ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን። (1 ቆሮንቶስ 15፥19)
ጳውሎስ ኢየሱስን በመከተል የመረጠው የሕይወት ጎዳና ትንሣኤ ከሌለው በየሰዓቱ የሚገጥመው አደጋ፣ በየዕለቱ ከሞት ጋር መጋፈጡ እና ከአራዊት ጋር መታገሉ ሁሉ ሞኝነት እንደሆነ ይደመድማል።
ጳውሎስ ሞት የነገር ሁሉ ድምዳሜ ሚሆን ከሆነ፣ “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፣ እንጠጣ” ይላል (1 ቆሮንቶስ 15፥32)። ታዲያ ይህ ማለት ትንሣኤ ከሌለ ሁላችንም ሆዳሞችና ሰካራሞች እንሁን ማለት አይደለም። ትንሣኤ ኖረም አልኖረም ሰካራሞች ምስኪኖች ናቸው። እያለ ያለው ግን፣ ትንሣኤ ከሌለ የምድራዊ ደስታን ለመጨመር የተደላደለ ኑሮን መኖር የተሻለ ይሆናል ነው።
ነገር ግን ጳውሎስ የሚመርጠው ያንን አይደለም። መታዘዝን ስለመረጠ፣ መከራን መረጠ። ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ላይ ከክርስቶስ ጋር ከተገናኘ በኋላ፣ ሐናንያ ወደ ጳውሎስ ከጌታ ኢየሱስ ይህንን ቃል ሰምቶ ይመጣል፦ “እኔም ስለ ስሜ ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበት አሳየዋለሁ” (ሐዋሪያት 9፥16)። ጳውሎስ ይህን መከራ የመጠራቱ አካል አድርጎ ተቀብሎታል።
ታዲያ ጳውሎስ ይህን እንዴት ማድረግ ይችላል? የዚህ በሥቃይ የተሞላ መታዘዝ ምንጭ ምን ነበር? መልሱ በ1 ቆሮንቶስ 15፥20 ላይ ተሰጥቷል፦ “ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በርግጥ ከሙታን ተነሥቶአል።” በሌላ አባባል፣ ክርስቶስ ተነሥቷል፤ እኔም ደግሞ ከእርሱ ጋር እነሣለሁ ማለት ነው። ስለዚህም ማንኛውም ስለ ኢየሱስ የምንቀበለው መከራ በከንቱ አይደለም (1 ቆሮንቶስ 15፥58)።
የትንሣኤው ተስፋ የጳውሎስን አኗኗር ፈጽሞ ለውጦታል። ከቁሳዊነትና ከአግበስባሽነት ነፃ አውጥቶታል። ብዙ ሰዎች በዚህ ሕይወት ውስጥ ከሚፈልጉት ምቾች እና ፍሰሓ ውጪ መኖር እንዲችል ኅይልን ሰጥቶታል። ለምሳሌ፦ ሚስት ለማግባት መብት ቢኖረውም ብዙ መከራን እንዲቀበል ስለተጠራ ያንን ደስታ እርግፍ አድርጎ ትቶታል (1 ቆሮንቶስ 9፥5)።
ኢየሱስ የትንሣኤው ተስፋ አመለካከታችሁን ሊቀይር ይገባል ያለው በዚህ መንገድ ነው። ለምሳሌ፦ በዚህ ሕይወት መልሰው ሊከፍሉን የማይችሉ ሰዎችን ወደ ቤታችን እንድንጋብዝ ይነግረናል። ይህንን ለማድረግ ምን ያነቃቃናል? “በጻድቃንም ትንሣኤ ብድራትህ ይመለስልሃል” (ሉቃስ 14፥14)።
ይህ የአሁኑን ሕይወታችንን በትንሣኤው ተስፋ የተቀረጸ እንዲሆን አጥብቀን እንድንሠራ የቀረበ መሠረታዊ ጥሪ ነው። ውሳኔዎችን የምንወስነው በዚህ ዓለም ይጠቅመናል በሚል ነው ወይስ በመጪው ዓለም? ትንሣኤ በመኖሩ ብቻ፣ ስለፍቅር ብለን የምንጋፈጣቸው አደጋዎችስ አሉ?
በዘመናችን ሁሉ ትንሣኤው ሥር ነቀል ለውጥ እንዲያመጣ ራሳችንን መስጠት እንድንችል እግዚአብሔር ይርዳን።