መለወጥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ

መለወጥ[1] ከኅጢአት መራቅ እና ወደ እግዚአብሔር መመለስ ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ምናልባት ይህን ፍቺ የሚይዘው ጥንታዊው ጥቅስ 1ኛ ተሰሎንቄ 1፥9 ነው። “እነርሱ ራሳቸው ወደ እናንተ መግባታችን እንዴት እንደነበረ ስለ እኛ ይናገራሉና፤ ለሕያውና ለእውነተኛ አምላክም ታገለግሉ ዘንድ፥ ከሙታንም ያስነሳውን ልጁን እርሱንም ኢየሱስን ከሚመጣው ቍጣ የሚያድነንን ከሰማይ ትጠብቁ ዘንድ፥ ከጣዖቶች ወደ እግዚአብሔር እንዴት ዘወር እንዳላችሁ ይናገራሉ።” እዚህ ላይ ወደ እግዚአብሔር መመለስ እና ከጣዖት መራቅን (ሁለቱን የመለወጥ ነጥቦች) በግልፅ እናያለን።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ መለወጥ፦ ከተስፋ ቃልነት ወደ በገሃዱ መገለጥ

በብሉይ ኪዳን  ላይ ተስፋ የተሰጠው ታሪክ፣ ማለትም በእባቡ ላይ የሚፈጸመው የእግዚአብሔር ድል ነሺነት ታሪክ (ዘፍጥረት 3፥15)፣ በአዲስ ኪዳን እውን ሆኗል። ብሉይ ኪዳን አዲስ ኪዳንን፣ አዲስ ፍጥረትን፣ አዲስ ዘጸአትን፣ እና አዲስ ልብን ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቃል ገብቶ ነበረ። እናም አዲስ ኪዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፣ ሞት እና ትንሣኤ እነዚህ ተስፋዎች ሁሉ በድምቀት ፍጻሜ እንዳገኙ አውጇል።

መለወጥ በሲኖፕቲክስ ወንጌላት ውስጥ

በሲኖፕቲክ[2] ወንጌላት (ማቴዎስ፣ ማርቆስ እና ሉቃስ) ውስጥ በብሉይ ኪዳን የተነገረው የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ፣ “የእግዚአብሔር መንግሥት” በሚለው ቃል ተገልጿል። በእነዚህ ወንጌላት ውስጥ የእግዚአብሔር መንግሥት ማዕከላዊ ሚና ቢኖረውም፣ ነገር ግን መንግሥቱ መለወጥን የሚጠይቅ እንደሆነ ልንረዳ ይገባል። መለወጥም በሁለት አካላት ማለትም በንስሐ እና በእምነት ሊገለጽ ይችላል። ማርቆስ 1፥14-15 እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና፦ ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ።” በኢሳይያስ የተሰበከው ከግዞት የመመለስ የምሥራችን (የእግዚአብሔር የማዳኑ ተስፋዎች ፍጻሜ የምሥራችን) ማጣጣም የሚችሉት ከኅጢአታቸው ንስሓ የገቡ እና በወንጌል የሚያምኑ ብቻ ናቸው።

በሲኖፕቲክስ ውስጥ ያለው ወንጌል፣ በኢየሱስ ሞት እና ትንሳኤ ላይ ያተኮረ ነው፤ ምክንያቱም በሦስቱም መጽሐፎች ውስጥ የኢየሱስ መሰቃየት እና መነሣት  ታሪኩን ገዝቶት እናያለን። የታሪኩ ቁንጮ ነው! ያለ መስቀል መንግሥት የለም። ኢየሱስ የመጣው “ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ለማዳን” ሲሆን (ማቴዎስ 1፥21) ይህም መዳን እውን የሚሆነው ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ በማድረግ ለእነርሱ ሲሞት ነው( ማቴዎስ 20፥28፤ ማርቆስ 10፥45)። ስለ መንግሥቱ የሚናገሩ አንዳንዶች ስለ መለወጥ ብዙም አይናገሩም፤ ነገር ግን በሲኖፕቲክ ወንጌላት መለወጥ ፍንትው ብሎ ይታየናል።

