መለወጥ እና ሕብረት

የመለወጥ አስተምህሮህ ውስጥ ሕብረት የተባለው መሠረታዊ ነገር ከሌለ፣ ከመላ አካሉ ዋነኛው ክፍል እንደጎደለ ያህል ነው። የኪዳኑ ራስ ከኪዳኑን ሕዝብ ጋር አብሮ ሚመጣ ነው።

አስቀድሞ ወደ ላይ፣ ቀጥሎ ወደ ጎን

ሕብረት ፊተኛውን ቦታ መያዝ አለበት እየተባለ አይደለም። አንድ ሰው መጽደቅ “ስለ ነገረ ቤተ ክርስቲያን የመሆኑን ያክል ነገረ ድነት ተኮር አይደለም፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን የመሆኑን ያክል ድነት ተኮር አይደለም” በማለት የተናገሩትን የኤን. ቲ. ራይትን የታወቀ አባባል ሊያስብ ይችላል። “አዲስ ኪዳን ቅድሚያ የሰጠውን ኋላ ማድረግ፣ አዲስ ኪዳን ከኋላ ያሰፈረውን ደግሞ ፊት ማድረግ” የሚለው እውቅ የሆነ የዳግላስ ሙ አባባል ለዚህ ግልጽ ምሳሌ ይሆንልናል።

ኅጢአተኞች አስቀድመው ከእግዚአብሔር ጋር እስካልታረቁ ድረስ፣ ከሰዎች ጋር እውነተኛ የሆነ እርቅ ሊኖራቸው አይችልም። ‘ወደ ጎን’ የግድ ‘ወደ ላይ’ን ተከትሎ ይመጣል። ነገረ ቤተ ክርስቲያን የግድ ነገረ ክርስቶስን ይከተላል። ለማለት የተፈለገው ሕብረት የተባለው ክፍል ቅድሚያ መሆን የለበትም፤ አለዚያ ሁሉን ማጣት ይሆናል።

ነገር ግን መከተል ይኖርበታል። በርግጥ ሕብረት የሚባለው ክፍል የመለወጥ[1] አስተምህሮ ውስጥ ሊኖር ይገባል። በክርስቶስ ያለን የሕብረት አንድነት የመለወጥ ምልክት ብቻ ሳይሆን ዋናው ክፍልም ነው። ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መታረቅ እና ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ ማግኘት የሚለያዩ ነገሮች ቢሆኑም ሊነጣጠሉም  ግን አይችልም።

አንዳንዴ በመለወጥ (በድነት) አሠራር ላይ ትኩረት እየሰጠን ነገሩን ችላ እንለዋለን (ማለትም በአስተምህሮው ላይ ያሉ ውይይቶቻችን፣ በእግዚአብሄር ሉዓላዊነትና በሰዎች ድርሻ ወይም የንስሓና እምነት አስፈላጊነት ላይ ብቻ የተገደቡ ይሆናሉ።) ቢሆንም ግን ስለ መለወጥ ሙሉ የሆነ መረዳት እንዲኖር ከተፈለገ ከየትና ወዴት እንደተሻገርን ታሳቢ መደረግ ይኖርበታል። መለወጥ ከሞት ወደ ሕይወት መምጣትን፣ ከጨለማ አገዛዝ ወደ ብርሃን ግዛት መሻገራችንን ያካትታል። ከሰው አልበኝነት ወደ ሰው ማኅበር፣ ተቅበዝባዥ በግ ከመሆን ወደ መንጋው፣ ከአካሉ ከመነጠል ወደ አካሉ መቀላቀልን ያካትታል።

ከጴጥሮስ ንግግር ይሄን መመልከት ይቻላል:-

“እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥10)

ምሕረትን (ከላይ የሆነ እርቅ) መቀበል ሕዝብ ከመሆን (ወደ ጎን ከሆነ እርቅ) ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። ኅጢአታችንን ይቅር በማለት እግዚአብሔር ምሕረት አደረገልን፤ ሊቀር የማይችል ውጤቱ ደግሞ ወደ ሕዝቡ መቀላቀል ነው።

