መለወጥ እና የእስራኤል ታሪክ

በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ የምናየው አንድ ወጥ ታሪክ ነው ብሎ አበክሮ ይናገራል፤ እናም ትክክል ነው። ይህም ታሪክ አብዛኛውን ጊዜ ፍጥረት፣ ውድቀት፣ ቤዝዎት እና መጠቅለል በሚል ይተነተናል። ከፍጥረት ተነሥቶ አዲስ ፍጥረት ላይ የሚያርፍ ታሪክ ነው።

ታዲያ በዚህ የታሪክ ቅደም ተከተል፣ መለወጥ[1]  (ዳግም ውልደት) የቱ ጋር ነው ያለው? መለወጥን የምናገኘው የቤዝዎት ክፍል ላይ ነው። በርግጥ መለወጥ የታሪኩ ዋና ርዕሰ ጉዳይ አይደለም። የዚህ ታሪክ ዋና ማዕከል ‘ለምን ዓላማ ሰዎች ዳግም ይወለዳሉ’ የሚለው ነው። የዚህ ታሪክ ዋና ማዕከል ለምን ዓላማ ተፈጠርን የሚለው ነው። የዌስት ሚኒስተር የእምነት መግለጫ እንደሚያትተው፣ የተፈጠርነው እግዚአበሔርን ለማክበር እና ለዘላለም በእርሱ ለመደሰት ነው። አዲስ ዓለም እየመጣ ነው፤ ከክርስቶስ ጋር ለዘላለም የምንነግሥበት አዲስ ዓለም እየመጣ ነው፤ እርሱንም ፊት ለፊት እናየዋለን (ራዕይ 22፥4)።

ይህም ሆኖ መለወጥ (ዳግም ውልደት) የታሪኩ ወሳኝ ክፍል ነው። ምክንያቱም ያለ መለወጥ የእግዚአብሔር አዲስ ፍጥረት መሆን አንችልም። ስለ ተቤዠን፣ ከጨለማው ግዛት ስለታደገን እና ወደሚወደው ልጅ መንግሥት ስላስገባን፣ በሰማያዊው ከተማ ሆነን ለዘላለም እንደምናመልከው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ነግሮናል። በክርስቶስ መስቀል እና ትንሣኤ በኩል፣ በሕይወታችን የታየውን ወሳኝ የእግዚአብሔር የማዳን ሥራ መቼም አንረሳውም። ሁሌም ቢሆን የአምልኳችን ማዕከል ይሄ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ አብዛኛው የታሪክ ዘውግ የእስራኤል ታሪክ ስለሆነ፣ ከዚያ በመነሣት መለወጥ ለምን ለዋናው ታሪክ ወሳኝ እንደሆነ በአጭሩ ማሳየት እፈልጋለሁ።

መለወጥ እና የእስራኤል ታሪክ

የእስራኤል ታሪክ ከአዳም ነው የሚጀምረው። አዳምና ሔዋን የተፈጠሩት እግዚአብሔርን ወክለው ዓለምን በመግዛት ለእርሱ ክብር እንዲያመጡ ነበር (ዘፍጥረት 1፥26-28)። እግዚአብሔር በፈጠረው ዓለም ላይ የእርሱ ምክትል ገዢ እንዲሆኑ ነበር የታቀደው። ከእግዚአብሔር ጌትነት በታች በመሆን፣ በእርሱ በመታመን እና ትዕዛዛቱን በማክበር እንዲገዙ ነበር። ነገር ግን በጌትነቱ ላይ ዐመፁ። ለፈጣሪ አምልኮን እና ምስጋናን ከመስጠት ይልቅ ፍጡራንን አመለኩ። ባለመታዘዛቸው ምክንያት ሞቱ (ዘፍጥረት 2፥17)። ኅጢአት ባደረጉ በዚያ ቅጽበት ከእግዚአብሔር ተለያዩ። ንስሓ ካልገቡ የዘላለም ሞት እንደሚያገኛቸው እርግጥ ሆነ።