መለወጥ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ

የመለወጥ ማዕከላዊነት በዮሐንስ ወንጌልም ውስጥ ይታያል። በርግጥም ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው ሰዎች “ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ” ነው ( ዮሐንስ 20፥31)። ዮሐንስ በወንጌሉ ውስጥ “ማመን” የሚለውን ግስ 98 ጊዜ ተጠቅሞታል። ይህም እምነት በወንጌሉ ውስጥ ያለውን አስፈላጊነት አጉልቶ አሳይቷል። ዮሐንስ የእምነትን ጥልቀትና ተግባር ለማሳየት ብዙ ቃላትን ይጠቀማል። ማመን እንደ መብላት፣ መጠጣት፣ ማየት፣ መስማት፣ መኖር፣ መምጣት፣ መግባት፣ መቀበል እና መታዘዝ አድርጎ ያቀርበዋል። ዮሐንስ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ማመንን ለመግለጽ የተጠቀማቸው ግሶች የመለወጥን ታላቅነት ያሳዩናል። እንግዲህ መለወጥ የዮሐንስ ወንጌል ዋና ማዕከል ነው። ኢየሱስ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” ነው ብለው የሚያምኑ ብቻ የዘላለም ሕይወት አላቸው (ዮሐንስ 1፥29)። በሌላ አነጋገር፣ የተለወጡ ብቻ የዘላለም ሕይወትን ያገኛሉ።

መለወጥ እና የእግዚአብሔር መንግሥት በሐዋርያት ሥራ

አስቀድመን ካነሣነው መረዳት እንደሚቻለው፣ መለወጥ በወንጌል ውስጥ ማዕከላዊ ሚና እንዳለው ሲሆን ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍም ተመሳሳይ የሆነ ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ወንጌል  የተብራራባቸው በርካታ ስብከቶችን እናገኛለን (ለምሳሌ፦ የሐዋሪያት ሥራ 2፥14-41፤ 3፥11-26፤ 13፥16-41)። ሰሚዎቹም ብዙውን ጊዜ ንስሐ እንዲገቡ ይጠራሉ (የሐዋርያት ሥራ 2፥38፤ 3፥19፤ 8፥22፤ 17፥30፤ 26፥20)። ይህም ንስሓ “ወደ እግዚአብሔር መዞር” ተብሎ ይገለጻል (የሐዋሪያት ሥራ 3፥19፤ 9፥35፣ 40፤ 11፥21፤ 14፥15፤ 15፥19፤ 26፥18፣ 20፤ 28፥27)። የወንጌል መልእክት ከኃጢአት እና ከአሮጌው ሕይወታችን እንድንርቅ አስቸኳይ ጥሪን ያቀርባል። በተመሳሳይም ምሥራቹን የሚሰሙት፣ እንዲያምኑና የሚያምኑትን እንዲኖሩ ተጠርተዋል (የሐዋሪያት ሥራ 16፥31 ፤ 26፥18)። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ “ማመን” የሚለው ቃል ክርስቲያኖችን ለመግለጽ 30 ጊዜ ያህል ተጠቅሷል፤ ይህም “እምነት” የክርስቶስ የሆኑትን ሰዎች ያመለክታል።

