሰት ማድረግ አይቻልም፤ ሆኖም ግን ለመዳን የግድ አስፈላጊ ነው።
  4. መለወጥ ጭውውት አይደለም። ወንጌልን ትሕትና በተሞላ መልኩ ለሌሎች ብናደርስም፣ ግባችን ግን አስደሳች የሆነ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ብቻ አይደለም። ሰዎች ሁሉ ከኅጢአታቸው ንስሓ እንዲገቡ እና በክርስቶስ ድነት ላይ መታመን እንዳለባቸው ልንነግራቸው ይገባል።
  5. መለወጥ ቀመር ያለው ጸሎት አይደለም። ጸሎት ለመለወጥ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ሰዎች በልዩ ቃላት ላይ እምነታቸውን እንዲጥሉ እንዳንፈትን መጠንቀቅ ይኖርብናል።

[1] Conversion ለሚለው የእንግሊዘኛ ቃል አቻ ትርጉም ስላልተገኘ፣ “መለወጥ” በሚለው አማርኛ ቃል መተካቱን ልብ ይሏል።