በቃል ኪዳኖች ውስጥ የሕብረት ተፈጥሮ

በርግጥ በመለወጣችን ውስጥ የሚገኘውን የሕብረት ሐሳብ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ካስቀመጠልን የቃል ኪዳን ምስል ውጭ ባለመመልከት፣ ነገሩን በሚገባ ማጤን እንችላለን። በብሉይ ኪዳን ያሉ ኪዳኖች ፍጻሜ የሚያገኙት በአብርሃም ዘር (ነጠላ) መሆኑ እውን ነው። ኢየሱስ አዲሱ እሥራኤል ነው። ሆኖም በአዲሱ ኪዳን ከክርስቶስ ጋር አንድ የሆነ ሁሉ የእግዚአብሔር እሥራኤልና የአብርሃም ዘር (ብዙ) መሆኑም እውነት ነው (ገላትያ 3፥29፤ 6፥16)።

በሌላ አነጋገር የኪዳኑ ራስ፣ ከራሱ ጋር የኪዳኑን ሕዝብ አብሮ ያቀርባል (ሮሜ 5፥12)። ስለዚህ በአዲሱ ኪዳን መካተት ማለት ወደ ሕዝብም መካተት ነው።

ስለዚህ በብሉይ ኪዳን የሚገኙ አዲስ ኪዳንን የሚያመለክቱ የተስፋ ቃሎች ስለ ሕዝብም ቃል የተገቡ ናቸው፦ “እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን፥ እያንዳንዱም ወንድሙን፦ እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም፤ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና፥ ይላል እግዚአብሔር። በደላቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ ወዲህ አላስብምና” (ኤርሚያስ 31፥34)። አዲሱ ኪዳን የይቅርታን (ወደ ላይ) ተስፋ ይሰጠናል፤ ጨምሮም የወንድሞች ሕብረትን (ወደ ጎን) ተስፋ ይገባልናል። 

“ወደ ጎን” እና “ወደ ላይ” በኤፌሶን 2

በሚገርም መንገድ ሙሉው ሐሳብ በኤፌሶን 2 ቀርቧል። ከቁጥር 1 እስከ 10 ስለ ይቅርታና ወደ ላይ ከእግዚአብሔር ጋር ስላገኘነው እርቅ ሲያብራራ “በጸጋ ድናችኋልና” ይላል። ከቁጥር 11 እስከ 20 ወደ ጎን ስለሆነው ደግሞ ፦ “ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና” ሲል ይናገራል (ቁ.14)።

የቁጥር 14 ክንውን በአላፊ ጊዜ ሰዋሰው የተቀመጠ መሆኑን ያስተውሏል። ክርስቶስ አስቀድሞ አይሁድና አሕዛብን አንድ አድርጓቸዋል። እዚህ ጋር ንግግሩ ትዕዛዝ ተኮር አይደለም። ጳውሎስ ተደራሲያኑ አንድነትን እንዲፈልጉ እያዘዛቸው ሳይሆን ይልቁን አስቀድሞ የሆነን ነገር አመላካች በሆነ አነጋገር ያስረዳቸዋል። የሆኑትን የሆኑት እግዚአብሔር ከፈጸመው ሥራ የተነሣ ነው፤ ይሄን ሥራም የፈጸመው ደግሞ ወደ ላይ የሆነውን እርቅ በፈጸመበት በክርስቶስ መስቀል ነው (“አመላካች” (indicative) እና “ትዕዛዝ” (imperative) በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት በኤፌሶን 4፥1-6 ይመልከቱ)።

በክርስቶስ ከሆነው ከአዲሱ ኪዳን ባሕርይ የተነሣ፣ የሕብረት አንድነት የመለወጥ ምልክት ውስጥ የሚካተት ነው። መለወጥ ማለት በክርስቶስ አካል ውስጥ ብልት መሆን ማለት ነው። አዲሱ ማንነታችን ሕብረትን ያካተተ ነው። ክርስቶስ ሕብረትን ማዕከል ያደረጉ ግለሰቦች አድርጎናል።

