መለወጥ፣ እግዚአብሔር እና ሁለንተናዊ ማንነት

ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ፣ ሰዎች እንዲድኑ እና እግዚአብሔርን እንዲያውቁ መለወጥ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ግልጽ ያደርጋሉ። ከኃጢአታችን ዞር ካላልን እና ወደ እግዚአብሔር ካልተመለስን፣ መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ  የልብ መገረዝ (ዘዳግም 30፥6፤ ሮሜ 2፥25-29) ብሎ የሚገልጸውን እውነት በተግባር እስካላወቅን ድረስ እግዚአብሔርን በማዳኑ አናውቀውም። ከፍርዱና ከቁጣው በታች አለን (ኤፌሶን 2፥1-3)።

ቶም ሽራይነር በ9ማርክስ ጆርናል በጻፈው ሁለት አምዶቹ እንዳሳየው፣ የመለወጥን አስፈላጊነት መላው መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራሉ። መለወጥ የቅዱሳት መጻሕፍት ዋና ሐተታ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን በርግጥ ለጠቅላላው የመቤዠት ታሪክ መሠረት ነው። በተለይም መቤዠት ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ባለው ተዛምዶ ከመለወጥ ጋር ይያያዛል። ከመለወጥ ውጪ እግዚአብሔርን በማዳኑ መንገድ ማወቅ አንችልም። የኃጢአትን ይቅርታ ማግኘት አንችልም። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እና የማዳኑ መንግሥት መግባት አንችልም።

ነገር ግን፣ አሁንም፣ መለወጥ ለምን አስፈለገ? ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል።

ንጽጽር፣ ስለመለወጥ ሰፊ ተቀባይነት ባለው ግንዛቤ እመጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነው ግንዛቤ መካከል

ጥያቄውን ከመመለሳችን በፊት፣ ስለ “መለወጥ” እየተነጋገርን ያለነው የቃሉን የተዛባ ትርጉም ይዘን ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንዛቤ መሠረት መሆኑን ማስተዋል ተገቢ ነው። ልዩነቱ ምንድን ነው?

በ “መንፈሳዊ ለውጥ” ላይ የጎግል ፍለጋን ካደረግን፣ ዋናዎቹ መልሶች ይህን ይመስላሉ፦ መለወጥ “አዲስ ሃይማኖት መቀበል ነው” ወይም “አዲስን እምነት መከታተል” ነው። እነዚህ ትርጓሜዎች “መለወጥ” የአንድ ሰው አስተሳሰብ ወይም አመለካከት ለውጥ አድርገው ይመለከቱታል። ይህም በአብዛኛው ጊዜ ግለሰቡን በቀድሞ ሕይወቱ እንዲቀጥል ያደርገዋል። ነገር ግን ይህ የክርስትና መለወጥ አይደለም።

ይልቅ፣ የክርስቲያናዊ መለወጥ በሰዎች ሕይወት ውስጥ በሚሠራው የሥላሴ ሉዓላዊ እና ልዕለ ተፈጥሮአዊ ሥራ ላይ የሚደገፍ ነው። በመለወጥ ሁናቴ ቅጽበት፣ እግዚአብሔር ሰዎችን ከመንፈሳዊ ሞት ወደ ሕይወት ያመጣቸዋል። ይህም በአንድ ወቅት የሚወዱትን ማለትም ኃጢአታቸውን እና በእግዚአብሔር ላይ ማመፃቸውን እንዲጸየፉ፣ ደግሞም ወደ ክርስቶስ እንዲመለሱ ያስችላቸዋል።

የመለወጥን አስፈላጊነት የሚያስረግጡ ሦስት እውነቶች

ይህ የመለወጥ ግንዛቤ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው? ሦስት መሠረታዊ እውነቶች ስለ መለወጥ መጽሐፍ ቅዱስ  የሚያስተምረውን ትምህርት ደግፈው ይይዛሉ። እነዚህም እውነቶች መለወጥ በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በሥነ መለኮት እና በወንጌል አዋጅ ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንድናይ ይረዱናል።

እነዚህ ሦስት እውነቶች ሙሉ በሙሉ እርስ በርስ የተሳሰሩ መሆናቸውን አጽንኦት ልስጥ። እነዚህን ሌሎች እውነቶች ካልተረዳን በስተቀር መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለወጥ የሚያስተምረውን በትክክል ልንረዳው አንችለም። ይህም በቀላሉ ሥነ መለኮታዊ እምነቶቻችን እርስ በርስ የሚደጋገፉ መሆናቸውን ያስታውሱናል። በአንድ ሥነ መለኮታዊ ጉዳይ ስሕተት ውስጥ መግባት በሌሎች ሥነ መለኮታዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረዋል። ይህም በእርግጠኝነት ስለ መለወጥ ባለን ግንዛቤም ተመሳሳይ ውጤት አለው።