ከኅጢአታቸው ቀጥሎ አዳም እና ሔዋን የሚያስፈልጋቸው መለወጥ ነበረ። ከእርሱ ጋር ትክክለኛ ግንኙነት በሌላቸው ጊዜ፣ ዓለምን ለእግዚአብሔር ማስተዳደር እና በረከቱንም ወደ ምድር ማስተላለፍ አይችሉም ነበረ። ሆኖም እግዚአብሔር በእባቡ እና በእባቡ ዘር ላይ የሴቲቱ ዘር ድል እንደሚቀዳጅ ቃል ገብቷል (ዘፍጥረት 3፥15)። የሰው ልጅ የመጀመሪያ ታሪክ የሰውን ልጅ አደገኛ ክፋት ያሳያል። ሰዎች ሁሉ የአዳም ወንድና ሴት ልጅ (ሮሜ 5፥12-19) ደግሞም የእባቡ ዘር (ማቴዎስ 13፥37-38፤ ዮሐንስ 8፥44፤ 1ኛ ዮሐንስ 5፥19) ሆነው ወደ ዓለም ይገባሉ። የእግዚአብሔርን የማዳን ጸጋ ያዩት ብቻ ከሰይጣን አገዛዝ ይድናሉ። ለምሳሌ ቃየን ጻድቁን አቤል በመግደል ከየትኛው ወገን እንደሆነ አሳይቷል (ዘፍጥረት 4፥1-16)። የክፋት ኅይሎች ምን ያህል ጠንካራ ነበሩ? በኖኅ ዘመን በዓለም ውስጥ የቀሩት ስምንት ጻድቃን ብቻ እስኪሆኑ ድረስ ክፋት ነበረ፤ የሰው ልጅ እጅግ ክፉ ነበር፤ ዘፍጥረት 6፥5 የኅጢአትን መስፋፋት ይመሰክራል። የእባቡ ዘር ምድርን ተቆጣጠረ፤ እግዚአብሔር ግን ኅጢአተኞችን በጎርፍ በማጥፋት ቅድስናውን እና ጌትነቱን አሳይቷል። ስለዚህ አዲስ ጅማሮ ሆነ። ነገር ግን የሰው ልብ ስላልተለወጠ ይህ አዲስ ጅማሮ መሻሻልን አላሳየም (ዘፍጥረት 8፥21)። በባቢሎን ግንብ ላይ የነበረው ሁኔታ አዲሱ ፍጥረት ለእነርሱ ሩቅ እንደነበር ያሳየናል (ዘፍጥረት 11፥1-9)። ዓለም ጌታን በሚወዱ ሰዎች አልተገዛችም ነበር። አዲሱ ፍጥረት ያለ አዲስ ልብ ሊመጣ አይችልም።

በባቢሎን የነበረው የሰው ልጆች መበተን እና ፍርድ በአብርሃም መጠራት ታደሰ (ዘፍጥረት 12፥1-3)። በተጨማሪም በክፉ ዓለም ውስጥ የሚኖር አንድ ሰው ነበር። ነገር ግን ይህ አንድ ሰው በእግዚአብሔር የተጠራ እና የበረከት ቃል የተገባለት ሰው ነበር።  በአንድ ጎን ከተመለከትነው ከነዓን አዲስ ዔደን፣ አብርሃም ደግሞ አዲሱ አዳም ነበር። የአብርሃም ልጆች የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ፤ ለአብርሃም የተሰጠው በረከት ደግሞ ቀስ በቀስ ወደ ዓለም ሁሉ ይሰራጫል። ከዚያም አዳምና ሔዋን እንዳደረጉት ሁሉ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ጌትነት ዓለምን ይገዛል።