ወንጌል ከኢየሩሳሌም ወደ ሮም መስፋፋቱን መጽሐፉ ስለሚዘግብ፣ መለወጥ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ትልቅ ሚና መጫወቱ  እምብዛም አያስገርምም (የሐዋሪያት ሥራ 1፥8፤ 1፥6፤ 14፥22)። ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ዋና ጭብጥ እንደሆነም ልብ ሊባል ይገባል። የመጽሐፉ መጀመሪያ (የሐዋርያት ሥራ 1፥3) እና መጨረሻ (የሐዋርያት ሥራ 28፥31) ይህን ያሳየናል። ጳውሎስ የእግዚአብሔርን መንግሥት በሮም ሰብኳል (የሐዋሪያት ሥራ 20፥35፤ 28፥23፣ 31)። ፊልጶስ ደግሞ “የእግዚአብሔርን መንግሥትና የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ምሥራች ሰበከ” (የሐዋሪያት ሥራ 8፥12)። ይህም መንግሥቱ ወንጌልን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ያሳያል። ከላይ እንዳየነው የተሰበከው ወንጌል፣ ሰሚዎቹ ንስሐ ገብተው እንዲያምኑ ጥሪ ያቀርባል። ስለዚህም መለወጥ ለመንግሥቱ አዋጅ መሠረት እንደሆነ እናያለን። አንዱ የአማኞች አስደናቂ ተስፋ፣ ዓለምን ወደ እግዚአብሔር አገዛዝ መመለስ ነው። ነገር ግን  የሚመጣውን አዲስ ዓለም የሚያጣጥሙት፣ ንስሐ የገቡ እና ያመኑት ብቻ ናቸው። የሐዋርያት ሥራ ደጋግሞ አጽንዖት እንደሚሰጠው፣ ለማመን ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ይፈረድባቸዋል።

መለወጥ በጳውሎስ ዕይታ

ጳውሎስ የእግዚአብሔር መንግሥት የሚለውን ቃል ብዙ ጊዜ አይጠቀምም። ነገር ግን የነገረ ፍጻሜ አተያዩ በደንብ የታወቀ  እና ከመንግሥቱ የፍጻሜ ባህሪ ጋር የተስማማ ነው። እንደ ወንጌላት ጽሑፎች፣ እርሱም “በመካከላችን ያለ ነገር ግን በምልዓት ያልተገለጠ” የነገረ ፍጻሜ ታሪክን ያውጃል። ጳውሎስ ብዙ ጊዜ መጽደቅ እና መዳን የሚገኘው በእምነት ብቻ እንደሆነ ያስተምራል (ሮሜ 3፥21-4፥25፤ 9፥30-10፥17፤ 1ኛ ቆሮንጦስ 15፥1-4፤ ገላትያ 2፥16-4፥7፤ ኤፌሶን 2፥8-9፤ ፊልጵስዮስ 3፥2-11)። ንስሐ የሚለውን ቃል ብዙ ጊዜ አይጠቀምም፤ ሆኖም ግን ጥቂት ቦታዎች ላይ እናያለን(ለምሳሌ፦ ሮሜ 2፥4፤ 2ኛ ቆሮንጦስ 3፥16፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 1፥9፤ 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥25)።
ጳውሎስ በክርስቶስ በኩል የተገኘውን የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ለመግለጽ ብዙ ቃላትን ይጠቀማል። እነርሱም መዳን፣ መጽደቅ፣ ቤዛነት፣ ማስታረቅ፣ ልጅነት፣ ማስተስረያ፣ ወዘተ የመሳሰሉ ናቸው። በጳውሎስ ነገረ መለኮት ውስጥ በክርስቶስ በኩል ያለው የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ትልቅ ሚና መጫወቱ የማያከራክር ቢሆንም፣ እንዲህ ያለው መዳን የሚሰጠው ግን ለሚያምኑት ወይም ለተለወጡት ብቻ ነው።

እንደ ጳውሎስ ገለጻ፣ አማኞች የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣትና የፍጥረትን መመለስ በጉጉት ይጠባበቃሉ (ሮሜ 8፥18-25፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 4፥13-5፥11፤ 2ኛ ተሰሎንቄ 1፥10)። ነገር ግን እየመጣ ላለው አዲስ ዓለም የታጩት፣ የተለወጡት ሰዎች ናቸው። ስለዚህም ከሚድኑት ወገን እንዲሆኑ ጳውሎስ ለአሕዛብ ወንጌልን ለማዳረስ ተግቶ ይሠራል (ቆላስይስ 1፥24-2፥5)፤ ወንጌልን ላልሰሙት ለማድረስ ይተጋል (ሮሜ 15፥22-29)። 

