ጥሶ ለመውጣት መጸለይ

ጥሶ መውጣት ወታደራዊ ጽንሰ ሐሳብ ነው። አንድ ሠራዊት የጠላቱን ኀይል እስከሚያሸነፍ ድረስ ማዳከም ከቻለ፣ ጥሶ መውጣት ይችላል። በዚህም የጠላቱን ግዛት መውረር ይችላል።

ነገር ግን በጦርነት መሃል ጥሶ መውጣት የሚቻለው ስልታዊ ቦታ ላይ መሆን ከቻልን ብቻ ነው። አንድ ቦታ ስልታዊ ቦታ ነው የምንለው፣ የጠላት ጦር ቦታውን ለመጠበቅ በብዛት ከሰፈረበት ነው። ልምድ ባላቸው የጦር አዛዦች የሚመራ የጠላት ኀይል፣ ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጠውን ቦታ በጥብቅ ይጠብቃል።

ይህ ማለት አንድ ወራሪ ጦር ጥሶ ከመውጣቱ በፊት፣ ጠንካራ የሆነ የጠላት ኀይልን መጋፈጥ አለበት። ሁልጊዜም ከስልታዊ ጥሶ መውጣት በፊት፣ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ውጊያ አለ። ስልታዊ ስፍራን በቀላሉ መቆጣጠር አይቻልም።

ጥሰን ለመውጣት ከኀያላን ጋር መፋለም አለብን

ይህ በምድራዊ ጦርነት እውነት እንደሆነው ሁሉ፣ ለመንፈሳዊውም ጦርነት እንደዚሁ ነው። ከምድራዊው ዓለም በተቃራኒ፣ በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ወራሪ ኀይል ነች። ምንም እንኳ በጋራ መከላከልን ብንመርጥም፣ ኢየሱስ ተከላካይ ሳይሆን አጥቂዎች እንድንሆን ይፈልጋል። ታላቁ ተልእኮም እንዲህ ነው፦ “ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴዎስ 28፥19)። “ዓለምም በክፉው ሥር እንደሆነ” የሚለው ገለጻ ከጦር ጋር የተያያዘ አገላለጽ ነው (1ኛ ዮሐንስ 5፥19)። ተልእኳችንም፣ ፈቃዱን ሊያስፈጽማቸው ምርኮኛ አድርጎ የያዛቸውን ሰዎች ከዲያብሎስ ወጥመድ ማስመለጥ ነው (2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥26)።

ነገር ግን ስልታዊ ስፍራን በቀላሉ መቆጣጠር እንደማይቻል መዘንጋት የለብንም። ከራሳችን ኀጢአት ጋር ቢሆን፣ ከምንወደው ሰው አለማመን ጋር፣ የሚስዮናዊ አገልግሎት እንዳይሰፋ ከሚያጋጥሙን መሰናክሎች ጋር ቢሆን፣ ስደት የደረሰባቸው ወይም ወላጅ አልባ ሕፃናትና ሴተኛ አዳሪዎችን ለመድረስ ከሚያጋጥሙን ችግሮች ጋር ቢሆን፣ ጦርነታችን፣ “ከሥጋና ከደም ጋር ሳይሆን ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች፣ ከሥልጣናትና ከኀይላት እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሠራዊት ጋር ነው” (ኤፌሶን 6፥12)። እነዚህ ኀይሎች እጅግ ጠንካራ እንደሆኑ ከማወቅ በቀር፣ ይህ ምን ማለት እንደሆነ በትክክል አናውቅም።

የዳንኤል ምሳሌ

ዳንኤል 10፥12-14 እየሆነ ስላለው ነገር ፍንጭ ይሰጠናል። ዳንኤል የተቀበለውን ራእይ ይበልጥ ለመገንዘብ፣ ለሃያ አንድ ቀናት ሲጸልይ እና በከፊል ሲጾም ቆይቷል (ዳንኤል 10፥3)። በዚህም ጊዜ አንድ መልአክ የጸሎቱን መልስ ይዞ መጣ። ይህ መልእክተኛም ወደ ዳንኤል አንዳይመጣ ለሃያ አንድ ቀናት “የፋርስ መንግሥት አለቃ” ተቋቁሞት እንደ ነበር፣ ደግሞም በመጨረሻ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል ነፃ እንዳወጣው ነገረው።

ይህ የዳንኤል ተሞክሮ ምሳሌ ሊሆነን ይችላል። ለሃያ አንድ ቀናት በጾምና ጸሎት ከቆየን፣ ሰማያዊ ኀይሎችን ሊዋጋልን ሚካኤል ይመጣል ማለት አይደለም። ነገር ግን ይህ ክስተት፣ ከእይታችን ውጪ እየሆነ ላለው ነገር የሆነ ምስል ይሰጠናል። እግዚአብሔር ስለ መላእክት ዓለም፣ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከገለጠው ውጪ እንድናውቅ አይፈልግም። ይህ ባይሆን ኖሮ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መላእክት ዓለም ገልጦ በተናገረ ነበር። ነገር ግን በዐይናችን ከምናየው ያለፈ ነገር እንዳለ እንድናውቅ እና በእርሱ ፊት በጾምና በጸሎት እንድንቆይ ይፈልጋል።