በጣም የሚገርመው ነገር ታሪኩ ሙሉ በሙሉ እስኪገለጥ ድረስ ረዥም ጊዜ ወስዷል። የተሰጡት ተስፋዎች ለሁለት ሺህ ዓመታት ያህል አልተፈጸሙም ነበር፤ የዘፍጥረት መጽሐፍም የሚያተኩረው ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ቃል የተገቡላቸው ልጆች መስጠት ላይ ነው። እነዚህ ሰዎች የከነዓንን ምድር አልወረሱም። በረከት ወደ ዓለም ሁሉ ሲሰራጭ አላዩም። ከዘጸአት እስከ ዘዳግም ድረስ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ነፃ መውጣታቸውን በመዘርዘር ይተርካል (ዘጸአት 1-15)። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ብዙ ልጆችን እንደሚሰጥ የገባውን ቃል እየፈጸመ ነበር፤ የእስራኤል ሕዝብ በብዙ ቁጥር እያደገ ነበር። ጌታ ከግብፅ ነጻ ያወጣቸው ወደ አዲሲቱ ዔደን፣ ወደ ከነዓን ምድር ሊያመጣቸው ነው። በዚህች ስፍራ (ከነዓን) የእግዚአብሔር ንጉሣዊ አገዛዝ በሕዝቡ ላይ ይገለጣል፤ በዚህም አሕዛብ በእግዚአብሔር ጌትነት ሥር የሚኖሩ ሕዝቦች ያላቸውን ጽድቅ፣ ሰላም እና ብልጽግና እንዲያዩ ነበረ። ነገር ግን ከግብፅ የወጣው ትውልድ ወደ ከነዓን አልገባም (ዘኁልቅ 14፥20-38)። ምንም እንኳን በግብፅ ታላቁን ማዳን እና የእግዚአብሔርን ምልክትና ተአምራት ቢያዩም፣ በእግዚአብሔር ቃል ላይ መደገፍን እምቢ አሉ። ከግብፅ የወጡት አብዛኞቹ የእስራኤል ሰዎች ግትር እና ዓመፀኞች ነበሩ። ጌታንም በእውነት አያውቁም ነበረ (1ኛ ቆሮንጦስ 10፥1-12፤ ዕብራውያን 3፥7-4፥11)። እግዚአብሔርን እንዲወዱና እንዲፈሩት፣ እንደ አምላካቸው እንዲደገፉበት እና በመንገዶቹም ሁሉ ይሄዱ ዘንድ ልባቸው መገረዝ – መለወጥ ነበረበት (ዘዳግም 30፥6)። በምድረ በዳ ከነበረው ትውልድ በኋላ የተነሡት ልጆች፣ ያለፈው ትውልድ በወደቀበት ፈንታ እነርሱ ተሳክቶላቸዋል። ኢያሱና እስራኤል እግዚአብሔርን በመታመን እና በመታዘዝ ለአብርሃም የተገባለትን የከነዓንን ምድር ወረሱ (ኢያሱ 21፥45፤ 23፥14)። በዚህ ጊዜ እስራኤል በአዲሱ ዔደን ውስጥ በመኖር በያህዌ ጌትነት ሥር የመኖርን ውበት እና ክብር ለማሳየት ተዘጋጅተው ነበር። ሆኖም ግን አሁንም በፍሬው እምብርት ትል ነበር። የእስራኤል ታዛዥነት ለአጭር ጊዜ ነበር። በመሳፍንት መጽሐፍ መሠረት፣ እስራኤል ለአሕዛብ በረከት አልሆነም፤ ይልቁንም እነርሱን መሰለ። ወደ አረማውያን መንገድ ተመለሱ። ሕዝቡ ንስሓ ሲገቡ ጌታ በተደጋጋሚ ያድናቸው ነበር፤ ነገር ግን ልባቸው አልተለወጠም፤ ወደ ኅጢአታቸውም ይመለሳሉ።