መለወጥ በሌሎቹ መልእክታት ውስጥ

የተቀሩት የአዲስ ኪዳን መልዕክታት አልፎ አልፎ የተጻፉ፤ የተለያዩ ሁነታዎችን በማስመልከት የተጻፉ ናቸው። ቢሆንም የመለወጥ አስፈላጊነት በእነዚህ መልዕክቶች በገሃድ ወይም በውስጥ ታዋቂነት ተገልጿል። ለምሳሌ፣ ወደ ዘላለማዊ ዕረፍት የሚገቡት ያመኑ እና የሚታዘዙት ብቻ እንደሆኑ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ እናገኛለን (ዕብራውያን 3፥18፣ 19፤ 4፥3፤ 11፥1-40)። ያዕቆብን ብዙ ጊዜ በተሳሳተ መንገድ ተረድተነዋል። የተናገረው በትክክል ሲተረጎም፣ የንስሐ እምነት ለመጽደቅ አስፈላጊ እንደሆነ ያስተምራል (ያዕቆብ 2፥14-26)። እንዲሁም ጴጥሮስ መዳን በእምነት እንደሆነ ያስተምራል (1ኛ ጴጥሮስ 1፥5; 2ኛ ጴጥሮስ 1፥1)። ደግሞም 1ኛ ዮሐንስ የተጻፈው ለሚያምኑት የዘላለም ሕይወት እንዳላቸው ለማረጋገጥ ነው (1ኛ ዮሐንስ 5፥13)።

 መለወጥ በዮሐንስ ራዕይ ውስጥ

የራእይ መጽሐፍ ታሪኩን ያጠናቅቃል፤ ይህም አስቀድሞ በኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው የእግዚአብሔር መንግሥት እንደሚፈጸም ለአማኞች ያረጋግጣል። ክፉን የሚያደርጉና ከአውሬው ጋር የሚስማሙ ለዘላለም ይፈረድባቸዋል፤ እስከ መጨረሻ የሚጸኑ ግን ወደ ሰማያዊቷ ከተማ ይገባሉ፤ እርስዋም አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ናት። የራእይ መጽሐፍ፣ ንስሓ የገቡት ብቻ ሕይወትን እንደሚያገኙ ያስረዳል (ራእይ 2፥5፣ 16፣ 21፣ 22፤ 3፥3፣ 19፤ 9፥20፣ 21፤ 16፥9፣ 11)።

ዋናው ጭብጥ ይሆንሙሉ ታሪኩ መሠረታዊ ነው

ለማጠቃለል ያህል መለወጥ በርግጥ የቅዱሳት መጻሕፍት ዋና ጭብጥ አይደለም። አማኞች እግዚአብሔርን እንዲያከብሩና ለዘላለም በእርሱ እንዲደሰቱ ተደርገዋል። እኛም በእርሱ እየተደሰትን በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው ዓለም እናከብረዋለን።

ነገር ግን በአዲስ ፍጥረት የሚደሰቱት የተለወጡ ሰዎች ብቻ ስለሆኑ፣ መለወጥ ለታሪኩ መሠረታዊ ነው። የሰው ልጅ ለመዳን ከኃጢአት ፊቱን መልሶ ወደ እግዚአብሔር መዞር አለበት። ከኃጢአታቸው ንስሐ ገብተው በተሰቀለውና በተነሣው በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ማመን አለባቸው። አንድ ሰው ለዚህ ዓለም መሻሻል በጥቂቱ ሆነ በብዙ መንገድ አስተዋጽዖ ቢያደርግም፣ ዳግም ካልተወለደ (ካልተለወጠ) በመጨረሻው ቀን ሥራው እርባና ቢስ ነው።

(ይህ  የመለወጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥነ መለኮት ክፍል 2 ነው።)

በቶማስ ሽራይነር


[1] “Conversion” ለሚለው የእንግሊዘኛ ቃል አቻ ትርጉም ስላልተገኘ፣ “መለወጥ” (‘መ’ ትጠብቃለች) በሚለው አማርኛ ቃል መተካቱን ልብ ይበሉ።

[2] ሲኖፕቲክስ ወንጌላት ተብለው የሚጠሩት ማቴዎስ፣ ማርቆስ እና ሉቃስ ወንጌላት ሲሆኑ ይህን ስያሜ ያገኙት እርስ በርሳቸው ስለሚመሳሰሉ ነው።