የሰው ችግር

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለወጥ የሚያስተምረው የመጀመሪያው መሠረታዊ እውነት፣ ስለ ሰው ልጆች ችግር ያለው ምልከታ ነው። ምንም እንኳን የሰው ልጆች በእግዚአብሔር መልክ በክብር ብንፈጠርም፣ በአዳም በኩል በፈጣሪያችን ላይ በማመፅ ለእግዚአብሔር ቁጣ የተገዛን ኃጢአተኞች ሆንን (ዘፍጥረት 3፤ ሮሜ 5፥12-21)።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኃጢአት ሲናገር እና ሰዎችን እንደ ኃጢአተኛ  ሲያቀርብ ይህን እንደ ትንሽ ችግር አይመለከተውም። የተሻለ ሰው ለመሆን በራስ ጥረት፣ በተጨማሪ ትምህርት ወይም በግል ውሳኔ እንኳ የሚስተካከል ነገር አይደለም። እንዲህ ያሉ በየወቅቱ የሚቀርቡ መፍትሔዎች ቅዱሳት መጻሕፍት በብርቱ እና በግልጽ የሚያብራሩትን የሰውን ልጅ ችግር ምንነት በእጅጉ ያቃልላሉ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ዕይታ፣ ኅጢአት በአዳም (የቃል ኪዳን ወኪላችን [ሮሜ 3፥9-12፣ 23፤ 5፥12-21፤ 1ኛ ቆሮንጦስ 15፥22]) ምክንያት ለሁሉም ሰው የተረፈ የዓለም ጦስ ብቻ አይደለም። ይህ እውነት በተፈጥሮ እና በድርጊት ኃጢአተኞች እንድንሆን ያደርገናል (ኤፌሶን 2፥1-3)። በአዳም እና በራሳችን ምርጫዋች፣ ወደዚህ ዓለም በውድቀት የተወለድን ፍጥረት በመሆን በእግዚአብሔር ላይ የሞራል ዓመፀኞች ሆነናል። ይህ ደገሞ በራሳችን ተነሳሽነት እና ተግባር መለወጥ ወደ ማንችልበት ሁኔታ ወስዶናል። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ከእግዚአብሔር ሉዓላዊ ጸጋ ውጭ ሁኔታችንን መለወጥ አንችልም። በውድቀታችን፣ በኃጢአታችን መደሰት እና የእግዚአብሔርን ትክክለኛ አገዛዝ በእኛ ላይ በፈቃደኝነት መቃወም፣ ራሳችንን ለማዳን እና ለመለወጥ እንደማንችል የሚያሳይ ማስረጃ ነው (ሮሜ 8፥7)። ውጤቱም (ዕውቅና ብንሰጠውም ባንሰጠውም) በእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣ ሥር እንቆማለን (ሮሜ 8፥1፤ ኤፌሶን 2፥1-3)። በኃጢአታችን ውስጥ ሆነን፣ በአጽናፈ ዓለሙ ዳኛ ፊት ያለንበት ሁኔታ በኩነኔ እና በጥፋተኝነት ነው (ሕዝቅኤል 18፥20፤ ሮሜ 5፥12፣ 15-19፤ 8፥1)። ቅዱሳት መጻሕፍት ይህንን ሁኔታ እንደ ሞት ይገልጹታል፤ መንፈሳዊ በመጨረሻም ደግሞ ሥጋዊ ሞት ነው (ዘፍጥረት 2፥16-17፤ ኤፌሶን 2፥1፤ ሮሜ 6፥23)።

ለዚህ ችግር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መድኃኒት የሆነው ደህንነት፣ ይህንን አስከፊ ሁኔታ ይለውጠዋል። በዚህ ክስተት ውስጥ ዋናው ነጥብ መለወጥ የሚለው ሐሳብ ነው።

በመጀመሪያ የሚያስፈልገን ለኃጢአታችን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋ የሚከፍል፣ በተጨማሪም የእግዚአብሔርን የጽድቅ መስፈርቶችና በእኛ ላይ ያለውን ፍርድ የሚያረካ አዳኝ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በሥጋ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ፣ ለእኛ ሲል በመስቀሉ ሥራው ይህንኑ አደረገ። የእግዚአብሔርን የፍትሕ መስፈርቶች ያሟላል፤ ኃጢአታችን ሙሉ በሙሉ ተከፈሏል (ሮሜ 3፥21-26፤ ገላትያ 3፥13-14፤ ቆላስያስ 2፥13-15፤ ዕብራውያን 2፥5-18)።