እስራኤል ምን ማድረግ ነበረበት? የተስፋው ቃል ለአብርሃም ከተሰጠ 1000 ዓመታት አልፈዋል። እስራኤል ብዙ ሕዝብ ሲኖረው በምድሪቱ (ከነዓን) ውስጥ ይኖሩ ነበር። ነገር ግን የዓለም አቀፍ በረከት ተስፋዎች እውን ወደ መሆን እንኳን አልቀረቡም። እንደ አሕዛብ ነገሥታት ከጠላቶቻቸው የሚያድናቸው ንጉሥን ፈለጉ (1ኛ ሳሙኤል 8፥5)። ሳዖል ንጉሥ ሆኖ በተሾመ ጊዜ ልክ እንደ አብርሃም፣ ለእግዚአብሔር ክብር እስራኤልን እንዲገዛ በእግዚአብሔር የተሾመ አዲስ አዳም ነበር። ሳዖል ግን እንደ አዳም በእግዚአብሔር ላይ ዐመፀ፤ ስለዚህም ከንግሥናው ተነሣ (1ኛ ሳሙኤል 13፥13፤ 15፥22-23)። በእስራኤል ላይ ያለው የጌታ አገዛዝ በሳዖል የግዛት ዘመን አልተገለጠም ነበረ። ከዚያም እግዚአብሔር ዳዊትን ንጉሥ አድርጎ ቀባው። ከሳዖል በተለየ መልኩ እንደ እግዚአብሔር ልብ የሆነ ሰው ነበር፤ ለእግዚአብሔር ክብር ሲል ሕዝቡን ይገዛ ነበር (1ኛ ሳሙኤል 13፥14)። ያም ሆኖ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ያደረገው ዝሙት እና ኦርዮንን መግደሉ የእግዚአብሔር በረከቶች ለዓለም ሁሉ የሚደርሱበት ወኪል እንደማይሆን አሳይቷል (2ኛ ሳሙኤል 11)።

ሰሎሞን ዙፋኑን በያዘ ጊዜ፣ የአዲሱ ፍጥረት ገነት በቅርብ ያለች ይመስላል (1ኛ ነገሥት 2፥13-46)። ሰላም የሰለሞን ግዛት መገለጫ የነበረ ሲሆን፣ ለጌታም ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠራ (2ኛ ነገሥት 3-10)። መጀመሪያ ላይ ሰሎሞን እግዚአብሔርን በመፍራት ሕዝቡን በጥበብ ይገዛ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን ትቶ ወደ ጣዖት አምልኮ ተመለሰ (1ኛ ነገሥት 11)። በዚህም ምክንያት ሕዝቡ በሁለት መንግሥታት (በሰሜን እስራኤል፣ በደቡብ ደግሞ ይሁዳ) ተከፈለ (1ኛ ነገሥት 12)። ወደ ኃጢአት የተጀመረው ረዥም መንሸራተት፣ እስራኤል በ722 ዓ.ዓ በአሦራውያን በመማረክ እና ይሁዳ በባቢሎናውያን በ586 ዓ.ዓ በመማረክ ተደመደመ (2ኛ ነገሥት 17፥6-23፤ 24፥10-25፥26)። እግዚአብሔር አብርሃምን ከጠራ ወደ 1500 የሚጠጉ ዓመታት አልፈዋል። ነገር ግን ለአብርሃም ቃል የተገባው የስፍራ፣ የዘር እና የበረከት ተስፋዎች ለመፈጸም ሩቅ ነበሩ። እስራኤል በምድራቸው ሳይሆን በግዞት ነበሩ። እስራኤል ለዓለም በረከት ከመሆን ይልቅ እንደ ዓለም ሆና ነበር።