እግዚአብሔር ሲሠራ፣ ሰይጣን ምላሽ ይሰጣል

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያየ ቦታ፣ እግዚአብሔር ከሚሠራቸው ሥራዎች በፊት ሁልጊዜ እየጨመረ የሚመጣ አስቸጋሪ እና ተስፋ አስቆራጭ ተቃውሞዎች ነበሩት። ኤፌሶን 6ዳንኤል 10 እና ሌሎች ጥቅሶችን አስተውለን ከተመለከትን፣ ይህ ለምን እንደ ሆነ መረዳት እንችላለን። የዚህ ምክንያቱ ሰይጣን ግዛቴ ብሎ የያዘውን ስፍራ እግዚአብሔር እየወሰደበት ስለሆነ ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት፣ የጨለማውን አገዛዝ እያሸነፈው ነው (ቆላስይስ 1፥13)።

ተቃውሞ ካላጋጠመን፣ ስልታዊ ስፍራን እያጠቃን አይደለም። ጥቃት ማድረስ ያለብን፣ ጠላት ኀይሉን በሚያጠናክርበት ቦታ ነው።

የጠላት ኀይል በተመሸገበት ቦታ ደግሞ፣ ጥሰን ለመውጣት ከባድ ውጊያ ማድረግ ይኖርብናል። የሚንበለበሉ የክፉ ፍላጻዎችን መጋፈጥ ይኖርብናል (ኤፌሶን 6፥16)። ከኋላ ጥቃት ሊደርስብን ይችላል፤ ሰላዮች በመካከላችን ሊኖሩ ይችላሉ፤ ስድብ፣ ማስፈራራት እና ውንጀላ ሊኖር ይችላል፤ ጽናታችንን እና ቁርጠኝነታችንን ለማጥፋት ብዙ ሙከራዎች ይኖራሉ።

በጽናት ጥሶ ለመውጣት የቀረበ ጥሪ

ይህ የቅዱስ ጽናት ጥሪ ነው። ሳትታክቱ ሁልጊዜ ጸልዩ (ሉቃስ 18፥1)። ልክ እንደ ማንኛውም ትልቅ ጦርነት፣ በውስጡ ብዙ ውጊያዎች አሉ። አንዳንዶቹ ውጊያዎች ጥሰን ለመውጣት ቀላል ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ጽናት እና ጥንካሬን ይጠይቃሉ። በሁለቱም መንገድ ጥሶ ለመሄድ፣ ጥቃቱን በቁርጠኝነት መቀጠል ይጠይቃል።

ብዙ ጊዜ ጥሶ ለመውጣት ጸሎት ብቻ በቂ አይደለም። የሚሠሩ ሥራዎች አሉ። ነገር ግን እውነተኛ ጥሶ መውጣት፣ በፍጹም ያለ ጸሎት ሊሳካ አይችልም። በመንፈሳዊው ዓለም፣ የሚገጥመንን ተቃውሞ ለማዳከም ሁለት እና ከዚያ በላይ ሆነን የማያቋርጥና ትኩረት ያለው ጸሎት መጸለይ አለብን (ማቴዎስ 18፥19)። ለዚህ ደግሞ ጾም እጅግ ይጠቅመናል። “ጾም ልባችን ያለበትን ስፍራ ይፈትሻል። ልባችን ከዓለም ጋር ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር እንደሆነ ሲገለጥ፣ የሰይጣን ኀይል ይመታል” (A Hunger for God)።

ስለዚህ ጥሰህ እንድትሄድ እየጸለይክ ከሆነና ከበፊቱ የበለጠ ተስፋ የሚያስቆርጥ፣ የሚያናድድ፣ የሚያደክም፣ እና የሚያጠራጥር ሁኔታ ከገጠመህ፣ ተስፋ አትቁረጥ። ከስልታዊ ጥሶ መውጣት በፊት ሁልጊዜ ጠንካራ ውጊያ አለ። ስልታዊ ስፍራን በቀላሉ መቆጣጠር አይቻልም። አንተ ከምታውቀው በላይ ጠላት አለህ። ነገር ግን፣ “ በእናንተ ውስጥ ያለው በዓለም ካለው ይበልጣል” (1ኛ ዮሐንስ 4፥4)። እርሱ ዓለምን አሸንፎታል (ዮሐንስ 16፥33)። ፈጥኖም ይፈርድልሃል (ሉቃስ 18፥8)።

ከፊትህ ጥሶ መውጣት ስላለ ተስፋ አትቁረጥ፤ በጽናት ተራመድ።

ጆን ብሉም