በተጨማሪም፣ ለኃጢአታችን መከፈል ብቻ ሳይሆን፣ ከመንፈሳዊ ሞት ወደ ሕይወት ልንመጣ ይገባናል። ይህም በማንነታችን ላይ ሙሉ በሙሉ መለወጥን ያስከትላል (ሮሜ 6፥1-23፤ ኤፌሶን 1፥18-23፤ 2፥4-10)። እግዚአብሔር ከሞት ወደ ሕይወት ሊጠራን እና በእግዚአብሔር መንፈስ በኩል አዲስ ልደት ሊሰጠን ያስፈልገናል (ኤፌሶን 1፥3-14፤ ዮሐንስ 3፥1-8)። ከኃጢአታችን በሽታ እንድንመለስ፣ በእግዚአብሔርና በአገዛዙ ላይ ያለንን ተቃውሞ አስወግደን ለወንጌል በንስሓና በእምነት ምላሽ እንድንሰጥ ከኪዳናችን ራስ ትንሣኤ ጋር የሚመሳሰል ትንሣኤ ያስፈልገናል (ዮሐንስ 3፥5፤ 6፥44፤ 1ኛ ቆሮንጦስ 2፥14)።

በጥቅሉ፣ መለወጥ አስፈላጊ የሆነው በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተገለጸው ለሰው ልጅ ችግር አሳሳቢነት የመፍትሔው አካል ስለሆነ ነው።

አስተምሮተ እግዚአብሔር

ሁለተኛ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የመለወጥ አስፈላጊነት ትምህርት የሚያጸናው እና ትርጉም እንዲሰጥ የሚያደርገው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ማንነትና እና ባሕርይ የሚያስተምረው እውነት ነው።

ከላይ እንደተገለጸው፣ እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ሁለት እውነቶች እርስ በርሳቸው ይቆራኛሉ። የሰው ችግር ከእግዚአብሔር ማንነት ጋር የተነካካ ነው። ችግራችን በእውነተኛ ቀለሞቹ ሊታይ የሚችለው ከእግዚአብሔር ጻድቅ እና ቅዱስ ባሕሪ አንጻር ብቻ ነው።

መለወጥ አስፈላጊ የሆነው ኃጢአተኛ እና ዓመፀኛ ፍጥረታት በእግዚአብሔር ቅዱስ መገኘት ውስጥ መኖር ስለማንችል ነው። ኃጢአት የአጽናፈ ዓለሙ ገዢ ከሆነው የእግዚአብሔር ባሕርይ ብቻ ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር የቃል ኪዳን መገኘትም ለየን (ዘፍጥረት 3፥21-24፤ ኤፌሶን 2፥11-18፤ ዕብራውያን 9)። እግዚአብሔርን እንድናውቅና የእርሱ ሠራተኞች ሆነን ለእግዚአብሔር ክብር ፍጥረትን እንድንመራ፣ እንደ ልዑላን እየገዛን በእርሱ ፊት እንድንኖር የተበጀነው እኛ፣ አሁን በእግዚአብሔር ቁጣና ፍርድ ሥር ቆመናል።

ስለዚህ፣ የእግዚአብሔር ቅዱስ ባሕርይ እግዚአብሔር በልጁ ባደረገው የመሥዋዕቱ መግቦት ካልተፈጸመ በስተቀር፣ በማዳኑ እግዚአብሔርን ማወቅ አንችልም (ሮሜ 6፤ ኤፌሶን 4፥20-24፤ ቆላስያስ 3፥1-14)። በተጨማሪም፣ በእግዚአብሔር ፊት በመጽደቃችን የፍርድ መሻር አስፈላጊ ቢሆንም፣ በቂ ግን አይደለም። ድነት ኃጢአትን ከውስጣችን ማስወገድን እና የወደቀውን ተፈጥሮአችንን መለወጥ ያካትታል። ይህ የሚጀምረው በመንፈስ ሥራ ዳግም በመወለድ ከክርስቶስ ጋር አንድ ስንሆን ነው። ይህም በፈቃደኝነት ከኃጢአት ተመልሰን በጌታችን በክርስቶስ የተጠናቀቀ ሥራ እንድናርፍ ያስችለናል።

በሌላ አነጋገር፣ እግዚአብሔር እርሱ ቅዱስ እንደሆነ እኛም ቅዱሳን እንዲሆኑ ግድ ይላልና መለወጥ የግድ አስፈላጊ ነው። ስለዚህ በፊቱ እንድንኖር የክርስቶስን ጽድቅ ልንለብስ፣ በመንፈስ ኃይል ተለውጠን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት ልንሆን ይገባናል (2ኛ ቆሮንጦስ 5፥17-21)። የኃጢአታቸው ዕዳ ሙሉ በሙሉ ሳይከፈል፣ በመንፈስ ዳግመኛ ሳይወለዱ፣ ከክርስቶስ ጋር በእምነት አንድ ሳይሆኑ፣ ሰዎች ወደ ተፈጠሩበት ዓላማ የሚመለሱበትና በአዲስ ፍጥረት የሚገኘውን ጥቅም ሁሉ የሚያገኙበት መንገድ የለም።