እስራኤል ለምን በግዞት ተቀመጠች? ችግሩ ምን ነበር? እስራኤል በኃጢአቷ ምክንያት በግዞት እንደነበረች ነቢያት ደጋግመው ያስተምሩ ነበር (ለምሳሌ፦ ኢሳይያስ 42፥24-25፤ 50፥1፤ 58፥1፤ 59፥2፣ 12፤ 64፥5)። ጌታ በኢሳይያስ በኩል አዲስ ዘጸአት (መውጣት) እና አዲስ ፍጥረት ቃል ገብቷል። ነገር ግን አዲሱ መውጣትና አዲስ ፍጥረት የሚመጣው በኅጢአት ሥርየት ብቻ ነው (ኢሳይያስ 43፥25፤ 44፥22) እና ይህ ይቅርታ እውን የሚሆነው በጌታ አገልጋይ ሞት ነው (ኢሳይያስ 52፥1-53፥12)። ኤርምያስም ተመሳሳይ እውነቶችን ያስተምራል። እስራኤል የሚያስፈልገው የተገረዘ ልብ ነበረ (ኤርሚያስ 4፥4፤ 9፥25)። በሌላ አነጋገር፣ እንደገና መፈጠር እና መለወጥ ነበረባቸው። ኤርሚያስ አዲስ ቃል ኪዳን እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሯል፤ ይህም እግዚአብሔር በሕዝቡ ልብ ላይ ሕጉን በመጸፍ እርሱን እንዲታዘዙት ያደርጋል (ኤርሚያስ 31፥31-34)። በተመሳሳይ መልኩ የሕዝቅኤል መጽሐፍ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከኅጢአት የሚያነጻበትን፣ የድንጋይ ልባቸውን አስወግዶ የሥጋ ልብ የሚሰጥበትን ቀን በጉጉት ይጠባበቃል (ሕዝቅኤል 36፥25-27)። የልባቸው መለወጥ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ውጤት ሲሆን በዚህ ለውጥ ምክንያት እስራኤል በእግዚአብሔር መንገድ ይሄዳሉ፤ ትእዛዛቱንም ይጠብቃሉ። በ536 ዓ.ዓ እስራኤል በሐጌና በዘካርያስ፣ በዕዝራ፣ በነህምያና በሚልክያስ ዘመን ታግለዋል። የተስፋው መንፈስ ሥራ ገና አልተፈጸመም። ንጉሥ እየጠበቁ ነበር። የአዲሱን ፍጥረት መምጣት እየጠበቁ ነበር።

እስራኤል በ536 ዓ.ዓ ከግዞት ተመልሳለች፤ ነገር ግን በነቢያት የተነገሩ ታላላቅ ተስፋዎች ሙሉ በሙሉ አልተፈጸሙም። እስራኤል በሐጌና በዘካርያስ፣ በዕዝራ፣ በነህምያና በሚልክያስ ዘመን ታግለዋል። በተስፋ የተሰጠው የመንፈስ ሥራ ገና አልተፈጸመም ነበር። ንጉሥ እየጠበቁ ነበር። የአዲሱን ፍጥረት መምጣት እየተጠባበቁ ነበር።

ያለ መለወጥ ለእስራኤልም ሆነ ለዓለም በረከት የለም

የእስራኤል ታሪክ ከኃጢአት ይቅርታ እና ከተገረዘ ልብ በቀር፣ አዲስ ፍጥረት እና አዲስ ዘጸአት እንደማይገኙ ያሳያል። ለአብርሃም የተሰጡት ተስፋዎች በእስራኤል ኃጢአት እና ዓመፅ ምክንያት አልተፈጸሙም። የሕዝቡ ታሪክ በተደጋጋሚ ባለመታዘዝ እና የጌታን ፈቃድ ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆን ይታወቃል። እስራኤል የኃጢአቶቿ መሰረይ አስፈለጋት። ኢሳይያስም እንዲህ ዓይነቱ ይቅርታ፣ በኢሳይያስ 53 በተጠቀሰው ሥቁዩ አገልጋይ በኩል እንደሚፈጸም አስተምሯል። ነገር ግን እስራኤል ለመዳን ከተፈጥሮ በላይ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ሥራም ያስፈልጋት ነበር። መለወጥ ነበረባት። ያለ መለወጥ (ዳግም ውልደት) ለእስራኤልም ሆነ ለዓለም ተስፋ የተገባው በረከት የእነርሱ ስለማይሆን፣ መለወጥ ለእስራኤል ታሪክ መሠረታዊ ነው።

በቶማስ ሽራይነር


[1] “Conversion” ለሚለው የእንግሊዘኛ ቃል አቻ ትርጉም ስላልተገኘ፣ “መለወጥ” (‘መ’ ትጠብቃለች) በሚለው አማርኛ ቃል መተካቱን ልብ ይበሉ።