ይህንን ለመረዳት ቀላል መንገድ እንጠቀም። እናትና አባት አንድን ልጅ በጉዲፈቻ ለማሳደግ ወደ ማደጎ ቤት በሄዱ ጊዜ፣ ልጁን ወደ ቤት ይዘው መጥተው ከአዲስ ወንድሞችና እህቶች ጋር እንዲሆን ወደ ቤተሰቡ እራት ግብዣ ያመጡታል። ልጅ መሆን ወንድም ከመሆን ጋር አንድ ዐይነት አይደለም። ልጅነት መቅደም አለበት። ነገር ግን ወንድምነት ይከተላል። ሊባል የተፈለገው መለወጥ የቤተሰቡ የጋራ ፎቶ ውስጥ ያካትትሃል።

የግል ተግባራዊ እርምጃ፦ ቤተ ክርስቲያንን መቀላቀል!

በእኛ ሕይወት እንዴት እንተግብረው? ቀላል ነው፦ በቤተ ክርስቲያን እንታቀፍ!

ጻድቅ ስለተደረግክ ጻድቅ ሁን። የአካሉ ብልት ሆነሃል፤ ስለዚህ የሚታየው አካል አባል ሁን። አንድ ተደርገሃል፤ ስለዚህ ከክርስቲያኖች ማኅበር ጋር አንድ ሁን።

የጋራ ተግባራዊ እርምጃ፦ አሠራሩ ላይ ትክክል መሆን!

ይህን ለቤተክርስቲያናችን እንዴት እንተርጉመው? ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው በአስተምህሯችን ውስጥ ወሳኝ የሆነውን የመለወጥ አሠራርን በትክክል መረዳት ማለት ነው። ስለ እግዚአብሔር ሉዓላዊነትና የሰዎች ድርሻ፣ ስለ ንስሓና እምነት ጠንካራ የሆነ እይታ እንዲኖረን እንፈልጋለን። ነገር ግን እዚህ ጋር ሚዛን ካልጠበቀን መጨረሻችን ብልሹ የሆነ ቤተ ክርስቲያን ይሆናል። በመለወጥ ሳህን የምናስቀምጠው ያ የቤተክርስቲያኒቱ ማዕድ ይሆናል።

የመለወጥ አስተምህሮህ ስለ እግዚአብሔር ሉዓላዊነት ጠንካራ አመለካከት ከጎደለው፣ ስብከትህና ወንጌል ስርጭትህም ጨቋኝና ሰውን ለማስደሰት የሚዳክር ይሆናል። በአመራር ጉዳይ ላይ የሚኖርህ መረዳት ተፃራሪ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው። ከአቅም በላይ የሆነ የፕሮግራም ሰሌዳ፣ ራስህንና ማህበሩን አሸክመህ ለዝለት ትጋልጣለህ። የአባልነት ልምምዶችህ “የተለየ” ስምና ጥቅም ተኮር ይሆናሉ። ተጠያቂነትህና ስርዓት ያለው ልምምድህ እየጠፋ መሄዱ አይቀሬ ስለሆነ፣ ቅድስናህ አደጋ ላይ ይወድቃል።  እያለ ዝርዝሩ ይቀጥላል።

የመለወጥ አስተምህሮህ የሰው ድርሻን በተመለከተ ጠንካራ እይታ ከጎደለው፣ ለራስህም ለሌሎችም ስጦታ ባለ አደራ ከመሆን ትሰንፋለህ። የስብከት ዝግጅትና የወንጌል ስርጭትን ለመፈጸም ስትሠራ፣ ጥቅም ፈላጊ በመሆን ትፈተናለህ። ለተጎዱት ፍቅርና ርኅራኄ ከማሳየት ትጎድላለህ። በአጥባቂነት ወይም ዝግ ባለ መንፈስ ወደ ሌሎች መቅረብ ትጀመራለህ። ደካማ በሆነ የጸሎት ሕይወት በማለፍ፣ አላስፈላጊ መከራ ልትቀበል ትችላለህ፤ በዚህም ያንተ ሊሆኑ ከሚችሉ በረከቶች ትተላለፋለህ። ፍቅርን አደጋ ላይ ትጥለዋለህ። እያለ ዝርዝሩ ይቀጥላል።