ቅዱሱና ፍጹም ጻድቁ እግዚአብሔር፣ ፍጥረታቱ እንደ ታዛዥ ልጆችና በአምሳሉ እንደተበጁ ፍጡራን ይታዘዙት እንደሚፈልግ መረዳት ካልቻልን፣ መለወጥ ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ፈጽሞ አይገባንም።

በተጨማሪም፣ የእኛ መለወጥ የሚከናወነው በሥላሴ ሉዓላዊ ጸጋ ብቻ እንደሆነ ካልተረዳን፣ እግዚአብሔር ለእኛ ለሕዝቡ ያለውን የፍቅሩን ጥልቀት እና ስፋት ሙሉ በሙሉ አናደንቅም።

መለወጥ —ሁለንተናችን ወደ እግዚአብሔር መዞሩንንስሓን እና እምነትን ያካትታል

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መለወጥ የሚሰጠውን ትምህርት እንድንረዳ የሚረዳን ሦስተኛው መሠረታዊ እውነት፣ መለወጥ ሁለንተናን የሚያካትት ለውጥ መሆኑ ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት፣ መለወጥ ሁለቱንም ማለትም ከኃጢአት መመለስን (ንስሓ) እና ወደ ክርስቶስ መዞርን (እምነት) ያካትታል። ሁለቱም ለመለወጥ አስፈላጊ ናቸው። በተጨማሪም ንስሓ እና እምነት እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው።

በሌላ አነጋገር፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መለወጥ በግለሰቡ ሕይወት ላይ ምንም ለውጥ የማያመጣ የዕውቀት አመለካከት ለውጥ ብቻ ሊሆን በጭራሽ አይችልም። እንደ አለመታደል ሆኖ፣ በብዙ ቤተ ክርስቲያኖቻችን ተለውጠናል የሚሉ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ እውነተኛ የለውጥ ማስረጃ ሳይኖር፣ ስለ ወንጌል ያላቸውን አእምሮአዊ ዕውቀት ብቻ ይገልጣሉ።

ቅዱሳት መጻሕፍት ይህን ዐይነት ዕውቀት ብቻ የሆነ ለውጥ እንደ ሐሰተኛ ለውጥ ይመለከቱታል (ማቴዎስ 7፥21-23)። እግዚአብሔር እንደ ቃል ኪዳኑ ፍጥረታት ለእርሱ ሁለንተናዊ ምላሽ እንድንሰጥ ይጠይቃል። ኃጢአታችን በእግዚአብሔር ላይ የተደረገ ሁለንተናዊ ዐመፅ ነው። የክርስቲያን መዳን ሁለንተናዊ የሆነ ለውጥ ነው። በቀላል አገላለጽ አዲስ ፍጥረት መሆን ነው። መለወጥ ከኃጢአት መመለስን እና ወደ ክርስቶስ መዞርን ያካትታል፤ ይህም ሁለንተናን ማለትም ሐሳብን፣ ፈቃድን እና ስሜትን ያካትታል (ሐዋሪያት 2፥37-38፤ 2ኛ ቆሮንጦስ 7፥10፤ ዕብራውያን 6፥1)።

ኢየሱስ ባርኔጣችንን ማውለቅ ብቻ በቂ አይደለም

መለወጥ አማራጭ አይደለም፤ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ድህነትን እና ወንጌልን ስለ መለወጥ ካለን ጠንካራ ዕይታ ውጭ ልንረዳው አንችልም።

በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የተንሰራፋው ‘ስም ክርስትና’ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክርስትና አይደለም። ባርኔጣችንን ማውለቅ ብቻ በቂ አይደለም። ይልቁኑ ንስሓ ለመግባትና ወንጌልን እንድናምን፣ በእግዚአብሔር መንፈስ ሥራ አዲስ ሕይወት በማግኘት በሕይወታችን ውስጥ ሉዓላዊ ጸጋ ከተሞላበት የእግዚአብሔር አሠራር ጋር ልንገናኝ ይገባል።

ስለ መለወጥ ያለን የተሳሳተ ግንዛቤ ብዙውን ጊዜ በተሳሳተ ሥነ መለኮቶቻችን ምክንያት የሚፈጠሩ ናቸው። ለዚህ መፍትሔው በመንበርከክ ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት መመለስ ነው፤ ታላቁ አምላካችን ቤተ ክርስቲያኑን እንደገና እንዲያነቃቃና በወንጌል አዋጅ ሰዎች ሁሉ ከኃጢአታቸው ንስሓ እንዲገቡና ጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ እንዲያምኑ መጠየቅ ነው።

በስቴፈን ጄ. ዌለም