የመለወጥ አስተምህሮህ ንስሓን በተመለከተ ጠንካራ ግንዛቤ ከጎደለው፣ ለሰዎች የድነትን እርግጠኝነት ለማቅረብ እየቸኮልክ ነገር ግን ክርስቶስን በመከተል ዋጋ እንዲከፍሉ ከማድረግ ትዘገያለህ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዓለማዊነትንና መከፋፈልን ችለህ ትቀመጣለህ፤ የቤተ ክርስቲያንህ አባላትም ከእምነታቸው ማነስ የተነሣ በእነዚህ ጉዳዮች አመቻምቸው እንዲቀመጡ ይሆናል። ጸጋም ስለ ሚረክስ ስም ብቻ ሆኖ የመቀመጡ ዝንባሌ ይስተዋላል። በጠቅላላው ቤተክርስቲያኒቱ ከዓለም በማይለይ መልኩ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እንጂ ስለ ጌትነቱ መዘመር የማትወድ ትሆናለች።

የመለወጥ አስተምህሮህ እምነትን በተመለከተ ጠንካራ ግንዛቤ ከጎደለው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ጭንቀት በሞላበት የራስን ጽድቅ ለማቆምና ሰውን ለማስደሰት በሚጥሩ ወግ አጥባቂዎች ትሞላለች። ራስን በመግዛት የተሻሉ የሚባሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት፣ ራሳቸውን በማሳት ስለራሳቸው መልካም ነገር ሲያስቡ ራስን በመግዛት ያልተሻሉት አባላት ደግሞ ስውር ኅጢአታቸውን በመደበቅ ራስን በተደጋጋሚ መውቀስን ይለማመዳሉ፤ በዚህም ሌሎችን ቅር ያሰኛሉ። ግልፅነት እየደበዘዘ ግብዝነት ስፍራ እየያዘ ይሄዳል። የጠፉትና በውጭ ያሉት የእውነተኛውን ጸጋ ግለትና ርኅራኄ ሳይካፈሉ ይቀራል። እንደየባህሉ ልዩነት ያላቸው ነገሮች ከሕግ ጋር መምታት ይጀምራሉ። ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለ ክርስቶስ ጌትነት ለመስበክ እየበረታች፣ በደም የተለወሰውን በግ ለእርሷ እንደታረደ መዘመርን ትዘነጋለች።

እርግጥ ነው ሰፊ ሐሳብ ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ። ነገሮች የዚህን ያክል ጥርት ባለ መስፈሪያ ላይገኙ ይችላል። ቢሆንም በእነዚህ ሁሉ ምሳሌዎች ውስጥ የተላለፈው ዋና ሐሳብ፣ በመለወጥ እና በቤተክርስቲያን መካከል ስላለው ጥብቅ ግንኙነት ያትታል። መለወጥ የግድ የሕብረትን ክፍል የሚያካትት ከሆነ፣ ወይም ጠንከር ባለ አነጋገር የግለሰብ መለወጥ ሕብረትን መመሥረቱ አይቀሬ ከሆነ፣ ከመለወጥ አስተምህሮህ ጋር የሚገናኝ ማንኛውም ነገር ምን ዐይነት ቤተ ክርስቲያን እንደምታገኝ ይወስነዋል።

ጤነኛ ቤተ ክርስቲያንን ትፈልጋለህ? በመለወጥ አስተምህሮህ ላይ በደንብ ሥራ፤ ለማኅበሩም የመለወጥ አስተምህሮ ሁሉን አቅጣጫ አስተምራቸው። በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያንህ የሚደረጉ ፕሮግራሞች ብዙ መልክ ካለውና ጠንካራ ከሆነው ከዚህ አስተምህሮ ጋር አብረው እየተጓዙ መሆኑን አረጋግጥ።

ጆናታን ሊማን


[1]  “Conversion” ለሚለው የእንግሊዘኛ ቃል አቻ ትርጉም ስላልተገኘ፣ “መለወጥ” (‘መ’ ትጠብቃለች) በሚለው አማርኛ ቃል መተካቱን ልብ ይበሉ።